Sunday, December 30, 2012

ሃዋሳ ነኝ

ሃዋሳ ነኝ፡፡ በወሰን ሰግድ
ዕለተ ቅዳሜ ታህሣሥ 20/2005 ዓ.ም በጠዋቱ ተነስቼ ጉዞ ጀመርኩ፡፡ ፀሃዩ ሳይገር ሃዋሳ ለመድረስ የትራንስፖርት ምርጫ አላስፈለገኝም፡፡ ለመንቀሳቀስ ሁለት ሰው የጎደለው ቅጥቅጥ የሚባል ሎንችን የመጨረሻው ወንበር ላይ ቦታ አገኘሁ፡፡ ወዲያው ከወጣትነት እድሜ የገፋችና ጠና ያለች ወፍራም ሴት የቀረውን ቦታ ሞላችው፡፡ አጣበበችን ሳይሆን አጨናነቀችን ማለት ይቻላል፡፡ እንኳንም አጨናነቀችን፡- አይ ዳሌ አይ ሰውነት፡፡
እኔ ግን ደንታ አልሰጠኝም፡፡ አቃቂን አልፈን፣ ዱከምን አልፈን፣ ደብረዘይት ከተማ እስክንደርስ የምናቋርጣቸውን ቦታዎች በመስታወት አሻግሬ ለማየት አንድ ጊዜ እንኳን ቀና አላልኩም፡፡ ባለፈው ሳምንት ለገበያ የቀረበው “ነገረ ሃበሻ” የተሰኘ መፅሃፍ ሰቅዞ ይዞኛል፡፡ አንዴ ያስፈግገኛል፤ አንዴ ያስገርመኝና ብቻዬን ያናግረኛል፡፡ አንዴ ያስቀኛል፡፡ አጠገቤ የተቀመጡት ሰዎች በልባቸው “ንክ ቢጤ ነው መሰል” ሳይሉኝ አይቀሩም፡፡ ሁኔታቸው ያስታውቃል፤ እየተገለማመጡ በትዝብት ያዩኛል፡፡
ይግረማችሁ ያልኩኝ ይመስል፣ የተሳፈርኩበት ሎንችን ደብረዘይት ከተማን እያቋረጠ ሳለ ከት ከት ብዬ ሳቅኩኝ፡፡ ተሳፋሪዎቹ ምን መጣ ብለው አፈጠጡብኝ፡፡ “ነገረ ሃበሻ” ገፅ 91 ላይ ያነበብኩት ወግ ትረካ ነው ሳቄን ፈንቅሎ ያወጣው፡፡ ደራሲው መልካም ሰው አባተ እዚህ ገፅ ላይ “ከአራት ኪሎ እስከ ቤተ መንግስት” በሚል ንሁስ ርዕስ ሥር የዚህ ተመን ትውልድ ሃገራዊ ጉዳዮች ከያዙ የህትመት ውጤቶች ይልቅ የሴት ዳሌ የሚያሳይ ፎቶ ያለባቸው መፅሔቶች ማንበበብን መርጧል ይላል፡፡ ከዚያም እንዲህ ሲል ወጋዊ ስላቁን ይቀጥላል፡-
“…መንግስት ‹ዓለም ከዳሌ ትሰፋለች› ብለህ ተመራመር እንዳይለው ይገለብጠኛል ብሎ ፈራ፡፡ ይኼ መንግስት መቼም የማይፈራው የለ፡፡ ወጣት ይፈራል፤ ተማሪ ይፈራል፤ አስተማሪ ይፈራል፤ ዲያስፖራ ይፈራል፤ ላሜቦራ ይፈራል፤ ሽብር ይፈራል፤ ተሸባሪ ይፈራል፤ ተቃዋሚ ይፈራል፤ ተደጋፊ ይፈራል፤ ምርጫ ይፈራል፤ ታንክ ይፈራል፤ እኔን ይፈራል፤ ከእግዚአብሄር በቀር ሁሉንም ይፈራል….”
ከት ብዬ ሳቅሁኝ፡፡ መንግስት እኔን ሲፈራ እንዴት አልስቅ? አይ “ነገረ ሃበሻ”፡፡ ብቻ በመጽሐፉ ተመስጬ እንዴት እንዴት ሻሸመኔ እንደደረስን ሳላስተውል ባለ 171 ገፁን መፅሐፍ አጠናነቅኩት፡፡
ከቀኑ ሰባት ሰዓት ሃዋሳ ገባሁ፡፡ ለምን? ሄድኩ መሰላችሁ፡፡ ግጥም ፍለጋ (ሃሃሃ!! ይህቺ አገላለፅ ለራሴ ጣመችኝ)፡፡ አዎ የግጥም ጉባዔ ላይ ለመታደም፡፡ እስከዚያው ከዚህ ቀደም የማውቃቸው ወዳጆቼን ማግኘት ነበረብኝ፡፡ አገኘኋቸው፡፡ በእነሱ ሰበብ አንድ ሰው ተዋወቅሁ፡- ዶ/ር፡፡ ሥነፅሁፍና ፊዚክስን እያቆራኘ አፌን አስከፈተኝ፡፡ ይኼን ነገረ ቁርኝት ሌላ ጓዜ ሰፋ አድርጌ አወጋችኋለሁ፡፡ ለማንኛውም በሃዋሳ አጭር ቆይታዬ ከአንድ አመት በፊት የፃፍኩት “አላለቀም” የሚለው ግጥሜ ታወሰኝ፡፡ እሱን አቋድሻችሁ በቀጠሮ ብንሰነባበትስ!?
አላለቀም
ተጀመረ እንጂ አላለቀም
ፈፅሞ በዚህ ዓለም ላይ የሚያልቅ ነገር የለም፤
የጨረስነው የሚመስለን ፈፅመናል ያልነው ነገር
አበቃ ካልነው ቦታ ላይ እንደገና ነው ሚጀመር
ሌሎች ቋጭተናል ያሉት የድምድማቱ ማረፊያ
ለእኛ መነሻችን ነው የሀሳብ መሰናዘሪያ
እና ያንተ ጅምር ጥረት ጥንቅቅ ያለ ከመሰለህ
የህይወትን ታላቅ መክሊት ከእጅህ መሀል ትጥላለህ
ይኼኔ ነው ቀድሞ ማሰብ ይኼኔ ነው ደግሞ ማለም
በዚህ ዓለም ጅምር እንጂ የሚጨረስ ነገር የለም፡፡
እውነት እውነት እልሀለሁ
የኦሪቱ የሙሴ ህግ - በአዲስ ኪዳን ተሻሽሏል
የሶቅራጥስ ፍልስፍና - በፕሌቶ ተጠናክሯል
የኒውተንን ቀመር ሳይንስ - አንስታይን ሰልቆታል
የእነ እንትና ቀመር ደግሞ - በእነ እንትና ተመንድጓል
በአንዱ ራስ ላይ አንዱ በቅሏል፤
በአንድ ነገር ፍፃሜ ስር - አዲስ ነገር ይወለዳል
ህይወት እንዲህ ይቀጥላል፡፡
እንጂ ጨርሶ አያበቃም - አንዳችም ነገር አያልቅም
ፈፅሞ በዚህ ዓለም ላይ - የሚያልቅ ነገር አይኖርም፡፡
ናዝራዊው ኢየሱስ እንኳ - ተፈፀመ ሲል በጣሩ
መጋረጃው ተቀርድዶ - ተከፍቷል ትንሳዔ በሩ
ከላይ ከሰማይ የመጣው - በምድር ማህፀን አልፎ
የእኛን ሞት በሞቱ አትርፎ
ቀጥሏል ህይወትም በዓለም
የሚጀመር ነገር እንጂ የሚጨረስ ነገር የለም፡፡
እና ያንተ ጅምር ጥረት - መነሻ እንጂ በአዲስ ብርታት
ፍፃሜ ነገር አይሆንም - እማኝ አይደለም ለብቃት
ደግሞም ሀሳብ ዕውነትህ - ተጀመረ እንጂ አላለቀም
ፈፅሞ በዚህ ዓለም ላይ - የሚያልቅ ነገር የለም፡፡