Sunday, January 13, 2013

አፄ ቴዎድሮስ - የትንሳዔው ሰማዕት ምጥን ዳሰሳ በወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ)


አፄ ቴዎድሮስ - የትንሳዔው ሰማዕት
ምጥን ዳሰሳ
በወሰንሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ)
“…ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ
ያንድ እውነት ይሆናል ዕዳ
እና ትንፋሼ አልሆነሽም - ሆኜብሽ መራር መካሪ
‹ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ›
እውነት ላንቺ መች ተስፋ ናት - ጉስቁል ልሳንሽ ነክሳሽ
ክንድሽን ካዛለ ቅርስሽ- መጠላለፍ ሲሆን እጣሽ
ከእንግሊዝ የሞት አማልክት - መተናነቅ ሲሆን ድርሻሽ
መልመጥመጡ መሽቆጥቆጡ - መስሎሽ ድንገት የሚያዋጣሽ
የእኔ እውነት ሆኖብሽ ዕዳሽ፡፡….”
ጸጋዬ ገ/መድህን
“እሣት ወይ አበባ” 1966 ዓ.ም
ይህንን ቅንጭብ የሎሬት ጸጋዬ ገ/መድን ቅንጭብ ግጥም ስናነብ፣ በኢትዮጵያ የብዙ ሺህ ዘመናት ታሪክ ሂደት ውስጥ “ለየት ያለ” ታሪክ ያላቸውን ንጉሥ ማስታወሳችን አይቀርም፡- አፄ ቴዎድሮስን፡፡
አፄ ቴዎድሮስ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ከነገሡት ነገሥታት ሁሉ “የተለዩ” የሚያደርጓቸው በርካታ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ከነዚህ ሁነቶች አንዱና ዋንኛው በትውልድ ዘር ሃረግ ይተላለፍ የነበረውን የሥልጣን ቅብብሎሽ በኃይላቸው ያቋረጡ በመሆናቸው ነው፡፡ በሌላ አባባል ከተራ ሽፍትነት ተነስተው የሃገሪቱን መንበረ ሥልጣን የተቆናጠጡና ለንጉሠ ነገስትነት የበቁ በመሆናቸው ነው፡፡ በዚህም የተነሳ የአፃ ቴዎድሮስ የንግስና ዘመን፤ ኢትዮጵያ ከቀደመው ታሪኳ በተለየ መልኩ፣ ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ የተሸጋገረችበት ጊዜ ተደርጎ እንደሚታመን የዘርፉ ምሁራኖች ያትታሉ፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፤ ሌላም ሌላም ታሪካቸው ከሌሎች ነገሥታቶች በተለየ መልኩ እንዲታዩ ምክንያት መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ይህ የአሁኑ ትውልድ ከቀደመው ትውልድ በተሻለ መልኩ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ያውቃል ማለት ይቻላል፡፡ ታሪካቸው በተለያዩ የትምህርት መማሪያ መፅሐፍቶች ውስጥ ተቀንጭበው ቀረበውለታል፡፡ በተለያየ ወቅት በሬድዮና በቴሌቪዥን ተተርኮለታል፡፡ በኢትዮጵያውያን ፀሐፍት የተዘጋጁ ዳጎስ ዳጎስ ያሉ መፅሐፎች ለህትመት በቅተውለት አንብቧል፡፡ ስለዚህ ይህ ትውልድ በደምሳሳው ወይም በግርድፉም ቢሆን የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ ያውቃል ብንል ስህተት አይሆንም፡፡ ይሁን እንጂ የአፄ ቴዎድሮስን ታሪክ በምልዐት ያውቃል ወይም እናውቃለን ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡
የአፄ ቴዎድሮስን ዘመነ መንግስት ከጅማሬው እስከፍፃሜው የሚተርኩ መፅሐፎች የታተሙ ቢሆንም፣ በእኛው ሰዎች (በኢትዮጵያውያን) የተዘጋጁ መፅሐፎች ቁጥር አነስተኛ ወይም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ በሌላ አገላለፅ ስለአፄ ቴዎድሮስ ያለን ዕውቀት፣ የዘመነ መንግስታቸው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳዩ ታሪካዊ ሰነዶች፣ የግለሰብ ምስክርነቶች፣ የደብዳቤ ልውውጦች….ወዘተ በተመለከተ ያሉን መረጃዎች ውስን ናቸው፡፡ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ የአፄ ቴዎድሮስን እና የመንግስታቸውን ተግባራት የሚተርኩ የተለያየ ይዘት ያላቸው 60 ያህል መፅሐፍቶች በእንግሊዘኛ እና በጀርመንኛ ቋንቋ ለህትመት በቅተዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ አፄ ቴዎድሮስ በተለየ መልኩ ከሚታወቁበት የመቅደላ ዘመቻ አስቀድሞ ወደ ኢትዮጵየ መጥተው የነበሩ አውሮፓውያን የአፄውን ባህርይ፣ የአስተዳደር ዘይቤ፣ እንዲሁም በወቅቱ የነበረውን የሥልጣን ሽኩቻ የወለዷቸውን የአመፅ እንቅስቃሴዎችን …ወዘተ በተመለከተ በርካታ መረጃዎችን መያዝ (ማኖር) መቻላቸው ነው፡፡
እንዲህም ተባለ እንዲህ የአፄ ቴዎድሮስ “ታሪካዊ ምስጢርነት” እስካሁን ድረስ በተለያዩ ፀሐፊዎች እየተገለጠ ይገኛል፡፡ ለዚህ አባባላችን አስረጅ የምናደርገው ከ5 ዓመት በፊት (እኤአ በ2007) በፈረንጅ አፍ ተፅፎ ለህትመት የበቃውን “THE BAREFOOT EMPERIOR” መፅሐፍ ነው፡፡ የዚህ መፅሐፍ ደራሲ በጉዞ መፅሐፍት ደራሲነቱ “ተመራማሪው ባለ ንስር ዓይን” የሚል ዝና ያተረፈው ፊሊፕ ማዲሰን ነው፡፡
በእርግጥም ደራሲው “ባለንስር ዓይን” ሊባል የሚገባው ነው ብለን ለመመስከር እንገደዳለን፡፡ “የማናውቃቸውን” አፄ ቴዎድሮስ በህይወት ያሉ እስኪመስለን ድረስ ታሪካቸውን በአስደናቂ ሁኔታ ከትቦልናልና፡፡ እዚህ ላይ ታዲያ አንባቢያን “የማናውቃቸውን” የሚለውን አገላለፅ ልብ እንዲልልኝ እሻለሁ፡፡ ለምን? ለማስረዳት ልሞክር፡፡
ፊሊፕ ማዲሰን “THE BAREFOOT EMPERIOR” በሚል ርዕስ የፃፈው የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክ፣ ለባለታሪኮቹ ኢትዮጵያውያን ይደርስ ዘንድ ወደ አማርኛ ቋንቋ ተመልሶ በታህሣሥ ወር 2005 ዓ.ም መጀመሪያ ለህትመት በቅቷል፡- በጋዜጠኛ ብሩክ መኮንን ተክለየስ ተርጓሚነት፡፡
በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ታሪክ ውስጥ በቀደምትነት ላቅ ያለ ሙያዊ ተግባር ከተወጡት ጋዜጠኞች መሀል አንዱ የሆነው ጋዜጠኛ ብሩክ መኮንን ተክለየስ፣ “አፄ ቴዎድሮስ - የትንሳዔው ሰማዕት” የሚል ርዕስ ሰጥቶ ነው የፊሊፕ ማዲሰንን መፅሐፍ የተረጎመው፡፡ጋዜጠኛ ብሩክ መኮንን ከዚህ ቀደም ሶስት ደጎስ ደጎስ ያሉ መፅሐፍቶችን ተርጉሞ ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡ ይህ መፅሐፍ አራተኛው የትርጉም ሥራው መሆኑ ነው፡፡
