Saturday, February 22, 2014

የኢትዮጵያን ገጽታ አደባባይ ያወጣው አውሮፕላን አብራሪ ሃይለመድህን አበራ (ዳኛቸው ቢያድግልኝ)

ልማታዊ ግስጋሴ እስከ ግድበ ህዳሴ በደረሰበት ታሪካዊ ወቅት፣ ኢትዮጵያ በፈጣን የእድገት መስፈርት ውስጥ ከአፍሪካ አንደኛ ከአለም ከቻይና ቀጥሎ ሁለተኛ ነች እየተባለ በመሪዎቿ በሚነገርላት ጊዜ። አሸባሪዎችን ከመነሻቸው ለማምከን በአይነቱ ልዩ የሆነ የአንድ ለአምስት አደረጃጀት የሰዎችን ድርጊት ብቻ ሳይሆን አስተሳሰብን ጭምር የሚመረምር ምትሃታዊ ሃይል ተደራጅቶ ባለበት ሁኔታ የዴርቶጋዳን ልብወለድ መሰል ነገር መታየቱ ብዙዎችን አስደምሟል። ለመሆኑ የዛሬ ልጆች ጀግና አይደሉም የሚል ማን ነው?
በውጭ ሃገር የዜና ማሰራጫዎች ወሬው እንደተሰማ አስተያየት ለመክተብ ጣታቸው እንደ ክላሺኒኮቭ ፊደል የሚያንጣጣ ሁሉ ፓይለቱ ጥገኝነት ለማግኘት ብሎ እንዲህ ማድረጉ አሳፋሪ ነው፣ አላዋቂ አፍሪካዊ መሆን አለበት፣ ይቀጣ! ይቀጣ! የሚሉ ሃረጎች በርክተው ነበር። እነዚህ በአብዛኛው አፍሪካ ማለት አንድ ሃገር የሚመስላቸው የእውቀት ብርሃን የጨለመባቸው ናቸውና ምንም ማድረግ አይቻልም።Ethiopian Airlines plane Co-Pilot Hailemedehin Abera Tagegn.
ሁለተኛው ሰሞኑን ነገረ ስራው አያምርም ነበር የሚልና አእምሮው ለየት ያለ ነገር የሚያሳየው ‘ሺዞፍሬንያ’ እሚሉት ነገር እየጀማመረው ነበር የሚለው ነው። እህት ሁሉም ይስማልኝ በማለት በመረጃ መረቦች በተነች የሚባለውን ያነበበ ሰው ለበረራ ብቁ ነው የሚለውን ፈቃድ ሰጪም ወፈፍ ያደረገው መሆን አለበት ቢል አላጋነነም። ይሄ እብድ እየመሰለ ሲሰልል የኖረ ወያኔ ወፈፌነትን በጣም ስለተለማመደው አማኑኤል ሆስፒታልን የደህንነት ማሰልጠኛ ኮሌጅ አድርጎ ቢመለከት አይፈረድበትም ብለን መሳቅም መብታችን ነው። ቁም ነገሩ ግን የበረራውን ደህንነት ለማስጠበቅ የአብራሪዎችንምጤናና ደህንነት መከታተል ስለሚገባው ያንንም ማድረግ ባለመቻሉ ወደ ትልቅ ስህተት ራሱን እየጨመረ ነው። በዚህ ሁኔታ ምን  ያህል ወፈፌ ፓይለቶች ይኖሩ ይሆን ብሎ መጠየቅም ያስፈልጋል። ከሆነም ምን አይነት አስተዳደር ቢኖር ነው ጨርቅ ጥሎ የሚያሳብደው፣ ሃገር ጥሎ የሚያስኮበልለው ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው። የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ እንደሚባለው በአንድ-ለአምስት ተጋግዞ መዋሸት ይቻል ይሆናል ከዚያ መረብ ውጪ ላለነው ግን አስቂኝ ትዕይንት ነው።
እኔ አውሮፕላኑን ጠለፈ የሚለው አገላለጽ እጅግም አልተመቸኝም።  ረዳት አብራሪው ድምጼ ይሰማልኝ በማለት ማቆም የማይገባው ስፍራ ላይ አውሮፕላኑን አቆመ ለዚያውም ያለ ፍርሃትና ሽብር መደናገጥና መርበትበት ተሳፋሪውም ኮሽታ ሳይሰማ። አቅጣጫ በቀየረው አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ሰራተኞች ለተሳፋሪዎቻቸው ቡና ሻይ እያቀረቡ ምቾታቸውን እየጠበቁ ዋናው አብራሪ ጋዜጣቸውን እያነበቡ ምቾታቸው ሳይጓደል አረፉ። ተሳፋሪዎች የሆነውን ሁሉ ሳያዩ ረዳቱ አብራሪ በገመድ ወርደው ለፖሊሶች እጃቸውን ሰጡ። እንግዲህ የአእምሮ በሽተኛ እንደዚህ ከሆነ ተጋግዘን ብንታመምስ ምን ነበረበት?
