Thursday, May 16, 2013

አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ኢትዮጵያና የአፍሪካ አንድነት/ኅብረት


አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ኢትዮጵያና የአፍሪካ አንድነት/ኅብረት

በፍቅር ለይኩን
(befikir12@yahoo.com/fikirbefikir@gmail.com)
Haile Selassie was known as a child as Lij Tafari Makonnen
‹‹ኢንሳክሎፒዲያ ብሪታኒካ›› ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ባቀረበው አጠር ያለ ጽሑፍ እንዲህ ብሏል፡- ‹‹Haile Selassie played a very important role in the establishment of the Organization of African Unity in 1963.››
ዕለታዊው የአዲስ ዘመን የወርኻ ግንቦት 15 ቀን 1955 ዓ.ም ዕትሙ በፊት ለፊት ገጽ ላይ፣ ‹‹ሠላሳ የአፍሪካ መሪዎች በተገኙበት ጉባኤ በአፍሪካ አዳራሽ ተከፈተ፡፡ ግርማዊ ጃንሆይም የጉባኤው የክብር ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመረጡ፡፡›› በሚል ዐቢይ ርዕስ ዜናና ሰፊ ሐተታን ይዞ ወጥቶ ነበር፡፡
የሰኞ ማለዳው የግንቦት 19 ቀን 1955 ዓ.ም የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ደግሞ በርእሰ አንቀጹ፣ ‹‹የካዛብላንካና የሞኖሮቪያ የሌሎችንም ብሎኮችና ቻርተሮች ሠርዞ የአፍሪካ አንድነትን የሚመሠርተው የአፍሪካና የማላጋሲ አገሮች ድርጅት ቻርተርግንቦት 17 ቀን ለግንቦት 18 ቀን አጥቢያ 1955 ዓ.ም. ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ45 ደቂቃ ላይ በአፍሪካ አዳራሽ ውስጥ ተፈርሟል፡፡ በአራቱ ቀን ጉባኤ ፍጻሜ አዲስ የአፍሪካ ታሪክ፣ አዲስ የዓለም ታሪክ ተጽፏል፣ ተመዝግቧል፡፡›› ሲል የምስራቹን ዜና አስነብቧል፡፡
የትላንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት የ50ኛ ዓመቱን የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ አገር አቀፍና አኅጉር አቀፍ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅቱን ከጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በተለይም ደግሞ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መመሥረት ግንባር ቀደም ሚና ባላትና ታላቅ አስተዋጽኦ ባደረገችው፣ የኅብረቱም ዋና መቀመጫ በሆነችው በአገራችን ኢትዮጵያ የበዓሉን ዝግጅት የደመቀና ልዩ ለማድረግ ሽር ጉድ እየተባለ ነው፡፡
ይህን በዓልም ባማረና በደመቀ ሁኔታ ለማክበር ራሱን የቻለ የበዓል ዝግጅት ሴክረታሪያት ቢሮ ተቋቁሞ፣ የአፍሪካ ኅብረት የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓሉን ዓመቱን ሙሉ ለማክበር፣ የተለያዩ ዝግጅቶችን ቀርጾ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ አይተናል፣ ሰምተናል፣ አውቀናልም፡፡
ከወራት በፊትም በመዲናችን በአዲስ አበባ ዋና ዋና ቦታዎችና አደባባዮች ላይ ‹‹I am African. I am the African Union›› የሚሉ የአፍሪካ ሕዝቦችን ማንነት፣ ታሪክ፣ ቅርስና ባህል የሚያንጸባርቁ፣ የአፍሪካዊነትን ስሜት፣ ኩራትና ወኔ የሚቀሰቅሱ ፖስተሮችን አይተናል፡፡ ከዑራኤል ወደ እስጢፋኖስ በሚወስደውም መንገድ ላይም የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ያቋቋሙ የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ የሆኑ አባቶች ምስልም በትልቁ ተሰቅሎ አይቻለሁ፡፡ ይህ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መልካም ሊባል የሚችል ነው፡፡
ለወደፊቱም በዓሉ በተለያዩ መጠን ሰፊ በሆኑ ዝግጅቶች እንደሚከበርና በበዓሉም ላይም የአፍሪካ አገራት ርዕሳነ ብሔራት፣ ተወካዮችና ባለ ሥልጣናት፣ ዓለም አቀፍ መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለ ሙያዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ደራሲያን፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች … ወዘተ በሚሳተፉበት በደመቀ ሁኔታ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የበዓሉ ዝግጅት ኮሚቴ በተደጋጋሚ አሳውቋል፡፡
በዚህ ጽሑፌ ከሰሞኑ መላው አፍሪካና አፍሪካውያን፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና እንዲሁም በአጠቃላይ የአፍሪካ ወዳጆች፣ የመንግሥታቱ ድርጅት፣ የተለያዩ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ታዋቂ ሰዎች አብርውን በደስታ ሊያከብሩት እየተዘጋጁ ስላለው የአፍሪካ ኅብረት የ50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ስናወራ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ትልቅ ቁም ነገር አለ፡፡
ይኸውም በዚህ በዓል ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን ትልቅ መሥዋዕትነት የከፈሉትንና ስማቸውን በወርቅ ቀለም በታሪክ ማሕደር የጻፉትን አፍሪካውያን አባቶቻችንን ማስታወስ የሚገባን ይመስለኛል፡፡ ይህ ጽሑፍም ለትላንትናው አፍሪካ አንድነት ድርጅት ለዛሬው የአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን የታገሉትን የፓን አፍሪካ አቀንቃኝ አባቶቻችንን ታሪክ በተከታታይ በአጭሩ ለማቅረብ ይሞክራል፡፡
ይህ ጹሑፍ የአፍሪካ ኅብረትን የ50ኛ ዓመት ወርቅ ኢዮቤልዩ በዓል ምክንያት በማድረግ በቅድሚያ የአፍሪካ አባት፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማትና የጥቁር ሕዝብ የነጻነት ዓርማ፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቋቋምና በሂደትም ለኅብረቱ እውን መሆን ትልቁን የመሠረት ድንጋይ ስላስቀመጡት ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ ታሪክ፣ ፖለቲካዊ ሰብእና፣ በአፍሪካውያንም ሆነ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ስለነበራቸው መወደድ፣ ተቀባይነትና ታላቅ ክብር በአጭሩ በማዘከር የታሪክ ማስታወሻውን አሐዱ ብሎ ይጀምራል፡፡
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ስለ አፄ ኃ/ሥላሴ መንግሥት ታሪክ በእሳቸው ዘመን ከነበሩ ከተራው የኅብረተስብ ክፍል ጀምሮ እስከ ታላላቅ ባለ ሥልጣናትና የሃይማኖት አባቶች፣ ዲፕሎማቶች፣ የውጭ አገር መሪዎች፣ ታላላቅ ሰዎችና ፖለቲከኞች በቃል ከተናገሩት፣ በጽሑፍ ካስቀመጡት፣ በግል ማስታወሻዎቻቸው ከተዉልን፣ እንዲሁም የአጼ ኃ/ሥላሴንና የኢትዮጵያን ታሪክ በተመለከተ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጸሐፍት በመጻሕፍቶቻቸው ካሰፈሯቸው መረጃዎች በመነሣት ነው ይህን አጠር ያለ የታሪክ ማስታወሻ ጽሑፍ ያዘጋጀሁት፡፡
በአጭር ቃል የዚህ ተከታታይ ታሪክ አቅራቢ የአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመን ጣእሙንም ሽታውንም አልደረስበትም፡፡ በእሳርቸው ዘመንም አልታሰበም፣ አልተፈጠረምም፡፡
ይሁን እንጂ እንደ ታሪክ ተማሪነቴና ባለሙያነቴ የኢትዮጵያን ታሪክ በሰፊውና በሚገባ ማጥናት ከጀመርኩበት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንስቶ አሁን እስካለሁበት የትምህርት ሕይወቴና የሥራ ልምዴ እንዳስተዋልኩት፣ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ አፄ ኃ/ሥላሴ በአብዛኛው በአዎንታዊ መልኩ የሚገለጹበት ታሪክ፣ በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዘንድም አንቱታን ያተረፉበትን ዝናና ክብር እንዲጎናጸፉ ያደረጋቸው በሳል የሆነ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ሰብእና እንዳላቸው ነው የተረዳሁትና ያስተዋልኩት፡፡
