Monday, January 28, 2013

“ገዳይ እና ሟች”

ማሳሰቢያ፡- ይህ ፅሁፍ ጥር 18 ቀን 2005 ዓ.ም በአውራምባታይምስ ድረ ገፅ ለንባብ የበቃ ነው)
“ገዳይ እና ሟች”
ይህንን ፅሁፍ ለማዘጋጀት ያሰብኩት ከሳምንት በፊት ነበር፡፡ “ለነገ ይደር” ብዬ አዘገሁት፡፡ እንዲያም ሆኖ ሀሳቡ ሽው ባለኝ ጊዜ፣ በአንድ ወጥ በመቆጨት ስሜት “ገዳይ እና ሟች” በሚል ርዕስ የከተብኩት ግጥም ነበር ቀድሞ ወደ ህሊናዬ የመጣው፡፡ ግጥሙ ዘለግ ያለ ቢሆንም፣ የብዙዎችን ስሜት የነካ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ በመድረክ ላይ ሳነበው የተቀረፅኩትም ባህርማዶ ተሻግሮ ተደምጧል መሰለኝ፡-እንደተነገረኝ፡፡ ለዚህ ዘለግ ያለግጥም ብርታትና ጉልበት የሆነው ከአንድ ሃሳብ ወደ ሌላ ሃሳብ መሸጋገሪያው ወይም ማቀንቀኛው ነው፡፡
“…ወንድም ወንድሙን ገደለው
እየለነው ገደለው
እየገደለው ለመነው…” ይላል፡- የግጥሙ ማቀንቀኛ፡፡
ማቀንቀኛው ገዳይ ለሟች፣ ሟችም ለገዳይ የወንድማማችነት ቦታ እንዳላቸው የሚያሳይ መሰለኝ፡፡ ይህንን ዕውነት እያውጠነጠንኩ ሳለ፣ ሁለት ሀገርኛ ተረቶች ታወሱኝ፡፡ የመጀመሪያው አንድ የአይነሥውርን ይወክላል፡፡ ሁለተኛው “የአይጦች ወግ” ሊባል የሚችል ነው፡፡ ሁለቱም ተረቶች ዝቅ ብዬ ለማነሳው ፈትለነገር (team) ማዋዣ ይሆኑኝ ዘንድ ወደ ኋላ ላይ ልጠቀምባቸው ወደድኩ፡፡ ለማንኛውም ወደ ዋናው ጉዳይ ልዝለቅ፡-
• 1 -
ጉዳዩ የተከሰተው ወደ ባህር ማዶ ነው፡- ሀገረ አሜሪካ፡፡ ጥር 1 ቀን 2005 ዓ.ም ነው ዜናው የተሰራጨው፡፡ “የFBI መርማሪዎች አበበ ገላውን ለመግደል የታቀደውን ሴራ አከሸፉ፤….በሴራው ከተሳተፉት አንዱ አበራ ጉዕሽ ነው፡፡…” የሚል ነው፡፡ ዜናው ከተሰማበት ደቂቃ ጀምሮ የኢትዮጵያውን ዲያስፖራ ድረ-ገፆች እና ሌሎች የመገናኛ አውታሮች ዋነኛ ጉዳይ ይኸው ዜና ሆነ፡፡ እስካሁንም ድረስ የሚወቀጠው፣ የሚሰለቀው፣ የሚደቆሰው፣ የአጀንዳዎች ሁሉ አጀንዳ ለመሆን የበቃው፤ አብዛኞቹን የሃገሬን ዲያስፖራ ድረ-ገፆች ሌሎች መገናኛ አውታሮችን እንዳስጨነቀ ያለው ይኸው ጉዳይ ሆኗል፡፡
በእርግጥም ጉዳዩ አነጋጋሪነት አለው፡፡ ዜናው ከዜናነት ባሻገር ይታይ ሊመረመር፣ ዕውነታው ጠርቶ ሊወጣ ይገባል፡፡ FBIን ያህል የዓለማችን ፊታአውራሪ የምርመራ ተቋም አነፍንፎ የደረሰበት ይህ “የግድያ ሴራ” እንዲህ በዋዛ የሚታይ አይደለም፡፡ የረቀቀ መሆን አለበት፡፡ ማን አረቀቀው? ለምን? በምን የተነሳ? የሚሉ ስስ ጥያቄዎች መልስ ያገኙ ዘንድ ግድ ነበር፡፡ እኔም የምጠብቀው ይህንን ነበር፡፡
ይሁን እንጂ ዜናው ከተሰማበት ድረስ እስካሁን (አንድ ወር ሙሉ) አብዛኞቹ የሃገሬ ዲያስፖራዎች እና ድረ-ገፆች እና ሌሎች መገናኛ አውታሮቻቸው ጉዳዩን በዋነኛ አጀንዳነት የያዙት በተቃራኒው መልኩ መሆኑ ነው ብእሬን እንዳነሳ ያስገደደኝ፡፡ ዕውነታውን ለይቶ ጥርት አድርጎ ከማውጣት ይልቅ ማደፍረስ፣ ማደፈራረስን የተያያዙ ነው የሆኑብኝ፡፡
አብዛኞቹ የሃገሬ ዲያስፖራዎች እና ድረ-ገፆች እና ሌሎች መገናኛ አውታሮቻቸው ዜናው ከተናፈሰበት ዕለት ማግስት አንስቶ፣ የሚዘግቧቸው ዘገባዎች፣ የአንባቢ የሚያቀርቧቸው መጣጥፎች፣ የሚያስተናግዷቸው የግለሰብ አስተያየቶች ልክም ለከትም የሌላቸው ዓይነት ነበሩ፡፡ ናቸውም፡፡ ፍፁም ሥነምግባር የሚባል ነገር ያልዳበሳቸው መረን የወጡ የሚያስጠይፉ ስድቦች የታጨቁባቸው ፍረጃዎች፣ “የዜናውን ዕውነትነት ካልተቀበልክ አንተም ነፍሰ ገዳይ ነህ” የሚሉ ዘለፋዎችና ተራ-አተካራዎች…ናቸው በየመገናኛ አውታሮቻቸው ላይ ሲናኙ የከረሙት፡፡ አሁንም የሚናኙት፡፡ የፌስቡክ ገፆቻችንንም ያጨናነቀው እንዲህ ያለው መረን የወጣ አተካራ ነው፡፡ ዝም ብሎ መጮህ መጯጯህ አይነት ነገር፡፡
“ሴራ” የተባለው ዜና በተሰማ በሳምንቱ ይሁን በቀጣዩ ሳምንት ያሬድ አይቼህ የተባሉ “ዲያስፖራዊ” (ላይሆኑም ይችላሉ) ዘ- ሐበሻ የተባለ ድረገፅ ላይ “ኧረ እንረጋጋ!” የሚል ፅሁፍ አስነብበውን ነበር፡፡ ፀሐፊው በዚህች መጣጥፋቸው ተጠርጣሪው ጉዕሽ አበራ በፓልቶክ ሲቪሊቲ የሰጠውን ያለምልልስ መስማታቸውን ጠቅሰው፡- “ጉዕሽ አበራ ከተናገረው የተረዳሁት፤ በፌስ ቡክ ሰጣ ገባ አንጀቱን ያሳርሩታል፤ እሱም የሚለውን ይላል፤ በቃ፤ እኛ ምን ይሁን ብለን ነው ነገሩን የምናጦዘው?” የሚል ሃሳብ ነበር በደምሳሳው የሰነዘሩት፡፡ ከዚህ በኋላ የወረደባቸው የስድብ ናዳ የሚነገር አይደለም፡፡ የሚቀፍ፣ የሚያሳቅቅ፣ ግብረገብነት የጎደለው የሥድብ ናዳ ወረደባቸው፡፡ እንደው ለአብነት ያህል ይህንን ጠቀስኩ እንጂ በየድረገፁና በሌሎች መገናኛ አውታሮች ያነበብኳቸውና የሰማኋቸው የሥነምግባር ቅንጣት የጎደላቸው መረን የወጡ “ሃሳቦች” በርካታ ናቸው፡፡ ከብዛታቸው የፀያፍነታቸው ነገር በ10 ሺህ ኪ.ሜ ርቀት ላይ የምገኘውን እኔን ባላገሩን ኢትዮጵያዊ የሚያሳቅቁ ናቸው ብል አላገነንኩም፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ የግድያ ሙከራ ታቅዶበታል በሚባለው በጋዜጠኛ አበበ ገላው ስም በፌስ የተለቀቀ (መቼም የፌስ ቡክ ስም አይታመንም) የ3 ደቂቃ የመሰዳደብ ዲስኩርም ሰምቻለሁ፡፡ ኧረ እንደውም ለመረጃነት ከፌስቡክ ገጼ ላይ አስቀርቸዋለሁ፡፡ እንደሚመስለኝ የአበበ ገላው ቤተሰብ የሆነች አንዲት ሴት ላይ የሥልክ ማስፈራሪያ እየተሰነዘረባት ነው፡፡ 3 ደቂቃ ሙሉ “የሚዝተውም”፤ “የሚዛትባትም” በስድብ እኩል ይሞላለጫሉ፡፡ ዛቻ ሰንዛሪውም “እናትሽን!” ይላል፡፡ ዛቻ እየተሰነዘረባትም “እናትክን” ትላለች፡፡ ጨዋ ለመሆን እንጂ ሁለቱም ያልሰደቡት ዘመድ አዝማድ የላቸውም፡፡
ይኼ የፌስቡክ ማስረጃ ዛቻ አልመስልህ ነው ያለኝ፡፡ ሁለቱም ወገኖች የስድብ ውድድር የያዙ ነው የመሰለኝ፡፡ ለሰማሁበት ጆሮዬ ነው ያዘንኩለት፡፡ በጣም ነው ያፈርኩት፤ ያዘንኩትም፡፡ እነዚህ የሚሳደደቡት እህትና ወንድሞቼ እውነት ኢትዮጵያዊ ናቸው? እስክል ድረስ፡፡ ቀድሞ ነገር እኔን ያስገረመኝና ያሳፈረኝ ይህን የስድብ ውርጅብኝ ስሙልኝ የሚባል ሆኖ መቅረቡ ነው፡፡ እንኳን ስሙልኝ ሊባል ሊታሰብም የሚገባ አልሆንህ ብሎኝ መፍረድ ቸገረኝ፡፡
• 2 -
የሆነ ሆኖ በዚህ መልኩ ዕለት ዕለት እየታደሰ ዋነኛው የዲያስፖራ አጀንዳ ሆኖ ለወር ያህል የቀጠለው የአበበ ገላው እና የግዑሽ አበራ ጉዳይ የዓይነስውሩን ተረት ነው ያስታወሰኝ፡፡
ሰውየው በተፈጥሮ ዓይነስውር ነው አሉ፡፡ ከበርካታ ዓይናማ ጓደኞቹ ጋር በፍቅር የሚኖር፡፡ አንድ ቀን ግን፣ ከአንዱ ዓይናማ ጓደኛው ጋር ተጠላ፡፡ እንደዘበት የተከሰተው አለመግባባት፣ ምርር ክርር ወዳለ ፀብ ተሸጋገረ፡፡ ዓይነ ስውሩ ራሱን መቆጣጠር ተሳነው፡፡ ዓይናማውን በጡንቻው መደቆስ አሰኘው፡፡ ዓይናማው ግን ሸሸ፡፡ የኋላ ኋላ የሚከሰተውን በማሰብ ከነገሩ ለመራቅ ሮጠ፡፡ አመለጠ፡፡ ይኼኔ ዓይነስውሩ ወደመሬት ጎንበስ አለና በእጁ እየዳበሰ ድንጋይ ፈለገ፡፡ እጁ የገባለትን ድንጋይ አንስቶ፣ ፀበኛው የሮጠበትን አቅጣጫ ሳይለይ ወረወረ፡፡ ወዲያው ራቅ ካለ ቦታ ጩኸት ሰማ፡፡ የ“እሪታ” ድምፅ ሲሰማ፣ ዒላማውን መምታቱን ቢያምንም ጆሮውን ተጠራጠረ፡፡ እናም በአቅራቢያው ያለውን ሰው እንዲህ ሲል ጠየቀ፡-
“መታሁት?”
“አልመታኸውም” አለው በአቅራቢያው ያለው ሰው፡፡
“ታዲያ የምን ጩኸት ነው የምሰማው?”
“ወርውረህ የመታኸው ፀበኛህን ሳይሆን፣ ምንም የማያውቀውን ሠላማዊውን ሰው ነው”
ከዚህ በኋላ ያለው የዓይነስውሩ ምላሽ ነው የሚያስገርመው፡፡ ለዚህ ፅሁፌም መልዕክታዊ አንደምታውን የሚያጎላልኝ የዓይነስውሩ ተከታዩ ምላሽ ነው፡፡ እነሆ፡-
“የወረወርኩት ድንጋይ ማንንም ይምታ ማንን፣ ዋናው ቁምነገሩ አለመሳቴ ነው!!”