መፅሐፉ 310 ገጾች ያሉት ሲሆን፣ በ11 ክፍሎች፣ በ83 ምዕራፎች እና በ2 “ማሳረጊያ” ትረካዎች ነው ደርዝ የተበጀለት፡፡ ከመጀመሪያው ገፅ አንስቶ የመፅሐፉን የመጨረሻ ገፅ ቅጠል እስክናጥፍድረስ ህሊናን ሰቅዞ የሚይዝ፣ ከገፅ ገፅ፣ ከምዕራፍ ምዕራፍ በእጅጉ የሚመስጥ፣ የአተራረኩ ፍሰትና የቋንቋው ለዛ የሚያመረቃ፣ እጅግ ልብ አንጠልጣይ የተዋጣላት መፅሐፍ ነው፡- “አጼ ቴዎድሮስ - የትንሳዔው ሰማዕት”፡፡ ለዚህም ነው “የማናውቃቸው” የሚለውን አገላለፅ አፅንኦት እንድሰጠው የተገደድኩት፡፡ ምክንያቱም የመፅሐፉ አተራረክ አጼ ቴዎድሮስን የማናውቃቸው ያህል እንዲሰማን ግድ ይላል፡፡ የታሪኩ ፍሰት፣ የታሪክ ሽግግሩ፣ የታሪክ ምልሰት ዘይቤው ከ150 ዓመታት በፊት ከአፄው ጋር በአካል የተገኘን ያህል፣ ሁነቶችን ሁሉ በዓይናችን ብሌን የተመለከትን ያህል እንዲሰማን ያደርጋል፡፡ ልክ እንደተንቀሳቃሽ ፊልም አፄውን ዘመናቸውን ቁጭ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው ብል ቅንጣት ማጋነን እንደሌለበት አምናለሁ፡፡
በታሪክ ምሁራን ዘንድ የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ “ሁለት መልክ” ያለው መሆኑ ይነገራል፡፡ ይህ “ሁለት መልክነት” በተርጊሚው የመግቢያ ፅሁፍ እንደሚከተለው ተጠቅሷል፡-
“….ብዙዎች አጼ ቴዎድሮስ በዘመነ መንግስታቸው አንድ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለመመስረት የቻሉ፣ አሁን ላለችሁ ኢትዮጵያ መሠረተ-ድንጋይ ያስቀመጡ፣ የባርያ ንግድን ለማስቆም የጣሩ፣ ሠራዊታቸው በደመወዝ እንዲተዳደር፣ዝርፊያና ውንብድና እንዲቆም ለማድረግ የሞከሩ፣ መድፍ (ሴባስቶፖል) እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች ለመስራትና ለመጠቀም የጣሩ፣ በጣና ሐይቅ ላይ የሚንሳፈፉ ጀልባዎችን፣ መለስተኛ መርከብ ለመስራት የሞከሩ ፋና ወጊ ንጉስ ናቸው ይላሉ፡፡…
“…. በሌላ ወገን ያሉ ደግሞ አጼ ቴዎድሮስ ያከናወኗቸው ተግባራቶች የሚካድ ባይሆንም፣ በሃገሪቱ የመሬት ስሪትን በተመለከተ ግብር ለመሰብሰብ ያደረጉት ሙከራ ከቤተ-ክህነት በደረሰባቸው ተቃውሞ የገጠማቸው…ያሳቡትን ሊያሳኩ አልቻሉም፡፡ …በዚህም ሰበብ በጊዜው የወሳዷቸው እርምጃዎች የተነሳ… ማዕከላዊ መንግስት የመመሰረት አቅም አልነበራቸውም፡፡…የአንድን ሰው ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝን ተግባዊ ያማረጉ ናቸው ይላሉ፡፡…..” (ገፅ) የአጼ ቴዎድሮስን ታሪክ “ሁለት መልክነት” ያመላክታል፡፡
በጋዜጠኛ ብሩክ መኮንን ተክለየስ ተተርጉሞ ለህትመት የበቃውን “አፄ ቴዎድሮስ - የትንሳዔው ሰማዕት” የተሰኘውን መፅሐፍ ስታነቡ ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን ሁነት ሁሉ በቦታው፣ በስፍራው፣ በዘመኑ ተገኝታችሁ ያያችሁ ያህል ይሰማችኋል፡፡ የአፄ ቴዎድሮስ ሁለት ዓይነት ስብዕና ማለትም ጀግንነትና አልበገር ባይነታቸው፣ ለአገራቸው ያላቸው ቀናዒነትና ምኞት፣ ቁጡነታቸውንና ሩህሩህነታቸውን፣ ፍፁማዊ ጭካኔያቸውንና ይቅር ባይነታቸውን፣ ዕብደታዊ ተግባራቸውንና የመጠቀ ፍልስፍናቸውን… በሚመስጥ የትረካ ስልት ትመለከታላችሁ፡፡
“ዕብደታዊ” የሚለውን አገላለፅ ስጠቀም ከመፅሐፉ ውስጥ ያነበብኩት እጅጉን የገረመኝ ታሪክ ታወሰኝ፡፡ በጥቂቱ ላካፍላችሁማ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ራሳም የተባለውን እንግሊዛዊ እንዲህ ሲሉ ጠየቁት፡-
“….‹ዴዎጋን የለየለት ዕብድ ነበር ወይስ ንክ?› አሉት፡፡…‹ታላቁ እስክንድር ዴዎጋንን ጠርቶ ምን ላድርግልህ? ምን ትፈልጋለህ? ብሎ ጠይቆት ነበር፤ ያን ጊዜ ዴዎጋን፣ ይልቅስ ፀሐይ ልሙቅበት፣ ከምትከልለኝ ዞር በልልኝ› አለው ይባላል ሲል ራሳም ነገራቸው፡፡”
“ቴዎድሮስ ‹እኔ የታላቁ እስክንድር ዝርያ እንደሆንኩ ታውቃለህ? የሜቄዶንያ ንጉሥ የታላቋን ኢትዮጵያ ግዛት ጎብኝቶ ነበር፤ ቆይ በደንብ ልግለፅልህ› አሉና ከንቲባ ኃይሉን ‹መፅሐፉን አምጣና ያንን ዜና እስክንድርን አንብብልን› ሲሉ አዘዟቸው፡፡…” (ገፅ 156)
ታሪኩ ይቀጥላል፡፡ ከንቲባው የታዘዙትን ዜና እስክንድር መፅሐፍ አምጥተው ማንበብ ጀመሩ፡፡
“…ታላቁ እስክንድር ንግስት ህንደኬን ለመጎብኘት ወደዚህ ምድር መጣ፡፡…ወደ ቤተመንግስቱ የሚያደርሱ መንገዶች በአልማዝ፣ በኤመራልድ የተጌጡ መሆናቸውን በደስታ ብዛት በአድናቆት አለቀሰ፡፡….”
ዜና እስክንድር ወደ ቤተመንግስት የሚወስደው መንገድ ወደ ገነት ገነት እንደሚያስገባ፣ ቤተመንግስቱ ተጣጥፎ ወደ ተፈለገው ቦታ ተወስዶ በአንድ ሰዓት ወስጥ እንደሚገነባ የሚተርከውን ክፍል አነበቡ፡፡ ቀጠሉ፡፡
“….‹ንግስቲቱ የለበሰችው ቀሚስ ከአልማዝ ማግ፣ ከዕንቁ ድር ሆኖ ጥለቱ በወርቅ የተዘመዘመ መሆኑን አስተዋለ፡፡… ሀንደኬ የእስክንድርን እጅ ይዛ ከተነጠፈው ውድ አልጋ ላይ አስቀመጠችው፤ በራሷ አድርጋው የነበረውን ዘው ጭንቅላቱ ላይ ደፋችለት፤ ስለተፈቃቀዱ አብረው አንድ አልጋ ላይ አደሩ፤ በነጋታው የማለዳ ፀሐይ እስክትወጣ ድረስ በህንደኬ ዕቅፍ ውስጥ ነበር ታላቁ እስክንድር የቆየው፡፡› እያሉ ቴዎድሮስ ዝም ብለው ያዳምጡ ነበር፡፡….”
ከዚያስ?
“…‹ስለታሪኩ ምን ተገነዘብክ? ምንስ አየህበት?› ሲሉ ቴዎድሮስ ጠየቁት፡፡ ራሳም ታሪኩ የሚታመን ስላልሆነለት፣ ቢያወጣውም ቢያወርደውም ከአፈ-ታሪክ በቀር ምንም ሊባል እንደማይችል በማመን ‹እውነቱን ለመናገር ጃንሆይ ታላቁ እስክንድር ወደ ገነት መግቢያውን በር አግኝቶ በዚያ የተወሰነ ሰዓታት ቢያሳልፍም፣ እንደ እኔ እምነት እዚያው መቅረት ሲገባው ወደ ምድር መመለሱ ሞኝ እንደነበር ያሳየኝ ታሪክ ነው› አላቸው፡፡…”
“አፄ ቴዎድሮስ አምቀውት የነበረውን ሳቃቸውን ለቀቁት፤ ከተቀመጡበት ወንበር እስቂወድቁ ድረስ ሲስቁ ከቆዩ በኋላ ‹አቶ ራሳም እኔ እንዲህ መሰሉን ቡትቶ ተረት ተረትን እውነት ነው ብዬ የምቀበል ይመስልሀል? ብለው እንደገና ሆዳቸውን ይዘው መሳቅ ቀጠሉ፡፡…›
(156- 157)