በስድስት ዓመታት ውስጥ ለሁለት ጊዜ ‹‹Man of the Year›› የዓመቱ ምርጥ ሰው በማለት የለንዶኑ ታይምስ መጽሔት የመረጣቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ ከፍ ያለ ሰብእና የነበራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ታላቅ መሪና አባት የሚታዩ የተዋጣላቸው ዲፕሎማቲክ፣ እንዲሁም በዓለማችን ከሚገኙ ታላላቅ መሪዎችና ፖለቲከኞች ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የነበራቸው ኢትዮጵያዊ ንጉሥ እንደነበሩ የታሪክ ድርሳናትና ብዙዎች ሰዎች ይመሰክራሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ኃ/ሥላሴ ከሀያ በየሚበልጡ የክብር ዶክትሬት ድግሪዎችን ከተለያዩ አገራት መሪዎችና ዩኒቨርስቲዎች ተቀብለዋል፡፡ ምናልባትም አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከምትታወቀበት ድርቅ፣ ራብና የእርስ በርስ ጦርነት ባሻገር በአንጻራዊ መልኩም ቢሆን በአዎንታዊነት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የአገራችንን ስም በመልካም እንዲነሣ ምክንያት ከሆኑ የኢትዮጵያ መሪዎች መካከል አፄ ኃ/ሥላሴ አንዱ፣ ብቸኛውና ዋንኛው ናቸው ብል፣ ብዙም ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡
ይህን ኢትዮጵያን አዎንታዊ በሆነ መልኩ እንድትነሳ በማድረግ ረገድና ዓለም አቀፉ የፖለቲካ መድረክ የነበራቸውን ተቀባይነት፣ ክብርና ዝና እንዲሁም ለባለ ቃል ኪዳን አገሮችና በኋላም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መመሥረት፣ ለ50ኛ ዓመቱ የወርቅ ኢዮቤልዩ በዓሉ ዋዜማ ላይ ለሚገኘው ለአፍሪካ ኅብረት እውን መሆን፣ ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ የነበራቸውን ትልቅ ሚና የሚያስታውስ አንድ ያጋጠመኘኝን ታሪክ እዚህ ጋር ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡
እውቁ የነጻነት ታጋይ ኔልሰን ማንዴላና በርካታ አፍሪካውያን የነጻነት ታጋዮች ለ27 ዓመታት በተጋዙበትና በመንግሥታቱ ድርጅት፣ ዩኔስኮ ዓለም አቀፍ ቅርስ አድርጎ በመዘገበው በሮቢን ደሴት ሙዚየምና በደቡብ አፍሪካ የአርትና ካልቸር ደፓርትመንት የሚሰጠውን የስኮላር ሺፕ አሸንፌ፣ በተማርኩበት በኬፕታውኑ የዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ የድኅረ ምረቃ ትምህርት ቆይታዬ ከኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስና ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጋር በተገናኘ አንድ በእጅጉ ያስደነቀኝ ነገር ገጥሞኝ ነበር፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በዋነኝነት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲና በኬፕ ታውን ዩኒቨርስቲ በሚገኙ ደቡብ አፍሪካውያንና የሌሎች አፍሪካ አገሮች የተቋቋመ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ (የራስ ተፈሪያን) የተማሪዎች እንቅስቃሴ ኅብረት በሚል መጠሪያ የሚታወቅ በዩኒቨርስቲው ግቢ ቢሮ ተሰጥቶት የሚንቀሰቀስ ማኅበር ነበር፡፡
በነገራችን ላይ በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ዩኒቨርስቲዎች እንደታዘብኩት በፖለቲካና በሃይማኖት፣ እንዲሁም ኪነ ጥበብን፣ ባህልንና ታሪክን መሠረት አድርጎ የተቋቋሙና በነጻነት በዩኒቨርስቲው ግቢ ቢሮ ተሰጥቷቸው የሚንቀሳቀሱ በተማሪዎች የተቋቋሙ የተለያዩ ድርጅቶችና ፓርቲዎች ይገኛሉ፡፡
