Saturday, March 8, 2014

የአፄ ምኒልክ የአመራር ስልትና የአድዋ ድል (ጌታቸው ኃይሌ)

 መቅድም፤

በዚህ ሰሞን ስለ አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ አድዋ ላይ ስላገኘችው ድል በአዎንታና በአሉታ በሰፊው ሲነገር እሰማለሁ፥ ተጽፎም
አንብቤያለሁ። በመጠኑም ቢሆን፥ እኔም አዎንታውን የሚደግፉ አማዛኝ ማስረጃዎችና አስታራቂ ሐሳቦች እያመጠሁ ከመሳተፍ
አላረፍኩም። አስታራቂና ገላጋይም ለካ በትር ያርፍበታል። ሆኖም በትር ፈርቶና እውነት ትመርራለች ተብሎ እውነት ሳትነገር፥ ሰላም
ሳይሰፍን ዝም ለማለት ቢሞከር ሕሊና ዕረፍት አይሰጥም። ደግሞም እኮ፥ የ"ዝም በሉ" ምክር ዓምና ጠቅሞ ይሆን ይሆናል እንጂ፤
ዘንድሮስ ከጥቅሙ ጉዳቱ አይሏል።

ስለ ኢትዮጵያ መጥፎ ገጽታ ለምን አትጽፍም የሚሉኝም ጥቂቶች አይደሉም። ምን ሳይጻፍ የቀረ አለና? መጥፎው ገጽታዋ በውሸት
እየተቀመመ ስለተጻፈና ስለተነገረ አይደለም እንዴ ዛሬ አገሪቱ ከዚህ ከአስከፊ ሁኔታ ላይ የወደቀችው? ሆኖም፥ አሁንም የሚታረም ነገር
ካየሁ፥ ካሁን በፊት እንዳደረግሁት፥ ለማረም ሥልጣን ላላቸውና ግዴታቸው ለሆነ ወገኖች ማመልከቴን አላቋርጥም። ከዚያ አልፎ
እንደገና አገርን በአደባባይ መወረፍ ግን ትርፉ ስድብ ለተሳዳቢማቀበል ብቻ ነው።

ለማስታወስ ወደተነሣሁበት ልመለስና፥ ስለርእሱ "በሰፊው ተነግሯል፥ በሰፊው ተጽፏል፥" ካልኩ በኋላ ተጨማሪ ለመጻፍ ብዕሬን
በማንሣቴ ሰው ሳይታዘበኝ ራሴን ቀድሜ ታዝቤዋለሁ። ስለዚህ፥ እስካሁን በተነገረውና በተጻፈው ውስጥ ያልጎሉ ወይም በአጭር
የተቀጩ ነጥቦችን ብቻ በጥቂት ገጾች ለማስፈር እሞክራለሁ። እንደ መግቢያ በንግሥ መብት (legitimacy to rule) ልጀምር።

ማነው ነጋሢው?

እስካሁን በደረሰን ባህል መሠረት፥ ሕዝብም የተቀበለው፥ የመንገሥ መብት ያላቸው ሰዎች ነበሩ። የመንገሥ መብት የሌለው ሰው
አይነግሥም ነበረ። የሚገርመው፥ አንዳንድ ሰነዶች እንደሚያመለክቱት የመንገሥ መብት ያለው ባይነግሥም "ንጉሥ" ይባል ነበር።
መንግሥትም እንደር ርስት አንድ ቤተሰብ ለልጁ የሚያወርሰው ሀብት ነበር። "አፄ በጉልበቱ" የሚባለው አነጋገር አንድ ጡንቸኛ
ተነሥቶ፥ የበላይ ለመሆን መብት ሳይኖረው የበላይ ልሁን ሲል ነው። በኢትዮጵያ ለመንገሥ የሚፈልግ ሰው መጀመሪያ ማድረግ ያለበት
መንግሥቱን ያቋቋሙት የአክሱም ቤተ መንግሥት ዝርያ መሆኑን ዐውጆ ነበር። የዛጔ ነገሥታት ምንም ጻድቃን ቢሆኑ፥ ተቀባይነት
ያጡት የአክሱም የንጉሥ ቤት ቀጣይዎች ባለመሆናቸው ነው። ቢቸግራቸው፥ ንግሥት ማክዳ ኢየሩሳሌም ሄዳ፥ ከንጉሥ ሰሎሞን ልጅ
ስታረግዝ የኛ እናት አሽከር ሆና አብራ ሄዳ ስለነበር፥ እሷም አርግዛ ተመልሳለች የሚል ታሪክ ፈጠሩ። ይኩኖ አምላክ በ1263 ዓ. ም.
(በ1270 ዓ. እ.)፥ ካሣ በ1848 ዓ ም. (በ1855 ዓ. እ.) ለመንገሥ ሲያስቡ መጀመሪያ ያደረጉት፥ የቤተ መንግሥት ዘር መሆናቸውን
ማስነገር ነበር።

