Sunday, August 19, 2012


አቦይ ስብሃት ነጋ ታገዱ



(ኢ.ኤም.ኤፍ) የህወሃት መስራችና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት ስብሃት ነጋ ከማንኛውም መንግስታዊ ስራ ታገዱ። ለኢ.ኤም.ኤፍ የደረሰው መረጃ እንደገለጸው ከሆነ፤ ስብሃት ነጋ የኢትዮጵያን መንግስትም ሆነ ኢህ አዴግን በመወከል ምንም አይነት መግለጫ እንዳይሰጡ መመሪያ ተላልፎባቸዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ አቶ ስብሃት ነጋ ከአሜሪካ ድምጽ እና ከጀርመን ሬዲዮ ጋር አድርገውት የነበረው ቃለ ምልልስ ከዋልታ ኢንፎርሜሽን፣ ከኢ.ዜ.አ፣ ከትግራይ ኦን ላይ እና ከአፍቃሬ ኢህአዴግ ድረ ገጾች ላይ እንዲነሳ ወይም እንዲሰረዝ ተደርጓል። አሁን ያለው ውጥረት የተፍጠረው በአቶ በረከት ስምኦን እና በአቶ ስብሃት ነጋ ቡድን መካከል መሆኑ ነው። ይህንን በድርጅት አገላለጽ ከመነዘርነው ደግሞ፤ ፍጥጫው በህወሃት እና በብአዴን መካከል የተፈጠረ ይመስላል። በአሁን ወቅት የጦር አዛዥነቱን ሚና የህወሃት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የተቆጣጠሩት ሲሆን፤ የደህንነት መዋቅሩን ደግሞ የበረከት እና የጌታቸው አሰፋ ቡድን እየተቆጣጠረው ነው።

በአሁኑ ወቅት የደህንነት ሚንስትሩ ጌታቸው አሰፋ እና በረከት ስምኦን በተለይ በከተሞች አካባቢ ያሉትን እንቅሳቃሴዎች በመከታተል ላይ ሲሆኑ፤ አሁን ባሉት ባለስልጣናት ላይ ጭምር ክትትል ያደርጉባቸዋል። ከዚህ ጠንካራ ክትትል ውስጥ ከገቡት ሰዎች መካከል አንዷ የጠቅላይ ሚንስትሩ ሚስት አዜብ መስፍን ሲሆኑ፤ በአሁኑ ወቅት የት እንዳሉ አይታወቅም። በተመሳሳይ ሁኔታ አሁን ደግሞ በስብሃት ነጋ ላይ ክትትል እየተደረገበት መሆኑን የደህንነት ምንጮች ገልጸውልናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በለንደን ኢምባሲ ይሰራ የነበረውና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለኢህአዴግ ተገዢነቱን በማረጋገጥ እራሱን ዝቅ አድርጎ ይሰራ የነበረውን ሙሉጌታ አስራተ ካሳ በፓትርያርኩ ሞት ጉዳይ ለቢቢሲ ቃለ መጠይቅ በመስጠቱ ከኢምባሲው እያለቀሰ በደህንነቶች መባረሩን ታውቋል።
ማስታወሻ - አቶ ስብሃት ነጋ እንደኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1928 ዓ.ም. በአድዋ ከተማ፣ በትግራይ ክፍለ ሃገር ተወለዱ። ህወሃትን በ1967 ዓ.ም. በመቀላቀል፤ ማንፌስቶውን ከነደፉት እና በህወሃት ውስጥ የድርጅት ሃላፊ ሆነው የሰሩ ሰው ነበሩ። አሁንም በህወሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ውስጥ ተራ አባል ሆነው እየሰሩ ይገኛሉ::

No comments:

Post a Comment