Tuesday, September 25, 2012

ወ/ሮ አዜብ የምኒልክ ቤተ መንግስትን የሚለቁ አይመስልም


(ኢ.ኤም.ኤፍ) በየትኛውም አገር አንድ መንግስት ሲቀየር አዲስ የሚመረጠው አካል፤ ወደ አስተዳደር ቢሮው መግባት ይኖርበታል። በራሺያ የክሬምሊን ቤተ መንግስት ወይም በአሜሪካ ኋይት ሃውስ የመንግስት መቀመጫ ስፍራዎች ናቸው።  ለኢትዮጵያ ደግሞ የመንግስት ስራ ማከናወኛ የአራት ኪሎው ምኒልክ ቤተ መንግስት መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ በሌሎች አገራት የመንግስት ለውጥ ሲደረግ፤ ፕሬዘዳንቱም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትሩ በጨዋ ደንብ ጨርቅ እና ማቃቸውን ይዘው ይወጣሉ። በኢትዮጵያ ግን ይህ አልሆነም። የቀድሞው እመቤት ቤተ መንግስቱን የሙጥኝ እንዳሉት ነው።
The new Ethiopian Prime minister Hailemariam Desalegn VS former first lady, Azeb.
አቶ ኃይለማርያም ምኒልክን ቤተ መንግስት ከሩቅ ከማየት ውጪ ከነቤተሰባቸው ወደ ቅጥር ግቢው አልተዛወሩም። ሌላው ቀርቶ በትላንትናው እለት የሁለቱን ሱዳኖች ልዑካን ተቀብለው ያነጋገሩት፤ ፕሬዘዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ በሚገኙበት ኢዮቤልዩ ቤተ መንግስት ውስጥ ነበር። ከዚህ በፊት በመለስ ዜናዊ ይደረጉ የነበሩ የእንግዳ አቀባበል ስርአቶች ይፈጸሙ የነበረው በአራት ኪሎው ምኒልክ ቤተ መንግስት ሲሆን፤ አሁን ግን ሴትዮዋ አልወጣም በማለቷ ምክንያት… አቶ ኃይለማርያም ፕሬዘዳንቱ የሚገኙበትን ቤተመንግስት በጋራ ለመጠቀም ተገደዋል።
በአሁኑ ወቅት ስልጣን ያለምንም ኮሽታ “ከኢህአዴግ ወደ ኢህአዴግ ተሸጋግሯል” ቢባልም፤ አዜብ መስፍንን ጨምሮ በርካታ የህወሃት ባለስልጣናት ደስተኛ አይመስሉም። ሌላው ቀርቶ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር (በፈጣሪ ፋንታ) ለመለስ ዜናዊ ዘላለማዊነትን በተመኙበት ፓርላማ፤ ወ/ሮ አዜብን ጨምሮ ሌሎች የህወሃት አባላት፤ የራሳቸውን ስብሰባ አዲስ አበባ ላይ ሲያደርጉ ቢቆዩም በፓርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ አልተገኙም ነበር። ይህ ብዙዎችን ቢያሳዝንም፤ ውስጥ ውስጡን ግን የርስ በርሱን ሽኩቻ አጉልቶ የሚያሳይ ነው።
ሌላው ቀርቶ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚንስትር ተብለው ከመሰየማቸው በፊት፤ ባስቸኳይ ለህወሃት አባላት የጄነራልነት ማዕረግ ማንበሽበሹ በራሱ፤ የርስ በርሱ የስልጣን ሽኩቻ ውጤት ነበር። ህወሃት በትግርኛ ባወጣው መግለጫ ላይ አስፈላጊ ከሆነ፤ እንደገና የትጥቅ ትግል ሊያደርግ እንደሚችል ማስፈራሪያ ቢጤ በመግለጫው ላይ አስፍሯል። ይህ ማስፈራሪያ ለማን እና ለምን እንዳስፈለገ እስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም የአራት ኪሎውን ቤተ መንግስት ከሩቅ ከማየት በቀር፤ በለቅሶ ሰሞን ጎዳና ተዳዳሪ ጭምር ሲንሸራሸርበት ወደነበረው የምኒልክ ቤተመንግስት እንዳይገቡ ተደርገዋል።