እንዲህ ያሉ በርካታ መሳጭና ስዕላዊነት ያላቸው ትረካዎችን ያጨቀ ነው “አፄ ቴዎድሮስ- የትንሳዔው ሰማዕት” መፅሐፍ፡፡ ደራሲው ፊሊፕ ማዲሰን መፅሐፉን ከመፃፉ በፊት የሰበሰባቸውን ሰነዶችና መረጃዎች ካጠናከረ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ አፄ ቴዎድሮስን እና ሴባስቶፖል የረገጡትን ምድርን ተከትሎ፣ የወጡትን ተራራ ወጥቷል፤ የወረዱትን ቁልቁለት ወርዷል፡፡ ደራሲው ታሪኩ የተፈፀመበትን ቦታ በአካል ተገኝቶ ጥናታዊ እይታ ማድረጉ እያንዳንዱን ትረካ ክፍል ስዕላዊ በሆነ መንገድ ለማሳየት (ለመቅርፅ) ሃያል ጉልበትና ብርታት የሆነው ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው መፅሐፉ የልብ ወለድ ትረካ ያህል ጥርት ያለ ስዕላዊ ድባብ የተላበሰው ቢባል ስህተት አይደለም፡፡
ይህንን የምለው ወይም ያልኩት እኔ ብቻ አይደለሁም፡፡ ዝነኛ የተባሉ የባህር ማዶ ጋዜጦችና መፅሄቶች ጭምር አስደናቂ ምስክርነታቸውን የቸሩት መፅሐር ነው፡፡ የጥቂቶቹን ምስክርነት መጥቀስ እንችላለን፡፡ እነሆ፡-
“..እጀግ አስደናቂ ከገፅ ወደ ገፅ እያነበቡ በተጓዙ ቁጥር ሙለ ትኩረትን የመሳብና የመቆጣጠር አቅም ያለው መሳጭ ታሪክ የያዘ መፅሐፍ ነው፡፡ እንዲህ ያለ መፅሐፍ ካነበብን ብዙ አመታት አልፎናል፡፡..የመፅሐፉ ደራሲ ፊሊፕ ማድሰን በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ብዙም ያልተሰማውን፣ በብዙዎች ያልታወቀውን እጅግ መሳጭ አሳዛኝና ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ሃገራቸውን ከተቀረው ዓለም ጋር ለማገናኘት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩርን የአቢሲኒያ ንጉሥን የሥልጣን ጉዞ ይተርካል፡፡… ”
- ስፔክታተር
“…ፊሊፕ ማዲሰን ኢትዮጵያን፣ በጊዜው የነበረውን አስገራሚ ክንውን በእያንዳንዱ የመፅሐፉ ገፅ ውብና ማራኪ በሆነ የታሪክ አወቃቀር በመገንባት ውብ በሆነ የአተራረክ ስልት አንብቡት ብሎ አቅርቦልናል፡፡..”
- ኒኮላስ ሼክስፒር (ዴይሊ ቴሌግራፍ)
“….በጣም ጥቂቶች ናቸው እንደ ፊሊፕ ማዲሰን ተሳክቶላቸው ከ150 ዓመት በፊት የነበረውን ክስተት ልብን እያንጠለጠለጠሉ መተረክ የሚችሉ፡፡ ፊሊፕ ከነዚህ ስኬታማ ደራሲዎች አንዱ መሆኑን አስመስክሯል፡፡….”
- ጀምስ ዳንሊንግ ፖል (ሜል ኦን ሰንደይ)
ሌሎች እውቅ ሃያሲያንም ደራሲውን አወድሰው ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ ይገባዋልም፡፡ እኛም መፅሐፉን ተርጉሞ ለባለታሪኮቹ እንዲደርስ ያደረገውን ተርጓሚውን ጋዜጠኛ ብሩክ መኮንን ተክለያስን በእጅጉ ልናደንቅ ግድ ነው፡፡ ከኢትዮጵያውያን ነባራዊ ባህል ጋር አጣጥሞ ውብ በሆነ የቋንቋ አጠቃቀምና ለዛ ጋር አዋህዶ፣ እስከመጨረሻዋ ገፅ ድረስ የታሪኩን ፍሰትና ልብ አንጠልጣይነት ጠብቆ መተርጎም እጅግ አድካሚ፣ ፈታኝና ታላቅ ክህሎትን የሚጠይቅ፣ በአያሌው የሚደነቅ ተግባር ነውና፡፡  በመጨረሻ ይህንን ዳሰሳዊ ፅሁፍ የምቋጨው ጋዜጠኛ ብሩክ መኮንን ተክለየስ “አፄ ቴዎድሮስ - የትንሳዔው ሰማዕት” በሚል ርዕስ ተርጉሞ ለህትመት ያበቃውን በ50 ብር ብቻ በመሸጥ ላይ ያለውን መፅሐፍ ለአንባቢያን በመጋበዝ ነዉ፡፡ መልካም ንባብ!!