ታዲያ እኔ በተማርኩበት በዌስተርን ኬፕ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የግርማዊ ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ የተማሪዎች ኅብረት እንቅስቃሴ ቢሮ ውስጥ የእንቅስቃሴው ደጋፊዎችና አባላት የሆኑት ተማሪዎች ለኢትዮጵውያን የስኮላር ሺፕ ተማሪዎች ባቀረቡላቸው ጥያቄ መሠረት የአማርኛ ቋንቋን የሚያስተምሯቸው ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ ተማሪዎች ነበሩ፡፡
እነዚህ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ከእኔ ቀደምው ትምህርታቸውን በመከታተል ላይ ያሉ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ለምርምር ሥራ፣ ለልምድ ልውውጥና ለተጨማሪ ጥናት ወደ አውሮፓ በሄዱበት አጋጣሚ ለእነዚህ አፍሪካውያን ወንድሞቻችን ከአንተ በተሻለ ስለ ኢትዮጵያችን የሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ የነጻነት ተጋድሎና ቋንቋችንን ሊያስተምራቸው የሚችል የለም በማለት ከራስ ተፈራውያኑ የዩኒቨርስቲው ማኅበረሰብ ጋር አስተዋወቁኝ፡፡
ከዚሁ ማኅበር አባላት ተማሪዎቹ ጋር በተዋወኩበት በአጭር ጊዜ ውስጥ በሚገባ ለመግባባት ቻልን፡፡ ለጥቂት ወራት እነዚህ ወጣት ተማሪዎች የአማርኛ ቋንቋ ማስተማር ቆይታዬ እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ሃይማኖት … ወዘተ ባደርግናቸው ውይይቶች በርካታ ቁም ነገሮችን አንስተን እንነጋገር ነበር፡፡
በአብዛኛው የውይይታችን ማእክል ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ለፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ፣ ለአፍሪካ የፀረ-ባርነትና የፀረ-ቅኝ ግዛት የነፃነት ትግል፣  በደቡብ አፍሪካ ፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ ስለነበራቸው ጉልህ ሚናን በተመለከተ ነበር፡፡ በዚህ ውይይታችን ውስጥ ደግሞ ደጋግመው ከሚነሱት መካከል አፄ ኃ/ሥላሴ አንዱና ዋናው መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
እኔ እንደ ኢትዮጵያዊነቴና የታሪክ ባለሙያነቴ ስለ አገሬ ኢትዮጵያ ታሪክና ስለ መሪዎቻችን ካለኝ ግንዛቤና እውቀት ይልቅ እነዚህ አፍሪካውያን ተማሪዎች ስለ አኅጉራችን አፍሪካና ስለ አገሬ ታሪክ ያካፈሉኝ እውቀታቸውና ያላቸው መረዳት በጊዜው በእጅጉ ግርምትን አጭሮብኝ ነበር፡፡
እነዚህ ተማሪዎች ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ በጥቁር ሕዝቦች ታሪክ፣ ቅርስ፣ ባህልና የነጻነት ተጋድሎ ውስጥ ያላቸውን ማእከላዊ ስፍራን በተመለከተ የሚያስረዱ በቢሮአቸው ያሰባሰቧቸው መጻሕፍቶችና መዛግብቶቻቸው፣ የምስልና የድምፅ መረጃ ክምችቶቻቸው በእጅጉ ነበር ያሰደነቀኝ፡፡
ከዚህም በላይ ደግሞ ሌላው በእጅጉ ያስደመመኝ ነገር ቢኖር በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በሚገኘው የራስ ተፈሪያኑ ተከታዮች ማኅበር ቢሮ ግድግዳ አንድ ጎን በሁለት የታሪክ መስመር ተከፍሎ በተለያዩ ሰዎች ምስሎችና መረጃዎች አሸብርቆ ያየሁት Wall of Fame እና Wall of Shame የሚለው የቢሮው ግድግዳ ክፍል ነው፡፡
በዚሁ Wall of Fame እና Wall of Shame ወይም ‹‹የታሪክ ዕንቁዎችናየታሪክ አተላዎች›› ተብሎ በተከፈለው ግድግዳ ላይ ‹‹በዎል ኦፍ ››ምስላቸውና ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከተለጠፉት መካከል የአፄ ኃ/ሥላሴና የባለቤታቸው የእቴጌ መነን በመጀመሪያው ረድፍ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም በዓድዋው ዘመቻ የኢጣሊያንን ወራሪ ኃይል አሸንፈው አዲስ የጥቁር ሕዝቦችን አዲስ ታሪክ የጻፉት የአፄ ምኒልክ፣ እንዲሁም ከእንግሊዞች ጋር ተዋግተው ራሳቸውን የሠዉት የአፄ ቴዎድሮስ ምስሎችና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በዚህ ‹‹የታሪክ ዕንቁዎች›› የክብር