Tuesday, July 30, 2013

ጴጥሮሳዊነት (ፕ/ር መሰፍን ወልደማርያም)

ጴጥሮሳዊነት (ፕ/ር መሰፍን ወልደማርያም)

July 30, 2013

ቀደም ሲል « እግዚአብሔርና እኛ» በሚለው ርዕስ ስር የተነገረውን አንዳንድ ሰዎች ሌላ ትርጉም በመስጠት ጸረ ሃይማኖት ሊያስመስሉት ይሞክሩ ይሆናል። አይደለም ። እንዲያውም ሃይማኖትንና ሃይማኖተኛነትን የሚያጸና ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ምንም ዓይነት ሃይማኖት ቢኖረው ለእግዚአብሔር ያለው ፍቅርና በእግዚአብሔርም ላይ ያለው እምነት ብርቱ ነው። ይህንን ከመገንዘብ የተነሳና በዚያው ፍቅርና እምነት ላይ የተመሠረተ ስለሆነ በምንም መንገድ ጸረ ሃይማኖት መስሎ ሊታይ አይገባም።Prof. Mesfin Woldemariam
ችግሩ ሌላ ነው። ችግሩ በኢትዮጵያ ውስጥ ለመንፈሳዊ ተግባርና ኃላፊነት የሚያበቃ ሁኔታ አለመኖርና ወደፍጹምነት የሚጠጋ የመንፈሳዊነት ድርቀት ነው። እ.አ.አ. በ1977 ዓ.ም. ጉለሌ በሚገኘው የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ለካቶሊክ ሚስዮናውያን ንግግር እንዳደርግ ተጠይቄ የኅብረተሰባችን የመንፈስ ውድቀት (ክስረት) በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ተናግሬ ነበር። በዚያ ንግግር ውስጥ የሚከተለው በከፊል ይገኝበት ነበር።
በየቀኑ የጭካኔ ወሬ እንሰማለን። ወጣቱ ለወደፊት መዘጋጀቱን ትቶ፤ ክፉኛ ለሁለት ተከፍሎ እርስበርሱ ለመጫረስ ተነሥቶአል። ለበለጠ ግድያና መጨራረስ ጩኸት እንሰማለን፤ የእናቶችና የሚስቶችን ጩኸት እንሰማለን፤ የሐዘን ልብሳቸውንም እናያለን። የሞትን አደጋ በየአቅጣጫው እናያለን። የፍቅርን አለመኖር እንሰማለን፤ እናያለን፤ የተስፋን አለመኖር እንሰማለን፤ እናያለን። ንዴትን እናያለን፤ እንሰማለን፤ ተስፋቢስነትን እንሰማለን፤ እናያለን፤ ሐዘንን እንሰማለን፤ እናያለን። ከዚህም በላይ ንዴቱም ተስፋቢስነቱም ሐዘኑም ይሰማናል። ሕይወት አጠራጣሪና በቀላሉ የሚጠፋ ሆኖአል። እንሰማለን፤ እናያለን፤ እናያለን፤ እንሰማለን። ምንም አናደርግም። ይህ ምንም ያለማድረግ ውሳኔና ይህ በኅብረተሰቡ ኑሮ ውስጥ ያገባኛል የሚል ስሜት መጥፋት ግልጽ የሆኑ የወላጆችን፤ የአስተማሪዎችንና የሃይማኖት መሪዎችን የመንፈስ ውድቀት የሚያመለክቱ ናቸው። ለግፍ፤ ለበደልና ለጥቃት እንድንገብር፤ ግፍን በደልንና ጥቃትን አየሰማንና እያየን ምንም እንዳናደርግ የሚያደርገን ምንድን ነው?