ልክ እንደዚያው ሁሉ፣ በ“ግድያ ሙከራው” ላይ የሚሰነዘሩ የአብዛኛው ዲያስፖራዎች (የሁሉም) አስተያየት መረጋጋት የሌለባቸው፣ ስክነት የጎደላቸው፣ በነሲብ የሚወረወሩ፣ ግብረ ገብነት የጎደላቸው፣ በፀያፍ ቃላት የታጀሉ፣ ዓላማቸውንም ዒላማቸውንም የሳቱ፣ በነሲብ የሚወነጨፉ ወዘተ ናቸው፡፡ ኧረ ያገር ያለህ የሚያሰኙ ናቸው፡፡
• 3 –
እንደ እውነቱ ከሆነ እኔን ብዕር ያስመዘዘኝ የጉዳዩ መነሻ አይደለም፡፡ ማንኛውም የዲያስፖራ ድረ-ገፅ፣ ማንኛውም የዲያስፖራ የመገኛኛ አውታር ጉዳዩን ጉዳዬ ሊለው አይገባም የሚል ሙግትም አልገጥምም፡፡ ዜናውን መዘገብ፣ ዕውነታውን መመርመር ለይቶ ማውጣት የመገናኛ ብዙሃናት አይነተኛ አይነተኛ ተግባር መሆኑንም ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን ጉዳዩን የያዙበት መንገድ ትክክል ነው ብዬ አላምንም፡፡ የአንዱን ወገን ትክክለኝነት ብቻ ማጉላት፣ የሌላውን ወገን ሃሳብ ማጣጣል ለማንም ለምንም የሚበጅ አይመስለኝም፡፡
የግድያ “ሴራ አሴረ” የተባለውን ሰው ጥፋትኛ ለማድረግና የሃገሪቷ ጠላት መሆኑን ለማጉላት የFBIን ሥም ማጣቀስ ብቻ ተዓማኒ አያሰኝም፡፡ እንኳንስ FBI የአ/በባ ፖሊስ ጥቆማ ከደረሰው፣ የደረሰውን ጥቆማ ማጣራቱ ግድ ነው፡፡ እንጂ FBI ነቢይ አይደለም፡፡ FBI ተጠርጣሪውን ጠይቆታል፡፡ ጉዳዩ የከፋ ነገር ባለመሆኑ አላሰረውም፡፡ የኋላ ኋላ ቪኦኤ ግዑሽ አበራን ሲያነጋግረው የተረዳሁት FBI በጥቆማ የጠየቀው መሆኑን ነው፡፡ ይኼ FBI የመግደል ሙከራውን ደረሰበት የሚያሰኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው ጉዳዩ ሳይሆን፣ የጉዳዩ አያያዝ (አጯጯህ፣ግነት፣ አጧጧዝ) አግባብ አልመሰለኝም የምለው፡፡
በሌላ በኩል አበበ ገላው የግድያ ሙከራ ሊቃጣበት እንደማይገባም አምናለሁ፡፡ እንኳን ሊቃጣበት ሊታሰብበት አይገባም ባይ ነኝ፡፡ አበበ ገላው፣ በካምፕ ዴቪድ ሜሪላንድ አለምአቀፍ ስብሰባ ላይ ተጋባዥ የነበሩትን ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊን “የነፃነት ያለህ” ብሎ የጠየቀ ደፋር ኢትዮጵያዊ ነው፡- ነፍሳቸውን ይማርና፡፡ አበበ ነፃነትን የመጠየቅ ፍፁማዊና ተፈጥሮአዊ መብት አለው፡፡ ነፃነትን በመጠየቁ፣ ስለነፃነት በመሟገቱ ብቻ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ መብት ግን ሊኖረው አይገባም፡፡ ከሌላው ኢትዮጵያዊ የተለየ መብት ሊኖረውም አይችልም፡፡ “አበበ ገላው ጀግና ነው” ማለት ይቻላል፡፡ እኔም አላለሁ፡፡ ሌላውም ሌላ ጀግና ሊኖረው ይችላል፡፡ ሁሉም እንደየአመለካከቱ፣ እንደየእምነቱ የመኖር መብት፣ የማሰብ መብት አለው ማለት ነው፡፡ የእኔን የእኔ ያላለ ጠላት ነው የሚል አስተሳሰብ የትም አያደርስም፡፡ ለራስም ለሃገርም አይጠቅምም፡፡ ሊጠቅምም አይችልም፡፡