ግድግዳ ላይ አፄ ኃ/ሥላሴ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በገፍ በወረረች ጊዜ በሊግ ኦፍ ኔሽን፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያቀረቡት አቤቱታና ንግግራቸው በልዩ ንድፍና በአገራችን ሰንደቀ ዐላማ አሸብርቆ በግድግዳው ላይ ይታያል፡፡ ‹‹የዎል ኦፍ ፌምን›› ግድግዳ ካስዋቡ የታሪክ ሰዎች ፎቶግራፎች በአብዛኛው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚሸቱት በዓይነትም በብዛትም እጅግ ልቀው ይገኛሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ‹‹በዎል ኦፈ ፌም›› የታሪክ መስመር ውስጥ ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ትልቅ ተጋድሎ ያደረጉ እንደ እነ ማርከስ ጋርቬይ፣ አፍሪካ አሜሪካዊው ማርቲን ሉተር፣ የፓን አፍሪካ አባቶች የጋናው ንኩርማ፣ የኬንያው ጆሞ ኬንያታ፣ ሴኔጋላዊው ሴዳር ሴንጎርና ሌሎችም የአፍሪካ የነጻነት ታጋዮችና መሪዎች በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማና በኃ/ሥላሴ ግንባር ቀደም አዝማችነት የክብር ግርግዳውን ተጋርተውታል፡፡
ሌላው አስገራሚው ነገር የንጉሡን የአፄ ኃ/ሥላሴን ልደትና የነገሡበትን ዕለት የራስ ተፈራውያኑ ማኅበር ተከታይ ተማሪዎች እንግዶችን ከውጭ ሁሉ ሣይቀር በመጋበዝ ጭምር የዩኒቨርስቲውን የተማሪዎች ማእክልንና የግቢውን ሜዳ በኢትዮጵያ ሰንደቀ ዓላማ፣ በኃ/ሥላሴና በባለቤታቸው እቴጌ መነን ፎቶ ግራፍ አሸብርቀውና በአፍሪካ የሬጌ ሙዚቃ ስልት አጅበው በታላቅ በሆነ የኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስ ቀናቱን ያከበሩ እንደነበረ ትዝ ይለኛል፡፡
የማስታውሰው በዩኒቨርስቲው የምንገኘው በጣት የምንቆጠር ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም በድርቅ፣ በራብና በእርስ በርስ ጦርነት ስማችን እየተነሳ የምንሳቀቅበትን ምስላችንን፣ እነዚህ የዩኒቨርስቲው የራስ ተፈራውያን ተከታይ ተማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት በግቢው ውስጥ የአገራችንን አረንዴ፣ ብጫና ቀይ ሰንደቀ ዓላማ ሰቅለው ሲያከብሩ ስናይ በአገር ፍቅር ናፍቆትና ትዝታ፣ በኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ስሜትና ኩራት ውስጣችን የተናጠበትን አጋጣሚ አልረሳውም፡፡
በእርግጥ የእነዚህ ተማሪዎች እንቅስቃሴና አካሄድ በአብዛኛው ሃይማኖታዊ መልክ ያለውና ኃ/ሥላሴን መለኮታዊ ሰብእና እንዳላቸው አድርጎ የሚያቀርብ ቢሆንም የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ከሃይማኖታዊ መልኩ ይልቅ አፍሪካዊነቱና ፖለቲካዊ አንድምታው በእጅጉ የጎላ ነው፡፡
እነዚህ ደቡብ አፍሪካውያንም ሆነ የሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተማሪዎች ልብም ሆነ በአብዛኛው ጥቁር ሕዝቦች ልብ ውስጥ ኢትዮጵያ የጥቁር ህዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ቅርስ፣ ሃይማኖት፣ ነጻነት ትልቅ ተምሳሌትና ማእክል ተደርጋ የምትወሰድ አገር ናት፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ባላት የሺህ ዘመናት የረጅም ዘመን ሥልጣኔ፣ ታሪክና ቅርስ የተነሣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ የሆነ የታሪክ እሴት ያላት አገር ለመሆን በቅታለች፡፡ በተለይም ደግሞ መላው አፍሪካንና የጥቁር ዘርን ሁሉ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያነቃነቀው ኢትጵያውያን በዓድዋ ጦርነት ያስመዘገቡት አንጸባራቂ ድል ኢትዮጵያን ከጥቁር ሕዝቦች ታሪክ ማማ ላይ እንድትወጣ አስችሏታል፡፡
