Sunday, February 23, 2014

እኛና “እነርሱ”! (ተመስገን ደሳለኝ)

‹‹…የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ተጠናቀቀ፡፡ የባሕር መዝገቡም ተዘጋ፡፡ …ቀፋፊ ምሽት ነበር፡፡
በእያንዳንዳችንም ፊት ፈገግታ አይታይም፡፡ ከአዳራሹ ሳንርቅ ከራሳችን ጋር ብቻ እየተነጋገርን
በሃሳብም ርቀን እየሄድን አመሸን፡፡ ከምሽቱ አራት ሰዓት አካባቢ ወደ አዳራሹ እንድንገባ ተነገረን፡፡
በፍጥነት ገብተን ቦታችንን ያዝን፡፡ ሊቀ-መናብርቱም ቦታቸውን ያዙ፡፡ ‹ዛሬ ስለወሰድነው እርምጃ
ለጦር አዛዦች ማሳወቁ ይበጃል በማለት ጠርተናቸው እዚሁ ይገኛሉ› ብለው ወደ አጃቢዎቻቸው
ፊታቸውን ዘወር አድርገው ‹አስገቧቸው!› የሚል ትዕዛዝ ሻለቃ መንግስቱ ሰጡ፡፡ ጄነራል ጃጋማ
ኬሎ፣ ጄነራል ግዛው በላይነህ፣ ጄነራል ታደሰ ገብሬ፣ ጄነራል ወርቁ መኮንን ተከታትለው ገቡ…››
 ለዚህ ፅሁፍ መግቢያ ያደረኩትን ሃሳብ ጨልፌ የወሰድኩት የቀድሞ መንግስት ጠቅላይ ሚንስትር ፍቅረስላሴ ወግደረስ
በቅርቡ ‹‹እኛና አብዮቱ›› በሚል ርዕስ ካሳተመው መፅሐፍ ሲሆን፣ የተጠቀሰው ሃሳብም በተለምዶ ‹ስልሳዎቹ› ተብለው
የሚጠሩት የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ባለሥልጣናት ላይ፣ የተወሰነው የሞት ቅጣት እንዴትና በምን ሁናቴ እንደተፈፀመ
ለጦር አዛዦች ማብራሪያ መሰጠቱን አስመልክቶ ከተረከበት ገፅ 152 ላይ ነው፡፡ ይሁንና የዚህ አጀንዳ ተጠየቅ በጓድ
ፍቅረስላሴ መጽሐፍ ዙሪያ ብቻ የሚያጠነጥን አይደለም፤ ይልቁንም ሶስቱ ስርዓታት (ንጉሣዊው፣ ደርግ እና ኢህአዴግ)
በሀገር ጉዳይና በመንግስት አስተዳደር ላይ የነበራቸውን አመለካከት እና የሄዱበትን ምዕራፍ ባለሥልጣናቱ ራሳቸው
ካዘጋጇቸው መጻሕፍት አንፃር በጨረፍታ መመልከት ነው፡፡ ስለዚህም ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ‹‹ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ››
(በሁለት ቅፅ)፣ ኮሎኔል መንግስቱ ‹‹ትግላችን››፣ ፍቅረስላሴ ወግደረስ ‹‹እኛና አብዮቱ››፣ መለስ ዜናዊ ‹‹የኤርትራ ሕዝብ
ትግል ከየት ወዴት?››፣ እና በረከት ስምዖን ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ›› በሚል ርዕስ ያዘጋጇቸውን መጻሕፍት
እናተኩርባቸዋለን፡፡
 በነገራችን ላይ በሀገራችን የዘመናት ታሪክ ከስልጣን ተባርረው፣ በሰከነ ልቦና ያለፉበትን ስንክሳር ለመጻፍ የሚችሉበትን
ዕድል ያገኙት የደርጉ መሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለዚህ ጽሁፍ ማጠናከሪያ ያደረኩት የአፄው ሁለት ቅፅ መጽሐፍ ታትሞ
የተሰራጨው፣ ከዙፋናቸው ሳይወርዱ (በ1965 እና 66 ዓ.ም) ነበር፡፡ አቶ መለስም እንደ ሚሚ ስብሃቱ አገላለፅ ‹ታንክ
ተደግፎ› በትግሉ ዘመን በ1979 ዓ.ም ያዘጋጀው ነበር፡፡ ‹‹የሁለት ምርጫዎች ወግ››፣ ደራሲም ቢሆን በጣፋጯ ሥልጣኑ ላይ
በመሆኑ መጽሐፉን ሙሉ በሙሉ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ አውሎታል፡፡ በግልባጩ እነኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም
ድርሳኖቻቸውን ባዘጋጁበት ወቅት፣ የስርዓታቸው ግብአተ-መሬት ከተፈፀመ ዓመታት ስላስቆጠረ ብዙዎች ለእውነትና
ለታሪክ ይታመናሉ የሚል አስተሳሰብ ቢይዙ አስገራሚ አይሆንም፡፡ ግና ከአዎንታዊው ቅድመ-ግምታችን በተፃረረ ‹አንብቡ›
ብለው የሰጡን ተቃራኒውን ሆኗል፡፡ በተለይም የኮሎኔሉ ‹‹ትግላችን›› ለሃያ ዓመታት ከሀገሩ የተሰደደ መፃጉ የፃፈው
ሳይሆን፣ ገና ለሥልጣን የቋመጠ (ዕድሉ ያልጨለመ) ደራሲ ያዘጋጀው ይመስላል (‹አብዮቱ ገና አላለቀም› ማለቱን ልብ
ይሏል) እናም የእርሱም እንደ በረከት ስምኦን መጽሀፍ ሁሉ በተራ ፕሮፓጋንዳና ቅጥፈት የተሞላ ሆኖ መገኘቱ ከማስተዛዘብ
አልፎ ዕድሜ ያላለዘበውን ግለኝነቱንና ኢ-ተአማኒነቱን አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ በአንፃሩ የፍቅረስላሴ ወግደረስ ‹‹እኛና
አብዮቱ›› ኢህአፓን በማውገዝ መጠመዱንና ‹ትክክል ነበርን› ትርክቱን ወደ ጎን ብለን፤ እንዲሁም ሳይብራሩ ሊታለፉ
የማይገባቸው የነበሩ ታሪካዊ ኩነቶች (የአፄው አሟሟት እና የኮሎኔል አጥናፉ አባተ ፍፃሜን የመሳሰሉ ታላላቅ ጉዳዮች)
ከመዘለላቸው ውጪ፤ ለእውነታው የቀረበ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በአናቱም ከሁሉም ባለሥልጣናት በተሻለ መልኩ
በዘመኑ የተፈፀሙ የተወሰኑ ስህተቶችንም ቢሆን አምኖ ለመቀበል የደፈረ ነው፡፡ እንደ ምሳሌም የ60ዎቹን ግድያ አስታክኮ፣
ለሀገር የደከሙ ሰዎችን በፈጠራ ወሬና አሉባልታ ለማጠልሸት የሚደረገውን ኢህአዴጋዊ መሯሯጥ አክሽፎ፣ አሳማኝና በቂ
መልስ በመስጠት ተጠያቂነቱ የደርግ ብቻ እንደሆነ ማብራራቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዚህ አሳዛኝ ጭፍጨፋ ገፊ-ምክንያት
የሆነውን፣ ከዕለታት በአንዱ ቀን መንግስቱ ኃይለማሪያም ከጊዜያዊው ኮሚቴ ህጋዊ መስመር አፈንግጦና ድንገት ንኡስ
ደርጎችንም ጭምር ሰብስቦ ሲያበቃ፣ ‹‹እገሌ ይገደል፤ እከሌ አይገደል›› በሚል ድምፅ አሰጥቶ እንዲረሸኑ ማድረጉ አግባብ
አለመሆኑን ገልፆ ጥፋቱን ለመቀበል የሄደበት ዕርቀት፤ እንዲሁም ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ወራሪውን የሶማሊያ ጦር
አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ ለማባረር ከማናቸውም በላይ እንቅልፍ አጥቶ የሰራ ስለመሆኑ መመስከሩ፤ በተመሳሳይ ጭብጥ
ከተዘጋጁ ድርሳናት በተሻለ ሁናቴ ጓድ ፍቅረስላሴን ለታሪክ ለመታመን ላሳየው ቁርጠኝነት እንድናከብረው እንገደዳለን፡፡
 ሶስቱ ስርዓታት (ኢህአዴግ ዛሬም በመንበሩ ላይ ቢሆንም፣ መጨረሻውን ከ‹ቆሪጥ› በቀር የሚያውቅ አለመኖሩ ታሳቢ
ይደረግና) ከአስራ ሰባት እስከ አርባ ሶስት ዓመታት ድረስ ከተዘረጉት የሥልጣን እርከኖች አኳያ፣ ‹የትኛው ይበልጥ ሚዛን
ይደፋል?› የሚለው ካላወዛገበ በቀር፣ ከጥፋታቸው ጎን ለጎን ሀገራዊ አበርክቶ ትተው ማለፋቸው አከራካሪ አይደለም፡፡
የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት የበላይ ጠባቂ የነበሩት አዛውንቱ ንጉሠ ነገሥት ጠዋት ማታ የፈጣሪያቸውን ስም ሲዘክሩ
ቢውሉም፣ የጠሉትን ወይም በክፉ የጠረጠሩትን ማንም ይሁን ማን፣ ዝሆን የረገጠው ሳር ከማስመሰል እንደማይመለሱ
በርካታ ማሳያዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ቆፍጣናው ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያምም ከርህራሄ አልባው የጎዳና ጭፍጨፋው
ባሻገር፣ በግዛት አንድነት ጉዳይ ላይ ስሜቱ ቶሎ የሚነካ ሆደ ብቡ ወታደር እንደነበር እናውቃለን፡፡ የእኛው ዘመን መለስ
ዜናዊም ከዚህ ቀደም በሀገሪቱ ላይ እንደቅንጦት የሚታዩ የዲሞክራሲና ፖለቲካዊ መብቶችን ቢፈቅድም፣ መልሶ በዚሁ
ምክንያት ብዙዎችን ገና በለጋ ዕድሜያቸው ወደ መቃብር አውርዶ ያለፈ ስለመሆኑ እኛው ራሳችን የታሪክ ምስክር መሆን
