Friday, January 25, 2013

ዳዊት ከበደ እየበራ ነው እየጠፋ!?


ዳዊት ከበደ እየበራ ነው እየጠፋ!?

አቤ ቶኪቻው
ዳዊት ከበደ እየበራ ነው እየጠፋ!? የቀድሞው አለቃዬ እና የአሁን ወዳጄ ዳዊት ከበደ ሰሞኑን አወዛጋቢ ሆኖ ሰንብቷል። ለምን አወዛገበ? ምን አወዛገበ? እንዴት አወዛገበ? ማንን አወዛገበ…? ወዘተ የሚሉትን ሁሉንም ዘርዝሬ መዝለቄን እንጃ ግን እስቲ ትንሽ ነካ ነካ ላድረግማ፤
ባለፈው ጊዜ ዳዊት ከበደ ስለ ኢትዮ ሚዲያው አበርሃ የፃፈውን ወቀሳ በአውራምባ ታይምስ ድረ ገፅ ላይ አንብቤ ነበር። በኢትዮ ሚዲያ ላይ ስለ ዳዊት ከበደ የወጣውን ፅሁፍ አላየሁትም። የዳዊትን ምላሽ ግን አልወደድኩትም። ይህንን ለዳዊትም ነግሬዋለሁ። ሳስበው ዳዊት ያንን ፅሁፍ ሲፅፍ ክፉኛ ተበሳጭቶ እንደሆነ እገምታለሁ። ምን መገመት ብቻ በደንብ አውቂያለሁ እንጂ…በተናደድን ጊዜ የምንወስናቸው ውሳኔዎች ብዙ ግዜ መልከ መልካም አይሆኑም። ወይም ውጤታቸው አያምርም። በብስጭት ሲወሰን እንኳን ሌላው ቀርቶ ራስን ማጥፋት እንኳ አይሳካም። ለሁሉም ነገር ስክነት ያስፈልጋል። በስክነት ውስጥ ብስለት አለ። በጥድፊያ ውስጥ ግን ያለው ጥፊያ ነው መጥፋት እና ማጥፋት።
ይህ በሆነ በስንተኛው ቀን እንደሆነ እንጃ እንደ ገጠር ቤተክርስቲያን ሰንበት ሰንበት ብቻ የሚከፈተው አባመላ የተባለ ፓልቶክ ሩም ዳዊት ከበደን ይዞ ባለፈው ቅዳሜ ብቅ ብሎ ነበር። ወዳጄ ዳዊት ከበደ ወደዚህ ፓልቶክ ሩም ለቃለ ምልልስ ሲሄድ በፊት ከነበረው አቋሙ በአንዳች ምክንያት ለውጥ እንዳደረገ ተገንዝቤ ነበር።
ምን አይነት አቋም…!?
ከዚህ በፊት አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ እየሰራን ሳለ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለቃለ ምልልስ ቢጠራው እምቢኝ ብሎ እንደነበር አስታውሳለሁ። ዛሬ ግን የኢህአዴግ ዋነኛ አቀንቃኝ የሚባል ፓልቶክ ሩም ለቃለ ምልልስ ሲጠራው “ምን ችግር አለው” ብሎ ሄዷል። ይሄ በጣም ያስደሰተኝ ለውጥ ነው። ጥያቄዬ ለውጡ የመጣው በብስጭት ነው ወይስ በብስለት ነው? የሚለው ነው። መልሱም እኔው ዘንድ አለ። ዳዊት የአቋም ለውጥ ያመጣው በብስጭት ነው።
ዴቭ በዚህ ፓልቶክ ሩም ሁለት ነገሮችን አንስቷል። አንደኛው፤ በውጪ ሀገር ያሉ የተቃዋሚው ፓርቲ አመራሮች የመፃፍ ነፃነቴን ተጋፉት የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ትግሬ ስለሆንኩ በውጪ ሀገር ባሉት ተቃዋሚዎች ዘንድ በጥርጣሬ አይን እየታየሁ ነው። የሚል ነው።