እኔ እንደሚመስለኝና እንደማምነውም የጉዳዩ ባለቤት ራሳችን መሆናችንን ተገንዝበን ኃላፊነቱንና የሚያስከትለውንም ውጤት ላለመቀበል የፈጠርነው የመከላከያ ዘዴ ጉዳያችንን ሁሉ ወደእግዚአብሔር መወርወሩን ነው። የሚደንቀው ነገር የሃይማኖት መሪዎችን መለየቱ ለምን አስፈላጊ ሆነ? የሃይማኖት መሪዎች «ሥጋቸውን የበደሉ፤ለነፍሳቸው ያደሩ» ናቸው ይባላል። የሃይማኖት መሪዎች ለጽድቅ ማለት ለእውነት እንዲሁም ለፍትሕና ለእኩልነት የቆሙ ናቸው ተብሎ ይታመናል። ለሃብትና ለሥልጣን ግድ ስለሌላቸው ከዚህ ዓለም ጣጣ ውጭ ናቸው ይባላል። እንግዲህ እንደዚህ ዓይነቶቹ ለእግዚአብሔር አድረናል የሚሉ ሰዎች ለግፍ ለበደልና ለጥቃት እንዲገብሩ የሚያደርጋቸው ከየት የመጣ ኃይል ነው? ከእግዚአብሔር ሊሆን አይችልም። ለዚህ ዓለም ሕይወት ካላቸው ጉጉት ብቻ የሚመነጭ ነው። የሚጎድላቸው ጴጥሮሳዊነት ነው።
የአቡነ ጴጥሮስ መንፈስ እንደሐውልታቸው የተረሳ ይመስለኛል። አቡነ ጴጥሮስ እንደሌሎቹ ሁሉ ኢጣልያ ኢትዮጵያን የወረረችው «የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ ነው»፤ በማለት የኢጣልያ ወታደር የኢትዮጵያን ሕዝብ አበሳውን ያሳየው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው በማለት ሊገብሩና የተደላደለ ኑሮ ለመኖር ይችሉ ነበር። አቡነ ጴጥሮስ የራሳቸውንና የአገራቸውን ጉዳይ ወደ እግዚአብሔር ሳይወረውሩ ኃላፊነታቸውን ሳይሸሹ «እምቢኝ አሻፈረኝ!» አሉ። በእምቢተኛነታቸውም የኢጣልያን ክርስቲያንነትና ሥልጡንነት ፈተና ውስጥ ከተቱት። በእምቢተኛነታቸው ለእግዚአብሔር ለአምላከ ጽድቅ ያላቸውን ፍቅርና ክብር፤ ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ጽናት፤ ለጨበጡት መስቀል ለመስዋዕትነት ምልክቱ ያላቸውን ስሜት ለአገራቸውና ለወገናቸውም ያላቸውን ታማኝነት አረጋገጡ። በመትረየስ ተደበደቡ።ዛሬ በዚህ ድርጊት ኢትዮጵያ ትኮራለች፤ ኢጣልያ ታፍራለች።
ጴጥሮሳዊነት የምለው የአቡነ ጴጥሮስን ዓይነት የእምቢተኛነት መንፈስ ነው። ጴጥሮሳዊነት በእግዚአብሔር አምላክ ጽድቅነት (ጽድቅ እውነት ማለት ነው) አምኖ የራስንም ኃላፊነት ከነውጤቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው ብሎ መቀበል ነው። ጴጥሮሳዊነት በመሠረቱ መንፈሳዊነት በመሆኑ የሚመካበት ኃይል መንፈሳዊ እንጂ አካላዊ ወይም ጠመንጃ አይደለም። የጴጥሮሳዊነትም ዓላማ አስፈላጊ ከሆነ ለእምነቱ ለመሞት እንጂ ለመግደል አይደለም። ሰው ሲገደል የሚቀረው በድን ሬሣ ነው። ገዳዩም ከዚያ ከበድን ሬሣ የተለየ፤ ወይም ከተጠቀመበት የመግደያ መሣሪያ የማይለይ ነው። በአካል ደረጃ ገዳይና