Friday, November 30, 2012

የጁነዲን መጨረሻ አልታወቀም


የጁነዲን መጨረሻ አልታወቀም(http://www.goolgule.com/)

junedin sado1
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የኢትዮጵያን ታላቅ የሥልጣን መቀመጫ ሲረከቡ “ለተደረገልን ምደባ አመሰግናለሁ” ማለታቸውን ተከትሎ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ሹመት “ምደባ” የሚል ስያሜ አግኝቷል። ትላንት ለተወካዮች ምክር ቤት በቀረበ የሽግሽግ ምደባ አቶ ጁነዲን ሳዶ ከምደባ ተዘለው ከሃላፊነታቸው መነሳታቸው ይፋ ሆኗል።
የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ጁነዲን ሳዶ ወንበራቸውን ለአቶ ሙክታር ከድር እንዲያስረክቡ ተደርጓል። ኦህዴዱ አቶ ሙክታር የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ታክሎላቸው አቶ ጁነዲን ሲመሩት የነበረውን የሲቪል ሰርቪስ ተቋም እንዲመሩ ሲደረግ አቶ ሃይለማርያም ስለአዲሱ ተሿሚ አቶ ሙክታር ቁርጠኛነትና ብቃት ሲያብራሩ ስለ አቶ ጁነዲን ከሃላፊነት መነሳት ግን ያሉት ነገር የለም።
አድሃና ሃይለ
ለዚህም ይመስላል የመድረክ አባል ብቸኛው ተቃዋሚ አቶ ግርማ ሰይፉ “ህዝብ የማወቅ መብት አለው” በማለት ስም ሳይጠሩ አቶ ጁነዲን የተነሱበት ምክንያት እንዲገለጽ “የተከበረውን” ፓርላማ የጠየቁት። ሚኒስትሮች ሲሾሙ መልካም ነገራቸው የሚገለጸውን ያህል ከስልጣን ሲነሱም ምክንያቱና በደላቸው ለህዝብ ሊነገር እንደሚገባው ሲጠይቁ መረጃው በፓርላማ ውስጥ ላሉት ሁሉ ጠቃሚ እንደሚሆን በማመላከት ነበር።
የነገሩ አካሄድ ያላማራቸው ህወሓቱ ዶ/ር አድሃና ሃይለ ምደባውን በተመለከተ “መክረንበታል” በማለት ምደባውን ወደ ማጸደቁ ስነስርዓት መሸጋገሩ እንደሚሻል ባሳሰቡት መሰረት ምክትል አፈ ጉባኤዋ መድረኩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰጡ።“አመሰግናለሁ ምክትል አፈጉባኤ” በማለት ምላሻቸውን የጀመሩት አቶ ሃይለማርያም ከምደባው በፊት በቂ የተባለ ግምገማና የተለያዩ ልምዶች መወሰዳቸውን ደጋግመው በመግለጽ አቶ ግርማ ላነሱት መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ሳይሰጡ አልፈውታል።
አቶ ጁነዲን ባለቤታቸው ከማንኛውም ችግር የጸዱና በእናታቸው ኑዛዜ አማካይነት መስጂድ ለማሰራት ከመንቀሳቀሳቸው ውጪ በተከሰሱበትና ፖሊስ ጠረጠርኳቸው ባለው ጉዳይ ሊገመቱ እንደማይገባ አቋማቸውን በመግለጽ ለሚዲያ ባሰራጩት መልክት ይፋ አድርገው ነበር። በዛው ሰሞን ኦህዴድ ውስጥ በተካሄደ “የመደብ ትግል” ግምገማ ከኦህዴድ ስራ አስፈጻሚነታቸው እንዲገለሉ መወሰኑ ይታወሳል።
በ1997 ዓ ም ምርጫ ኢተያ ወረዳ ተወዳድረው ከተሸነፉ በኋላ በይግባኝ እንደገና ለመመረጥ የቻሉት አቶ ጁነዲን በድጋሚው ምርጫ ሃይማኖታቸውን ተገን በማድረግ ያካሄዱት ቅስቀሳ ቀደም ሲል የኦሮሞ ኮንግረንስ ተወካይ የሆኑትን የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ እጩ የመረጡትን ሰዎች መቆሚያና መቀመጫ ያሳጣ እንደነበር የሚስታውሱ በሰጡት አስተያየት “አቶ ጁነዲን በልዩ ክትትል ስር እንዲሆኑና ከኦሮሚያ ፕሬዚዳንትነታቸው እንዲነሱ የተደረገበትም ምክንያት አርሲ ኢተያ ላይ ያካሄዱት የዳግም ምርጫ ዘመቻ ጣጣ ነው” ይላሉ። በወቅቱ የተደረገውን ቅስቀሳ ዛሬ መድገም አስፈላጊ እንዳልሆነ የጠቆሙት አስተያየት ሰጪዎች “ወቅቱን ስናስበው ይዘገንነናል” በማለት ዝርዝር ከማቅረብ ተቆጥበዋል።
