መኢአድ በአማራ እና በአፋር ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲቆም ጠየቀ
ሚያዚያ ፲፪ (አስራ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የመላው አንድነት ድርጅት ዛሬ በሊቀመንበሩ በኢንጂነር ሀይሉ አማካኝነት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ህገመንግስቱ በአንቀጽ 25 ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸው ቢልም የአማራ ህዝብ ሀገርና ትውልድን ለመታደግ በተደረጉ ጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ሁሉ ከመላው ኢትዮጵያውያን ጋር በመሆን ደሙን አፍስሶ አጥንቱን ከስክሶ እንዳልኖረ ዛሬ በየደረሰበት ቦታ እንደ ውሻ ውጣውጣ እየተባለ ለአመታት ደክሞ ያፈራውን ንብረቱን እና መጠለያ ቤቱን ተነጥቆ መደብደብ፣ መባረር እና መገደል እጣ ፈንታው ሆኗል ብሎአል።
መኢአድ በ አፋር ህዝብ ላይ ስለደረሰው ጉዳት ሲዘረዝር ደግሞ ” የአፋር ህዝብ ተወልዶ ካደገበት እና ለዘመናት ከኖረበት ቀየው ለራሱም ሆነ ለከብቶቹ ህለውና ወሳኝ ከሆነው የአዋሽ ወንዝ ተፈናቅሎ፣ የእርሳና ግጦሽ መሬቱን ተነጥቆ ጊዜ ለሰጣቸው አምባገነን ባለስልጣናት እና የአነሱ አጫፋሪ ለሆኑ አጊብዳጅ ባለሀብቶች ተሰጥቶበታል” ይላል።
የህዝቡ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ከብት እርባታ መሆኑ እየታወቀ ምንም አይነት አማራጭ ሳየቀርብለት ተገቢውን ካሳ ሳይከፈለው የታጠቀ ሀይል በማሰማራት ህጋዊ መብቶቹ ተገፈው በቆ ውሀ በሌለባቸው አካባቢዎች እንዲሰፍር በመደረጉ ህዝቡ ለከፋ ረሀብ ሲጋለጥ ከብቶቹም በድርቅ እያለቁ ነው የሚለው መኢአድ ፣ አሳኢታ ውስጥ ከእነ ስድስት ህጻን ልጆቻቸው የታሰሩት እና በስቃይ ላይ የሚገኙት ወ/ሮ ሀሲና ሀመሩን በምሳሌነት ጠቅሷል።
መኢአድ በቤንሻንጉል ጉሙዝ በአማራ ተወላጆች ላይ ስለደረሰው ችግር ሲዘረዝር ደግሞ ” ከመጋቢት ወር 2005 ዓም ጀምሮ ከአሶሳ ዞን ባምቢስ ወረዳ 2 ሺ፣ ከከማሺ ዞን ያሶ ወረዳ ከ8 ሺ በላይ እንዲሁም ከቡለን ወረዳ ከ5 ሺ በላይ እንዲሁም ከሌሎች ወረዳዎች በብዙሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ተባረዋል ብሎአል።
በባምቢስ ወረዳ የከተማው ህዝብ ለአማራ ቤቱን እንዳያከራይ ፣ በሆቴሉ አማራ እንዳይስተናገድ ትእዛዝ መሰጠቱን፣ የአካባቢው ተወላጆችም መሬታቸውን ለአማራ እንዳያከራዩ ጥብቅ መመሪያ መተላለፉን ድርጅቱ አስታውሷል።
የክልሉን አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ናስርን ጨምሮ ሌሎች የህወሀት አመራሮችን ተጠያቂ ያደረገው መኢአድ ፣ ሰዎቹ ወደ መጡበት ቦታ እንዲመለሱ የተደረገው በመላው አለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን የደረሰባቸውን ተቃውሞ በማርገብ ለማዘናጋት እንጅ አማራን ከእየአካባቢው የማጽዳቱን የቆየ እቅዳቸውን ተግባራዊ ከማድረግ አይመለሱም ብሎአል መኢአድ።
መኢአድ በመጨረሻም እንዲመለሱ ለተደረጉት ወገኖች የህግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፣ ለደረሰባቸው አካላዊና ሞራላዊ ጥቃት ተገቢውን ካሳ እንዲከፈላቸው፣ ድርጊቱን የፈጸሙት ለህግ እንዲቀርቡ፣ ጥላቻንና ክፍፍልን የሚያራግቡ ሀይሎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ እንዲሁም ህዝብን በዘርና በሀይማኖት በመከፋፈል የስልጣን እድሜን ለማራዘም የሚደረገው ጥረት ላለፉት 21 አመታት ደም ያፋሰሰ በመሆኑ በአስቸካይ እንዲቆም ጠይቋል።
የአማራውን ህዝብ እንወክላለን የሚለው ብአዴን እስካሁን አንድም ቃል አልተነፈሰም። ኢሳት የብአዴን ባለስልጣናትን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ፣ አመራሮቹ ለምሳ ወጥተዋል፣ ስብሰባ ላይ ናቸው፣ ከእንግዳ ጋር ናቸው ፣ የሻሂ ረፍት ላይ ናቸው” በሚሉ ምክንያቶችን ሊሳካለት አልቻለም።
በሰለጠኑት አገራት በአንድ ዜጋ ላይ ጥቃት ሲደርስ መሪዎች ጉብኝታቸውን በመሰረዝ ከህዝባቸው ጋር እንደሚቆሙ ቢታወቅም፣ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒሰትር ሀይለማርያም ደሳለኝ 10 ሺ ህዝብ በተፈናቀለበትና ህጻናት እና እናቶች እንደቅጠል መርገፋቸው በተነገረበት እለት የውጭ ጉብኝት ለማድረግ መነሳታቸው በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያንን ማበሳጨቱን ለኢሳት የሚደርሱት መልእክቶች ያሳያሉ።
No comments:
Post a Comment