ለአፍሪካ፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና በጃማይካና በካረቢያ ላሉ የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ትግል መለኮስ ይኸው የአድዋው ድል ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው፡፡ የእነ ማርከስ ጋርቬይና የትግል አጋሮቹ የጥቁር ሕዝቦች የነፃነትና የመብት ጥያቄ ውሉ የሚመዘዘው ከኢትዮጵያዊነት የነጻነት መንፈስ፣ የአባቶቻችን የአይበገሬነትና ቆራጥ የተጋድሎ ታሪክ ውስጥ ነው፡፡
የአፍሪካውያኑ የፓን አፍሪካ አቀንቃኞችና የፀረ ቅኝ ግዛት ታጋዮች የእነ ንኩርማ፣ የእነ ጆሞ ኬንያታ የአፍሪካዊነት ስሜትና ቆራጥ መንፈስ መፍለቂያ ምንጩም ይኸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ከተሸከሙት ክቡር የነጻነት ተጋድሎ አኩሪ ታሪክና ቅርስ የሚመዘዝ ነው፡፡
ከአፄ ምኒልክ የዓድዋው ድል በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኃያላኑ አገሮች እኩል የተሠለፈችው ብቸኛው የጥቁር ሕዝብ አገር ኢትዮጵያ ይህ ገናና የነጻነት ተጋድሎ ታሪኳ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከአውሮፓ እስከ ኤዥያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እስከ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ጃማይካና ካረቢያን ምድር ድረስ ዘልቆ ተሰምቶ ነበር፡፡
ይህ የኢትጵያዊነት የነጻነት መንፈስ ውሉ ሳይቋረጥ በአፍሪካውያንና በጥቁር ሕዝቦች ደም ውስጥ በሚገባ ተዋህዶ፣ በተባበረ ክንድ የጸናችና አንድ የሆነች አፍሪካ በዓለም መድረክ ከፍ ብላ እንድትታይ ደግሞ ትልቁን ሚና በመጫወት ረገድ አፄ ኃ/ሥላሴ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡
ይህን ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ኢትዮጵያና አፄ ኃ/ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽኦና ተደናቂ ሥራ በተመለከተ በወቅቱ በአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ላይ የተገኙት የናይጄሪያው ጠቅላይ ሚኒስቴር የሆኑት፣ ክቡር ሰር አል ሃጂ አቡበከር ታፌዋ ባሌዋ እንደሚከተለው ነበር ያሉት፡-
መላው የአፍሪካ መንግሥታት መሪዎችና የመንግሥታት ባለ ሥልጣኖች በአዲስ አበባ ላይ ሊገኙ ለመቻላቸው በግርማዊነትዎ ጥረት ስለሆነ በተለይ ለግርማዊነትዎ እጅግ ከፍ ያለ ክብር የሚያሰጥ ነው፡፡ በዚህ ጉባኤ ላይ አንድነት እንዲገኝ የምናደርገው ጥረት ወደፊት የኢትዮጵያን መናገሻ ከተማ የአዲስ አበባ ስም ደጋግሞ የሚያወሳ ስለሆነ የአዲሲቱ አፍሪካ ታሪክ የግርማዊነትዎን ስም በተቀዳሚው ገጹ ላይ አሳምሮ የሚያኖረው ለመሆኑ ጥርጥር የለበትም፡፡ 
አፄ ኃ/ሥላሴ በ1930ዎቹም ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽን አባል እንድትሆን በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ኢትዮጵያንም ብቸኛዋ አፍሪካዊትና የጥቁር አገር ሊግ ኦፍ ኔሽን አባል በማድረግ ጥረታቸውን በሚገባ አሳክተዋል፡፡
በኋላም በተባበሩት መንግሥታት ምሥረታ ስብሰባ ወቅትም ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዜቬልት፣ ከብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችልና ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ፕሬዝዳንት ጆሴፍ ስታሊን ጋር በያልታ ጥቁር ባሕር ልዩ ስብሳባ ላይ ተሣትፈዋል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጋራ ስምምነት መሠረትም በኮሪያ ልሣነ ምድር የኢትዮጵያን የሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ በዚህም አፄ ኃ/ሥላሴ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲታወቁ ትልቁን ሚና ተጫውተው አልፈዋል፡፡
ፍቅር፣ ወንድማማችነት፣ ሰላም፣ አንድነትና ኅብረት ለአፍሪካና ለአፍሪካውያንን ወሳኝና ተቀዳሚ ነገር መሆኑ የተረዱት አፄ ኃ/ሥላሴ አፍሪካውያን አባቶችን፣ ፖለቲከኞችንና መሪዎችን በማስተባበር የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም የላቀ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
በወቅቱ ድርጅቱ ሲቋቋም የነበሩ ሰዎች እንደመሠከሩት አፄ ኃ/ሥላሴ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የአፍሪካ መሪዎችን ጉባኤ ስብሰባ በመምራት፣ ይህ የአፍሪካውያን የወንድማማችነት፣ የአንድነትና የፍቅር ሰነድ ሳይፈረም ማንኛችንም ብንሆን ከዚህ ስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በጭራሽ አንወጣም በማለት የተኮራረፉና የተለያዩ ፖለቲካዊ ቁርሾ ውስጥ የገቡትን የአፍሪካ አገራት መሪዎችን በማግባባትና በማሸማገል ንጉሡ ኅብረቱ እውን እንዲሆን ታላቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡
የትላንትናው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የዛሬው የአፍሪካ ኅብረት በሁለት እግሩ እንዲቆም በማስቻል የኢትዮጵያ የሺህ ዘመናት ታሪክ፣ ሥልጣኔና ቅርስ፣ የቀደሙ አባቶቻችን ጽኑና አይበገሬ የሆነው የኢትዮጵያዊነት ብሔራዊ ኩራትና መንፈስ እንዲሁም ጥቁር ሕዝቦችን ሁሉ ያኮራውና አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲራመድ ያስቻለው የኢትዮጵያውያኑ የነፃነት ተጋድሎ፣ በባርነትና በቅኝ ግዛት ስር ይማቅቁ ለነበሩ ለአፍሪካ አገሮች ነፃነትና አንድነት እውን መሆን ትልቁን መሠረት ጥሏል፡፡
ይህን የኢትዮጵያንና የኢትጵያውያንን ታላቅ ታሪክ፣ ሥልጣኔ፣ ብሔራዊ ኩራትና የአባቶቻችንን አኩሪ የነፃነት ገድል ለዘመናዊው ዓለም በማስተዋወቅና ረገድ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኃ/ሥላሴ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ክቡር ስምና ዝናና የፈተረላቸውን በርካታ አኩሪ ስራዎችን ሠርተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል ዛሬ የ50ኛ ዓመቱን የወርቅ ኢዮቤልዩ ልደቱን ለማክበር ዋዜማ ላይ ያለውን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት/ኅብረት እንዲቋቋም ከሐሳብ ወይም ከጽንሱ አንስቶ እስከ ተግባራዊነቱ ድረስ የላቀ ተሣትፎ ነበራቸው ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ፡፡
ንጉሡ ቀዳማቂ አፄ ኃ/ሥላሴ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ባደረጉት የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው እንዲህ ነበር ያሉት፡-
በዚህ በዛሬው ቀን በዚህች በዋና ከተማችን በአዲስ አበባ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተካፋይ ለመሆን የመጣችሁትን የነፃ አፍሪካ አገር መሪዎች፣ ወንድሞቻችን በራሳችንና በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም ስንቀበል በጣም ደስ ይለናል፡፡ ይህ ዛሬ እኛ የአፍሪካ ነፃ መንግሥታት መሪዎች የምናደርገው ጉባኤ በዓለም ላይ እስካሁን ድረስ ተወዳዳሪ የለውም፡፡ የዚህን ታላቅ ጉባኤ መደረግና የመላው አፍሪካ አገሮች መሪዎች ተካፋይ በመሆን ለዚህች ክፍለ ዓለማችን በውስጧም ለሚገኙት ሕዝቦቻችን ላለን ጥልቅ አሳቢነት ዓይነተኛ ምስክር ነው፡፡ ባጭሩ ይህ ቀን ለአፍሪካና ለአፍሪካውያን በመላ ታሪካዊና ታላቅ ቀን ነው  ፡፡
የጊኒ ፕሬዝዳንት የነበሩት ሴኮ ቱሬም በአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ለአፍሪካ አንድነት ምስረታ ኢትዮጵያና ንጉሡ አፄ ኃ/ሥላሴ ያደረጉትን ታላቅ አስተዋጽኦና ሥራ በተመለከተ ሲናገሩ እንዲህ ነበር ያሉት፡-