የተገዳዩ ሬሣ ቢመሳሰሉም፣ በመንፈስ ደረጃ የማይገናኙ ናቸው። እውነትን እገድላለሁ ብሎ የሰውን ሕይወት የሚያጠፋ በድን፣ እውነትና የሰው ደም እንዳስደነበረውና እንዳቃዠው ከበድንነት ወደበድንነት ይተላለፋል። ለእውነት የተገደለው ግን እውነትን በሕይወቱ መስዋዕትነት አዳብሮና አፋፍቶ ያልፋል። መግደል የአእምሮ በሽተኞችና የልጆች ጨዋታ ነው። ለመሞት መዘጋጀትና ለእውነትና ለእምነት መሞት ግን ወኔን ይጠይቃል፤ መንፈሳዊ ወኔን።
የኢትዮጵያ ባህል ለጠመንጃ የሚሰጠው ክብር ከራሱ ከሰውነት ክብሩ ጋር የተያያዘ ነው። ጠመንጃ ኃይል ይሆናል፤ አያስጠቃም። ገዳይ ጀግና ተብሎ ይከበራል። ሠርቶ ከመክበር ያንድ መኳንንት ሎሌ ሆኖ ጠመንጃ መሸከም ያስከብር ነበር፤ አሁንም አልቀረም። ይህንን ክፉና የማይጠቅም ባህል በጴጥሮሳዊነት መለወጥ ያስፈልገናል። በጠመንጃ ኃይል ከመተማመን በመንፈሳችን ኃይል መተማመኑ ወደተሻለ የእድገት ጎዳና ያመራናል። ለጠመንጃ የማይበገር መንፈስ በመሀከላችን ሲዳብር ከጠመንጃ ይልቅ በጽሑፍ፤ ከጥይት ይልቅ በቃላት ቅራኔዎቻችንን ማለሳለሱ ወደሥልጣኔ ፈር ውስጥ ያስገባናል። እምነታችን የቱንም ያህል ቢለያይ፣ ሃሳባችን ቢራራቅና መግባባት የሚያስቸግር ቢሆንም ሃሳቦቻችን ይጋጩ፣ይፋጩ እንጂ እኛ ጎራዴ መዝዘን ወይም ጠመንጃ አጉርሰን፣ ከአእምሮና ከመንፈስ ደረጃ ወደእንሰሳነት ደረጃ ወርደን ስንጋደል እምነቶቻችንና አሳቦቻችን ያደፍጣሉ እንጂ እንደማይሞቱ ይግባን።
ጴጥሮሳዊነት በአቡነ ጴጥሮስ መስዋዕትነት ላይ የተመሠረተ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው። አቡነ ጴጥሮስ ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው፣ የተሰውበትም ዋና ምክንያት የኢትዮጵያ ነፃነት በመሆኑ ጴጥሮሳዊነትን ኢትዮጵያዊነት እንበለው እንጂ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የሰው ልጆች ታሪክ በየአገሩ የሚያሳየው የሰው መንፈስ ነው። ስለዚህም ጴጥሮሳዊነት ዓለም አቀፋዊነት ባሕርይም አለው።
እውነትን ክዶ በውሸት ከመኖር ለእውነት ሞቶ እውነትን ሕያው ማድረግ የመንፈስ ዕርገት ነው። እንዲህ ዓይነቱ የመንፈስ ዕርገት የሚቀጥለውን ትውልድ ከእንሰሳት ደረጃ ወደላቀ የሰውነት ደረጃ ያነሣዋል። ከዚህ የተሻለ ውርስ አይኖርም። ጠመንጃ የያዘ ሁልጊዜም እንዲያሸንፈን መንፈሳችን ከተዳከመ ለጠመንጃ መድኃኒቱ ጠመንጃን ማንሣት እየሆነ እስከዛሬ እንደነበረው ወደፊትም ይቀጥላል። ይህንን የቁልቁለት መንገድ በጴጥሮሳዊነት ልናቆመውና ወደዕርገት እንዲያመራን ማድረግ እንችላለን። የእያንዳንዳችንን ውሳኔ የሚጠይቅ ነው።
ኢትዮጵያዊነት ከየት ወዴት? ገጽ 42-43
ተጻፈ 1986 ዓ.ም.