1 comment:

  1. ታሪካዊ ሃቆች፡-
    (የታሪክ መፅሃፍት ስለ አፄ ቴዎድሮስ)
    1-መልካቸው
    -መልካቸው ከመደበኛው ኢትዮጵያዊ በተለየ መልኩ በጣም ጥቁር የነበሩ(አሁን የምናየው እውነተኛው መልካቸው ሳይሆን የኮምፒውተር ስራ ነው)
    -አይናቸው አነስ አነስ ያሉና ገባ ገባ ያሉ
    2- ጭካኔ
    -በኢትዮጵያ ታሪክ ቤተክርስቲያን ያቃጠሉ ብቸኛው ንጉስ ናቸው ይባላሉ
    -ወደ መቅደላ ሸሽተው በተሰደዱበት ወቅት ደብረ ታቦር ከተማን ሙሉ በሙሉ በእሳት አቃጥለዋል
    -ጎንደር ቤተመንግስትና ቤተክርስቲያንን አቃጥለዋል
    -ሴቶችና ህፃናትን ሳር ቤት ውስጥ አጉረው አቃጥለዋል
    -የሰው ልጅ ከነነፍሱ እጅ እግሩን ብቻ ቆራርጠው ገደል ወርውረዋል
    -መድፍ ፊት አቁመው የረሸኑ በታሪክ ብቸኛው ሰው ናቸው
    -ኢትዮጵያን በተመለከተ ከተናገሩት ውስጥ ፡እኔ የተላክሁት የኢትዮጵያን ህዝብ ልቀጣ ነው
    -ስልጣናቸውን ካጡ ተመልሰው ዘረፋ እንደሚገቡ ደጋግመው ይዝቱ ነበር
    -በሳቸው ዘመን አገር በሙሉ አንድ የነበረው ሁሉም ለሳቸው ባለመታዘዙና ራሳቸውን ባጠፉ ጊዜ ሬሳቸውና የሚያነሳው ጠፍቶ ቀኑን ሙሉ ፀሃይ ላይ የዋለ መሆኑንና፡ልጆቻቸውን ለማስጠጋት አንድም ዘመድ እንኳን አልተገኘም ነበር
    -ታሪካቸው መነሳት የጀመረው ደርግ ለክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት ማጀቢያነት እና የሰውን ልጅ የጭካኔ ጥግ ባሳየበት አገዛዙ የተጠቀመበት በታዋቂ ደራሲዎች በግድ እንዲፃፍና ለተውኔት እንዲቀርብ ካደረገበት ዘመን ጀምሮ ካለፉት 40 አመታት ወዲህ ነው
    3-ባህሪ
    -ዘወትር ይሰክሩ የነበሩ
    -ከ 38 በላይ ቁባቶች(ውሽሞች) ነበሯቸው
    -ጥሩወርቅን ሲያገቡ የ12 አመት ህፃን ነበረች
    -ማታማታ ልብሳቸውን እየቀየሩ እየተሸፋፈኑ ወደ መንደር ይገቡ ነበር
    -ህዝቡና የውጭ ፀሃፊዎች እብዱ ንጉስ እያሉ ይጠሯቸው እንደነበር ራሳቸው ተናግረዋል
    4-የመጨረሻቸው ወቅት
    -ከመቅደላ ለማምለጥ ከገብርዬ(ፊታውራሪ ገብረሕይወት ጎሹ) ጋር ሲማከሩ፤ገብረሕይወት (ገብርዬ) ግን ያልጨፈጨፍነው አገር የታለና ወዴት እንሄዳለን ህዝብ አይምረንም ና እዚሁ አሟሟታችንን እናሳምር ብለው መለሱ
    -ቴዎድሮስ ግን ከተራራው ግርጌ ሲደርሱ እንዳያመልጡ ተብሎ ይጠበቅ ስለነበር ዙሪያው በየጁ ሰራዊት ተከቦ ስላገኙት ተመልሰው ወደተራራው አናት ወጡ

    የመረጃ ምንጭ፡-
    የራሳቸው ታሪክ ፀሃፊ አለቃ ዘነብ፡የታሪክ አባት ተክለፃዲቅ መኩሪያ፡ጳውሎስ ኞኞ፡ብርሃኑ ዘሪሁን፡ሉዊስ ክራፍ፡ሄነሪ ስተርን…

    አመሰግናለሁ፡፡

    ReplyDelete