አንድ ጊዜ በዘመነ መሳፍንት የኢትዮጵያ መንግሥት ወራሲ ነኝ የሚል ጀግና ጠፍቶ ነበር። የሆነውን የታሪክ ዘጋቢው እንዲህ ሲል
መዝግቦታል፤

በአልጋው ላይ ማንም የሚቀመጥበት ታጣ። ድሉ የራስ ወልደ ገብሬል ሆነ፤ ልጃቸውን ባባትህ አልጋ ተቀመጥ ቢሉት ስለ አባቱ
ሞት እያለቀሰ እምቢ አለ። አሉላም ጕግሣን እንዲህ አለው፤ “ባልጋው አንተ ተቀመጥ።” ጕግሣም አሉላን እንዲህ አለው፤ “ማን
ሰጠን ብለን በሰው አልጋ እንቀመጣለን?” አሉላም እንዲህ አለ፤ “ረቢ ሰጠን ብለን።” ከዚያ ወዲያም አሉላ ዐዋጅ ነገረ፤ እንዴህ
ብሎ፤ “የሞትነም እኛ፥ ያለነም እኛ፥ ለጕግሣ ያልታጠቀ ወንዱን ቁላውን፥ ሴቱን ጡቱን ይሰለብ” ብሎ ነገረ።

አልጋውን የየጁ እስላም ኦሮሞዎች የንግሥ መብቱን ረቢ (እግዚአብሔር) ሰጠን ብለው ያዙት። አቶ ካሣ የሚባሉ ጀግና፥ "መብቱ የእኔ
የነገሥታቱ ዘር ነው" ብለው ተነሥተው፥ "ደጃዝማች ውቤንና ራስ ዓሊን ደብዛቸውን አጥፍተው፥" የቴዎድሮስን ስም ይዘው
እስኪነግሡ ድረስ ገዙ። ልጅ ምኒልክም ሲነግሡ፥ ከልብነ ድንግል ተነሥቶ፥ በሣህለ ሥላሴ አባ ዲና ከዚያም በአባታቸው በኀይለ
መለኮት በኩል አድርጎ የደረሰው የጥንቱ አልጋ ወራሽ መሆናቸውን አሳይተው ነው።

የምኒልክ አርቆ አስተዋይነት ከምን እንደመጣ ገና ብዙ ጥናት ያስፈልገዋል። ትልቁ ምክንያት ግን በመቅደላ የአፄ ቴዎድሮስ እስረኛ
በነበሩበት ጊዜ ከሀገር ሊቃውንትና ከውጭ ሀገር እስረኞች ጋር መጎልመስ ሳይሆን አይቀርም። ዜጋቸው "እምየ ምኒልክ" እንዲላተው
አድርገውታል። የአፄ ተዎድሮስ ጭካኔ ሽንፈትን እንዳስከተለ ስላዩ፥ ተቀናቃኞቻቸውንም በፍቅር አሸነፏቸው። የቅኝ ገዢዎችን ተንኮልና
ዲፕሎማሲ አይተው በዘዴያቸው መቷቸው። የአፄ ምኒልክ አስተሳሰብ ምን ዓይነት እንደነበረ፥ ካቶሊካዊው አለቃ ዐፅሜ ያዩትን
እንዲህ ሲሉ አስፍረውታል፤
 2

አፄ ምኒልክ ዘውድ የደፉ ዕለት ከንጉሥ ሥልጣን ሰገድ ሱስንዮስ ጀምሮ የተሠራውን ሠላሳ አምስት ሹመት ለጦር አበጋዞቻቸው ሰጡ።
አፄ ዮሐንስም እንደባህሉ አድርገዋል። ሹመቱን የሰጡት ግን ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ነበር። አፄ ምኒልክ ግን ከሌላ አካባቢ ለመጡት
ጭምር እንጂ ለሼዎች ብቻ አልነበረም።