 ኢትዮጵያዊ ታላቅ ሕዝብ ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ነፃነት በጀግንነት የተዋጋ፣ ነፃነትም ቋሚ እንዲሆን፣ ሕዝቦቻችን ያለ ምንም የውጭ መንግሥታት ተቆጣጣሪነትና ጣልቃ ገብነት በተገቢ ሥልጣናቸው እየተመሩ የገዛ ራሳቸውን ዕድል እንዲመሩ ያላቸው ሥልጣን እንዲጠበቅላቸው የደከመ አፍሪካዊ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ በንጉሠ በአፄ ኃ/ሥላሴ አስተባባሪነትና መሪነት፣ የአፍሪካውያኖችም ጉባኤ የተደረገው በኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ስለሆነ፣ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ አሁንም የበለጠ ከአፍሪካ ታሪክ ጋር የተሳሰሩ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ወደፊት በአንድ አኅጉር ሕዝቦች ፈቃድ ተነሳስቶ በሚመራው የዕድገት ፍላጎትና ሥራ ሁሉ ሳይቋረጥ ስማቸው ተያይዞ የሚኖር ይሆናል  ፡፡
ለአፍሪካ አንድነት እውን መሆን ከአገራችን ኢትዮጵያና ከአፄ ኃ/ሥላሴ ጋር አብሮ ስማቸው የሚነሡ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ድርጅቱንም በጸሐፊነት ያገለገሉ ባለ ታሪክ የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ እነርሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስተሩ አቶ ከተማ ይፍሩና የድርጅቱ የመጀመሪያ ዋና ጸሐፊ ሆነው የተመረጡት አቶ ክፍሌ ወዳጆ ናቸው፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ አቶ ከተማ ይፍሩ በመላው አፍሪካ አገራት በመዞርና መሪዎቹን ወደ ጉባኤው እንዲመጡ በመጋበዝና በማግባባት ታላቅ የሆነ ሚና ተጫውተዋል፡፡ አንዳንድ ጸሐፊዎችና ታሪክ አዋቂዎች እንደሚሉትም አቶ ከተማ ይፍሩ ከመሪዎቹ ማረጋገጫ እስከሚያገኙ ድረስ ወደ አገራቸው መሄድ እንደማይችሉ በመግለጽ አፍሪካውያን መሪዎች በስብሰባው ላይ እንዲገኙ በማድረግ ትልቅ ጥረት ማድረጋቸውን ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡
የዛሬውን መጣጥፌን ከማጠናቀቄ በፊት በቀጣይ ጽሑፌ ስለ ፓን አፍሪካ አመሠራረትና፣ በፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ውስጥ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውን ድርሻ ምን እንደነበር ከታሪክ ማሕደር በማጣቀስ ለመጻፍ እሞክራለሁ፡፡ በጽሑፌም ቀንደኛ ፓን አፍሪካኒስት ስለነበረው የጋናው ዶ/ር ንኩርማ በጥቂቱ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡
የዛሬውን አጭር መጣጥፌን ኢትዮጵያ፣ ጀግና ልጆቿና ንጉሠ ነገሥቷ የነበሩት አፄ ኃ/ሥላሴ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅትና መመሥረትና በኋላም ለኅብረቱ እውን መሆን ያበረከቱትን ትልቅ አስተዋጽኦ ያዘከርኩበትን አጭር የታሪክ ማስታወሻ፣ አፄ ኃ/ሥላሴ በአዲስ አበባ ላይ በተደረገው የግንቦት 15ቀን 1955 ዓ.ም. የአፍሪካ መሪዎች መክፈቻ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ታሪካዊ ንግግራቸው ጽሑፌን ልቋጭ፡፡
ዛሬ የገጠመን ዕድል በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ መቼም ያልተገኘ ትልቅ ዕድል ነው፡፡ በፊታችን የተደቀኑት ችግሮች ያንኑ ያህል ከፍ ያሉና ከባድ ናቸው፡፡ ታሪክና ጊዜ የጣሉብን ከፍተኛ ኃላፊነት ሁላችንም ረጋ ብለን እንድናስብና እንድናመዛዝን ያስገድደናል፡፡ የተነሳንበትን ከፍተኛ ተግባር በመልካም አከናውነን ብንገኝ ስማችንና ተግባራችን በታሪክ መልካም ስም ይኖረዋል፡፡ ተግባራችንን ሳንፈጽም ብንቀር ግን ይታዘንብናል፡፡ ስለዚህ እምነታቸውን የጣሉብንን ሕዝቦቻችን በሚመጡት ጊዜያቶች ውስጥ ከእኛ የሚጠብቁትን ሁሉ ለመፈጸም እንዲያበቃን ሁሉን የሚችለውን ፈጣሪያችን ጥበብንና አስተዋይነትን እንዲሰጠን እናምነዋለን፣ እንለምንዋለን፡፡
ክብር ለአፍሪካ አንድነት ለደከሙ አፍሪካውያን አባቶቻችንና ጀግኖቻችን ሁሉ!
ሰላም! ሻሎም!