አቶ ኃይለማርያም በአሁኑ ወቅት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንደመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን ሳይሆን፤ እንደበታች የኢህአዴግ ሰራተኛ ነው። በፓርላው ቃለ መሃላ በፈጸሙበት ወቅት፤ “ከኋላ ደግፉኝ፤ ከፊትም ሆናችሁ ምሩኝ!” እንዳሉት፤ ሌሎች የሚመሯቸው እንጂ ሌሎችን የሚመሩ አይነት ጠቅላይ ሚንስትር አልሆኑም። ወ/ሮ አዜብም ቢሆኑ፤ “የመለስን አልጋ ማንም አይተኛበትም!” ብለው ከመፎከር አልጋውን ይዘው ቢወጡ፤ የርስ በርስ የስልጣን ሽግግሩን ይበልጥ ሰላማዊ ያደርገው ነበር። ይህ ግን አልሆነም። ሌላው ቀርቶ በአቶ መለስ ዜናዊ ጠቅላይነት ዘመን፤ የመንግስት ከፍተኛ ሹሞች (ጠቅላይ ሚንስትሩን ጨምሮ) ከስራ በሚሰናበቱበት ወቅት የሚያርፉበት ትላልቅ ቪላዎች እያንዳንዳቸው በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ ተሰርተዋል። በቂ ጥበቃም ይደረጋል። ወ/ሮ አዜብ ግን ወደነዚህ ቪላዎች ለመሄድ ዝግጁ አልሆኑም። ይልቁንም ከቤተ መንግስቱ የመውጣት ምንም አይነት አዝማሚያ አላሳዩም።
አሁን ያለው ችግር… አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ማዘዝ አለመቻላቸው እና የቀድሞዋ እመቤትም በዙሪያቸው የሚገኙ የህወሃት ጄነራሎችን በመተማመን ለመታዘዝ ዝግጁ አለመሆናቸው ነው። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እልህ እየተናነቃቸው፤ “የመለስን ሌጋሲ አስቀጥላለሁ” ቢሉም፤ አሁን ደግሞ እንባ እየተናነቃቸው ከቤተ መንግስቱ ውጪ ቆመው ነው ያሉት። ከሳቸው ጎን የቆሙት አቶ በረከትም ቢሆኑ፤ ከወ/ሮ አዜብ መስፍን ጋር ሊታረቅ በማይችል የግል ጸብ ውስጥ ከገቡ አመታት በመቆጠራቸው፤ ጠንከር አድርገው ሴትዮዋን “ለቀው ይውጡ!” ማለት አይችሉም። በዚህ ጉዳይ እርምጃ መውሰድ የሚችሉት፤ የቤተ መንግስቱን ጥበቃ ጭምር በሃላፊነት የሚመሩት የደህንነት ሚንስትሩ አቶ ጌታቸው አሰፋ ነበሩ። ምንም እንኳን አቶ ጌታቸው አሰፋም የህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ቢሆኑም፤ የቤተ መንግስቱ ጥበቃ ከእጃቸው ወጥቶ በመከላከያ ሚንስትር ስር የሚመሩ ልዩ ታጣቂዎች ተሰማርተዋል። እነዚህን ቀላል የሚመስሉ ልዩነቶችን ገጣጥመን ስናነባቸው ግን የሚሰጠው ስዕል እምብዛም ደስ የሚያሰኝ አይደለም።
እንዲህ ያለው ነገር በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያጋጠመው የዛሬ መቶ አመት፣ በ1902 ዓ.ም. እቴጌ ጣይቱ፤ ከልጅ እያሱ አሳዳጊ ከነደጃዝማች ተሰማ ጋር በተጣሉበት ወቅት ነው። ከምኒልክ ሞት በኋላ እቴጌይቱ ከሌሎቹ መኳንንት እና እንደራሴ ጋር ስላልተስማሙ፤ “በሉ ወዳገሬ ወደ የጁ ላኩኝ” ቢሉ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እንደራሴ ከሌሎቹ ሚንስትሮች ጋር መክረው፤ “አገሬ መልሱኝ ያሉት፤ ወንድማቸው ራስ ጉግሳ ወሌን ይዘው ወሎን ሊያስሸፍቱ ነው” በሚል፤ እሳቸው ከቆረቆሯት አዲስ አበባ ከተማ እንዳይወጡ  ከለከሏቸውና አዲስ አበባ ውስጥ የአሁኑ ተክለሃይማኖት አካባቢ ብዙ ሰራተኞችና አጃቢዎች ተመድቦላችው፤ በክብር ቤተ መንግስቱን ለቀው በሰላም መኖር ጀመሩ። አሁን ግን ወ/ሮ አዜብ መስፍን አገር እንደሌለው ሰው፤ ቢያንስ እንደ እቴጌ ጣይቱ “ወዳገሬ መልሱኝ” ሳይሉ፤ ወደተዘጋጀላቸውም መኖሪያ ቤት ሳይዛወሩ፤ ቤት አይቶ እንደማያውቅ ሰው “ከምኒልክ ቤተ መንግስት አልወጣም” ብለው በማንገራገር ላይ ናችው። ለነገሩ ወ/ሮ አዜብ “ወዳገሬ መልሱኝ፡” ቢሉ፤ የሚወስዷቸው ወደአያቶቻቸው ራስ ጎላ አገር ወልቃይት ነው። ወልቃይቴዎች ደግሞ በሴትዮዋ አዝነውባቸው ከተቀያየሙ ሰንብተዋል። ወደ ትግራይ እንዳይሄዱ ደግሞ፤ የትግራይ ህዝብ  ደግሞ ውስጥ ውስጡን የመለስ ዜናዊን የሞት ምክንያት ከወ/ሮ አዜብ ጋር እያያዘ ውስጥ ውስጡን ስለሚያወራ፤ ሴትዮዋ የአድዋንም ሆነ የመቐለን ህዝብ የማየት፤ እነሱን የሴትዮዋን አይን ማየት የሚፈልጉ አይመስልም። የሆኖ ሆኖ ግን የአቶ መለስ ዜናዊ የሞት መንስዔ እንደማይታወቀው ሁሉ፤ ሴትዮዋም ለምን ከምኒልክ ቤተ መንግስት መውጣት እንዳልፈለጉ ግልጽ አይደለም።