ቅድመ አድዋ ኢትዮጵያ እንደ ቴዎድሮስና እንደ ዮሐንስ ያሉ ታላላቅ ነገሥታት አግኝታ ነበር፤ ጀግንነትን፥ ሃይማኖታዊነትን፥
ብልሃተኝነትን ጎንጒኖ የታጠቀ ግን ምኒልክ ብቻ ነበር። አንድ ጸሐፊ አህያ ለማትችለው መጽሐፉ በጅቦች መንጋጋ ማህል (Richard
Caulk, Between the Jaws of Hyenas: A Diplomatic History of Ethiopia [1876-1896]) የሚል ርእስ የሰጠው፥
ከምዕራባውያን መንጋጋ ገብተው ሲያመልጡ አይቶ ነው። ለአህያዋ እዘኑላት።

ሌላው ታሪክ ጸሐፊያቸው (ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ) ደግሞ እንዲህ ይሉናል፤

ጥፋት የተገኘበት ሰው ገንዘቡን ተወርሶ እጁን ታስሮ መሬቱ ይሸጥ ነበር። ነፍስ የገደለ ሰውም ራሱ ቢያመልጥ ዘመዱ እስከ ሦስት
ትውልድ መሬቱ ይነቀል ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ ግን . . . ከዋያት በመለስ አዋሽ ድረስ ያለውን የጋሻ መሬት ሁሉ እንደመንዝ ርስት
አድርጌልሃለሁ። ምንም ብታጠፋ በገንዘብህ ተቀጣ እንጂ መሬትህ አይነቀል ብለው አዋጅ ነገሩ።

የኢየሩሳሌሙ የኢትዮጵያ ገዳም ታሪክም አፄ ምኒልክን የሚያስከብር ድርጊት እንዲህ ሲል መዝግቧል፤

ጥንት የክርስቲያን ሀገሮች በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም ቦታ ሲይዙ ኢትዮጵያም ይዛ ነበር። ግን እዚያ የሚኖሩ መነኮሳት ሕይወት
ነገሥታቱን ሁል ጊዜ ያስቸግር ነበር። በተለየ መንገዱ በሙስሊሞች ኃይል ስለተያዘ እንኳን ገንዘብ ሊላክላቸው ጳጳስ ከግብጽ
የሚመጣው እንኳን በስንት ጭንቅ ነበር። አርቆ አስተዋዩ አፄ ምኒልክ መነኮሳቱን በወለዱ ሊያኖራቸው የሚችል ገንዘብ ኢየሩሳሌም
በሚገኝ ባንክ አስቀመጡላቸው። መኳንንቶቻቸውም እዚያ ቤት እንዲያሠሩ መክረዋቸው፥ የሠሯቸው ቤቶች እስከዛሬ ይከራያሉ።

የአፄ ምኒልክ ስልተኛነት፤

ዋና ዋናዎቹን በአጭር በአጭሩ ልዘርዝራቸው፤

አንደኛ፤ የአፄ ቴዎድሮስ እስረኞች መቅደላ ላይ ሲማቅቁ ልጅ ምኒልክና አጃቢዎቻቸው ምንም ሳይነካቸው አመለጡ።

ሁለተኛ፤ የወሎ ገዢ ልዕልት ወርቄም ልጇ ስለታሰረባት፥ ምኒልክና አጃቢዎቻቸው በእሷ ግዛት ሲያልፉ፥ ይዛ ለልጇ መድን ለአፄ
ቴዎድሮስ አሳልፋ ትሰጣቸዋለች ተብሎ ተፈርቶ ነበር። ግን ወሬው እውነት ይሁን አይሁን ሳይታወቅ፥ ያመለጡት ልጇን ገደል ሲሰዱት
በማየት ለራሳቸው ፈርተው መሆኑን አስወሩ። ወርቄ በዚህ ተናድዳ፥ እነምኒልክን ዘብ ሰጥታ፥ ሸኘቻቸው።

