Thursday, November 1, 2012

በደብረብርሀን ዩኒቨርስቲ በተቀሰቀሰ ግጭት ተማሪዎች መጎዳታቸው ተሰማ


ጥቅምት ፳፪ (ሀያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ትናንት ጥቅምቅ 21 ቀን 2005 ዓም በደብረብርሀን ዩኒቨርስቲ የሚማሩ ተማሪዎች ዩኒቨርስቲው ያወጣውን አዲስ የውጤት አሰጣጥ ደንብ በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ አድረገዋል።
ተማሪዎች ጥያቄያቸውን በሚያቀርቡበት ወቅት፣ የወረዳው ፖሊስ አባላት ወደ ዩኒቨርስቲው ገብተው አስለቃሽ ጭስ በመበተን ተማሪዎችን ደብድበዋል።
ተማሪዎቹ እንዳሉት መብታቸውን ተጠቅመው  ጥያቄያቸውን ቢያቀርቡም የዩኒቨርሲቲው ባለስልጣናት ግን ጥያቄያቸውን በቅንነት ከመመለስ ይልቅ ዛቻና ማስፈራሪያ መጠቀማቸውን ተማሪዎች ገልጠዋል።
በዚህም ምክንያት ውዝግብ መነሳቱን የገለጹት ተማሪዎቹ፤ ፖሊሶቹ  በስፋራው በመድረስ ወደ ሀይል እርምጃ መግባታቸው በተማሪዎቹ ዘንድ ይበልጥ ቁጣ በመቀስቀስ የተፈጠረውን ውዝግብ ወደ ወደ ተቃውሞ ቀይሮታል።
ፖሊስ ዱላና አስለቃሽ ጭስ ጭምር በመጠቀም በወሰደው የሀይል እርምጃ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ተማሪዎች መጎዳታቸውንና አንዳንዶችም ተጎድተው ወደ ህክምና ቦታ መወሰዳቸውን ተማሪዎቹ ተናግረዋል።
ፖሊሶች ሌሊቱን ወደ ተማሪዎች መኖሪያ ግቢ በመግባት ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፣ በርካታ ተማሪዎችም ከዩኒቨርስቲው ውጭ በቤተክርስቲኖች እና በተለያዩ ነዋሪዎች ቤት ተጠልለለው ለማደር መገደዳቸውን ተማሪዎች ገልጠዋል።
ኢሳት ከአንዳንድ ተማሪዎች ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ሠራተኛ አቶ ደጀን መዝገብ ተማሪዎቹ አዲሱን  የአገር አቀፍ ፈተናዎች ድርጅት የውጤት አሰራር በመቃወማቸው ሳቢያ ችግሩ መከሰቱን ጠቅሰው፤ ጥያቄያቸው ወደ አመጽ በመለወጡ የፌዴራል ፖሊስ ሊመጣ መቻሉን ለሸገር ኤፍ ኤም ተናግረዋል።
ተማሪዎቹ መስተዋቶችን፣ወንበርና ጠረጴዛዎችን ጨምሮ በርካታ የዩኒቨርሲቲውን ንብረቶች ሠባብረዋል ሲሉም አቶ ደጀን ከሰዋል።
“እጅግ በርካታ ተማሪዎች ተጎድተዋል ይባላል?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ደጄን፦<< ፖሊስ እስከመጣ ድረስ ጉዳት መፈጠሩ የሚጠበቅ ነው>> የሚል አስገራሚ ምላሽ ሰጥተዋል።
”ምን ያህል ተማሪዎች እንደተጎዱ ሊገልጹልን ይችላሉ?” በሚል ለቀረበላቸው ተጨማሪ ጥያቄ፦ ረብሻው ገና  ስላልበረደ ምን ያህል ተማሪዎች እንደተጎዱ በትክክል መረጃው እንደሌላቸው ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment