Sunday, May 25, 2014

ዐባይን ያላቅም (በዶ/ር ከፍያለው አባተ)

 1. መግቢያ የዐባይ ነገር በተነሳ ቁጥር የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቃትና ሀዘን የሚሰማው ይመስለኛል። ያገራችን ነገር (በብዙ መልኩ) “እያዩ ማዘን” ነው። ሕዝብ በፍትህ እጦት እንዳሻሮ ሲታመስ እያዩ ማዘን፣ ወገን በርሀብና በበሽታ ሲማቅቅ እያዩ ማዘን፣ ያገር ልጅ በድርቅና በጦርነት የተነሳ እንደ ቅጠል ሲረግፍ እያዩ ማዘን፣ ሰው ሀገሩን ጥሎ ሲሰደድ እያዩ ማዘን፣ ዐባይ ያለ አንዳች ጥቅም አገር አቋርጦ ሲሄድ እያየን ማዘን። አቅም የሌለው ሰው እያየ ከማዘን ሌላ ምን ሊያደርግ ይችላል? የኢኮኖሚ አቅም የለን፣ ወታደራዊ አቅም የለን፣ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል አቅም የለን፣ እንዲያው ሁሉንም በአርምሞ እያየን ማዘን ነው ልምዳችን። የሚገርመው፣ አቅመቢስነታችን የምናባብሰው እኛው እራሳችን ነን። 
ከታሪካችን መማር አንችል፣ ተጣልተን መታረቅ አንችል፣ ተከራክረን መተማመን አንችል፣ ሙያችን እንዲሁ መነታረክ ብቻ ሆነ። ለስልጣን ስንል እርስ በርሳችን ስንራኮት፣ ስንዋጋና ስንጨፋጨፍ አቅማችን ልንገነባ ቀርቶ ይበልጥ ስናዳክመው ኖርን። ያቅመቢሶች ባላቅም፣ የጡንቻቢሶች ባለጡንቻ፣ የስልጣን-የለሾች ባለስልጣን፣ የደካሞች አውራ፣ የዐይነ ስውሮች አንድ-አይና መሪ ለመሆን ስንል፣ ሀገራችን አቅም-የለሽ፣ ኋላ-ቀር፣ የተናቀችና ለጥቃት የተጋለጠች ሀገር አደረግናት። የዐባይ ወንዝ አጠቃቀም ጉዳይም አቅመ ደካማነታችንና ለጥቃት የተጋለጥን መሆናችን የሚያንጸባርቅ አንድ ጉልህ ማስረጃ ነው። 
የዐባይን ወንዝ በተመለከተ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስር የሰደደ የረዥም ጊዜ ሀዘን፣ እሮሮና ቁጭት አለበት። ዐባይ ግብጽን የመሰለች፣ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የከፈተች፣ አጼ ዮሐንስን ከጦር ጀኔራላቸው ከራስ አሉላ ዕቁቢ (አባ ነጋ) እና ከሰራዊታቸው ጋር እረፍት አሳጥታ ስታንከለክል የኖረች፣ ብዙ ንብረትና የሰው ሕይወት መስዋእትነትን ያስከፈለች ባላጋራ የፈጠረብን ወንዝ ነው። የዐባይን ወንዝ የመጠቀም አቅም እንዳይኖረን ( ለ ኢ ት ዮ ጵ ያ ጠ ላ ቶ ች ከ ለ ላ በ መ ሆ ን ፣ የ ው ስ ጥ ብጥብጥንና መከፋፈልን በመፍጠር፣ ብጥብጡ እንዳይበርድ በማራገብ፣ ለውጭ ጠላቶቻችን ድጋፍ በመስጠት፣ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ስውር ደባ በመፈጸም ወ.ዘ.ተ ) ድክመትና ውድቀታችን ስትመኝ የምትኖር፣ አብሮ መጠቀምና መተባበር እማይታያትን፣ ግብጽን የመሰለ አውራ ባላጋራ ያፈራብን ወንዝ ነው። ዐባይን ባስጠቂነቱ እንጂ በጠቃሚነቱ አናውቀውም። 
አጼ ዮሐንስን
ሲያሳስቱና ሲያታልሉ 1 የኖሩት እንግሊዞች በ1882 ዓ.ም2 ግብጽን ሲቆጣጠሩና፣ በ1898 ዓ.ም ደግሞ ሱዳንን እንደገና ሲይዙ ያነጣጠሩት ዐባይ ውሀ ላይ ነበር። የእንግሊዞች ዓይነተኛ ዓላማ በግብጽና በሱዳን የተንጣለለ የዐባይ ሸለቆ ላይ (ለእንግሊዞች የጥጥ ፋብሪካዎች ፍጆታ የሚሆን) ካመት እስካመት ጥጥ የሚመረትበት ሰፊ የመስኖ እርሻ ማልማት ነበር። ይህ ጥጥ የበጋና የክረምት ወራት ሳይጠብቅ ያለማቋረጥ እንዲለቀም፣ የዐባይ ውሀ መጠን ከፍና ዝቅ እንዳይል፣ እስከመነሻው (እስከጣና ሀይቅ ድረስ) በቁጥጥራቸው ስር አድርገው የወንዙን ውሀ መጠንና አወራረድ መቆጣጠር (regulate) ነበረባቸው። በዚህም የተነሳ እንግሊዞች በኢትዮጵያዊያን ላይ ከትውልድ እስከ ትውልድ ሊፋቁ የማይችሉ (በኋላ በተደጋጋሚ የፈጸሙብን በደል ሳይቆጠር) ሦስት ግዙፍ በደሎችን ፈጸሙ። 
በደል1.  በ1902 ዓ.ም ከአጼ ምኒልክ ጋር የድምበር ውል ሲዋዋሉ፣ ላቀዱት የጥጥ እርሻ ሲሉ ሰፊ ደልዳላ መሬት ወደቅኝ ግዛታቸው (ወደሱዳን) ክልል ውስጥ እንዲገባ አደረጉ። ወደ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የገባው (ከቀጭን/ከጠባብ ደልዳላ መሬት በስተቀር) ተራራማውና ለመስኖ ስራ አመቺ ያልሆነው ወጣ ገባው መሬት ነበር። 
በደል 2. በዚያው ዓመተ ምህረት (በ1902 ዓ.ም) ግንቦት ወር ውስጥ በሱዳንና በግብጽ ውስጥ ለማምረት ላሰቡት የጥጥ ምርት በቂ ውሀ ለማግኘት ሲሉ፣ የእንግሊዝ መንግሥትና የሱዳን መንግሥት ካልፈቀዱ በስተቀር በጥቁር ዐባይ፣ በጣናና በሶባት ወንዝ ላይ የወንዞቹን ውሀ ‘የሚያስቀር’ (arrest the flow of their waters) ምንም ዓይነት ስራ እንዳይሰራ ከአፄ ምኒልክ ጋር ተዋዋሉ3። 
በደል 3. እንግሊዝ በ1929 ዓ.ም ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት የዐባይን ውሀ ለግብጽና ለሱዳን የሚያከፋፍል የውል ስምምነት4 አዘጋጅታ ሁለቱን ሀገሮች (ግብጽንና ሱዳንን) አፈራረመች። 
ታዲያ ይህ ሁሉ ደባና ጥቃት እየተሰማው ይመስለኛል፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ በዐባይ እንዳዘነ ይኖራል። የዐባይ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር በንዴት ከንፈሩን የሚመጠው ዜጋ ብዙ ነው። በዐባይ ላይ እማይሸለል ሽለላ፣ እማይቅራራ ቀረርቶ፣ እማይዘፈን ዘፈን፣ እማይገጠም ግጥም የለም። የዚሁ ሕዝብ ውስጣዊ ስሜት ተካፋይ የነበሩት እንደነሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ያሉ ታዋቂ ገጣሚዎች ሳይቀሩ “ዐባይ አቫይ” እያሉ ዐባይን ይወቅሱታል። 
ተገንዝበነው እንደሆነ ወይም አልተገነዘብነው እንደሆነ እርግጠኛ አይደለሁም እንጂ፣ በዐባይ ላይ የሚሰነዘረው ሀዘንና ወቀሳ ሁሉ በመንግሥቶቻችን (በፓለቲካ ባለሥልጣኖቻችን) ላይ ያነጣጠረ ይመስለኛል። ዐባይማ ግዑዝ ነውና ቆም ብሎ ሀዘንና እሮሮ አይሰማ! አቤቱታ አይቀበል! በየተራ የመንግሥት ስልጣን ይዘው የነበሩት ገዢዎቻችን ካለፈው ጥቃት ተምረው የኢኮኖሚና የጦር ኃይል ጡንቻችን እንዲፈረጥምና በባላጋራዎቻችን እንድንታፈር አላደረጉም። ከኢኮኖሚውና ከተደራጀው የጦር ኃይል በተጨማሪ፣ በተለያዩ መድረኮች ላይ የግብጽ ኃይል ሚዛን እንዳያደፋ፣ በኛ በኩል የሚሰለፍ የተማረ/የሰለጠነ የሰው ኃይል አላፈሩልንምና በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚሰነዘረው ወቀሳ፣ ሀዘንና እሮሮ ሁሉ በገዢዎቻችን ላይ ያነጣጠረ ይመስለኛል። 
ሀገራችን አቅመ-ደካማ በመሆኗ፣ በድምበሯ ውስጥ ከሚፈ(ስ)ሰው የዐባይና የገባሮቹ ውሀ ድርሻ እንዳይኖራት በተፋሰሱ ታችኛ ክፍል የሚገኙት ሀገሮች (በተለይ ግብጽ) ዓይናቸውን አፍጥጠው ይጠብቋታል። ሽንጣቸውን ገትረው ይከራከሯታል። የዐባይን ውሀ አጠቃቀም በተመለከተ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ክርክር ረዘም ያለ ጊዜ የፈጀ ነው። አሁንም ክርክሩ እንደቀጠለ ነው። 
ላንባቢዎች ለማስታወስ ያህል፣ በዐባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይ የኢትዮጵያና የግብጽ የክርክር አቋም ባጭሩ እንደሚከተለው ነው።  
2. የኢትዮጵያና የግብጽ አቋም በዐባይ አጠቃቀም ላይ 
2.1. የኢትዮጵያ አቋም፡ ኢትዮጵያ የያዘቺው የክርክር አቋም በ1966 ዓ.ም በወጣው የሄለስንኪ ደምብ (Helsinki Rules) በመባል በሚታወቀው የሀገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ድንጋጌን የተመረኮዘ ነው። የኢትዮጵያ አቋም የዐባይን ወንዝ ውሀ ‘ሚዛናዊ’ (equitable distribution) በሆነ መልኩ ‘ተዛዝነን’ (fairly) እንጠቀምበት የሚል ነው። ዐባይ ወንዛችን ነውና (ለግብጽ የሚያስፈልገው ውሀ ሳይዛባ) እኛም ተጠቃሚዎች መሆን ይገባናል። በሀገራችን ክልል ውስጥ የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት እንዳንጠቀም መከልከል የተባበሩት መንግሥታት ያጸደቀውን ያንድን ሀገር ሉዐላዊ መብት መጋፋትና መድፈር ነው። ስለዚህ የሱዳንንም ሆነ የግብጽን ሕዝብ ጥቅም በማያናጋ መንገድ ወንዛችን እንጠቀምበታለን የሚል ነው። የዐባይን ወንዝ (ለግብጽም፣ ለሱዳንም፣ ለኢትዮጵያም) ሚዛናዊና ተመጣጣኝ (equitable) በሆነ መልኩ እንድንጠቀም ግብጽ ፈቃደኛ ካልሆነች፣ ኢትዮጵያ (የግብጽን አወንታ ሳትጠብቅ) በግሏ ትወስናለች ወይም እርምጃ ትወስዳለች (unilateral decision) የሚል ነው የኢትዮጵያ አቋም። 2.2. የግብጽ አቋም፡ የግብጽን የመከራከሪያ አቋም በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል።  ሀ) ከ5,000 ዘመናት በላይ ከኢትዮጵያም ሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ተነስቶ ወደግብጽ የሚፈሰው (የጥቁር ዐባይና የነጭ ዐባይ) ውሀ ታሪካዊ ተጠቃሚ ነኝ። አሁንም ዋናዋ ተጠቃሚ (primary user) እኔ ነኝ፣ የውሀው ታሪካዊ ባለቤትም እኔ ነኝ ባይ ናት። ግብጽ ይህን ታሪካዊ ተጠቃሚነት መከራከሪያ የምታደርግበት ምክንያት፣ በተባበሩት መንግሥታት ተቀባይነት ያለው “ዓለም አቀፍ የሕግ ኮሚሽን” (International Law Commission/ILC) ካወጣቸው ሕግጋት አንዱ “መጀመሪያ የ ው ሀ ው ተ ጠ ቃ ሚ የ ሆ ነ ፣ የ ው ሀ ው ባ ለ መ ብ ት ይ ሆ ና ል ። በ ኋ ላ የ መ ጣ ው የ መ ጀ መ ሪ ያ ው ን ተ ጠ ቃ ሚ መ ብ ት ሊ ገ ስ ስ አይችልም ”5 ስለሚል ነው። እንደዚህ ያለውን ባለመብትነት በእንግሊዝኛ acquired rights or prior appropriation  እያሉ ይጠሩታል። ግብጽ ይህንን ደምብ ተንተርሳ፣ በስተላይ ካሉት የተፋሰስ ሀገሮች አዲስ የሚወጠን ፕሮጀክት ሁሉ ታሪካዊ ጥቅሜን ማዛባቱ አይቀርም (leads to ‘appreciable’ harm) ትላለች።  በዐባይ ተፋሰስ ላይኛው ክፍል (upper catchments) የሚታቀድና የሚወጠን የልማት ስራ ሁሉ ታሪካዊ ጥቅሜን ስለሚነካ፣ እኔ ያየሁት/ያወቅሁት፣ ያመንኩበት፣ የተስማማሁበትና ያጸደቅሁት ካልሆነ በስተቀር፣ የሚታቀደው የልማት ስራ ተፈጻሚነት ወይም ተግባራዊነት አይኖረውም የሚል ነው። ስለዚህ ግብጽ የያዘቺው አቋም ባጭሩ፣ በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ ለሚታሰቡና ለሚወጠኑ ፕሮጀክቶች ሁሉ ፈቃጅና ከልካይ፣ ሰጪና ነሺ እኔ ነኝ የሚል ነው። 
ለ) በእንግሊዞች አማካይነት በ1929 ዓ.ም፣ በኋላ ደግሞ በ1959 ዓ.ም በግብጽና (በእንግሊዞችና በግብጽ ጣምራ ግዛት ስር /Anglo-Egyptian Condominium በነበረቺው) በሱዳን ከተፈረመው የዐባይ ውሀ አጠቃቀም ስምምነት ውጪ፣ ከዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር ሌላ ድርድር አልደራደርም፣ ሌላ ውል አልዋዋልም፣ ሌላ ፊርማም አልፈራረምም የሚል ነው። 
3. የ1929ኙና የ1959ኙ ውሎች ባጭሩ የአንባቢዎቼን ትውስታ ለመቀስቀስ ያህል፣ የዐባይ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የ1929 ዓ.ም እና የ1959 ዓ.ም የውል ስምምነቶች በየመድረኩ በተደጋጋሚ (በተለይ በግብጾች) የሚነሱ ናቸውና ባጭር ባጭሩ እንደሚከተለው ላቅርብላችሁ። 
ሀ) የ1929ኙ የዐባይ ውል ተፈራራሚዎች፣ 1) ከቅኝ ተገዢነት ነፃ የወጣች ቢሆንም በብዙ መልኩ (በተለይ በመንግሥት አስተዳደር ዘርፍ) ገና በእንግሊዞች ተጽእኖ ስር የነበረቺው ግብጽ ናት። 2) በእንግሊዝና በግብጽ ጣምራ ተገዢ የነበረቺው ሱዳን ናት። አድራጊ ፈጣሪዋ እንግሊዝ ብትሆንም የ1929ኙ የውል ስምምነት (በተለምዶ) ግብጽና ሱዳን የተስማሙበት ውል እንደሆነ ተቆጥሮ ነው የሚወሳው። የ1929ኙ ውል ባጭሩ የሚከተለውን ይመስላል። 
 በዚያን ጊዜ በእንግሊዞች አማካይነት ግብጽና ሱዳን በተማመኑበት መሠረት በያመቱ በጠቅላላ 80 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (cubic meters) ውሀ ግብጽ/አስዋን ይደርስ ነበር። ከዚህ 80 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ውስጥ ግብጽና ሱዳን በዚያን ጊዜ ሊጠቀሙበት ይችላሉ ተብሎ የተተመነው የውሀ መጠን (utilizable water) 52 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነበር። ይህም ማለት (80 – 52 = 28) ወደ 28 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ከግብጽ ተርፎ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር እንደሚገባ ነበር የታመነበት። 