ሦስተኛ፤ ሸዋ ሲገቡ ግዛቱ ይገባኛል በሚል ሹም ተይዛ ደረሱ። እሱን በጥቂት ሠራዊት ማሸነፍ ትልቅ ዕውቀተ ያስፈልጋል።

አራተኛ፤ አፄ ዮሐንስ ነግሠው ምኒልክን ገብር ሲሏቸው፥ መኳንንቶቻቸው "እንዋጋለን እንጂ ለአፄ ዮሐንስ አንገብርም፤ ንጉሠ ነገሥት
ዘኢትዮጵያ ከተባሉ በኋላ፥ ንጉሠ ሸዋ መባልዎን አንቀበልም፤ ውርደት ነው" ሲሉ፥ እንግሊዞች ለአፄ ዮሐንስ የሰጧቸው መሣሪያ ምን
ያህልና ምን ዓይነት እንደሆን ስለሚያውቁ፥ ለጊዜው መገበርን መረጡ፤ ድንጋይ ተሸክመው ይቅርታ ጠየቁ። አፄ ምኒልክ ሊያሸንፉት
የማይችሉትን፥ ለማሸነፍ ጊዜና ዘዴ ይፈልጉለታል እንጂ፥ ጦር አይገጥሙትም።

አምስተኛ፤ አፄ ዮሐንስ በንዴት በሱዳን ደርቡሾች ላይ ሲዘምቱ፥ አፄ ምኒልክ ከደርቡሾች ጋር በእንግሊዞች ላይ የጋራ ግምባር ፈጠሩ።
እንግሊዞች ሪር አድሚራል ሂወትን ልከው አፄ ዮሐንስን እንደቀለዱባቸው፥ ሬነል ሮድን ልከው አፄ ምኒልክን ሊቀልዱባቸው ቢሞክሩ
አልተሳካላቸውም። አምባሳደር ሬነል ሮድ አፄ ምኒልክ እንደቀለዱበት ያወቀው ወደመጣበት ከተመለሰ በኋላ ነው። ግን እዚያው ባለበት
ጊዜ የውል ውይይት ሳይጀምሩ ከማን ጋር እንደሚዋዋል በምልክት ሲያስጠነቅቁት፥ "ጣሊያን ምጽዋን እንድትይዝ ለምን ጋበዛችኋት?"
አሉት። ሲሰማ ክው አለ። ምንም ከማያውቅ የዋህ ሰው ጋር የሚነጋገር መስሎት ነበር። የመጣው ኢትዮጵያ ከሱዳን ደርቡሾች ጋር
እንዳትስማማ ቃል እንዲገቡለት ነበር። የማይከበር ቃል ያለው እንግሊዝ አገር ብቻ መስሎታል። "ግዴለህም፥ ደርቡሾች የሃይማኖታችን
ጠላቶች ናቸው። እኛ እንደናንተ ክርስቲያኖች ነን" ሲሉትና በሰማው ሲደሰት፥ የደርቡሽ መልእክተኞች ከጓዳ ሆነው ይስቁ ነበር።
እንግሊዝና ፈረንሳይ በኮሎኒ ሽሚያ ጊዜ በማህላቸው ግጭት እንዳይነሣ ሁለቱ ሀገሮች መስማማታቸውን ንጉሡ ስለሚያውቁ፥ የሱዳኖቹ
መልእክተኞች ከመመለሳቸው በፊት የሰጧቸው ምክር፥ "በምሥራቅ (ከግብጽ) እንግሊዞች ሲመጡባችሁ፥ የፈረንሳይ ባንዲራ ሰቅላችሁ
ጠብቋቸው። በምዕራብ (በፋሹዳ) ፈረንሳዮቹ ሲመጡባችሁ የእንግሊዝ ባንዲራ እያውለበለባችሁ ተቀበሏቸው" የሚል ነበር። ሰይጣን
መስቀል ሲያይ እንደሚበረግግ ይበረግጋሉ ማለታቸው ነው።

የተንኮታኮተችውን ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ሌሎቹ ሲሳናቸው አፄ ምኒልክን የቀናቸውም በዚሁ በዘዴኛነታቸው ነው።
 3

የአፄ ምኒልክ ስልተኛነትና የአድዋ ድል፤

አፄ ምኒልክ ስልተኛ ገዢ መሆናቸውን ታሪካቸው ሲያሳየን፥ እውነትም እኮ አድዋ ላይ የተገኘው ድል ከውጊያው ይልቅ በንጉሡ የጦር
አቅድ አውጪነት ነው ለማለት ያስደፍራል። እነዚህን በታሪክ ምንጮች የተደገፉ ነጥቦች እንመልከት፤