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የታዛዥነት እንጅ የአዛዥነት ስብእና የላቸውም ተባለ


መስከረም ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያን ለ 21 ዓመታት የገዙዋት አቶ መለስ ዜናዊ በህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ እርሳቸውን የተኩዋቸው አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፣  ትሁት፣ ቅንና ደግ ቢሆኑም፣ የህወሀት ባለስልጣናትን ተጋፍተው ለውጥ የሚያመጡ ሰው አለመሆናቸውን እርሳቸውን በቅርብ የሚያውቁና አብረዋቸው የሰሩ ሰው ለኢሳት ተናግረዋል። አቶ ሀይለማርያም ተሿሚዎቻቸውን እንደፈለጉ ለማሽከርከር ለሚፈልጉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የተመቸ ጠባይ እንዳላቸው የገለጡት ከእርሳቸው ጋር በአንድ ወቅት አብረዋቸው የሰሩት በአሁኑ ጊዜ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር አባልና የደቡብ ክልል ተወካይ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ለኢሳት ገልጠዋል።
ከአቶ ሀይለማርያም ጋር የቀረበ ግንኙነት የነበራቸው አቶ ዳንኤል በቤተሰብም ሆነ በግል ባህሪያቸው እጅግ የተመሰገኑ ሰው መሆናቸውን ተናግረዋል::
አቶ ሀይለማርያም ጥሩ የግል ስብእና ቢኖራቸውም ሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ከሚወገዘው ኢህአዴግ ጋር አብረው መስራታቸው አድርባይ ተደርገው እንዲተቹ መንገድ  እንደከፈተና እርሳቸውም እንዲህ አይነቱን አስተሳሰብ እንደሚጋሩት አቶ ዳንኤል ተናግረዋል::
አቶ ሀይለማርያም በሚቀጥሉት የስልጣን ጊዜያቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ ያመጣሉ ብለው እንደማያስቡ አቶ ዳንኤል ሽበሺ ይናገራሉ::
አቶ ዳንኤል አቶ ሀይለማርያም እንደ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደፋር እርምጃ በመውሰድ ለለውጥ እንዲነሱም ጥሪ አቅርበዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የህወሀት ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ስዩም መስፍን የአቶ ሀይለማርያምን እና የአቶ ደመቀ መኮንንን ሹመት የህወሀት ኢህአዴግ አባላትና አንዳንድ የአመራሩ አካላት ተቃውመውት እንደነበር አምነዋል። ነባር የኢህአዴግ አባላት ይች አገር ብዙ ውስብስብ ችግሮች ያሉባት መሆኑዋን እያወቃችሁ እንዴት ምንም ልምድ ለሌላቸው ሰዎች ታስረክባላችሁ በማለት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ተናግረዋል።  አቶ ስዩም መስፍን  አዲሱ አመራር ብቻውን የሚንቀሳቀስ ሳይሆን እስከመጨረሻው በነባሩ አመራር ድጋፍ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ግልጽ አድርገዋል::