 ግብጽና ሱዳን ሊጠቀሙበት ይችላሉ ከተባለው 52 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ (cubic meters) ውስጥ ሱዳን 4 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (7.7%) ውሀ እንድትጠቀም፣ ግብጽ ደግሞ 48 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (92.3%) ውሀ እንድትጠቀም ተስማሙ። 
 በበጋው ወቅት (ከጥር መጨረሻ እስከ ሐምሌ አጋማሽ ድረስ/January 20 to July 15) የሚፈስሰው የዐባይ ውሀ ግን ሙሉ በሙሉ ለግብጽ ጥቅም ብቻ እንዲውል ተስማሙ። 
 በላይ በኩል የሚገኙትን የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ለመቆጣጠር (monitor) የግብጽ መብት የተጠበቀ ስለመሆኑ ተስማሙበት። 
 በላይ በኩል ያሉትን የተፋሰሱን ሀገሮች ፈቃድ ሳታገኝ (without the consent of upstream riparian states) በዐባይ ላይና ከዐባይ ጋር የሚገናኝ ማንኛውንም ፕሮጀክት ለመስራት የግብጽ መብት የተጠበቀ መሆኑን ተስማሙበት። 
እንግዲህ አንባቢዎች እነዚህን ውሎች አይታችሁ የየራሳችሁን ሚዛናዊ ፍርድ ስጡ። እነዚህ ውሎች በሁለቱ ሀገሮች መካከል ብቻ መፈረማቸው ልክ ነውን? በነዚህ ውሎች የማን መብት ተጠበቀ? የማን መብት ተደፈረ? ከውሎቹ እንደምትረዱት ይህ ውል የዐባይን ተፋሰስ ሀገሮች6 በሙሉ የሚመለከት ነው። ተደራዳሪዎቹና ተፈራራሚዎቹ ግን ‘ግብጽና’ ‘ሱዳን’ ብቻ ናቸው። የላይኞቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ከዐባይ ወንዝ ውሀ የተተወላቸው ድርሻ የለም። በኔ እይታ ይህ ውል በላይ በኩል ያሉትን የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ሉዐላዊነት ገፍፎ፣ መብታቸውን ደፍሮ፣ አድራጊ ፈጣሪዋ ግብጽ ብቻ እንድትሆን ያደረገ ውል ነው። 
ለ) የ1959ኙ የዐባይ ውል ስምምነት ሱዳን ከእንግሊዞች ቅኝ ተገዢነት ነፃ ከሆነች በኋላ (ማለትም በሁለት ነፃ ሀገሮች) በግብጽና በሱዳን መካከል የተደረገ ስምምነት ነው። የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች ባጭሩ የሚከተሉት ናቸው። 
 አስዋን ላይ ለሃምሳ ዓመታት ያህል ተለክቶ የተገኘ ነው በማለት ጠቅላላው የዐባይ ውሀ 84 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ነው ብለው ተመኑ። ከዚህ 84 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ውስጥ 10 ቢሊዮን ሜትር ኩብ በትነትና (surface evaporation) በስርገት (seepage) ሊጠፋ/ሊባክን ይችላል ተብሎ ተገመተ።
 ቀሪውን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ግብጽና ሱዳን ላገልግሎት ያውሉታል ተብሎ ታመነበት። ይህ ተመን ከ1929ኙ ተመን የ22 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ብልጫ ያሳያል። በዚህ ተመን መሠረት ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር የሚገባ የዐባይ ውሀ የለም። 
 ይህንን 74 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ፣ ሱዳን 18.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (25%) ውሀ እንድትጠቀም፣ ግብጽ ደግሞ 55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ (75%) ውሀ እንድትጠቀም ተከፋፈሉ። 
 ሱዳን ነፃ ከወጣች ከሁለት ዓመት በኋላ (በ1958 ዓ.ም) የተስማሙበትን፣ የዐባይን ወንዝ ውሀ ሙሉ በሙሉ ይይዛል ብለው ያመኑበትን፣ የአስዋንን ግድብ ግብጽ እንድትገነባ ስምምነታቸውን አጸደቁ። 
 ሱዳን የውሀ ኮታዋን እስካላለፈች ድረስ ሮሲዬርስ (Roseires Dam) የተባለውን ግድብ ጥቁር ዐባይ ላይ ገድባ ለኃይል ማመንጫና ለመስኖ አገልግሎት እንድትጠቀምበት ተስማሙ። 
 ሱዳን ከግብጽ ጋር በመስማማት የዐባይን ውሀ ፍሰት እሚያጠነክሩ (ወደ ሱድ/Sudd ረግረግ እየገባ በትነት የሚባክነውን ውሀ የሚቀንሱ) በኋላ እንደተወጠኑት እንደነ ጆንገሌይ ቦይ (Jongelei Canal) የመሳሰሉ ፕሮጀክቶች አውጥታ መስራት እንደምትችል፣ ይህ ዓይነቱ ስራ በሚያስከትለው ወጪና ገቢ ግብጽ ተሳታፊ/ተካፋይ እንደምትሆን ተስማሙ።    በስተላይ ከሚገኙ የተፋሰሱ ሀገሮች የሚሰነዘር አቤቱታ ቢኖር ጉዳዩን ግብጽና ሱዳን በጋራ ሊያዩትና፣ በጋራ ሊያስተናግዱት ስምምነት አደረጉ። 
 ከሁለቱ ሀገሮች (ከሱዳንና ከግብጽ) ውጪ የዐባይ ውሀ ይገባኛል የሚል፣ በተፋሰሱ ውስጥ የሚገኝ ሀገር ቢነሳ፣ የቀረበው ጥያቄ በግብጽና በሱዳን ከታመነበት፣ አስዋን ግድብ የሚደርሰው የዐባይ ውሀ ተለክቶ በሚገኘው የውሀ መጠን መሠረት፣ ለጠያቂው ሀገር ተቀንሶ የሚሰጠውን ውሀ ግብጽና ሱዳን እኩል ሊካፈሉ ተስማሙ። 
 ቴክኒካዊ የሆኑ የውሀ ልማት ስራዎችንና ትብብሮችን የሚያከናውን ቋሚ የጋራ የቴክኒክ ኮሚሽን (Permanent Joint Technical Commission/PJTC) እንዲቋቋም ተስማምተው አቋቋሙ። 
እነዚህን ውሎች ነው ግብጽ በድፍረት የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች የጋራ ውሎች በማስመሰል በያጋጣሚው በተደጋጋሚ መከራከሪያ ነጥብ እያደረገች የምትጠቅሳቸው። በነዚህ የውል ስምምነቶች እኛ አልተሳተፍንባቸውም በማለት ሌሎቹ የተፋሰሱ ሀገሮች (riparian states) ቢወተውቱም፣ ግብጽ በአዲስ መልክ በሚረቀቅ ሌላ የውሀ አጠቃቀም ወይም ክፍፍል ላይ ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆኗን እስካሁን እንዳጸናች ነች። 
በ1995 ዓ.ም የግብጽ የውጭ ጉዳይ ምንስቴር ረዳት ሚኒስትር የነበሩ (ማርዋን በድር/Marwan Badr) የተባሉ ግብጻዊ “ የሕዝባቸው ቁጥርና ኢኮኖሚያቸው እያደገ የመጣው የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች የውሀ ጥያቄ ፣ ፓለቲካ ብቻ ሳይሆን እውን እየሆነ ነውና ግብጽ ከ1959ኙ የውሀ ኮታ ለየት ባለ የውሀ ድርሻ ላይ ለመደራደር መዘጋጀት አለባት ” የሚል (ካንድ ግብጻዊ ባለስልጣን እማይጠበቅ) ሀሳብ በማቅረባቸው ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል። የግብጾች ግትር አቋም በ1959 ዓ.ም ከሱዳን ጋር ተደራድረን ካገኘነው (55.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ) የተለየ መደራደሪያ ሀሳብ አንቀበልም የሚል ነው።  
4. ያገር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ተመክሮ ወንዞች የተፈጥሮ ፀጋ ናቸው። ወንዞቹ በሚፈስሱበት አቅጣጫ የሚገኙ ሀገሮች ሁሉ ሊጠቀሙባቸው ይገባል። አጠቃቀሙ ግን ካገር አገር መለያየቱ የማይቀር ነው። ምክንያቱም የተለያየ የውሀ አቅርቦት አማራጭ (ዝናም፣ ሀይቅ፣ ምንጭ፣ የከርሰ ምድር ውሀ፣ ሌላ ወንዝ) ያለው ሀገር አለ። እንደ ግብጽ ያለው ደግሞ ከወንዝ ውሀ በስተቀር ሌላ አማራጭ የሌለው (primary user) ሀገር አለ። በእድገት ደረጃው ከፍተኝነት ምክንያት የውሀ ፍላጐቱና ፍጆታው ከፍተኛ የሚሆንበት ሀገር አለ። ኋላ-ቀርና ብዙ ውሀ እማይጠቀም (እማያስፈልገው) ሀገር አለ። ኋላ-ቀር የነበረው ሀገር በኢኮኖሚ እያደገ ሲሄድ የውሀ ፍላጐቱና ፍጆታውም እየጨመረ ስለሚሄድ የውሀ ድርሻው/ኮታው በየጊዜው መታየት ይኖርበታል። ባጭሩ ለማስቀመጥ ያህል የውሀ ፍላጐትና ፍጆታ ከጊዜ ጊዜ ይለዋወጣል። የውሀ ክፍፍልም እንደዚሁ በየጊዜው እየተጠና መስተካከል አለበት። አንድ ጊዜ የተመደበ የውሀ ኮታ ለዘላለም ቋሚ ሁኖ መኖር የለበትም። ግብጽ ይህንን ሁሉ አላጣቺውም፣ ግን ልትቀበለው፣ ሊዋጥላት አልቻለም። 
ይህንን (የወንዝን ውሀ) የመሰለ የተፈጥሮ ሀብት በድርድር መከፋፈል እንደሚገባ የዓለም ሕዝብ ያምንበታል። የተባበሩት መንግሥታት ያጸደቃቸው የድምበር አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ደምቦችና ሕግጋት አሉ። በጋራ ወንዞቻቸው አጠቃቀም ላይ የተለያዩ ሀገሮች (ባፍሪካ ውስጥም ካፍሪካ ውጭም) ስምምነት7 እየተፈራረሙ ሲጠቀሙባቸው እናያለን። ለናሙና ያህል ጥቂቶቹን ልዘርዝርላችሁ።
ምዕራብ አፍሪካ፡ - ሴኔጋል ወንዝ (Senegal River) እሚፈስባቸው ሀገሮች (ማሊ፣ ሞሪታኒያ፣ ጊኒና ሴኔጋል) የወንዙን አጠቃቀምና እንክብካቤ በሚመለከት ተደራድረው የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል። ማሊ ውስጥ የሚገኘው ማናንታሊ (Manantali Dam) የተሰኘው ግድብ በተፋሰሱ ሀገሮች ኅብረት በትብብር የተሰራ ነው። ግድቡ ማሊ ውስጥ ቢሆንም የተፋሰሱ ሀገሮች በሙሉ በጋራ ባለቤትነት የሚያ(ዝ)ዙበት፣ የሴኔጋል ሸለቆ ባለስልጣን (OMVS/ Office de Mise-en-Valeur du Vallee du Senegal) ብለው ባቋቋሙት ቢሮ የሚተዳድር የኅብረት ግድብ ነው። - የናይጀር ወንዝ (Niger River) ተፋሰስ ማሊን፣ ናይጀሪያን፣ ኒጀርን፣ ጊኒን፣ በርኪናፋሶን፣ ካሚሩንን፣ ቤኒንን፣ አይቮሪኮስትን፣ ቻድን ያጠቃልላል። እነዚህ የናይጀር ወንዝ ተፋሰስ ሀገሮች የውል ስምምነት ተፈራርመው የተፋሰሱን ውሀ በጋራ ይጠቀሙበታል። ባንዳንዶቹ የተፋሰሱ ሀገሮች ቅሬታ መሰንዘሩ ባይቀርም እንደ ዐባይ ጐልቶ የወጣ ችግር የለባቸውም።
መካከለኛው አፍሪካ፡ - የዛምቤዚ ወንዝ (Zambezi River) ተፋሰስ ዛምቢያን፣ ዚምባቡዬን፣ ሞዛምቢክን፣ ማላዊን፣ አንጐላን፣ ናሚቢያን፣ ቦትስዋናን፣ ታንዛኒያን ያካትታል። ከነዚህ ሀገሮች መካከል ዛምቢያና ዚምባቡዬ የጋራ አጠቃቀም ስምምነት ተፈራርመዋል። እንዲያውም ካሪባ ግድብ (Kariba Dam) የሚባለውን ከአፍሪካ ታላላቅ ግድቦች አንዱ የሆነውን ግድብ በጋራ ነው የገደቡት። የዛምቤዚን ወንዝና የግድቡን አጠቃቀም የሚከታተልና የሚያስተዳድር (Zambezi River Authority የሚባል) ባለስልጣን መስሪያ ቤትም በጋራ አቋቁመዋል። ሌሎቹ የዛምቤዚ ተፋሰስ ሀገሮች በወንዙ ውሀ አጠቃቀም ላይ እምብዛም ስለሆኑ፣ በተፋሰሱ አጠባበቅ ግዴታ ውስጥ መግባት ስላልፈለጉ ይመስላል የስምምነቱ ተሳታፊ አልሆኑም። - ካጌራ ወንዝ (Kagera River) ሩዋንዳና ቡሩንዲ የሚነሳ ወደ ቪክቶሪያ ሀይቅ የሚገባ ትልቅ ወንዝ ነው። በዚሁ ወንዝ ሩሱሞ ፏፏቴ (Rusumo Falls) ላይ የኃይል ማመንጫ ግድብ ገድበው የኤሌትሪክ ኃይሉን ለታንዛኒያ ለመሸጥ ፕሮጀክት ወጥነው ነበር። የገንዘብ አቅማቸውን ለማጐልበት ከሩዋንዳና ከቡሩንዲ በተጨማሪ ታንዛኒያንና ዩጋንዳን አስተባብረው (አባል አድርገው) የካጌራ ሸለቆ የልማት ድርጅት የሚባል አቋቁመው ነበር። ነገር ግን በመካከል አካባቢው በጦርነት ስለተመሰቃቀለ ፕሮጀክቱ በውጥን ቀርቷል። 
አውሮፓ፡ - የዳኒዩብ ወንዝ (Danube River) ተፋሰስ ሀንጋሪን፣ ዩጐዝላቪያን፣ ሮማንያን፣ ኦስትርያን፣ አልባኒያን፣ ፓላንድን፣ ጣሊያንን፣ ስዊትዘርላንድን፣ ቡልጋሪያን፣ ስሎቫኪያን፣ ጀርመንን፣ ቼኮዝለቫኪያን፣ ራሽያን (የድሮውን ሶቪዬት ኅብረት) ያካተተ ነው። እነዚህ ሀገሮች ሁሉ በተፋሰሱ አያያዝና አጠቃቀም ላይ ተፈራርመው ወንዙን በጋራ ይጠቀሙበታል። - የራይን ወንዝ (Rhine River) ደግሞ ቤልጅዬምን፣ ኔዘርላንድን፣ ኦስትሪያን፣ ፍራንስን፣ ስዊትዘርላንድን፣ የሚያስተሳስር ስለሆነ በዚህ ወንዝ አያያዝና አጠቃቀም ላይ እነዚህ ሀገሮች የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል። 
ሰሜን አሜሪካ፡ - ኮሎራዶና ሪዮ-ግራንድ (Colorado and Rio Grande) አሜሪካንና ሜክሲኮን ስለሚያስተሳስር ሁለቱ ሀገሮች የስምምነት ውል ተፈራርመዋል። - ኮሎምቢያና ታላላቆቹ ሀይቆች (Columbia and the Great Lakes) ካናዳና አሜሪካ በጋራ ስለሚጠቀሙባቸው ስምምነት ተፈራርመዋል። 
ደቡብ አሜሪካ፡ - ፕሌት ወንዝ (Plate or La Plata) የሚባለው ብራዚልን፣ አርጀንቲናን፣ ፓራጉዋይን፣ ኡራጉዋይን፣ ቦሊቪያን ያስተሳስራል። ስለሆነም እነዚህ ሀገሮች በዚህ ወንዝ ውሀ አጠቃቀም ላይ የውል ስምምነት ተፈራርመዋል። - አማዞን ወንዝ (Amazon River) ፔሩን፣ ኢኳዶርን፣ ኮሎምቢያን እና ብራዚልን የሚያስተሳስር፣ በዓለም ከታወቁት ታላላቅ ወንዞች አንዱ ነው። የአማዞን ተፋሰስ ሀገሮች (በጆግራፊያዊ አቀማመጣቸው የተነሳ) ከሚፈልጉት በላይ ከዓመት እስከ ዓመት ዝናም ያገኛሉ። ስለሆነም የመስኖ ውሀ አያስፈልጋቸውም። የገንዘቡን አቅም ካገኙት ከአማዞን ገባር ወንዞች ለኃይል ማመንጫ የሚሆኑ ግድቦች ሊገድቡ ይችላሉ። ስለዚህ በአማዞን ተፋሰስ ውስጥ ከላይ እስከታች ውሀ እንደልብ ስለሚገኝ የውሀ ክፍፍል ውል አልተፈራረሙም። በአማዞን ተፋሰስ ውስጥ ያለው ችግር የድንግል ጫካዎች አጠባበቅና አያያዝ ጉዳይ ነው። ወደዚያ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባም።
 እስያ፡
- ኢንዱስ ወንዝ (Indus River) ፓኪስታንና ሕንድ በጋራ የሚጠቀሙበት ወንዝ ስለሆነ ሁለቱ ሀገሮች በዚሁ ወንዝ አጠቃቀም ላይ ውል ተፈራርመዋል። - ሜኮንግ ወንዝ (Mekong River) ቻይናን፣ ካምቦዲያን፣ ላዎስን፣ ታይላንድንና ቪየትናምን ያስተሳስራል። ስለሆነም ከቻይና በስተቀር ሌሎቹ የሜኮንግ ተፋሰስ ሀገሮች የውል ስምምነት ተፈራርመዋል። - ቲግሪስና ዩፍራጥስ (Tigris and Euphrates) ቱርክን፣ ሲሪያንና ኢራቅን ያስተሳስራል። ቱርክ የሁለቱም ወንዞች መነሻ ነው። ሲሪያ ከዩፍራጥስ ወንዝ ወገብ (መካከል) ላይ ነች። ኢራቅ ደግሞ ሁለቱ ወንዞች ተገናኝተው ከሚወርዱበት ዝቅተኛው፣ ደልዳላውና በረኻማው ክፍል ላይ ይገኛል። በዩፍራጥስ ወንዝ ላይ በሲሪያና በቱርክ መካከል ለብቻ አንድ ስምምነት ተደርጓል። በሲሪያና በኢራቅ መካከል ደግሞ ሌላ ስምምነት ተደርጓል። በኢራቅና በቱርክ መካከል ግን የተደረገ ስምምነት የለም።
አንባቢዎቼ ዝርዝሩ ረዥም ነው። ለማስረጃ ያህል ይህ የሚበቃ ይመስለኛል። በዐባይ ወንዝ ላይ ግን (በ1929 ዓ.ም እና በ1959 ዓ.ም) ግብጽና ሱዳን ተፈራረሙ ከሚባለው ውል በስተቀር ሌላ ውል የለም። የግብጽ አቋም ግልጽ ነው። ደጋገምኩባችሁ እንጂ፣ የግብጽ አቋም የዐባይን ውሀ ከተፋሰሱ ሀገሮች ጋር ለመካፈል አልደራደርም ነው። 
ግብጽ ወደ ድርድር ለመቅረብ የማትፈልግበት ምክንያት ግልጽ ነው። አዲስ ድርድር ከተጀመረ ሚዛኑ ወደ ብቸኛ ተጠቃሚነቱ (sole acquired rights) ሳይሆን ይነስም ይብዛም ለሌሎቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮችም ድርሻ ይኑራቸው (equitable distribution) ወደሚለው ማድፋቱ አይቀርም። ሌሎቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ድርሻ ከተሰጣቸው፣ ግብጽና ሱዳን በብቸኝነት ሲጠቀሙበት የቆዩት የውሀ መጠን መቀነሱ የማይቀር ነው። ግብጽ አዲስ ድርድር የምትጠላውም ለዚህ ነው። ዘመን ከመቆጠሩ በፊት ጀምራ እስካሁን ድረስ ከሚገባት/ከድርሻዋ በላይ የዐባይን ወንዝ ስትጠቀም የኖረች ስለሆነች፣ ለአዲስ የውሀ አጠቃቀም ድርድር አልሰለፍም በማለት ጸንታለች። እናንተ ውሀ ሲጠማችሁ የወንዝ ውሀ በመዳፋችሁ ያለዚያም በእንስራና በቅል ቀድታችሁ ከመጠጣት በስተቀር ሌላ የውሀ አጠቃቀም ታሪክ የላችሁምና፣ ከዚያ የተለየ አዲስ አመል አታምጡ ማለቷ ይመስላል። 
አንባቢዎቼ፣ የውሀ አጠቃቀም በጥንታዊነትና በታሪክ ቢሆንማ ኑሮ፣ የትግሪስንና የዩፍራጥስን ወንዝ የጥንቱ ሜሶፓታሚያ ስልጣኔ ምንጭና እምብርት የሆነቺው ኢራቅ ብቻ ትጠቀምበት ነበር። የውሀ አጠቃቀም ግን ከታሪክና ከጥንታዊነት ጋር ሳይሆን ከኢኮኖሚ ጥንካሬና ከኃይል ሚዛን ጋር ወይም ከአቅም ጋር የሚሄድ ስለሆነ፣ የቲግሪስና የዩፍራጥስ ውሀ ባለ ሙሉ መብት ተጠቃሚ ቱርክ ሁናለች። 
ቱርክ 1.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማትና የውሀ ኃይልም ለማመንጨት፣ አናቶሊያ ግድብ (Anatolia Dam) የሚባል በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ትልቅ ግድብ ስትገነባ፣ ሲሪያና ኢራቅ8 ተቃውመው ነበር። በ1992 ዓ.ም የቱርክ ፕሬዚደንት የነበሩት ሱሌማን ደሚረል (Suleiman Demirel) “በሳውዲ አረቢያ የነዳጅ ሀብት ማንም ጣልቃ እንደማይገባ ሁሉ፣ በቱርክ የውሀ ሀብትም ማንም ጣልቃ ሊገባ አይችልም፣ የፈለግነውን እናደርግበታለን” በማለት በሀገራቸው ድምበር ውስጥ የሚገኘው የዩፍራጥስ ወንዝ ውሀ ብቸኛ ባለሙሉ መብት መሆናቸውን ተናገሩ። 
ግብጽ ኢትዮጵያን ለማዳከም ለረዢም ጊዜ ስታደርገው እንደኖረቺው ሁሉ፣  ሲሪያም የቱርክን ኢኮኖሚ ለማዳከምና የግድቡን ስራ ለማደናቀፍ ስትል፣ የኩርድ ሽምቅ ተዋጊዎችን (Kurdish guerrilla fighters) እያሰለጠነች ወደቱርክ ማስገባትና ፀጥታ ማደፍረስ ጀምራ ነበር። ይህንን የሲሪያን ተንኮል የተገነዘበቺው ቱርክ የጦር ሠራዊቷን አንቀሳቅሳ ሲሪያ ድምበር ላይ ስታሰፍር፣ ሲሪያ (ቱርክን የመቋቋም ወታደራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አቅም/ጥንካሬ ስላልነበራት) አንገቷን ደፍታ ቁጭ አለች። ቱርክም “በሀገሯ ክልል ውስጥ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት የወንዙን ውሀ ጭምር ያለማንም ፈቃድ ሙሉ በሙሉ መጠቀም ትችላለች” የሚል ዛቻ ስታሰማ ከቆየች በኋላ፣ በ1987 ዓ.ም በሲሪያ የውሀ ባለመብትነት ሳይሆን፣ በቱርክ ሰብአዊነት ወይም በርኅራሄ፣ ለሲሪያ በየሰከንዱ 500 ሜትር ኩብ (cumsec) ውሀ የምትለቅ መሆኑን ገለጸች። ሲሪያም በተራዋ ቱርክ ‘በርኅራሄ’ ከምትለቅላት የዩፍራጥስ ውሀ ሀምሳ ስምንት ከመቶ (58%) የሚሆነውን ለኢራቅ እንደምታስተላልፍ ገለጸች። ይህ ታዲያ የኃይል ሚዛንን ነው እሚያሳየው? ወይስ ጥንታዊ ተጠቃሚነትን? በጥንታዊ ተጠቃሚነት ቢሆንማ ኑሮ፣ ከላይ እንዳልኩት፣ የቲግሪስና የዩፍራጥስ ወንዝ ዋና ተጠቃሚ መሆን የነበረባት ኢራቅ ነበረች። 
በንጹሕ ኅሊና እንደምናስበው ቢሆን ኑሮ፣ የዮርዳኖስን ወንዝ ሲሪያ፣ ሌባኖስ፣ ጆርዳን፣ ፍልስጤምና እስራኤል ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ተከፋፍለው ሊጠቀሙበት ይገባ ነበር። ነገር ግን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ዋናዋ ተጠቃሚ (በአሜሪካ ተገንነት የምትተማመነው ባለጡንቻዋ) እስራአኤል ነች። እስራኤል ከሚገባት በላይ የወንዙ ተጠቃሚ ሁናለች በማለት (ሲሪያ) ከዮርዳኖስ ገባር ወንዞች መካከል ትልቅ ከሚባለው ያርሙክ ወንዝ (Yarmouk River) ውሀ ጠልፋ ለመስኖ ለመጠቀም ስትሞክር፣ ለመስኖ ውሀ መጥለፊያ የገነባቺውን ግድብ እስራኤል በቦምብ ደብድባ አፈራርሳባታለች።
በ1975 ዓ.ም ሕንድ ጋንጀስ ወንዝ (Ganges River) ላይ ፋራቃ (Farrakka Barrage) የሚባል ግድብ ገደበች። የግድቡ ዓላማ በበጋ/በደረቅ ጊዜ ከትልቁ ጋንጀስ ወንዝ ውሀ ተጠልፎ ሁግሊ (Hoogli River) ወደሚባለው አንስተኛ ወንዝ እንዲቀላቀልና የወንዙ ውሀ፣ ብክለት የሚበዛበትን የካልከታን ወደብ እንዲያጸዳው፣ ወይም ደለሉንና ቁሻሻውን አጣጥቦ ወደሕንድ ውቅያኖስ እንዲወስደው ለማድረግ ነበር። ነገር ግን ይህ ጋንጀስ ወንዝ ላይ የተገደበ (ፋራቃ (Farrakka) የተሰኘ) ግድብ ከታች በኩል ሩዝ አምራች የሆኑትን የባንግላዲሽ ገበሬዎች ውሀ አስቀረባቸው። በዚህም የተነሳ ባንግላዲሾች እስከ 1977 ዓ.ም ችግሩን ከሕንድ ጋር በድርድር ለመፍታት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። ከሕንድ ጋር የመፎካከር አቅም ስለሌላቸው፣ አድማጭ አጥተው፣ አንጀታቸው እያረረ ጥቃታቸውን ‘ተቀብለው’ ይኖራሉ። ሕንድም እንዳሰበቺው በበጋ ጊዜ ከጋንጀስ ወንዝ እየጠለፈች (ጸድቶ እማይጸዳ ወደቧን) ካልከታን ታጸዳለች። 
ቻይና ሜኮንግ (Mekong River) በተሰኘው ወንዝ ደጋማው ክፍል ላይ ትልቅ የኃይል ማመንጫ ግድብ ስትገድብ የታችኞቹን ሀገሮች (ካምቦዲያን፣ ላዎስን፣ ታይላንድን፣ ቪዬትናምን) አላማከረችም፣ አላሳወቀችም። በራሷ የግል ውሳኔ ብቻ ሜኮንግ ወንዝ ላይ ትልቅ ግድብ ገድባለች። 
አንባቢዎቼን ያሰለቻል እንጂ በደቡብ አሜሪካም ሌሎች ምሳሌዎችን መጨማመር ይቻል ነበር። ኃይል ያለው የፈለገውን ማድረግ እንደሚችል፣ ደካማው ጥቃት ቢደርስበትም አድማጭ/ተቆርቋሪ እንደማያገኝ ለማሳየት ያህል ያቀረብኳቸው ምሳሌዎች የሚበቁ ይመስለኛል። የዓለም አቀፍ ሕግ ኮሚሽን (International Law Commission) ደምብ፣ አንድ የተፋሰስ ሀገር ሌሎች ሀገሮች በሚጋሩት ወንዝ ላይ ፕሮጀክት የሚነድፍ ከሆነ ለሚመለከታቸው የተፋሰሱ ሀገሮች ማሳወቅ ይገባዋል የሚል ቢሆንም፣ የተፋሰሱ ሀገሮች የኃይል ሚዛን/አቅም ከሞላ ጐደል ተመጣጣኝ ካልሆነ ተፈጻሚነት ወይም ተግባራዊነት እንደማይኖረው ያቀረብኳቸው ምሳሌዎች ያሳያሉ። ተጨባጩ ሁኔታ እንደሚያሳየን ከሆነ የድምበር አቋራጭ ወንዞችን አጠቃቀም አስመልክተው የወጡ ዓለም አቀፍ ሕግጋት ብቻቸውን ፋይዳ የላቸውም፣ አይሰሩም። ፋይዳ የሚኖራቸውና የሚሰሩ የሚመስሉት የኃይል ሚዛን/አቅም ሲጨመርባቸው ብቻ ነው። 
የወንዝ ተጠቃሚዎቹ ሀገሮች የኃይል ሚዛን ከሞላ ጐደል ተመጣጣኝ በሚሆንበት ጊዜ የውሀ አጠቃቀሙም ከሞላ ጐደል ተመጣጣኝ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል የኢንዱስን ወንዝ (Indus River) አጠቃቀም በሚመለከት ሕንድና ፓኪስታን (ሁለቱም ባለኒዩክሊየር ሀገሮች በመሆናቸው ይመስላል) በዓለም ባንክ አደራዳሪነት፣ የኢንዱስን ወንዝ ገባር ወንዞችም ሆነ የዋናውን ኢንዱስ ወንዝ እኩል ተካፍለው ለመጠቀም በ1960 ዓ.ም ተፈራርመዋል። በዚያው ውል መሠረት እስካሁን ድረስ ወንዙን በጋራ ይጠቀሙበታል። በወንዙ አጠቃቀም የተነሳ ሕንድና ፓኪስታን ሲጋጩ ተሰምተው አያውቁም። ኔፓልና (Nepal) ባንግላዲሽ (Bangladesh) ግን የጋንጀስንና የብርሀማፑትራን (Brhamaputra River) ወንዞች ከሕንድ ጋር እንዴት እንደሚከፋፈሉ የተፈረመ ውል የለም። ሕንድ እንደፈለገች ብቻዋን ውሳኔ የምትወስን ዓይነተኛ ተጠቃሚ ነች። 
የዐባይን ወንዝ አጠቃቀም በተመለከተ ደግሞ ፈላጭ ቆራጯ ግብጽ ነች። ከ1970ዎቹ ጀምራ የተፋሰሱን ሀገሮች ሳታማክር በዐባይ ውሀ (በቱቦ ሱዊዝ ካናልን አሻግራ የሰላም ካናል /”Peace Canal” የተባለ ትልቅ ቦይ/ ካናል በመቅደድ) ሲናይ (Sinai) ውስጥ ሕዝብ ለማስፈርና የመስኖ ልማት ለማስፋፋት የያዘቺውን እቅድ በመከታተል ላይ ነች። ይህ ግዙፍ እቅድ የሲናይን በረሃ ለማልማት ብቻ ሳይሆን፣ ለእስራኤል ውሀ ለመሸጥም ጭምር የተወጠነ ፕሮጀክት እንደሆነ ይታማል።  
ይህ እንደተሰማ፣ ሀ) ግብጽ የዐባይን ወንዝ ከተፈጥሮ ተፋሰሱ ውጪ በቱቦና በካናል ስባ ልትወስድና ልትጠቀም አይገባትም፣ ለ) የግብጽ እርምጃ ሌሎቹን የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ሳታሳውቅ በግል ብቻዋን የወሰነቺው ነውና አግባብ አይደለም በማለት ኢትዮጵያ ተቃውማ ነበር። ተቃውሞዋን ጆሮ የሰጠው፣ ያዳመጠው የለም። ከግብጽ ባለስልጣኖችም የተሰጠው መልስ “ከተፋሰሱ የመጨረሻ ታችኛ ስለሆንን የማሳወቅ ግዴታ የለብንም” የሚል ነው። ግብጾች ይህን የሚሉት ያለምክንያት አይደለም። ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ብድር በመስጠት ተጽእኖ በማሳደር የማይናቅ ሚና የሚጫወተው የዓለም ባንክ፣ የተፋሰሶችን ላይኛ ሀገሮች ፕሮጀክት ሲወጥኑ ለተፋሰሱ ታችኛ ሀገሮች ማሳወቅ እንዳለባቸው ሲደነግግ፣ የታችኞች ሀገሮች ግን ለላይኞች ሀገሮች እንዲያሳውቁ ግዴታ አልጣለባቸውም።  
በዚህ የሰላም
ካናል /”Peace Canal” ላይ ኢትዮጵያ ለሰነዘረቺው ተቃውሞ ግብጾች ሲያፌዙ/ሲያሾፉ “የዐባይ ወንዝ በጥንት ጊዜ ሲናይ ድረስ ይፈስ ስለነበር የሰላም ካናል ፕሮጀክታችን ከወንዙ የተፈጥሮ ተፋሰስ ውጪ አይደለም” ይላሉ። የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች የጅኦሎጂ እውቀት ውሱን ሁኖ ነው እንጂ፣ ከብዙ ሚሊዮን ዓመታት በፊትማ ዐባይ አዋሽ በሚፈስበት አቅጣጫ ይፈስ ስለነበር ኢትዮጵያ የዐባይን ወንዝ አቅጣጫ ወደ አዋሽ ወንዝ ትቀይራለች በማለት ፌዙን በፌዝ መመለስ ነበረባቸው። 