አንደኛ፤ የታሪኩ መምህር ዶክተር ሹመት ሲሻኝ እንደጻፈው፥ አፄ ምኒልክ የአድዋ ጦርነት እንደሚነሣ ቀደም ብለው ስላወቁት፥
ሠራዊታቸው ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ ድረስ ሲጓዝ እንዳይቸገር በሚሰፍሩበት ቦታ ሁሉ አስፈላጊውን ስንቅ ቀደም ብለው
አከማችተው ነበር።

ሁለተኛ፤ አድዋ ላይ የኢጣልያን የጦር ሠራዊት ከምሽጉ ውስጥ እንዳለ ሊገጥሙት ፈልጎ ነበር፤ አልፈለጉም። የመሸገን ጠላት
ለማሸነፍ እንደማይቻል በአፄ ዮሐንስ ላይ ሰሐጢ ላይ ከደረሰው ሽንፈት ስለተማሩ፥ በዘዴ አስወጡት። የምኒልክ ጦር ተዳክሟል
የሚል ሰላይ ላኩበት። እውነት መስሎት ሲወጣላቸው ልብ-ራሱን አሉት።

ሦስተኛ፤ አፄ ምኒልክ ጦርነት እንደ ቸዝ ጨዋታ መሆኑን ያውቁ ነበር። በቸዝ ጨዋታ ንጉሡ ከሞተ፥ ሠራዊቱ እንዳለ ቢሆንም፥
ንጉሡ የሞተበት ተጫዋች ተሸናፊ ይሆናል። ኢትዮጵያ ከሱዳን ደርቡሾች ጋር መተማ ላይ ባደረገችው ጦርነት ያገኘችውን ድል
ያጣችው ንጉሣችን አፄ ዮሐንስ ጦሩን ስለመሩት ነው። ንጉሡ ተመትተው ሲወድቁ፥ ሠራዊታችን ተበተነ። አፄ ምኒልክ ግን
የአድዋን ጦርነት ያዋጉት አደጋ በቀላሉ ከማይደርስባቸው ሰዋራ ቦታ ላይ ሆነው ነበር። ሆኖም፥ ከኢትዮጵያ ብዙ ሰው ሞቷል።
ግን ከሞቱት ውስጥ አንዱ ንጉሡ ቢሆኑ ኖሮ፥ የተሸነፈው ጠላት መሸሹን ትቶ ተመልሶ መጥቶ ድላችንን ይቀማን ነበር፤ አድዋም
ሌላዋ መተማ ትሆን ነበር። ግን በንጉሡ የጦር ስልት ዐዋቂነት ተሸንፎ ሸሸ።

ድርሰቴን ስለ አድዋ ድል የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስተር የነበረው ዊንስተር ቸርችል (Sir Winston Churchill) የጻፈውን በመጥቀስ
ልደምድም፤

On the 1st of March, 1896, the Battle of Adwa was fought and Italy, at the hands of Abyssinia,
sustained a crushing defeat. Two results followed which affected other nations. First, a great
blow had been struck at European prestige in North Africa. Second, the value of Italy as a factor
in European politics was depreciated.

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ. ም. የአድዋ ጦርነት ተካሂዶ፥ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ እጅ ያደቆሳት ሽንፈት ደረሰባት። (ይህም) ሌሎች
ሕዝቦችን የሚነካ ሁለት ውጤቶች አስከተለ፤ አንደኛ፥ ሰሜን አፍሪካ ላይ አውሮፓዊ ክብርን ትልቅ ምች መታው። ሁለተኛ፥ በአውሮፓ
ፖለቲካ ማንነት ረገድ የኢጣልያ ዋጋ ወደታች ወረደ።

ቸርችል ስለ ኢጣልያ ሽንፈትና ውጤቱ ከመጻፍ ይልቅ ስለ ኢትዮጵያ ድልና በአፍሪካና በሌሎቹ ጭቁን አገሮች ዘንድ የኢትዮጵያን
ማንነት ሽቅብ መናሩንና ለድኩማን የልብ ልብ መስጠቱን ቢጽፍ ተገቢ ነበር፤ ግን አልፈለገም።