Sunday, December 9, 2012

ምሁራንና ‘አክቲቪስቶቻችን’ ሆይ ትግላችን ከመለስ ዜናዊ ወይስ ከሥርዓቱ?


ምሁራንና ‘አክቲቪስቶቻችን’ ሆይ ትግላችን ከመለስ ዜናዊ ወይስ ከሥርዓቱ? (ዳኛቸው ቢያድግልኝ)
አንዳንድ በትኩሱ ስሜታዊነትን እንዳዘሉ የሚሰነዘሩ ሀሳቦችን ትንሽ ፋታ መስጠትና ማስተዋል የታከለበት የታረመና የተስተክካለ
ሀሳብን መጠበቅ መልካም ምግባር ነው። የጠቅላይ አስለቃሻችን ነብስ ሙታኑን ከተቀላቀሉ በሁዋላ በአሳርና በመከራ ያልታሰበው ሰው
ሁሉም ወደሚያስበው ስልጣን ላይ መምጣቱን ተከትሎ የሚሰነዘሩት ሀሳቦች ግን አሁን ድረስ ስክነት አሳይተዋል ብዬ ላስብ
አልቻልኩም። ስህተቱ የኔ ከሆነ እዳው ገብስ ነው። የኔ አይነት ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ብዙ ከሆኑ ግን መመለስ ያለበት ጥያቄ አለ ማለት
ነው።
አቶ ኃይለማርያምን በተመለከተ ከፈጣሪ ጋራ ቀጥታ የግንኙነት መስመር አላቸው ከሚሉን አንስቶ ስለመልካም ባህሪያቸውና
የአስተዳደር ችሎታቸው የሚነግሩንን ሰዎች የተለያዩ መድረኮች አስተናግደዋል። ፍትህን እውነትንና ነጻነትን በምድር፣ ሰማያዊ አምላክን
ደግሞ ለነብሱ የያዘ ሰው ራሱ ተኩሶ ባይገድል እንኳን በአባሪነትና በተባባሪነት ወንጀል ስሙ ሊነሳ የግድ ነውና እንደምን ሆኖ
መልካሙ ሁሉ እንደተቸራቸው ማሰብ ይከብዳል። በአንድ ስርዐት ውስጥ ያገለገለ ሁሉ የግድ ወንጀለኛ ነው ለማለት ፈጽሞ አይደለም።
ነገር ግን የፖለቲካ ስልጣን ይዞ ቁንጮ ሆኖ የተቀመጠና በግድ ያልተመደበ ሰው እሺ ወይም እምቢ የማለት መብት አለውና
የማይጠየቅበት ምክንያት የለም። እራሴን ለማዳን ሌሎቹን ማደን ግዴታዬ ነበር የሚል ካለ የፍትህ አካል የሚዳኘው ጉዳይ ይሆናል።
የሀገራችን ልሂቃን፣ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞች በአብዛኛው ያቀርቡ የነበረው ሀሳብ ወያኔ ወይም የሽፍታው መንግሥት በጉልበቱ
ስልጣን ላይ የተቀመጠና ተልዕኮውም አፍራሽ የሆነ ነው የሚል ነው። የዚያ ማስረጃውም  ፍትህ የጎደለበት ጎጠኞች እንዳሻቸው
የሚፈርዱበትና አሸባሪዎች ተሸባሪዎችን እየከሰሱ ጭለማ ቤት የሚያጉሩበት መሆኑ ነው። ጥላቻ ባደረባቸው የህብረተሰብ ክፍል ላይ
የተነጣጠረ ጥቃት በመፈጸም የዘር ጥፋት የሚያስከትሉ ናቸው። የሀገሪቱን ሉዐላዊነት በማፍረስ፣ የተፈጥሮ ሀብትዋን በመመዝበር
ከፍተኛ ዘረፋ ማድረጋቸው፤ በሀገሪቱ ስም ከሚመጣው እርዳታ በላይ ለሁለትና ሶስት መጪ ትውልድ የሚተርፍ ብድር በመበደር
አገሪቱን ባለሀብቶች እንዳሻቸው የሚያደርጉበት አደገኛ ሁኔታ መፈጠር፤ የመናገር ብቻ ሳይሆን የማሰብም መብት መነፈግ ነው እያሉ
ድህረ ገጾችን አጣበዋል፣ ኮንፈረንስ ላይ ተናግረዋል፣ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ መፈክር አሰምተውበታል። ነገር ግን ለዚሁ ሥርአት ትንሽ ፋታ
እንስጠው የሚሉት ደግሞ ከዚሁ ወገን ያሉ መሆናቸው ግራ ያጋባል። ምክንያቱም የምንረካው በሰው ለውጥ ወይስ በሥርአት ለውጥ?