የምንችል ይመስለኛል፡፡
 እነርሱ እና ‹‹እውነታዎቻቸው››
 ከሞላ ጎደል አፄው እና ደርጉ በሀገር አንድነት ተቀራራቢ አቋም የነበራቸው ከመሆኑም በላይ ማንም በመናፍቅነት
ወንጅሏቸው አያውቅም፡፡ ይህም በታሪክ ባህረ-መዝገብ የሰፈረ እጅግ የሚያስመሰግናቸው የማይካድ እውነታ ነው፡፡ ነገር
ግን የአገዛዝ መሰረታቸው የተዋቀረው ከሕዝብ ጥቅም አኳያ እንደሆነ ደጋግመው በመጻሕፍቶቻቸው ለመስበክ
መሞከራቸው ከንቱ ድካም ነው፤ ‹ከፍላጎታችን ውጪ ሥልጣን እጃችን ላይ ስለወደቀ ብቻ ነው የነገሥነው›ም የምትል
ዘመነኛ ቀልዳቸውን በሰማን ቁጥር በምፀት ፈገግ ለማለት የምንገደደውም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ አፄው ‹‹ህይወቴና
የኢትዮጵያ እርምጃ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት ክፍል አንድ መጽሐፍ (ተቃዋሚዎቻቸው ‹‹ህይወቴና የኢትዮጵያ እርግጫ››
እያሉ ይቀልዱባቸው ነበር) ‹‹በኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ምንሊክ ጀምሮ ሦስት ሺ ዘመን ያህል የተለመደው አገዛዝ ንጉሠ ነገሥቱ
ብቻ በሥልጣኑ እያዘዘ እንጂ የምክር ቤት አቁሞ በሕገ መንግስት የገዛ ንጉሥ አልነበረምና፣ በተለይ ወዳጆቻችን የሆኑ
አንዳንድ ሰዎች ነገሩ ስላልገባቸው ‹እንዴት በገዛ እጅዎ የመንግስትዎን ሥልጣን ለሕዝብ ይለቃሉ፣ እባክዎ እንዲቀር
ያድርጉ› እያሉ›› ይመክሯቸው እንደነበረና፤ እርሳቸው ግን ሕዝብ ይቀድማል በሚል ለሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን ሕገ-
መንግስት መፅደቅ አስመልክቶ ባደረጉት ንግግር መግቢያ ላይ ቀልዷን አሰማምረው የነገሩን ‹‹እኛ ኢትዮጵያን ለመጠበቅ
ከእግዚአብሔር ለተቀበልነው አደራ…›› በማለት ነበር (መቼም የአፄው ሕገ-መንግስት ንግስናው ከቤተሰቦቻቸው
እንደማይወጣም ሆነ ተወካዮቻቸውን ቀጥታ ራሳቸው እንደሚመርጡ መደንገጉን ስናስተውል ‹‹እባክዎ እንዲቀር ያድርጉ›
ተብዬ ተመክሬ ነበር›› ሲሉን የተኮረኮረን ያህል መሳቃችን አይቀርም) ጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያምም በበኩሉ ሁለትም ሶስትም
ሰው በተሰበሰበበት ሁሉ ‹ታሪክና ሕዝብ የጣለብን አደራ› በማለት ይደሰኩር እንደነበር ከቶ ማን ይረሳዋል፡፡ በአናቱም
ስርዓቶቹ ‹የሥልጣን ዘመናችን ምሉዕ-በኩለሄ ነበረ› እያሉ ሲተርኩልን ድንቅፍ አለማለታቸው አስገራሚ ነው፡፡ አቶ መለስ
እና በረከትም ቢሆኑ፣ ዜጎችን በጠራራ ፀሀይ እየረሸኑና በየእስር ቤቱ እያጎሩ፤ ‹ሕዝቡ በካርዱ ፈቃዱን ሰጥቶናል› ብለው
ተጃጅለው ሊያጃጅሉን ሲሞክሩ ታዝበናል፤ በንቀት ተሞልተንም እስኪሰለቸን ሰምተናል፡፡
 ከዚህ ባሻገር ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከላይ በተጠቀሰው መፅሃፋቸው መግቢያ ላይ ሀገሪቱን የተሻለችና የሠለጠነች
ማድረጋቸውን የገለፁት እንዲህ በማለት ነበር፡-
‹‹የኢትዮጵያ መንግስት በፊትም በእንደራሴነት፣ በኋላም በንጉሠ ነገሥትነት አደራ ከተቀበልንበት ከ፩፱፻፱ ዓ.ም ጀምሮ
እስካሁን ያገሩን ውስጥ ሥራ በየጥቂቱ ለማሻሻል የምዕራባውያንንም የሥልጣኔ ሥራ ባገር ውስጥ አስገብተን ሕዝባችን ወደ
ትልቅ ደረጃ የሚደርስበትን በሚቻለን ሁሉ ጀምረናልና ሕሊናችንን አይወቅሰንም፡፡››
 ጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያምም እስከተሰደደበት ዕለት ድረስ ስለገነባት ‹‹የታፈረችና የተከበረች አብዮታዊት ኢትዮጵያ›› በርካታ
