Tuesday, October 16, 2012

አቶ ስብሐትና የተንኮል ፖሊቲካ በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም 
ጥቅምት 2005

አቶ ስብሐት ነጋ ሙሉ ነጻነቱን የሚወድ ሰው መሆኑን አደንቅለታለሁ፤ አስቦም ይሁን ሳያስብ አንደልቡ የመናገር ባሕርይ አለው፤ በበኩሌ ይህንን ባሕርዩንና በመብቱ መጠቀሙን አከብርለታለሁ፤ ሀሳቡ የተሳሳተ ይሁንም አይሁንም፣ እኔ የምስማማበት ሆነ አልሆነም፣ እኔ ልቀበለውም አልቀበለው ስብሐት ነጋ በሙሉ ነጻነቱ ተጠቅሞ ሀሳቡን ሁሉ መግለጹን አከብርለታለሁ፤ እሱም የእኔን ሀሳብ የመግለጽ ነጻነት አንደሚያከብርልኝና እንደሚያስከብርልኝ ተስፋ አለኝ፤ ከዚያም በላይ ነጻነት ሁልጊዜም፣ የትም ቦታ ከኃላፊነት ጋር የተቆራኘ መሆኑን እንድንገነዘብ ያሻል፤ ኃላፊነት የሌለበት ነጻነት የለም፣ ኃላፊነት የሌለበት ነጻነት ስሙ ሌላ ነው፡፡
በቅርቡ አቶ ስብሐት በአደረገው ቃለ መጠይቅ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የተሾመው ወያኔ ዱሮም አስቦበት ወንበሩን ከአማርኛ ተናጋሪዎችና ከኦርቶዶክስ አማኞች ለማጽዳት በተዘጋጀበት እቅድ ነበር ብሎአል፤ ልብ ላለው አነጋገሩ በሁለት በኩል ስለት ያለው ቂል የያዘው ሰይፍ ነው፤ ከፊት ለፊት የተሰነዘረው አማርኛ ተናጋሪውንና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አማኙን ለመምተር ነው፤ ቂል የሚያደርገው አማራ የሚባል ጎሣ ቢኖርም የኦርቶዶክስ ሃይማኖት በአማርኛ ተናጋሪዎች ታጥሮ ትግሬንና ኦሮሞን፣ ወላይታንና ጉራጌን፣ ሌሎችንም የማይነካ መስሎት ከባድ ስሕትት ላይ መውደቁ ነው፤ ከሁሉም በላይ እሱን የሚያህል ሰው የተክለ ሃይማኖትን ታሪክ አለማወቁ ያሳዝናል፡፡
አማራንና የኦርቶዶክስ ተከታዮችን መትሮ ሲመለስ ደግሞ ሰይፉ የሚቀላው ወላይታንና ጴንጤነትን፣ ምናልባትም እስልምናን ይሆናል፤ አማራን ለመምተር ተነሥቶ ሌላውን ስንቱን ቀላው! እስልምናን በጥርጣሬ ያስገባሁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስላም ነው የሚባል ያልተጣራ ወሬ በመስማቴ ነው፡፡
አቶ ስብሐት በፊት ለፊት የተናገረው ገና የዛሬ ሀያ አንድ ዓመት ‹‹እንዳያንሰራራ አድርገን አከርካሪቱን እንሰብረዋለን›› ተብሎ ያለቀለትን አማራ ዛሬ ወንበር ማጣቱን ለማብሰር አልነበረም፤ ይህ በጣም ግልጽና ከማንም ያልተሰወረው እውነት ነበር፤ ስውር ዓላማም አለው፤ ያንን ብዙ ሰው አይገነዘበውም ይሆናል፤ በአቶ ስብሐት አነጋገር ውስጥ ዋናውና ተንኮልን ያዘለው ዓላማ ወንበሩን የያዘው ዋናው የወላይታ ጴንጤ ሲሆን ምክትሉ ደግሞ እስላም መሆናቸውን ለመናገር ያለው ፍላጎት ላይ ነው፤ ከአቶ ስብሐት ነጋ በቀር የአዲሶቹን ሹሞች ዘርና ሃይማኖት ከጉዳይ ያስገባ ያለ አይመስለኝም፤ አቶ ስብሐት በፊት-ለፊት ዓላማው ተስፈንጣሪ ተራማጅ ሲመስል በስውሩ የተንኮል ዓላማው ግን ኋላ-ቀር ወግ-አጥባቂ ይሆናል፤ በዘርና በሃይማኖት ላይ ሲያተኩር ዋናውን ቁም-ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩና ምክትሉ ሰዎች፣ ከዚያም ቀጥሎ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ፈጽሞ ዘንግቶታል፤ ለእኛ ትልቁ ነገር ይህ ነው፤ በሁለታችን መሀከል ያለው ልዩነት ስብሐት ኢትዮጵያውያንን የሚያዛምዳቸውን ሁሉ አያይም፤ እኔ ደግሞ ኢትዮጵያውያንን የሚለያያቸውን ሁሉ አላይም፡፡