Thursday, November 29, 2012

ህወሃት አረጋግቶ አገገመ


ህወሃት አረጋግቶ አገገመ

ብቸኛው ተቃዋሚ የንግድ ሚኒስትሩን ሹመት ኮነኑ(source:goolgule.com)

ኢህአዴግ “አረጋግቶ አገገመ” ከተባለው አዲሱ “ምደባ” መካከል የንግድ ሚኒስትር  ተብለው በተሰየሙት ላይ ብቸኛው የፓርላማ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ ጠንካራ መከራከሪያ በማቅረብ ተቃወሙ። አቶ ግርማ የሚሾሙ ብቻ ሳይሆን የሚነሱ ባለስልጣናት ከሃላፊነታቸው የተነሱበት ምክንያትም ለህዝብ መቅረብ እንዳለበት አሳሰቡ። አቶ ሃይለማርያም ተቃውሞውን “መክረንና ገምግመን ያደረግነው ነው” ሲሉ ተከላከሉ። አቶ ግርማ ብሩ (አሁን አምባሳደር) ሲመሩት የነበረውን ሚኒስቴር መ/ቤት “ስያሜና ምልክት መለየት የማይችል” በማለት አንቋሸሹት።
ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አገሪቱን በመሩበት ሶስት ወራት ካቢኒያቸውን በደንብ መገምገማቸውን በግምት በመግለጽ ተቃውሞ ያቀረቡት አቶ ግርማ ሰይፉ በምደባው በተወሰነ ደረጃ እንደሚስማሙ ተናግረዋል። የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔን ምደባ የተቃወሙት በማስረጃ ነው። የዓለም ባንክ ለንግድ ምዝገባ የማያመቹ አገሮችን ዝርዝር ጥናት ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ከ185 አገሮች የ165ኛ ደረጃ ማግኘቷን፣ ለዚህም የዳረጉት ቀደም ሲል በተጠባባቂ ሚኒስትርነት ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት አቶ ከበደ ጫኔ በመሆናቸው አዲሱ ሹመት እንደማይገባቸው አቶ ግርማ በተቃውሞ ተናግረዋል። በተጨማሪም ህዝብ የማወቅ መብት ስላለው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሃላፊነታቸው ሲነሱ ምክንያቱ ይፋ ሊሆን እንደሚገባው ማሳሰቢያ አቅርበዋል።
አቶ ግርማ ብቻ የተቃውሞ አስተያየት ያቀረቡበት ምደባ በስፋት ሃሳብ ሲሰጥበት ለነበረው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወንበር መልስ በመስጠት ተጠናቋል። ምደባውን ህወሃት ሲያሸንፍ የተመደቡት ሚኒስትር አቶ መለስ በህይወት እያሉ ይተኳቸዋል የተባሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ናቸው። የግራ ዘመሙን የፖለቲካ ጎዳና እምብዛም የማያውቁት ዶ/ር ቴዎድሮስ “ልምድ ያላቸው ታጋይ አይደሉም” በሚል ህወሃትን በከፍተኛ አመራርነት ስለመወከላቸው ጥያቄ የሚያቀርቡባቸው ነበሩ።
ለሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን እጅግ ቅርብ  የሆኑት አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ድር /ኔትዎርክ/ አካል ናቸው። በምደባው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ሆነው የተመደቡት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልም በተመሳሳይ የአቶ መለስ ቅርብ ሰው ናቸው። ጎልጉል ዶ/ር ደብረጽዮን ወደ ከፍተኛው ስልጣን ርካብ እንደሚሻገሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሆኑ ዘግቦ ነበር።
ክፍት በነበሩና በአዲሶቹ ሶስት አደረጃጀቶች መሰረት የተካሄደውን የባለሥልጣናት ምደባ አስመልክቶ አቶ ሃይለማርያም “ጠ/ሚኒስትሩ በቀጥታ ከሚከታተላቸውና ከሚመራቸው የመከላከያ፣ የደህንነት፣ የዲፕሎማሲ፣ የማክሮና ሜጋ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ ያሉትን የማህበራዊ፣ የመልካም አስተዳደር፣ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ዘርፎችን የመከታተል ስራ እንዲሰሩ ክላስተሮች ተቋቁመዋል” ብለዋል። አይይዘውም  አደረጃጀቱ ስራዎችን በየደረጃው ለመምራት የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል።
የኢህአዴግ ፓርላማ በዛሬው ዕለት የቀረቡለትን ምደባዎች ሲያጸድቅ ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ያቀረቡት የከፍተኛ ባለሥልጣናት ምደባ ከአቶ ደመቀ መኮንን በተጨማሪ ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን አካትቷል። ምደባው ከትግራይ ሁለት፣ አንድ ከኦሮሚያ፣ አንድ ከጉራጌ ብሄረሰብ የተካተቱበት መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለተመዳቢዎቹ ሲያስታውቁ ገልጸዋል።