ተረት ተረቶችን አውርቶ የሚጠግብ እንዳልነበር አይዘነጋም፡፡ የኢሰፓ መንግስት ሁለተኛ ሰው የነበረው ጠቅላይ ሚንስትር
ፍቅረስላሴ ወግደረስም ቢሆን፣ ደርጉ ሀገሪቱን ‹ልማት በልማት› ማድረጉን የነገረን በሚከተለው መልኩ ነው፡-


‹‹ሰፊ የልማት እንቅስቃሴ የተጀመረው በእኛ መንግስት ዘመን እንደሆነ ይገመታል፡፡ ለዘመናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ
መሰናክል ሆኖ የቆየውን ፊውዳላዊ የመሬት ይዞታ ሥርዓት ካስወገድን በኋላ ሰፊ የኢኮኖሚና የባህል እንቅስቃሴ ጀመርን፡፡
የልማት እንቅስቃሴ ይካሄድ የነበረውም በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ነበር፡፡›› (‹‹እኛና አብዮቱ›› ገፅ 411)
 ወደእኛ ዘመን ስንመጣ ደግሞ ኢህአዴግ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በረሃብ እየረገፉ፣ ጎዳና እየተኙ፣ እጆቻቸውን
ለልመና በሃፍረት ዘርግተው፣ ሴተኛ አዳሪነትን ነፍስ የማሰንበቻ አማራጭ አድርገው፣ በሞት ሸለቆ ማለፍን ሳይቀር
የሚጠይቅ ስደትን ተጋፍጠው… እያየን፣ ኢትዮጵያችንን ‹ወተትና ማር የሚዘንብባት የተስፋይቷ ምድር ከነዐን› ስለማድረጉ
ትላንትም፣ ዛሬም ያለማቋረጥ ሃያ አራት ሰዓት ሙሉ እየደሰኮረልን በመሆኑ፣ እዚህ ጋ ደግሞ መጥቀስ አንባቢን ማሰልቸት
ይመስለኛልና አልፈዋለሁ፡፡
 ሌላው የሀገሬን ገዥዎች የሚያመሳስላቸው ጉዳይ የገለበጡትን አስተዳደር በመኮነን ላይ የተመሰረተ የገፅታ ግንባታ
ስልታቸው ነው፡፡ አፄው የልጅ እያሱን ዘመን ለሀገራዊ ኋላቀርነት ብቸኛ ተጠያቂ ያደርጉታል (በነገራችን ላይ የቀደሙት
ኢትዮጵያውያን ታሪክ ፀሀፊዎች ድርሳናትን በጥርጣሬ እንድንመለከት ከሚገፉን ምክንያቶች አንዱ፣ በልጅ እያሱ የሥልጣን
ዘመን ዙሪያ የተዘጋጁ መጻሕፍት ሀራምባና ቆቦ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ምሳሌም የኃይለስላሴ አብሮ አደግ ጓደኛ
የነበሩት ፊት-አውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማሪያም እና ጎበዜ ጣፈጠ የጻፏቸውን ሁለት መጽሐፍት ማነፃፀር ይቻላል፡፡ ፊት-
አውራሪ በ‹‹በአውቶባዮግራፊ››ያቸው፤ ልጅ እያሱ ከአስተዳደር ይልቅ ለፌዝ፣ ለቧልት፣ ለሴሰኝነት… የበለጠ ጊዜ ሰጥተው
አገሪቷን ወደ ጥልቅ ጨለማ መገፍተራቸውን ሲነግሩን፤ ከእያሱ ጋር በአንድ ጅረት የተንቦራጨቁትና የመኢሶኑ ዶ/ር ነገደ
አባት የሆኑት ጎበዜ ጣፈጠ ደግሞ ‹‹አባ ጤና እያሱ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ፤ ልጅ እያሱን ወደር የማይገኝላቸው
አርቆ አሳቢ ከማድረግም አልፈው ከአፋር እስከ ጅማ፤ ከአዳል እስከ ሶማሌ… የተበተኑ ቅምጦቻቸውን የሚጎበኙት ለዝሙት
ሳይሆን ለሀገር አንድነት (በዚህ ዘመን ቋንቋ ለብሔር ብሔረሰብ እኩልነት) ስለመሆኑ ተግተው መስበካቸውን ስናስታውስ፤
ድቅን የሚልብን ጥያቄ የታሪክ ነጋሪዎቻችን አምታችነት እስከ ምን ድረስ ነው? የሚል ይሆናል፡፡)
 የሆነው ሆኖ የደርግ ስርዓትም ንጉሡን ‹‹ደም መጣጭ አቆርቋዥ የፊውዳል ሥርዓት›› እያለ የሚያጥላላበትን ፕሮፓጋንዳ
እንኳ ሳይቀይር ነው፣ ሻዕቢያ እና ህወሓት ‹ደረስንባቸው ሳይታጠቁ!› በማለት ፎክረው መሳቂያ መሳለቂያ ያደረጉት፡፡
በግልባጩ የመለስ ዜናዊ መንግስትን ከሁለቱ ስርዓት ነጥለን ለማየት የምንገደድበት ምክንያት፣ ከአምባገነን ባህሪው እና
ያሸነፈውን ስርዓት ከመኮነኑ ባሻገር በአደባባይ የተገለጠው ፀረ-ኢትዮጵያዊ አመለካከቱ ነው (ይሄን ስል ‹‹የትኛዋን ኢትዮጵያ
