Sunday, November 4, 2012

በውጭ አገር የሚገኘው ሲኖዶስ አዲስ ፓትሪያርክ ለመሾም የሚደረገው እንቅስቃሴ ተቀባይነት አይኖረውም አለ


ጥቅምት ፳፬ (ሀያ አራት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- ሲኖዶሱ ” በብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ  የሚመራው ህጋዊው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ 34ኛው መደበኛ ጉባኤ መግለጫ” በሚል ርእስ ባወጣው መግለጫ ፣ የቤተክርስቲያንን ሰላምና አንድነት፣ በተለይም ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ መንበራቸው ስለሚመለሱበት ሁኔታ ቅዱስ ሲኖዶስ በሰፊው መነጋገራቸውን ጠቅሷል።
በመግለጫው” በአዲስ አበባ ያሉት አባቶች ቅዱስ ፓትርያርኩን ወደ መንበራቸው እንደሚለሱ ከተስማሙ ቅዱስ ሲኖዶሱም አንድ፣ እረኛውም አንድ፣ ቤተክርስቲያኒቱም አንዲት ትሆናለች ብሎ ስለሚያምን ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ መንበራቸው ተመልሰው ቤተክርስቲያን የሰጠቻቸውን ሀላፊነት እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ድረስ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋግጣል ” ብሎአል።
በቀኖና ቤተክርስቲያን ምክንያት የተፈጠረው ልዩነት ለ21 አመታት ምእመናንን ከምእመናን ፣ ካህናትን ከካህናት ፣ አባቶችን ከአባቶች መለያየቱ፣ ብዙዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን እውነተኛ ልጆች ማሳዘኑን የገለጠው፣ የሲኖዶሱ መግለጫ ፣ በአዲስ አበባ ከሚገኙት ሊቃነ ጳጳሳት መካከልም የተወሰኑት አባቶች በዚህ የልዩነት ታሪክ ላይ እንዳለን በሞት ማለፋቸው አሳዛኝ ሆኖ ሳለ፣ እኛ በህይወት ያለነው ማስተካከል የሚገባንን ሳናስተካክል ፣ ህገቤተክርስቲያንን ሳናስጠብቅ፣ ቤተክርስቲያንን አንድ ሳናደርግ ብናልፍ በህይወት በህዝባችን ፊት ፣ በሞትም በእግዚአብሄር ፊት ተወቃሾች ያደርገናል። “ብሎአል።
በአዲስ አበባ ያሉት ጳጳሳት ” የተጀመረው የሰላም ድርድር መልክ ሳይዝ፣ ወደ ሌላ ፓትርያርክ ምርጫ እንሄዳለን የሚለው ሀሳብ የቤተክርስቲያንን አንድነት በር እንደሚዘጋ፣ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳዊያን በሙሉ ላለፉት 21 አመታት የነበረው የቤተክርስቲያን ልዩነት ተወግዶ ለማየት በታላቅ ተስፋ በሚጠባበቁበት ወቅት የምእመናንን ልብ ያሳዝናል፣ የቤተክርስቲያንንም ክብር ያዋርዳል። ” በማለት ሲኖዶሱ ገልጿል።
በአንድ በኩል ለድርድር እንቀርባለን እየተባለ ፣ በአንድ ዘመን በአንድ መንበር በአንዲት ቤተክርስቲያን ላይ ሁለት አባት ለማስቀመጥና ከቀኖና ቤተክርስቲያን ውጪ የሆነ ተግባር ለመፈጸም መዘጋጀት፣ አራተኛውና ህጋዊው ፓትርያርክ በህይወት እያሉ ሌላ ፓትርያርክ ለመሾም ማሰብ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው በማለት አትቷል።
ሲኖዶሱ ” በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉበኤ የቀረበለትን ጥሪ ምክንያት በማድረግ ህጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ የመነጋገሪያ አጀንዳዎችን ቀርጾና ተደራዳሪ የሰላም ልኡካንን ሰይሞ በተወሰነው ቀንና ቦታ ለመላክ መወሰኑንም” ጠቅሷል።
የአቡነ መርቆርዮስ ወደ መንበራቸው መመለስ አማራጭ የሌለው ብቸኛ መፍትሄ ነው በማለት  የገለጠው ሲኖዶሱ፣ በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ ያለው መንግስትም ለዚህች ቅድስት ቤተክርስቲያን መለያየት ምክንያት ከመሆን እንዲቆጠብ፣ የቤተክርስቲያኒቱን የአንድነት አቅጣጫ መወሰን የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ማለትም ሊቃነ ጳጳሳት፣ ካህናቱና ምእመናኑ ብቻ ስለሆኑ መንግስት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቤተክርስቲያኒቱ ውሳኔ ላይ ተጽእኖ እንዳያደርግ ቅዱስ ሲኖዶሱ አሳስቦአል።
ሲኖዶሱ መግለጫውን ያወጣው ከጥቅምት 21 -23/ 2005 ዓም በኮሎምበስ ኦሀዮ ደብረ መድህኔአለም ካቴደራል ጉባኤውን ካካሄደ በሁዋላ ነው።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላለፉት 21 አመታት ከሁለት ተከፍላ ቆይታለች። ለክፍፍሉ ምክንያት ናቸው የተባሉት የቀድሞው ፓትርያርክ፣ አቡነ ጳውሎስና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሁለቱም በተካካይ ሳምንታት ውስጥ ከዚህ አለም በሞት በመለየታቸው ፣ ቤተክርስቲያኑዋን ወደ አንድነት ለማምጣት የሽምግልና ጥረት መጀመሩ ይታወቃል።
የብጹወ ቅዱስ አቡነ ጳውሎስና የአቶ መለስ ዜናዊ ተከታትሎ ማረፍ ብዙዎችን ያስገረመ ክስተት እንደነበር ይታወሳል።

    No comments:

    Post a Comment