Sunday, August 26, 2012

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሕይወታቸው አሳዛኝ ስለሚሏቸው ገጠመኝ ተጠይቀው ሦስት ነገሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ “የመጀመሪያው የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የቀረበለትን የሰላም ሐሳብ አልቀበልም፣ አሻፈረኝ በማለቱ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተሰው ዜጐች ሁሌም ያሳዝኑኛል፡፡ ሁለተኛው በምርጫ 97 ጊዜ በተፈጠረው ግርግር ሕይወታቸውን ያጡ ዜጎች ናቸው፡፡ በወቅቱ እኔ እንደ ግለሰብ ብሞት እንኳን ምንም አይሰማኝም፡፡ ሆኖም እኔ የአገር መሪ እንደመሆኔ መጠን በሰላም ሳይሆን በእንደዚያ ዓይነት ግርግር ሥልጣን ብለቅ አገሪቱ ወደማትወጣው አዘቅት ውስጥ ልትገባ ትችል ነበር፡፡ በመሆኑም ያ ውሳኔ ቢያሳዝነኝም ማንም በእኔ ቦታ ቢሆን የሚያደርገው ነገር ነበር፡፡ ሦስተኛ የሚያሳዝነኝ ጉዳይ የሕክምና ትምህርቴን ስከታተል አውቀው የነበረው አንድ ሻይ ቤት ከሰላሳ ዓመት በኋላ ተመልክቼው ምንም ዓይነት ለውጥ ባለማየቴ በጣም አዝኛለሁ፡፡ አገሪቱን ለመለወጥ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተረድቼ የበለጠ ለመሥራት ወስኛለሁ፤” ብለዋል፡፡ 

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ብዙ ጊዜ ሲስቁ ስለማይታዩ፣ ለምን? እንደማይስቁ ተጠይቀው “ለምን እስቃለሁ” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል፡፡ “እኔ ቢሮ ውስጥ ሆኜ በየቀኑ የማነባቸው ደብዳቤዎች በሰቆቃ የተሞሉ ናቸው፡፡ እንደዚህ ዓይነት በደል ደርሶብኛል፣ ፍትሕ አጣሁ፣ ያሰርካቸውን ሰዎች ፍታ፣ የሚሉ በርካታ ይህን መሰል ደብዳቤዎች ይደርሱኛል፡፡ አብዛኞቹም ሁሉን ነገር የማደርገው እኔ እንደሆንኩ የሚገልጹ ደብዳቤዎች ናቸው፡፡ በአገሪቷና በአካባቢው ያሉትን በርካታ ችግሮች ለመፍታት በየጊዜው እታገላለሁ፡፡ ታዲያ ምን የሚያስቅ ነገር ኖሮ ነው የምስቀው፤” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment