Thursday, February 28, 2013

ብፁዕ አቡነ ማትያስ 6ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ


ብፁዕ አቡነ ማትያስ 6ኛው ፓትርያርክ ሆነው ተሾሙ

የካቲት ፳፩ (ሃያ አንድ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም 
ኢሳት ዜና:-ብፁዕ አቡነ ማትያስ 6ኛው    ስት ከፍተኛ ድጋፍ የነበራቸው በትግራይ አጋሜ አውራጅ በስቡህ ወረዳ የተወለዱት ብፁዕ አቡነ ማትያስ   6ኛው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ሆነው የፊታችን እሁድ ይሾማሉ።
በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ብፁእ አቡነ ማትያስ በቤተክርስቲያኗ ጉዳይ እጁን የከተተው የሕወሃት/ኢሕአዴግ መንግስት ምርጫም እንደሆኑ አስቀድሞም ሲነገር የነበር ሲሆን፣ እርሳቸውን ለዚሁ ሹመት ለማግባባት ባለፈው ታህሳስ ወር አንድ የልኡካን ቡድን ወደ ኢየሩሳሌም አቅንቶ እንደነበር በቤተክርስቲያኗ ጉዳይ የሚያተኩረው ደጀ ሰላም ድረ ገጽ በወቅቱ መዘገቡ ይታወሳል።
ለይስሙላ እንደተካሄደ በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራጨ ባለው ምርጫ አቡነ ማትያስ ከ800 መራጮች ውስጥ 500 ድምጽ እንዳገኙ ተነግሮላቸዋል። የአቡነ ማትያስን መመረጥ ተከትሎ ከቤተክርስቲያኗ አባቶችም ሆነ ከምዕመናኑ ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ እንደሚችሉ የሚገመት ሲሆን በተለይም በቅርቡ ተረቅቆ በሲኖዶሱ የፀደቀውን የፓትርያርክ ምርጫ ሕግ ከነዚህ ውስጥ ዋነኛው ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በተለይም ይህንን ሕግ በማርቀቁ ስራ ላይ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ብፁዕ አቡነ ሳሙዔል፣ ብፁእ አቡነ አብርሃምና ብፁእ አቡነ ገብርዔል ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የሲኖዶሱ ጉባዔ ላይ የአሜሪካ ዜግነታቸውን ከመለሱ ወደ ኢትዮጵያ የመጡበትን ፓስፖርት እንዲያሳዩ ጠይቀዋቸው ለማሳየት አለመቻላቸውን ኢሳት በወቅቱ መዘገባችን ይታወሳል። በተጨማሪም ሶስተኛው የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ በነበሩት በብፁእ ወቅዱስ አቡነ ተክለ-ሃይማኖት ተላፎባቸው የነበረው ውግዘት ሌላው አጠያያቂ ጉዳይ ይሆናል ተብሎአል።
በ1971 ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት ኤጲስ ቆጶስ ኾነው የተሾሙት ብፁዕ አቡነ ማትያስ፣ በ1974 ዓ.ም በስደት ወደ አሜሪካ በማቅናት እስከ 1984 ዓ.ም ከቆዩ በኋላ ወደ አገር ተጠርተው መጀመሪያ የአሜሪካ፣ ቀጥሎም የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ በመኾን ተመድበው እስካሁን ድረስ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
አዲሱን ፓትርያርክ መመረጥ ተከትሎ የተለያዩ ወገኖች አስተያየታቸውን አስፍረዋል። በኦሮቶዶክስ አማንያን ዘንድ ከፍተኛ ተጽኖ ከሚያሳድሩ ድረገጾች መካከል ታዋቂ የሆነው ደጀሰላም ፣ ከጳጳሱ ሹመት በሁዋላ ” ድራማው ተጠናቀቀ” ብሎአል።
ድረገጹ ” ለረዥም ጊዜ እንደታየው፣ ብዙዎች ቀጣዩ ፓትርያርክ አቡነ ሳሙኤል ይሆናሉ ወይም አቡነ ጎርጎርዮስ የሚል የተሳሳተ ግምት ነበራቸው። ሁለቱም የጨዋታው አዳማቂዎች እንጂ በጨዋታው ውስጥ ቦታ አልነበራቸውም። ወይም ርዕስ መሆናቸው በራሱ የጨዋታው አንድ አካል ነበር። ብዙ ሰው አሁንም ከጠቅላላው ድራማ አንዱ ክፍል ላይ ብቻ በመከራከር ጊዜውን እያጠፋ ነው። ጉዳዩ ቤተ ክርስቲያን ነጻ ናት ነጻ ወይስ አይደለችም የሚለው ነው። ” በማለት የአቡኑን መመረጥ አጣጥሎአል።
ማህሌት ሰለሞን  የተባሉ ሰው በፌስቡክ ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ ” መራጩም መንግስት ተመራጩም አቡነ ማቴያስ እንደሆኑ እያወቀን ምንም እንደማናውቅ ሊያታልሉት ይፈልጋሉ። ሐዋርያዊት ለሆነችው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በእኔ እድሜ አይናችን እያየ ለሁለተኛ ጊዜ ኢመንፈሳዊ በሆነ መንገድ ፓትሪያርክ ተሾመላት:: ይሄ አሳፋሪ የታሪክ ማህተም በምን ይሻር ይሆን ? በዘመኑ የነበርነውስ መልሳችን ምን ይሆን ? የተደረገልን እንደ ገዢው መንግስት ፈቃድ ነው:: እውነታው እሱ ነው።’ ብለዋል።
በስደት ላይ የሚገኘው ሲኖዶስ አዲስ የሚሾሙትን ፓትሪያርክ ህዝቡ እንዳይቀበል ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ሲኖዶሱ ” ላለፉት 21 አመታት በመንግስት አስተባባሪነትና ደጋፊነት በህገ ወጥ መንገድ በተቀመጡት አባት ምክንያት ቤተ ክርስቲያናችንን ክፉኛ የጎዳው መከፋፈል እና መለያየት ሳያንስ አሁን ደግሞ እነዚህ ጥቂት ጳጳሳት በስልጣን ያለውን የመንግስት ሀይል መከታ አድርገው ፓትሪያርክ ብለው የሚሰይሙትም ፣ አባትነቱ የሀሰት አባት፣ ሹመቱም የሲሞን መሰርኢ ስለሆነ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ያወግዘዋል በማለት ሹመቱን ውድቅ አድርጎታል።
ታዛቢዎች እንደሚገልጹት የአዲሱ ፓትርያርክ ሹመት ዘረኝነትና ፖለቲካዊ ወገንተኝነት በእጀጉ የተነጸባረቀበት ነው። ላለፉት 21 አመታት ተከፋፍላ የቆየችው ቤተክርስቲያን በአቡነ ጳውሎስ ሞት አንድ ልትሆን ተችላለች በማለት ተስፋ አድርገው የነበሩ ምእመናን ተስፋቸው ከተስፋነት ሳይዘል ቀርቷል።
አቶ ተፈራ ዋልዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ክርስቲያን የነፍጠኛው ዋሻ ሆናለች በማለት በ 97 ምርጫ ወቅት መናገራቸው ይታወሳል።