እንደእኔ እንደኔ አበበ ገላውም ሆነ ጉዕሽ አበራ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ የጆሮ ጌጥ እና የአንገት ኃብል ናቸው እንደማለት፡፡ ሁለቱም ለሃገራቸው የማሰብ እኩል መብት አላቸው፡፡ እኩል የማለም መብት አላቸው፡፡ በአስተሳሰባቸው ወይም በአመለካከታቸው ልዩነት የተነሳ አንዱን ፍፁም ኢትዮጵያዊ አንዱን የኢትዮጵያ ጠላት ማድረግ የሚቻል አይመስለኝም፡፡
ለማለት የፈለግኩት የአበበ እና የጉዕሽ ጉዳይ ብቻውን ተነጥሎ ይህንን ያህል የሚጎላበት ምክንያት የለም ነው፡፡ ሰዎቹ ልዩ አጀንዳ ሆነው፣ ሌላውን አጀንዳ ሁሉ የሚያስጥሉበት ምክንያት የለም ነው፡፡ በአጭሩ ሀገር አይደሉም ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የእነሱን ጉዳይ ስናባትል የጋራ ሃገራችንን ጉዳይ ቀስ በቀስ ጥላን ባዶ እጃችንን የሚያስቀረን ሊሆን አይገባም ነው፡፡ ከእነሱ በላይ፣ ከማንኛችንም በላይ ኢትዮጵያ የምንላት ሃገር አለች፡፡ አቶ መለስ ከዚህ ዓለም በሞት አልፈዋል፡፡ ብዙ ታሪክ የሰሩ ሰዎችም ሞተዋል፡፡ አበበ ገላውም ያልፋል፡፡ እኔም አልፋለሁ፡፡ ሌላውም ሰው እንዲሁ፡፡ ኢትዮጵያ ግን ለዘላለም ትኖራለች፡፡ ይህንን ስል የአይጧ ተረት ታወሰኝ፡፡
• 4 -
ከወደ ሰሜን ሸዋ ነው ተረቱን የሰማሁት፡፡ አንዲት በጠና የታመመች አይጥ ልጆቿን ሰብስባ እንዲህ አለቻቸው - አሉ፡- “እንግዲህ መሞቻዬ ተቃርቧል፤ ስሞት የምትቀብሩኝ ታዲያ ደብረሊባኖስ ነው…”
ልጆቿ “…ይኼ ጉዳይ ከባድ ስለሆነ እንወያይበትና መልሱን እንነግርሻለን..” አሏት፡፡ ከአጠገቧ ዞር ብለው መከሩና ምላሽ ይዘው መጡ፡፡ “…እናታችን ነሽ፡፡ ትዕዛዝሽን ሰምተናል፡፡ ትዕዛዝሽን ልንፈፅምም ይገባን ነበር፡፡ ግን ትዕዛዝሽን መፈፀም ይቸግነረናል፡፡…”
“ችግሩ ምንድነው?” ስትል እያቃሰተች ጠየቀች እናት፡፡
“…አንቺን ለመቅበር በሰማይ እንዳንሄድ አሞራ ይበላናል፤ በምድር ሬሳሽን ይዘን እንዳንጓዝ ድመት ያስቸግረናል፡፡” ሲሉ መልስ ሰጧት ልጆቿ፡፡ የተናገሩትን በፅሞና ከሰማች በኋላ የመጨረሻ ቃሏን ሰነዘረች፡፡
“አይ!...እኔም የጠየቅኳችሁ ይፈፀማል ብዬ አይደለም፤ ሳትናገር ሞተች እንዳልባል ብዬ ነው፡፡” አለች አሉ፡፡
እኔም ነገሩ አላግባብ ሲከር ሲካረር፣ ፅንፍ ለፅንፍ ሲያነታርክ፣ ሲያጠዛጥዝ፣ ሲያናችፍ፣ ዲያስፖራ ወገኖቼን እርስ በእርስ ሲያባላ፣ ሲያብላላ ዝም ከማለት ብዬ ነው ሃሳቤን የምሰነዝረነው፡፡ እከሌን ጠላት ነው ብለን ስንፈርጅ፣ እሱም እኛን በጠላትነት ሲፈርጅ፤ እከሌን የጠላት ቅጥረኛ ነው ብለን ጥርስ ስንነክስበት፣ እሱም ጥርሱን ሲነክስብን….እርስ በርስ ተጠላልፈን፣ እርስበርስ ተሻኩተን እርስ በርስ ተጣጥለን፣ እርስበርስ ተናክሰን…መቀበሪያችንን፣ ሃገራችንን፣ ኢትዮጵያችንን እንዳናጣት ነው ስጋቴ፡፡ አበው “ከአነጋገር ይፈረዳል ከአያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ፤ ዲያስፖራ ወገኖቼ ሆይ አያያዛችሁ አላማረኝም ለማለት ነው ይህንን ሁሉ የምዘበዝበው፡፡ አበቃሁ፡፡

No comments:

Post a Comment