በተመሳሳይ እዛው ኢተያ ምርጫ ጣቢያ በዝረራ ከተሸነፉ በኋላ መንገድ ላይ የምርጫ ኮሮጆ በማዘረፍ እንዲደገም በተደረገው ምርጫ ተወዳድረው ያሸነፉት አባዱላ ገመዳ የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በተወሰነው መሰረት ስልጣን የማስተላለፉ ስነስርዓት እንዳለቀ አቶ ጁነዲን “በሃላፊነቴ እንደማልቀጥል አስቀድሜ ከዓመት በፊት አውቀው ነበር” ማለታቸው በወቅቱ አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር።
በቅርቡ ኦህዴድ ውስጥ ተፈጥሯል በተባለው ችግር ሳቢያ በተካሄደ ግምገማ ከስራ አስፈጻሚነት የተነሱት አቶ ጁነዲን ሳዶ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ህግ ፊት እንደሚቀርቡ ኦህዴድ ያካሄደውን ግምገማ አስመልክቶ ውስጥ አዋቂዎችን በመጥቀስ ሰንደቅ ጋዜጣ መዘገቡ አይዘነጋም። ሪፖርተር ጋዜጣ በበኩሉ በተመሳሳይ ከድርጅት ስራ አስፈጻሚነት መነሳታቸውን ዜና ሲያደርግ ወደፊት ወደ ቀድሞው ሃላፊነታቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ ተናግሮ ነበር። ከወራት በኋላ አቶ ጁነዲን ከስልጣናቸው ቢነሱም መጨረሻቸው ምን ሊሆን ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል።
ለጀርመን ድምጽ አማርኛው ክፍለጊዜ አጭር አስተያየት የሰጡት የአፍሪቃ ቀንድ ፖለቲካ በመተንተን የሚታወቁት አቶ ዩሱፍ ያሲን አቶ ጁነዲን ሳዶን አስመልክተው ለቀረበላቸው ጥያቄ “ምንም ማለት አይቻልም” በማለት ነበር መልሳቸውን ጀመሩት።ሲያብራሩም የአቶ ጁነዲን ባለቤት ቢከሰሱም እሳቸው ግን በሽብርተኛነት ከተከሰሱት 29 ተጠርጣሪዎች መካከል የሉበትም፣ በግምገማም ወቅት ተነሳ የተባለው ትክክለኛ ፍርድ አልሰጡም የሚል በመሆኑ ለጊዜው በግልጽ የታወቀ ነገር ስለሌለ አሰተያየት ለመስጠት እንደማይቻል በመጥቀስ አስተያየታቸውን ደምድመዋል። አስተያየት ሰጪው እንዳሉት ከመንግስት በኩል እስካሁን ጥርት ያለ መረጃ ባለመቅረቡ ጉዳዩ አስተያየት ለመስጠት እንደሚያስቸግር በተመሳሳይ ጎልጉል ያነጋገራቸው ገልጸዋል።
አቶ ዩሱፍ አጠቃላይ ምደባውን አስመልክቶ ግን በብሄር ተደራጅተው እንዲወዳደሩ የተፈጠሩት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች በስልጣንና በሃብት ክፍፍል የተነሳ የገቡበት ችግር በዚህ ሽግሽግ መፍትሄ ያገኛል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል። ከአቶ መለስ ሞት በኋላ በስብሳባ የተጠመዱበት ችግር የጠና እንደሚመስላቸው የገለጹት አቶ ዩሱፍ፣ ወደፊት ኢህአዴግ በሚያካሂደው ጉባኤ፣ አሊያም ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ እስከሚያካሄደው ምርጫ ድረስ ችግሩን ለማስታመም የታቀደ እንደሚመስላቸው አመልክተዋል። የተደረገውን ሽግሽግ ችግር ፈቺ ሳይሆን በአገሪቱ ዋና ስልጣን እርከኖች ላይ የአንበሳው ድርሻ የማን ነው የሚለው ጉዳይ ያስከተለው ችግር በዚህ ውስን በሆነ ሽግሽግ መፍትሄ ሊያገኝ እንደማይችልም ጠቁመዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የጠ/ሚ/ር መንበር የተነፈገው ኦህዴድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነቱንም መቀመጫ በትላንትናው ምደባ ተዘልሏል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ የኦህዴድ ጉባዔ አቋም ወዴት እንደሚያመራ ከወዲሁ ፍንጭ የለም፡፡ ይሁን እንጂ ጁነዲንን አስመልክቶ የኦህዴድ ምክርቤት በተለይ የሚወስነው ውሳኔ ከአቶ ሙክታር የምክትል ጠ/ሚ/ርነት ምደባ በላይ አጓጊ ሆኗል፡፡ የዛሬ አራት ዓመት አካባቢ አቶ ሙክታር ከኦሮሚያ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ተነስተው በኢህአዴግ ቢሮ ያለሥራ እንዲቀመጡ ሲደረግ በወቅቱ ሚ/ር የነበሩት አቶ ጁነዲን በወዳጆቻቸው አማካኝነት አቶ ሙክታር ወደ ጠ/ሚ/ር ቢሮ ኃላፊነት እንዲጠጋጉ ታላቁን ሚና መጫወታቸው በተለያየ ወቅት መገለጹ ይታወሳል፡፡