ተናንቅን?›› የሚለውን ነባር ቀልዳቸውን ሳልዘነጋ ነው)፡፡ እውነታውን የሚያስረግጥልን ሟቹ ጠ/ሚንስትር ‹‹የኤርትራ
ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት?›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ ጉዳዩን አጉኖ ማቅረቡ ነው፡፡ መቼም መጽሐፉን ያነበበ ሁሉ
እውን ይህ ደራሲ ኢትዮጵያዊ ነውን? ብሎ ለማመን መቸገሩ አይቀሬ ቢሆንም፣ መራራው ሀቅ ያውም ሀገሪቱን ለሁለት
አስርታት እንደሰም አቅልጦ፣ እንደብረት ቀጥቅጦ የገዛው መለስ ዜናዊ መሆኑ ነው፡፡ እርሱ በመጽሐፉ ላይ ባቀረበው ስሁት
ትንተና ኢትዮጵያ፣ ‹ኤርትራን በቅኝ ግዛት የያዘች ኢምፔሪያሊስት› ስለመሆኗ ለትውልድ ሊሻገር በማይገቡ ፀያፍ ቃላት
ጭምር ሊያሳምነን በከንቱ የዳከረው እንዲህ በማለት ነበር፡-
‹‹ገና ድሮ ጀምሮ ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል ነበረች በማለት የአማራው ብሔር የገዥ መደቦቻቸውና ቡችላ የሆኑት የታሪክ
ፀሀፊዎቻቸው በታሪክ ስም የሚያቀርቡትንና የሚዘረጉትን አፈ-ታሪክ ቁጥሩ የማይናቅ ሕዝብ እንደትክክለኛና ሀቀኛ ታሪክ
አድርጎ ይቀበለዋል፡፡ ዳሩ ግን ይህ ከአንድ ተራ አፈ-ታሪክ በምንም አይነት መንገድ የማይለይ ፍፁም በሀሰት ላይ
የተመሰረተ አባባል ነው፡፡ …ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል እንዳልሆነች ግራም ሆነ ቀኝ የማያሰኝ በቂ ሕጋዊና ታሪካዊ መረጃዎች
አሉ፡፡ ስለዚህ የኤርትራ ሕዝብ ጥያቄ የፈለገው ስም ቢሰጠውም የባዕድ ወረራን የመከላከልና ብሔራዊ ነፃነትን የማረጋገጥ
ፍትሀዊ ጥያቄ ለመሆኑ የሚያከራክር አይሆንም፡፡›› (‹‹የኤርትራ ሕዝብ ትግል ከየት ወዴት?››)
እነሆም ህልፈቱን ተከትሎ ለቀናት ሀገሪቷን ወደ ሀዘን ድንኳንነት ከመቀየር አልፈው፣ እኛም ጎዝጉዘን እንድንቀመጥ በጋሻ
ጃግሬዎቹ የተገደድንበት የባለ‹‹ራዕዩ›› መሪያችን መለስ ዜናዊ ‹‹ኢትዮጵያዊነት›› በዚህ መልኩ የተቀኘ ነበር፡፡
በአናቱም አብዛኛው የህወሓት አመራር (ከአብርሐም ያየህ እና ገ/መድህን አርአያ በቀር) ከኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ ኤርትራን
በማስቀደም፣ በታሪካችን ላይ በመሳለቅ፣ በሀገር አንድነት ላይ ደባ በመፈፀም… ተመሳሳይ አቋም ሲያንፀባርቅ የቆየ መሆኑ
አይሳትም፡፡ ለማሳያ ያህልም አቶ መለስ የአሰብ ወደብ በሕግም በታሪክም የኢትዮጵያ መሆኑን እያወቀ፡-


‹‹ወደብ ተገኘ አልተገኘ ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም የሚውል አይሆንም መሰረታዊው የወደብ ጥቅሙ ተሟልቶ ወደብ ቢታጣም
በሰፊው ሕዝብ መሰረታዊ ጥቅም ላይ የሚያስከትለው መሰረታዊ ችግር አይኖርም፡፡ የወደብ አለመኖሩ ችግር በጭቁኖች
ሕዝቦችና አገሮች መካከል በሚደረግ መደጋገፍና እገዛ አማካይነት ሊፈታ የሚችል ችግር ነው››
በሚል ኑፋቄያዊ ሀቲት፣ ታላቁን ጉዳይ አቃልሎና አራክሶ ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፉ አሳትሞ፣ በድርጅቱ ስም ሲያሰራጭ
የአመራሩ ይሁንታ አልነበረውም ማለት የዋህነት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
 በነገራችን ላይ አቶ መለስ ዜናዊ በራሱ ብዕር በደረሰው በዚሁ መጽሐፍ ትርክት ለኢትዮጵያ አንድነት ከህወሓት ይልቅ
ሻዕቢያ ተሟጋች እንደነበረ አስረግጦ የነገረን እንዲህ ሲል ነው፡-
‹‹ህግሐኤ በዚያን ጊዜ ይህን ጥያቄ አስመልክቶ ያቀረበው አስተያየት እንደሚከተለው ሊጠቃለል ይችላል፡፡ በአጠቃላይ