ከዚህም በተጨማሪ፣ ግብጽ ውስጥ ከዐባይ ሸለቆ በስተምእራብ በኩል የሚገኙትን የበረሃ ገነቶች (oases) በዐባይ ውሀ ሊያለሙ መዘጋጀታቸውን ፕሬዚደንት ሙባረክ በ1996 ዓ.ም ይፋ አድርገዋል። ይህ ፕሮጀክት የአዲሱ ሸለቆ ፕሮጀክት (New Valley Project or Toshka Project) ወይም ቶሽካ ፕሮጀክት በመባል ይታወቃል። የአስዋን ግድብ ከመጠን በላይ በሚሞላበት ጊዜ ትርፉን ውሃ ለማፍሰስ (spill way) የሚረዳ ነው ብለው ከግድቡ መኻል ወገብ ላይ ወደምእራብ አቅጣጫ ቶሽካ (Toshka) በሚል መጠሪያ የሚታወቅ የውሀ መሄጃ ቆፍረው ነበር። ያንን አስፋፍተው ወደ ውሀ ማጠራቀሚያነት በመለወጥ ከዐባይ ወንዝ በስተምእራብ 70 ኪሎ ሜትር ርቆ እስከሚገኘው የበረሃ ገነት ድረስ የመስኖ እርሻ ለማስፋፋት ማቀዳቸውን ገልጸዋል። በዚህ እቅድ በያመቱ ካስዋን ግድብ 5 (አምስት) ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ እየጠለፉ 200,000 (ሁለት መቶ ሺህ) ሄክታር መሬት ሊያለሙ ማቀዳቸው ታውቋል። ይህ የልማት እቅድ በዐባይ ሸለቆ ዳርና ዳር ተጣ(ብ)ቦ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል 7 (ሰባት) ሚሊዮን ሰው ተቀንሶ ባዲሱ የልማት ሸለቆ እንዲሰፍር ታቅዷል። ይህ ፕሮጀክት ቀስ በቀስ የሚካሄድና በሃያ ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ነው። ይህ የግብጽ የግል ውሳኔ (በ1997? ዓ.ም) ይፋ ሲደረግ፣ የወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (ስዩም መስፍን) ለዓለም ባንክ ፕሬዝደንት (James Wolfensohn)፣ ለተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሐፊ (Kofi Annan)፣ ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጽሐፊ (Salim Ahmed Salim) ተቃውሟቸውን በደብዳቤ ገልጸዋል። አቶ ስዩም መስፍን ተቃውሟቸውን ካስመዘገቡ ካንድ ዓመት በኋላ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር (አቶ ተቀዳ ዓለሙ) የ1959ኙ የሱዳንና የግብጽ ስምምነት እንዲሰረዝ በአፍሪካ አንድነት ስብሰባ ላይ ጥሪ አቅርበዋል። 
ነገር ግን የኢትዮጵያ ተቃውሞ እስካሁን ድረስ ያስከተለው/ያሳየው ውጤት የለም። የዐባይን ወንዝ አጠቃቀም በተመለከተ ኢትዮጵያ ባገኘቺው መድረክ ሁሉ ተቃውሞዋን ከመግለጽ ተቆጥባ አታውቅም። ግን ባዶ ተቃውሞ ነው። ተቃውሟቸውን በተግባር ሲገልጹ፣ በተለያየ ጊዜ (ከኃይለ ሥላሴ ጀምሮ እስካሁን ድረስ) በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ ባስጠኗቸው ፕሮጀክቶች ላይ ስራ በመጀመር ባለመብትነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሞክሩ ታይተው አይታወቁም። እንዲያውም አድማጮች “ዐባይ በተነሳ ቁጥር ኢትዮጵያዊያን” ተቃውሞ ማቅረብ ልማዳቸው ነው” ሳይሏቸው አይቀሩም። ባዶ ተቃውሞ፣ ጉልበት የለሽ ተቃውሞ፣ አቅም የለሽ ተቃውሞ ሰሚ የለውም። አቅመ ደካማ አቅሙን ገምብቶ የራሱን ማንነት ካላሳየ/ካላስመሰከረ በስተቀር ጩኸቱ አድማጭ አያገኝም። 
ኢትዮጵያ አቅሟን ሳትገነባ (ባቅመ ደካማነቷ) እኔም ባለመብት ነኝና በዐባይ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ በምትልበት ጊዜ ከግብጽ የሚሰነዘረውን ተቃውሞ በሚገባ ልናጤነው ይገባል። ከውግዘት ለመዳንና ጥፋተኛ ላለመምሰል፣ ከሆነላትም ዲፕሎማሲያዊና የሞራል ድጋፍ ለማግኘት፣ ግብጽ የዓለም አቀፍ ሕግጋትን አክባሪ መስላ ለመታየት ከመጣር አትቆጠብም። ይህንኑ የፓለቲካ ስራ በሚገባ ሊሰሩ የሚችሉ፣ ብዙ ልምድ ያካበቱ፣ የበሰሉ ፓለቲከኞች፣ ምሁሮች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ወ.ዘ.ተ. አሏት። ያም ሆኖ ግን ግብጽ የምትመካውና የምትተማመነው በዓለም አቀፍ ሕግጋት አይደለም። ግብጽ የምትመካው በጉልበቷ (በተፋሰሱ ውስጥ ባላት የኃይል ሚዛን) ነው። ግብጽ የምታቅደው እቅድ፣ የምትሰነዝረው ተቃውሞ፣ የምታቀርበው ሀሳብ አድማጭና ድጋፍ እሚያገኘው በተፋሰሱ ውስጥ ባላት አንጻራዊ ጥንካሬ (ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊ፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል)  ብቻ መሆኑን ጠንቅቃ ታውቃለች። 
አቅመ-ደካማዋ ኢትዮጵያማ እንግዳው፣ እኔም ወንዞቼን ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ እጠቀምባቸዋለሁ ባለች ቁጥር፣ ከግብጽ የሚሰነዘረው ተቃውሞ የጦርነት ማስፈራሪያ ነው። ጉዳዩ የአቅም ጉዳይ፣ የኃይል ሚዛን ጉዳይ ነውና፣ ያለግብጽ አወንታ የዐባይን ውሀ (የግብጽን ጥቅም በሚነካ መልኩ) ለመጠቀም የሚሞክር የዐባይ ተፋሰስ ሀገር ቢኖር፣ ሙከራው ወደጦርነት የሚያመራ እንደሚሆን የግብጽ ባለሥልጣኖች ደጋግመው አስጠንቅቀዋል። ይህ የተደጋገመ የጦርነት ዛቻ የሚሰነዘረው በተለይ በኢትዮጵያ ላይ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ “ኢትዮጵያ በእስራኤል ድጋፍ ዐባይ ላይ ግድብ ልትገድብ ነው” ከሚል ወሬ ተነስተው፣ የግብጽ ፕሬዝደንት የነበሩት አኑዋር ሳዳት፣ በ1979 ዓ.ም በግንቦት ወር (May 30) ባደረጉት ንግግር፣ ከዐባይ የምናገኘውን ውሀ ለመጠበቅ ስንል (ከኢትዮጵያ ጋር) ጦርነት እንከፍታለን ሲሉ ተናግረዋል። በዚያው ንግግራቸው ላይ የግብጽ ብቻ ሳይሆን የሱዳንም የውሀ አጠቃቀም (በኢትዮጵያ) ቢነካ ግብጽ ጦርነት ታስነሳለች፣ ምክንያቱም ሱዳን ስትነካ ግብጽም መነካቷ አይቀርምና በማለት ዝተዋል (J. Waterbury, 2002, 71)። በኋላም (በ1991 ዓ.ም) የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጽሐፊ የነበሩት ግብጻዊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ፣ ኢትዮጵያ የዐባይን ውሀ ከነካች “ጦርነት” የግድ ነው ብለዋል። ቡትሮስ ጋሊ የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች በውሀ ኮታ (ክፍፍሎሽ) ላይ ከሚነታረኩ ይልቅ፣ ከዐባይ ውሀ ሌላ አማራጮችን በማፈላለግ፣ ተፋሰሶችን በመንከባከብ፣ የምርምር ጥናቶችን በማጠናከር፣ በመጓጓዣ፣ በቱሪዝም፣ በጤና፣ በፀጥታ አጠባበቅ፣ ወ.ዘ.ተ. ላይ ቢያተኩሩና ቢተባበሩ የተሻለ ነው፣ አስተባባሪነቱንም ግብጽ ልትወስድ ትችላለች በማለት የተፋሰሱን የውሀ ድርሻ/የኮታ ጥያቄ ለማስወገድ ጥረት ያደርጉ ነበር።  