ረዳት አብራሪው ሃይለመድህን አበራ ማስተላለፍ የፈለገው መልዕክት ስለመኖሩ መጠራጠር አውቆ መጨፈን ይሆናል። በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሀገሪቱ አስተዳደርን ገጽታ የሚያበላሽ ድርጊት ተከናውኗል። ስለምን የሃገሪቱን ገጽታ የሚያጎድፍ እንደሚባል አይገባኝም። የሀገሪቱን ገጽታ የሚያጠለሹት ጎጠኞችና አምባገነኖች ናቸው። የነርሱ አስተዳደር መበስበሱን፣ ሁሉንም ዘርፍ ማለትም ብዙሃኑን የሀገሪቱ ሕዝብ ማሳዘኑን በዚህም ምክንያት ምሬት መኖሩን ነው ይህ ወንድማችን አደባባይ ያወጣው። አዎ የአስተዳደሩን ብልሹነትና እንዳይድን ሆኖ መታመም ነው አደባባይ ያወጣው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ገጽታ ሳይሆን ዓለም የተመለከተው የአስተዳደሩን መጥፎነት ነው።
ቤተሰቦቹ ተገድደው የሚያወጧቸው መግለጫዎች ይበልጥ የሚያጋልጡት ይህ ማፍያ ቡድን እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችልና በቤተሰብ ችግርና ሃዘን ውስጥ እንኳን በመግባት ሊፈጽም የሚችለውን አረመኔያዊ ድርጊት ነው። ቤን የሚሉት ለማጅ ጋዜጠኛ ወሎ ሄዶ ባላቸውን አለቆቹ ገድለው እርሱ ደግሞ በሙስሊም አክራሪዎች እንደተገደሉ ለማስመሰል ሃዘንተኛዋን ባለቤት ሌላ ፖለቲካ ሲያሰራ እንደነበረው ያለ ዜናን ማስታወስ ተገቢ ነው። ያለንበት ዘመን የራሽያ አብዮት የፈነዳበት ጊዜ አይደለም በአይነቱ በተለይም በመረጃ ቅብብሎሹ ረገድ እጅግ በጣም የተለየ ዘመን ነው። የዚያን ጊዜ ታክቲክ በመጠቀም አሁን የሚታየውን አመጽ ማፈን አይቻልም። ይልቁኑ እብዶቹ መንግስት ነኝ ባዮችና ወፈፌዎቹ ጋዜጠኛና ካድሬዎች ከአሳፋሪ ተግባር ቢታቀቡ ነው የሚሻላቸው።
ረዳት አብራሪው ሃይለመድህን አበራ ቃል ሳይተነፍስ ማለት የሚፈልገውን የተናገረ ይመስለኛል። የምቾት ህይወትን ትቶ ሙያውን ተሰናብቶ መሄዱ ጀግንነት ነው። የብዙዎችን ሰቆቃና ቁጣ ያለውን የአስተዳደር በደልና ዘረኛነት ማጋለጡ ጀግንነት ነው። ራሱን ከዚህ ጨቋኝ ስርዓት ነጻ ማውጣት ለርሱ ቀላል እጅግ በጣም ቀላል ነገር ሆኖ ሳለ በሙያው በክህሎቱ የአለምን ትኩረት የሚስብን ነገር የአንድ ሰው ሕይወት ሳያጠፋ ማስተላለፍ መቻሉ ጀግንነት ነው። ይልቁንም ደግሞ የታወከ አእምሮ ኖሮ(አዋኪውና አስቀዋሹ ምክንያት ምን እንደሆነ ይታወቃልና) በዚህ አይነት የተረጋጋ መንፈስ እንዲህ ያለ መልዕክት ማስተላለፍ መቻሉ ይበልጥ አስደናቂ ያደርገዋል። ምናልባትም በሽታ መሆኑ ቀርቶ ልዩ ስም የሚሰጠው የመንፈስ ጥንካሬ ተብሎ የሚታወስ ይሆናል።  ለወንድማችን ሃይለመድህን አበራ መልካም ጤንነትና ፍትህን እመኛለሁ። ቤተሰቡና ወዳጆቹ ተመሳሳይ የመንፈስ ጥንካሬ ያድርባቸው ዘንድም አሳስባለሁ።
biyadegelgne@hotmail.com