ሁለቱም ነገሮች ቢሆን ተደርገው ከሆነ በእውነቱ በተቃዋሚዎቻችን እጅጉን ተስፋ ቆርጠን ፍራሽ አውርደን ልቅሶ መቀመጥ አለብን። በተለይም እዚህ ውጪ ሀገርም የፕሬስ አፈና የሚደረግብን ከሆነ በተለይ ከኢትዮጵያ ሸሽተን የመጣን ሰዎች ድጋሚ ሸሽተን ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ሊኖርብን ነው ማለት ነው።
ለማንኛውም ዳዊት በዚህ የተነሳ ብስጭቱን ገልጿል። እኛም “ጎበዝ ዳዊት” ብለን አሞካሽተን ችግሩ ግን ብለን እንቀጥላለን…
ችግሩ ግን ዳዊት በቃለ ምልልሱ ወቅት አባ መላ የተባለው ጠያቂው በቀደደለት ቦይ ዝም ብሎ ሲፈስለት መመልከቴ ነው። ይሄኔ ነው ዳዊት እየጠፋ ይሆንን!? ስል ሰጋት የገባኝ።
ነገር ቢያበዙት በአህያ አይጫንም እንዲሉ አንድ ለምሳሌ ላንሳ፤
ጠያቂው አባ መላ “እስክንድር ነጋ በአሸባሪነት ከተሰየሙ ድርጅቶች ጋር ሲፃፃፍ ተይዞ ለምን ታሰረ? የሚሉ ሰዎች ዛሬ ግኡሽ አበራ በፌስ ቡክ ላይ ስሜቱን በመግለፁ ሲቃወሙ አግባብ ነው ትላለህ?” ብሎ ሲጠይቀው የዳዊትም መልስ ለመስማት ጆሮዬን አቆምኩ ወዳጄ ዳዊትም “ልክ ነህ!” ብሎ ገና ሲጀምር ታመምኩኝ።
እንደኔ እምነት እና እንደ አቃቤ ህግ ማስረጃ እስክንድር ነጋ ከአሸባሪ ቡድን ጋር ኢሜል መለዋወጡን የሚያስረዳ ነገር አላየንም። እንደኔ እምነት እስክንድር ነጋ የታሰረው ሀቅን ስለፃፈ ብቻ ነው። እንደኔ እምነት ዳዊት ከበደም የተሰደደው ሀቅን ስለፃፈ ብቻ ነው። እናም ወዳጃችን ዳዊት ጠያቂው አባ መላ በመላ ወደ ስርጡ ሲወስደው ሰተት ብሎ ሲሄድለት አየሁ። ይሄኔም ሰጋሁ ዳዊት እየጠፋ ይሆን!?
በጥቅሉ ዳዊት ከፍቶታል። ጥሩ ነው መከፋት። “ብሶት የወለደው ጀግናው የኢህዴግ ሰራዊት!” እንዲሉ ብሶት የለውጥ መነሻ ነው። ግን ምን አይነት ለውጥ!?
ዳዊት የትግራይ ተወላጅ ስለሆንኩ ተቃዋሚ ስለመሆኔ በጥርጣሬ ታየሁ እንደውም ተቃዋሚ አይደለሁም የማንም ሳይሆኑ መኖር ይቻላል ብሎናል።
ድሮውንም በግሌ ዳዊት ከበደ ተቃዋሚ ነው ብዬ አላምንም። ልክ እኔ ተቃዋሚ እንዳልሆንኩት ማለት ነው። መንግስትን መተቸት ተቃዋሚ መሆን አይደለም። ለገባው መንግስት እንደውም ትችት ደጋፍ ነበር። የእኛ መንግስት የገባው ሳይሆን ግራ የገባው በመሆኑ፤ ደጋፊ አልፈልግም ብሎ አባረረን እንጂ…!
በመጨረሻም፤
እንደኔ እምነት የትግራይ ተወላጆች ተቃዋሚውን ዳዊት በሚያይበት መነፅር እያዩ ከሆነ በእውነቱ ሀገራችን ትልቅ ኪሳራ ላይ ናት።
አሁንም እንደኔ እምነት ተቃዋሚዎች የትግራይ ተወላጆችን፤ ዳዊትን በሚያዩበት መነፅር እያዩ ከሆነ ትልቅ እብደት ውስጥ ነን!