ለኃይለማርያም የምንሰጠው ፋታ ለሥርዓቱ የሚሰጥ ፋታ አይደለምን? የሚለው ጥያቄ መመለስ ይገባዋልና ነው።
በዚህ ጉዳይ ውስጥ መሪና ዋናው ተዋናይ ከጠቅላይ አስለቃሹ ቀጥሎ የትግራይ ተገንጣይ ቡድን ነው። አቶ ኃይለማርያም በዚህ ቀመር
ውስጥ ምንም ኃይልና ተደማጭነት ያልነበረው ግለሰብ ነው። የፖለቲካ ጡንቻም ያለው ግለሰብ አይደለም። አቶ ኃይለማርያም
እውቀቱን ያሰመረበት ጽሁፍ፣ ስለሀገሩ ያለውን ስሜትና እውቀት እንኳን አደባባይ የተናገረበት ነገር አላየሁም። ለሕዝብ የተበተነን ሰለ
አቋሙም ሆነ ፖለቲካ ዝንባሌው የሚታወቅ ነገር የለም። የሚታወቀው ነገር የሥርአቱ አሻንጉሊት መሆኑ ነው። ሀገሬ ኢትዮጵያ ብሎ
ለኢትዮጵያውያን በሙሉ ያለውን ፍቅርና መልካም ምኞት የገለጸበት አጋጣሚ ስለመኖሩ የሚታወቅ ነገር ትንሽ ነው። አስተዳደሩ ደግ
ስም ያልነበረው አሁንም ተቀባይነት የሌለው ሰው ነው። ታድያ ምን ለመጠበቅ? ምን ለውጥስ በማለምና ምንስ የፖለቲካ ስሌት
በማስላት ነው ፋታ እንስጣቸው ራሳቸውን እስኪሆኑ እንጠብቃቸው የሚለው ምርቃት አይሉት እርግማን የሚነገረን? ታክቲካዊ
አይሉት ስትራቴጅያዊ ምክር የሚሰጠን ወደ ምን አይነት ውጤት እንዲያንደረድረን ይሆን?
ምሁራኖቻችንና የፖለቲካው ሞተረኞች ትግሉን ከስርአቱ ላያ ሳይሆን ከመለስ ጋር ብቻ በማድረግ መልሰው እስኪደራጁና እኛን
እስኪያንጫጩ ዝም እንበል ማለት ለኛ የተመቸን ተቃዋሚነት እንጂ አሸናፊነት አይደለም አይመስልብንም? የተንገዳገደን ሥርአት
ለመጣል ትግል ከማድረግ ይልቅ ትኩረቱ የነበረው አቶ ኃይለማርያም ቢሮ መግባት አልቻሉም፣ ቤተመንግስት አልገቡም ትራፊክ
አጨናነቃቸው የሚል ፕሮፓጋንዳ ነው ስንሰማ የነበረው። ቤተመንግስቱ እኮ ቀድሞውንም ቢሆን አይገባውም ነበር። ኖረበትም
አልኖረበትም የሚያመጣው ለውጥ የለም አይኖርምም። መለስ ትልቅ ሀይል ነበር አዎ? ፈላጭ ቆራጭ ነበር? ትክክል። የመለስ ሞት ግን
ትግሉን አጠናክሮታል? እንዲያውም። ጉልበቱን አጠናክሮ ለትግል የተበራታ ሀይል በርክቶአል? ምንም። የተደበቁና ዝም ያሉ ሰዎች
መድረክ አጨናንቀውበታል? አለን አለን ብለዋል? አዎን እስኪታከተን ድረስ። አሁንስ አሉ? ጋደም ብለዋል። ወያኔ አቶ ኃይለማርያምን
ይዞ እየተደላደለ ነው? በትክክል። ታድያ አቅጣጫችን ምንድን ነው? የማሸነፍ ተስፋ ሕዝባችን ውስጥ እየታየ ነው? እና የኛ ልሂቃን
እስከመቼ ነው ለኃይለማርያም ፋታ እንድንሰጠው የሚነግሩን?
አቶ ኃይለማርያም ስልጣን ላይ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ስዎች ተፈናቅለዋል? በመቶ ሺህዎች። ቤቶች ፈርሰዋል? አዎን በቡልዶዘር!!
ታሪካዊ ቦታዎች ተደፍረዋል? አዎ የአቡነ ጴጥሮስና የሚኒሊክ ሀውልት ሊፈርሱ መሆኑን ሰምተናል። መለስ ትግራይን የማሳደግ
ስትራቴጂ መንደፉ ይፋ ሆኖአል? አዎ። ኃይለማርያም የመለስ ዜናዊ ራዕይ አስፈጻሚ ነኝ ብሎናል? አዎ በኩራት። አፈናና እስር
ተንሰራፍቶአል? በሚገባ። ጋዜጠኞችን አሸባሪዎች ብለዋል? አዎን። ኃይለማርያም አደባባይ እግዚአብሄርን ከጠራበት ለመለስ ዜናዊ
ፍጹማዊና ዘለአለማዊነት የመሰከረበት አይበልጥም? እንዴታ!! ታድያ የምንጠብቀው ምንድን ነው?
ትግላችን ከዘረኛውና ከአፍራሹ ሥርዓት ጋር ከሆነ አዘናጊ ምክሮች መቅረባቸውና ወደ ዝምታ መመለሱ የስቃይ ቋጠሮን ማጥበቅ ነው
እላለሁ። ምሁራንና ፖለቲከኞች ሆይ በሀሳባችሁ እንዳሰራችሁን በእውቀታችሁ ደግሞ ፍቱን።