የአቶ ስዩም ንግግር በኢህአዴግ ውስጥ  የቡድን አመራር መፈጠሩን የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን አዲሱ አመራር ራሱን ችሎ ለማስተዳደር ሀላፊነት እንዳልተሰጠው የፖለቲካ ተቺዎች የሚያቀርቡትን ትችት የሚያጠናክር ተደርጎ ታይቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢህአዴግ ውስጥ አሁንም የስልጣን ፍትጊያው እንደቀጠለ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኢህዴዶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ስልጣን እንኳን ይገባናል በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ህወሀቶች በበኩላቸው ከመከላከያ፣ ደህንነትና ፖሊስ ተቋማት በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ይገባናል እያሉ ነው።
አቶ ሀይለማርያም አዲሱን መንግስታቸውን ሳያዋቅሩና ሚኒስትሮቻቸውን ሳይሾሙ በ67ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላይ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ወደ ኒዮርክ ማምራታቸው አስገራሚ መሆኑን የአዲስ አበባው ዘገባ ገልጧል።
አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ እውነተኛ ስልጣን ቢኖራቸው ኖሮ ወደ ኒውዮርክ ከማምራት ይልቅ ሌሎች አጣዳፊ ስራዎችን መስራት ነበረባቸው ያለው ዘጋቢያችን፣ ማንኛውም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያደርገው ካቢኔያቸውን አዋቅረው እና ለህዝብ አሳውቀው ራእያቸውን ወደ መትግበር በቀጥታ መግባት እንጅ ውጤት ወደ ሌለው የኒዮርኩ አመታዊ ጉባኤ ማምራት አልነበረባቸው ብሎአል።

አቶ በረከት የኢቲቪና የፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጆችን አንስተው ታዛዦቻቸውን ሊሾሙ ነው ተባለ


መስከረም ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኮሙኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ በረከት ስምዖን  የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እና የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ሥራ አስኪያጆችን በማንሳት ለእርሳቸው ታዛዥ የሆኑ ሰዎችን ለማስቀመጥ  እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተጠቆመ።
በዚህም መሰረት ከደቡብ ክልል ያስመጡትና በኢትዮጵያ ራዲዮ ውስጥ በምክትል ሥራ አስኪያጅነት ሢሰራ የቆየው ሰለሞን ተስፋዬ የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሰይፈ ደርቤ ደግሞ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት  ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሆኑ ወስነው ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን ምንጮቹ ገልጸዋል።