ምደባው በደፈናው ሁሉም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የተካተቱበት ቢመስልም ጎልጉልን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች አስቀድሞ እንደተነገረው ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ ተግባራዊ ተደርጓል ለተባለው የቡድን አመራርማረጋገጫ ተደርጎ ተወስዷል። በጸደቀው ምደባ መሰረት ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አቶ ሙክታር ከድር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፣ ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር፣ አቶ ከበደ ጫኔ የንግድ ሚኒስትር እንዲሆኑ  ተደርጓል።
በዚሁ ምደባ መሰረት ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪ ሆነው ቢመደቡም ከደህንነት ጋር የተቆራኘውን የመገናኛና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትርነታቸውን አልተነጠቁም። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ሃላፊነታቸውን ስለመቀጠላቸው በይፋ ያልተገለጸው አቶ ሙክታር ከድር በምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ማሻሻያ ዘርፍ አስተባባሪና የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር ሆነዋል። አቶ ሙክታር ከኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንትነታቸው ተነስተው ለሁለት ዓመት ኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ያለ ስራ እንዲቀመጡ ተደርጎ የነበረው በመልካም አስተዳደር ችግርና አቅም ማነስ እንደነበር በማስታወስ አስተያየት የሰጡ “ምደባው ኦህዴድ የምክትል ጠ/ሚኒስትርነት ቦታ አገኘ በሚል የፖለቲካ ጨዋታ ለመጫወትና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነቱን ቦታ በመጠየቁ ለማስተዛዘኛ ነው” ብለዋል። በሌላ በኩልም አቶ ሙክታር ለባለሃብቱ አላሙዲ ቅርበት ያላቸውና በዚሁ ቅርበታቸው ሳቢያ ኦሮሚያ ክልል ባለሃብቱ ግብር እንዲከፍሉና የወሰዱትን ቦታ እንዲያለሙ ለማስገደድ ሲንቀሳቀስ አቶ ሙክታር በመቃወማቸው በኦህዴድ ስራ አስፈጻሚ በጉድለት መገምገማቸውን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ።
ደመቀ መኮንን እና ሃይለማርያም ደሳለኝ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የትምህርት ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጨምሮ ሶስት  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሚደገፉት አቶ ሃይለማርያም፣ አቶ መለስን ተክተው መስራት በጀመሩ ማግስት “የምንሰራውና የምንመራው በቡድን ነው” ባሉት መሰረት በሶስት ም/ጠቅላይ ሚኒስትሮች መታጀባቸው ይፋ ሆኗል። ጎልጉል ብዙም ትኩረት ያልተሰጣቸውን ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ጠ/ሚኒስትር ለማድረግ ታስቦ በአሜሪካን  ተጽዕኖና በቅድመ ማግባባቱ ላይ የኦህዴድን ድጋፍ ሊያገኙ ባለመቻላቸው አቶ ሃይለማርያም በነበሩበት እንዲቀጥሉ መደረጉ መዘገቡ ይታወሳል
በአዲሱ ምደባ የዶ/ር ቴዎድሮስን ቦታ በመረከብ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር የሆኑት ምክትላቸው ዶ/ር ከሰተብርሃን አድማሱ ናቸው። የአምስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ምደባ ይፋ በሆነበትና በዛሬው ዕለት አቶ ሃይለማርያም እንደ ወትሮው ሁሉ ንግግራቸውን የጀመሩት የአቶ መለስን ስም በማስቀደም ነበር። በዚሁ ንግግራቸው “ቀደም ሲል የተያዘው የአመራር መተካካት ከታቀደው በፊት ተግባራዊ ይደረጋል” ሲሉ ተደምጠዋል።
አቶ ግርማ ሰይፉ ላቀረቡት ተቃውሞ መልስ የሰጡት አቶ ሃይለማርያም ቀደም ሲል አቶ ግርማ ብሩ ይመሩት የነበረውን የንግድ ሚኒስቴር “የንግድ ምልክትና የንግድ ስያሜ እንኳን መለየት የማይችል እጅግ ኋላ ቀር” ሲሉ ነው ያንኳሰሱት። የዓለም ባንክ ሪፖርት ይፋ ባይደረግም አቶ ከበደ ጫኔ ችግር እንዳለ በማወቅ አዲስ አዋጅ በማዘጋጀትና ዘመናዊ አሰራር በመዘርጋት ተቋሙን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመለወጥ እየሰሩ ያሉ ሚኒስትር መሆናቸውን በመግለጽ አቶ ሃይለማርያም ተከራክረውላቸዋል። አዳዲሶቹ የፌደራል ስራ አስፈጻሚዎች ቃለመሃላ ፈጽመዋል። ኦህዴድ ያገኘዋል የተባለውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነት መቀመጫ ማጣቱን ተከትሎ አስተያየት ለማሰባሰብ ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ምደባው እንደተለመደው በአንድ ድምጸ ታቅቦ ነው የጸደቀው። በዕለቱ ምክንያቱ ባይታወቅም አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ አልተገኙም።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