ተጨቋኝ ብሔሮችና ብሔረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት እስከመገንጠል ድረስ አላቸው፡፡
በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን መብት የዲሞክራቲክ አንድነት መብት እንጂ በመገንጠል የገዛ ራስን መንግስት
መመስረት የመቻልን መብት መጨመር አይችልም፡፡ ምክንያቱም አንድ ፀረ-ሕዝብ እስካለ ድረስ አንዲት ብሔር ታግላ የገዛ
ራሷ ነፃ የሆነ መንግስት የማቋቋም አቅምና ችሎታ አይኖራትም፡፡ ፀረ-ሕዝብ የሆነው መንግስት ተደምስሶ ፍትህ የነገሰበት
ስርዓት ከተመሰረተ ደግሞ የመገንጠል ጥያቄ አይነሳም ዲሞክራቲክ አንድነት ብቻ ነው መኖር ያለበትና የሚገባው፡፡ ስለዚህ
ህወሓት እንደ አንድ አማራጭ አድርጎ በፕሮግራሙ ማስፈር የሚገባው የዲሞክራቲክ አንድነት ምርጫን ብቻ እንጂ
ዲሞክራሲያዊ አንድነት ወይም መገንጠል የሚሉትን ሁለት አማራጮች ማስቀመጥ የለበትም፤ እንዲህ ማድረጉ ደግሞ
ስህተት ነው፡፡›› (‹‹የኤርትራ ሕዝብ ከየት ወዴት?››)
 የእነርሱ ‹‹ዲሞክራሲ››
የአፄው በሁለት ክፍል የቀረበው ድርሳን በ‹‹ፀሀዩ›› የንግሥና ዘመናቸው ያዘጋጁት እንደመሆኑ፤ በስውር ስላስገደሏቸው
ልሂቃን፣ አሊያም ስላጋዟቸው የስርዓታቸው ሰዎች እንዲጠቅሱልን አንጠብቅም፡፡ ይሁንና በድህረ-ጣሊያን ወረራ
ተሰበጣጥረው የፖለቲካ ማሻሻያ አስፈላጊነትን አበክረው ያሰሙ የነበሩ ድምፆችን ረግጠው በመሻገራቸው፣ የነዋይ ልጆችን
በደም የተደመደመ ቁጣን ለማስተናገድ መገደዳቸው ክሱት ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ስዒረ-መንግስት ከተሳተፉት መካከል
የሞቱትን አማፂያን በድን አካል ጭምር በከተማይቱ አደባባይ እስከ መስቀል መሄዳቸውን፤ እንደ ሕገ-መንግስታቸው ሁሉ
‹‹ለሕዝባችን ስንል…›› በማለት ሊመጣ ያለውን መከራ በጊዜ አስፀንሰውታል ብሎ መደምደምም የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ለአመታት በተካሄደ ሕዝባዊ አመፅ የተዳከሙትን ንጉሠ ነገሥት ለመጨረሻ ጊዜ ከሥልጣናቸው የተወገዱበትን እንቅስቃሴ
የመራው ደርግ መሆኑ ባይካድም፣ አብዮቱ የሁሉም ተራማጅ ምሁራን፣ ሰራተኞች፣ ተማሪዎች… ብርቱ ተጋድሎ ውጤት
እንደነበረም አይዘነጋም፡፡ ይሁንና ደርጉ ጠብ-መንጃ ያነገበውን ኃይል ማዘዝ የሚችል በመሆኑ፣ አብዮቱንም ሆነ ትሩፋቶቹን
ጠቅልሎ የግሉ ከማድረጉም በላይ፤ የመጻፍ፣ የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት… የመሳሰሉትን መብቶች አግዶ ሲያበቃ፣
በወቅቱ ሀገሪቱ በወታደር መመራት እንደሌለባት በመቃወም ‹‹ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት ይመስረት›› የሚል ጥያቄ
ያቀረቡትን ዜጎች የጥይት ራት ማድረጉ የትላንት አሰቃቂ ክስተት ነው፡፡ ይህንን ኩነት የፖለቲካ ተንታኞች ‹‹አዝጋሚ
መፈንቀለ መንግስት›› (Creeping Coup d’état) የሚል ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ በግልባጩ የሻምበል ፍቅረስላሴ መጽሀፍ
ደግሞ ጥያቄውንም ሆነ አቅራቢዎቹን እንዲህ በማለት ያጣጥላቸዋል፡-
‹‹ሥልጣን ለመጨበጥ ምንም ዕቅድ ያልነበረው የጦር ኃይሎች አስተባባሪ ኮሚቴ በሁኔታው አስገዳጅነት የጊዜያዊ መንግስት
ሲመሰርት ከግራው ብርቱ ተቃውሞና ውግዘት ገጠመው፡፡ ‹የሕዝብ ወገን የሆነ ጊዜያዊ መንግስት መቋቋም አለበት› አሉ፡፡
በጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት ውስጥ በአባልነት የሚሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎችንም ጠቆሙ፡፡ ‹ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት
መቋቋም ያለበት ከተማሪው፣ ከሠራተኛው፣ ከገበሬው፣ ከአስተማሪው፣ ከዝቅተኛ ነጋዴው፣ ከዝቅተኛ የመንግስት
ሠራተኞች፣ ከወታደሮችና ከሌሎች ተራማጆች በተወጣጡ ሰዎች መሆን አለበት› አሉ፡፡ የተወሰኑ የኀብረተሰብ ክፍሎችን
ባሕሪ ብንመለከት፡- ተማሪዎች በዕድሜአቸው ወጣቶች ናቸው፡፡ ወጣት በመሆናቸውም ችኩሎች ናቸው፡፡ የሥራም ሆነ
የኑሮ ልምድ የላቸውም፡፡ ቤተሰብ ማስተዳደር እንኳን በቅጡ አያውቁም፡፡ ተማሪዎች እንደ ፖለቲካ ድርጅት በፖለቲካ
አካል ውስጥ ተወክለው መንግስት የተመሰረተበት አንድም አገር አይታወቅም፡፡ የተማሪዎች ዋናው ተግባር ተምረው
የወደፊት ኃላፊነትን ለመረከብ መዘጋጀት እንጂ በትምህርት አምባ ተሰባስበው በመገኘታቸው ብቻ እንደፖለቲካ ድርጅት ተቆጥረው በመንግስት ሥልጣን ውስጥ ተካፋይ መሆን አለባቸው የሚል ሃሳብ ማቅረብ ከግዴለሽነት ወይም ግራ ከመጋባት
የመነጨ ይመስላል፡፡›› (‹‹እኛና አብዮቱ›› ገፅ 225-226)
 በርግጥ ይህ ትንታኔ እውነታውን ያላገናዘበና በቁንፅል ሃሳብ የተመሰረተ መሆኑን ለመረዳት አያዳግትም፡፡ ምክንያቱም
በመጽሐፉ አገላለፅ እንኳ ‹‹ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት ይመስረት›› የሚል ጥያቄ የቀረበው በተማሪዎች ውክልና ብቻ
አልነበረም፤ ነገር ግን ሻምበል ፍቅረስላሴ ጉዳዩን ለማጣጣል ማሳያ ያደረገው ተማሪዎች ለሥልጣን ብቁ አለመሆናቸውን
በማውሳት ብቻ ነው፡፡ ይሁንና ራሱ የጠቀሳቸው ሌሎቹ የሕብረተሰብ ክፍሎችም መንግስት ለመመስረት የወታደርን ያህል
ብቁ አለመሆናቸውን ሳያብራራ አልፎታል፡፡ የሆነው ሆኖ በእንዲህ አይነት ምርጫን ለማካሄድ የሚያስችል ተቋምም ሆነ
የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባሌሉበት ማሕበረሰብ የተካሄደ አብዮት ማሳረጊያው ከሁሉም መደብ የሚወክል ጊዜያዊ
መንግስት መመስረት እንጂ፣ ከጦር ሰፈሩ ተምሞ በወጣ ወታደር ብቻ መተዳደር ትክክል ሊሆን አይችልም፡፡ እንዲህ አይነቱ
ለውጥ ከአብዮት ይልቅ ለመፈንቅለ መንግስት ነው የሚቀርበው፡፡ ይህ ሁነትም ህወሓት ‹ሁሉም የፖለቲካ ሥልጣን ለታገለ
ብቻ› የሚል ያልተፃፈ ሕግ እንደነበረው ሁሉ፣ ደርግንም ‹ሀገር ለመምራት ከወታደር በቀር የተሻለ ማንም የለም› የሚል
እብሪት ወደተፀናወተው ብያኔ አድርሶት ነበር፡፡ የጓድ ፍቅረስላሴ መጽሐፍም መከራከሪያውን ያስረግጥልናል፡፡
 ከዚህ በተጨማሪ የዛሬው ገዥ ፓርቲ ባለፉት ሃያ ሁለት አመታት ተነስተው የነበሩትን የዲሞክራሲ ጥያቄዎች፣ በተራው
ለመጨፍለቅ የመረጠባቸው ከግድያ እስከ እስር የዘለቁ አማራጮቹ በግላጭ ፍንትው ብለው የሚታዩ በመሆናቸው
መዘርዘሩ ደክሞ ማድከም ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ከዚህ ጽሁፍ አኳያ፤ ከአቶ በረከት ስምኦን መጽሀፍ አንድ ነጥብ ጠቅሼ
አልፋለሁ፡፡ በሁለቱ አስርታት ውስጥ የበቃም ባይባል የተሻለ የዲሞክራሲ ጥያቄ የተነሳበትን የ1997 ዓ.ም ምርጫ
አስመልክቶ በአደባባይ እርሱና ጓዶቹ የረሸኗቸውን ዜጎች፣ በመጽሐፉ ‹‹ገዳይ ሲዘግይ ሟች ይገሰግሳል›› በሚል ሀገርኛ ብሂል
ሊያላግጥባቸው ሞክሯል፡፡ አልፎ ተርፎም የድህረ-ምርጫውን ‹‹ድምፃችን ተነጥቋል›› እንቅስቃሴ ጭፍለቃን፣ ‹‹ኢህአዴግ
የነደፋቸው የአመፅ ማክሸፊያ ስልቶች›› ሲል በማያሻማ ቋንቋ ነግሮናል፡፡
 የአገር አባት ናፍቆት
ከላይ በጥቂት ጫፎች ዙሪያ ድርሳኖቻቸውን እየጠቀስን ለማየት የሞከርናቸው ገዥዎቻችን በአንድ ጉዳይ ላይ የጋራ መልክ