ሰይፈ ደርቤ የፍትህ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ ላይ በምክትል ዋና አዘጋጅነት በሚሠራበት አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተከታታይ በሚያወጣቸው  የፕሮፓጋንዳ ጽሁፎች፤ የሀሰት ክስ ሲደረድር መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ ለ አዲስ ሹመት የታጩት ሁለቱም ሰዎች የ አቶ በረከት ታዛዦች መሆናቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል።
አቶ በረከት እነዚህን ሁለት ታዛዦቻቸውን ወደ ላይ ለማምጣት የፈለጉትም እንደተለመደው <ጠላቴ>የሚሏቸውን ለማጥቃት ይረዱኛል ብለው ነው-ብለዋል-ምንጮቹ።
የደቡብ ክልሉ ሰለሞን ተስፋዬ እና የብአዴኑ ሰይፈ ደርቤ በጓደኞቻቸውም ሆነ በመስሪያ ቤቱ ሠራተኞች ዘንድ የሚታወቁት አፍቃሬ በረከት በመሆናቸው እንደሆነም ተመልክቷል።
ምንጮቹ  እንደሚሉት አቶ በረከት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት፦ “የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ  ሆኖ እየሠራ ያለው ዘርአይ የትግሉ ውጤት በመሆኑ ለበረከት ጥሩ መሳሪያ ሊሆን ስላልቻለ ነው።”
አቶ ከፍያለው አዘዘን ተክቶ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የነበረው ሰብስቤም እንዲወገድ የተፈለገው እንደታሰበው  ለአቶ በረከት መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል ባለመቻሉ ነው ተብሏል።
አቶ በረከት ብዙ ጊዜ ፦‹ሰብስቤ ደነዝ ከሚባሉ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ስራውን አያውቀውም፤ የሱ ስራ መጠጥ መጠጣትና ጫት መቃም ነው ›  በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
“አሁን በመለስ ሞት ምክንያት የተፈጠረውን አቅም በመጠቀም ዘርዓይንና ሰብስቤን  ገፍትሮ ለማስወጣት ዝግጅቱ ተጠናቋል ፡፡”ያሉት የዜናው ምንጮች፤ ሰሎሞን እና ሰይፈም አዲሶቹ ስራ አስኪያጆች ለመሆን በዝግጅት ላይ ናቸው”ብለዋል።
<<ለዚህም ዕቅዳቸው አቅጣጫ ለመስጠት፤ <ኢህአዴግ ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር የልምድ ልውውጥ ያደርጋል> በሚል፤ አቶ በረከት ቀጣዮቹን የሚዲያዎቹን ሀላፊዎች ማለትም አቶ ሰለሞን ተስፋየን እና አቶ ሰይፈ ደርቤን  ቻይና ወስደው እያሰለጠኑ ነው ብለዋል።>>እነኚሁ በድርጅቶቹ ውስጥ ያሉ የኢሳት ምንጮች።
እንደ ዜናው ምንጮች መረጃ ፤የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሽመልስ ከማል የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ስላጠናቀቁ  መገፋት እየደረሰባቸው ነው።
በምርጫ 97 ማግስት የቅንጅት መሪዎችንና የጋዜጠኞችን የፍርድ ሂደት በፈቃደኝነት ግንባር ቀደም አቃቤ ህግ ሆነው የመሩት አቶ ሽመልስ ቀደም ሲልም በአቶ መለስ ፦<ሌቦች> ተብለው ተባርረው ከነበሩት ዳኞች አንዱ ናቸው።
ገለልተኛ አስተያዬት ሰጭዎች  በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትና በኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ውስጥ የተፈጠረውን ቅራኔ-  የህወሀትና ብአዴን ፍትጊያ ነጸብራቅ ነው ሲሉ አስተያዬታቸውን ይሰጣሉ።