አላቸው፤ ይህም በመቀባት፣ በሕብረተሰብአዊነት አሊያም በምርጫ ካርድ ስም የመሩትን ሕዝብ ለሰቅጣጭ መከራዎች
የመዳረጋቸው እውነታ ነው፡፡ ባለፉት አምስት አስርታት ይህችን ሀገር ወደፊት ሊያራምዷት ይችሉ የነበሩ ዕድሎችን
አዳፍነዋቸው አልፈዋል (ለማዳፈንምም እያዘገመ ነው)፡፡ አፄው ‹‹ከተራማጅነት ወደ ቀልባሽነት›› ሲሻገሩ፣ ሀገሪቷን ወደ ደም
ውቂያኖስ ገፍተዋት አልፈዋል፡፡ የወታደሮቹ ስብስብም በበኩሉ፣ የአደረ ሸክሙን በኃላፊነት መፍታት ባለመቻሉ ኤርትራን
አሳጥቶን፣ በሕብረ-ብሔራዊው ልሂቃን መቃብር ላይ ለገነገኑ፣ ብሔርተኛ ኃይሎች አሳልፎ ሰጥቶን ወድቋል፡፡
ከኃይለማሪያም ደሳለኝ ጀርባ ያለው ገዥ ቡድንም በተራው፣ ልክ እንደ አንድ በሳጠራ የተገነባ ቤት እነሲ.አይ.ኤ እና ሌሎች
ምዕራባዊ ተቋማት ሀገሪቷ የምትፈርስበትን ቀነ ቀጠሮ (እ.ኤ.አ. 2030 ዓ.ም ድረስ ማለታቸው ልብ ይሏል) እስኪሰጡን
ድረስ የመበታተን ጥርጊያ መንገዱን ከማበጀት አልሰነፈም፡፡ እናም ይህ ስርዓት በሰላማዊ የከተማ አብዮት ይቀየራል ከሚል
መነሾ፣ በድህረ-ኢህአዴግ ስለምንናፍቀው አገር ተሸካሚ አባት (State Man) የመብሰልሰላችን ገፊ-ምክንያት እንዲህ አይነቱ
ከባቢያዊ አደገኛ የመበታተን ስጋት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
 የትኛዎቹም ለዘብተኛ ምሁራን እንደሚስማሙት የኢትዮጵያ የአገረ-መንግስት ግንባታ (Nation Building) በክሽፈት
ተጠናቋል፡፡ የተገንጣይ እንቅስቃሴዎች ብዛት (ቢያንስ ሰባት ደርሷል)፣ በሀገር ምንነት ብያኔ ላይ የምናስተውላቸው ተጣራሽ
አቋሞች፣ የብሔራዊ ቋንቋ (ዎች) ዕጦት፣ የዘውግ ማንነት ኢ-ምክንያታዊ ጡዘት፣ ያላቋረጡ የማንነት ጥያቄዎች መበራከት…
የሀገር ግንባታው ሂደት የውርጃው ውጤቶች ማሳያ ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ እነርሱ ‹‹ለምለሚቷ ሀገሬ›› እያልን
እንድንዘምርላት የሚገፉን እና እኛ የምናውቃት (ስቃይ፣ መከራ፣ ጭቆና፣ እርዛት… መገለጫዋ የሆነችው) ኢትዮጵያ ፍፁም
የተለያዩ ናቸው፡፡ ግና፣ አንዳቸውም ቢሆኑ ከምናየውና ከምንኖረው ይልቅ የሚነግሩንን እንድናምን በጠንካራ መዳፋቸው
ከመደቆስ ባለፈ ከታሪክ ለመማር የሚያበቃ አስተውሎት ርቋቸዋል፡፡
 በጥቅሉ ሶስቱም ስርዓታት እርስ በእርሳቸው በሚፃረሩ መልኮች ቢዋቀሩም፣ ፍፃሜያቸው የሀገሪቱን ህልውና ወደ ክፉ
መዳረሻ የገፋ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህም እኒህን ሀገረ-መንግስታዊ ክስረቶች ተሻግሮ ኢትዮጵያን ለማሰንበት እና የተሻለች 6


ለማድረግ የተጣረሱ የመሰሉንን ምልከታዎች በአንድ አቅፎ፣ በዜግነት ላይ ብቻ የሚቆም ማዕከላዊ መንግስት የሚያበጅልን
ሆደ-ሰፊ፣ ከሴራ የነፃ፣ ከጥላቻ የተፋታ፣ ከቂም-በቀል የራቀና አቻችሎ የተጋረጠውን አደጋ የሚያሻግር መሪ የግድ
ያስፈልገናል፡፡ ከወደቁት ሁለቱ ሥርዓታትም ሆነ፣ ከሚያዘግመው ኢህአዴግ የሚወረሱ በጎ ሁነቶች ላይ ቆሞ፣ ከዛሬ ወደ ነገ
የሚወስድ ድልድይ በጠንካራ ማህበረ-ፖለቲካዊ ጡቦች የሚያዋቅር መሪ ያሻናል፡፡ ከተወሰኑ የፖለቲካ ፍላጎቶች በዘለለ፣
ከትላንት የፖለቲካ ታሪክ የታረቀ፣ ካሳለፍናቸው የምዕተ-ዓመታት ሀገራዊ መከራዎች ክምር ስር በጎ ዕሴቶችን አሰባስቦ፣
የክሽፈቶቻችንን ጉድጓዶች ደፍኖ ሀገረ-መንግስቱን በማሻሻል የሚገነባ መሪን ከመናፈቅ የተሻለ ምርጫ ያለን አይመስለኝም፡፡
በግልባጩ ይህንን ማድረጉ ካልተሳካ ወደ መበታተን የምንቃረብበትን የተጠመደ የሰዓት ቦንብ ዕድሜ እንደሚያፋጥነው
ለማስጠንቀቅ ነብይ መሆንን አይጠይቅም፡፡