በ1995 ዓ.ም አዲስ አበባ ላይ የግብጽ ፕሬዝደንት በነበሩት በሆስኒ ሙባረክ ላይ በተቃጣው የግድያ ሙከራ የሱዳን እጅ አለበት በመባሉ ግብጽና ሱዳን ተቃቅረው ነበር። “ወንጀለኞቹን ለመያዝ በቂ ክትትል አላደረገችም” በሚል ግብጽ ኢትዮጵያንም ከሱዳን ጋር አብራ ስትወቅስ ነበር። በዚያ መቃቃር የተነሳ ባመት አራት ጊዜ በሚሰበሰበው (በሱዳንና በግብጽ በ1959 ዓ.ም በተቋቋመው) የቴክኒክ ኮሚሽን (Permanent Joint Technical Commission/PJTC) መደበኛ ስብሰባ ላይ ሱዳን ሳትገኝ ቀረች። ሱዳን ለስብሰባው ተሳታፊ አለመላኳ ብቻ ሳይሆን፣ የተፈጠረውን መቃቃር ምክንያት በማድረግ፣ “እንዲያውም ከነአካቴው ወደግብጽ የሚወርደውን የዐባይን ውሀ እቀንሰዋለሁ” የሚል ጉራ መንፋት ጀምራ ነበር። በዚያን ጊዜ (በ1995 ዓ.ም) የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አምር ሙሳ (Amr Musa) “የዐባይን ውሀ መነካካት ውጤቱ ጦርነት ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል። አሁንም በሕዳሴ ግድብ የተነሳ በግብጽ ባለስልጣኖች የሚሰነዘረው ማስፈራሪያ “ጦርነት” ነው።  
ባጭሩ ለማስቀመጥ ያህል ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ ላይ የሆነ ሀሳብ አስባለች፣ ውጥን ወጥናለች በተባለ ቁጥር ከግብጽ ባለስልጣኖች አፍ የሚወጣው ቃል “ጦርነት” ነው። ጦርነትን በማስፈራሪያነት በመጠቀም ከየትኛውም የተፋሰሱ ሀገሮች የተሻለ ኃይል እንዳላቸው ደጋግመው ከሚያስታውሱ በስተቀር፣ ግብጾች በዐባይ ወንዝ ውሀ አጠቃቀም ላይ መደራደር አይፈልጉም።
አንዳንዴ ሁኔታውን በጥሞና ስናስተውለው የሚደራደሩበት ምክንያት እንደሌላቸው እንገነዘባለን። ድርድር እኮ የሚመጣውና እውን ሊሆን የሚችለው በኃይል ሚዛን ተመጣጣኝ ሁኖ ሲገኙ ብቻ ነው። ሩቅ ሳንሄድ ታህት፣ የኤርትራ ነፃ አውጭ ግምባር እና የኦሮሞ ነፃ አውጭ ግምባር ባንድነት ተሰልፈው አቅማቸውን ባያጠናክሩ ኑሮ በኸርማን ኮኸን ‘ሸምጋይነት’ ሎንዶን ላይ ከደርግ ጋር ለድርድር መሰለፍ ይችሉ ነበር? ወይም በተቃራኒው ደርግ አቅም ባያጣ ኑሮ ከነታህት ጋር ለድርድር ይቀርባል ተብሎ ይታሰብ ነበር? አይታሰብም። ደካማና ኃይለኛ እንዴት ሁነው በእኩልነት ይደራደራሉ? አይደራደሩም። ለድርድር ቢቀርቡም እንኳን ድርድሩ መሳ ለመሳ የሚካሄድ አይሆንም። ድርድሩ የሚካሄደው ኃይለኛውና ጉልበተኛው በሚፈልገው አቅጣጫ ነው። የኃይለኛው ፍላጐት ተፈጻሚነት ሲያገኝ፣ የደካማው ድምጽ አድማጭ ሲያጣ ነው ስንታዘብ የኖርነው። በተለይ በፖለቲካው ዓለም ይህ የማይታበል ሀቅ ነው።  
4. የላይኛው ዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች አቅምና የትብብር ተስፋ የላይኛው ዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች በሙሉ አቅመቢሶች ስለሆኑ ከግብጽ ጋር
( በ ኢ ኮ ኖ ሚ ፣ በ ወ ታ ደ ራ ዊ ኃ ይ ል ፣ በ ተ ማ ረ ና
በሰለጠነ የሰው ኃይል) በእኩልነት ሊሰለፉ የማይችሉ፣ ለግብጽ ዓይን የማይሞሉ ደካሞች ናቸው። ዩጋንዳ? ኬንያ? ታንዛኒያ? ኤርትራ? ሩዋንዳ? ቡሩንዲ? ኮንጐ? ኢትዮጵያ? ከነዚህ ሀገሮች መካከል ግብጽን የመመዘን አቅም ያለው ሀገር የትኛው ነው? መልሱ ግልጽ ይመስለኛል። የትኛቸውም ሚዛን የሚደፉ አይደሉም። ስልጣን ለመጨበጥ ሲሉ ለዘመናት እርስ በርሳቸው (በጐሳ፣ በዘውግ፣ በምን? -----) ሲጨፋጨፉና ሲገለባበጡ፣ በኢኮኖሚ ግምባታ፣ በወታደራዊ ድርጅትና በሰለጠነ የሰው ኃይል ወደኋላ የቀሩ፣ አንዳንዶቹም ከወደቁበት ለመነሳት ያልቻሉ፣ ገና በመንፈራፈር ላይ ያሉ ናቸው። በዚሁ የስልጣን አያያዝና ተቃዋሚ ቡድኖችን በማስጠጋት የተነሳ እስካሁን ድረስ ሩዋንዳ ከኮንጐ ጋር፣ ኮንጐ ከዩጋንዳ ጋር፣ ዩጋንዳ ከሱዳንና ከሩዋንዳ ጋር ከመናቆር ያልተቆጠቡ ናቸው። ስለዚህ አንድ ጠንካራ ግምባር ፈጥረው ግብጽ ለአዲስ ድርድር እንድትሰለፍ አስገዳጅ ሁኔታ የሚፈጥሩ አይደሉም። 
ከዚህም በተጨማሪ ዐባይን በተመለከተ የሁሉም የተፋሰሱ ሀገሮች ችግር፣ አንድ ወጥ ያልሆነና እኩል ክብደት የሌለው ስለሆነ፣ የግብጽን እብሪት ለማርገብ እስካሁን ድረስ አንድ ህብረት ወይም ግምባር አልፈጠሩም። ቢፈጥሩም በችግሮቻቸው መለያየትና በመካከላቸው በየጊዜው በሚፈጠረው ፖለቲካዊ ፍትጊያ የተነሳ የሚፈጥሩት ህብረትና ግምባር ጠንካራ ይሆናል የሚል እምነት የለም። የዐባይን ውሀ አጠቃቀም በተመለከተ፣ ችግራቸውና ፍላጐታቸው የተለያየ መሆኑን ለማየት እንድንችል ባጭር ባጭሩ እንደሚከተለው አቅርቤዋለሁ። 
1. ኮንጐ፡ አብዛኞቹ ወንዞቿ ወደራሷ ክልል የሚፈስሱ ናቸው። የገንዘብ አቅሙ ካላቸው የፈለጉትን የኃይል ማመንጫ ግድብ በፈለጉት መጠን መገንባት ይችላሉ። ሞቡቱ ሴሴሴኮ “ኢንጋ” የተባለውን ትልቅ ግድብ በኮንጐ ወንዝ ላይ ሲሰሩ፣ (ወንዙም ግድቡም ከኮንጐ ድምበር ውስጥ ስለሆኑ) ከየትኛውም ሀገር ጋር አላጋጫቸውም። እንዲያውም ኮንጐ ብዙ ኃይል ሊያመነጭ የሚችል የውሀ ኃይል ስላላት፣ በ1989 ከግብጽ ጋር ተነጋግራ (ተሻርካ) ለምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች፣ ለሱዳን፣ ለግብጽ፣ ለቱርክና ለደቡብ አውሮፓ ሀገሮች የውሀ ኃይል ለመሸጥ አስባ ነበር። ይህንንም ሀሳብ ግብጽ ትደግፈው ስለነበር ኮንጐና ግብጽ የቅርብ ወዳጆች እንጂ በዐባይ የተነሳ የሚፎካከሩ አይደሉም። 
2. ዩጋንዳ፡ ነጭ ዐባይ ከሚወጣበት ከቪክቶሪያ ሀይቅ ጫፍ፣ ጂንጃ (Jinja) ከሚባለው ቦታ ላይ ከሚገኘው ኦውን (Owen Falls) ፏፏቴ ላይ ኦውን የሚባል(Owen Dam) ግድብ ገድባ በቂ የኤሌትሪክ ኃይል ታገኛለች። እንዲያውም ከራሷ አልፋ ተርፋ የኤሌትሪክ ኃይል ለኬንያ ትሸጣለች። ዩጋንዳ ይህን ግድብ (ኦውን ግድብ) በመገደቧ ከግብጽ ተቃውሞ አልተሰነዘረባትም። እንዲያውም ከግብጽ ድጋፍ ታገኛለች። በ1947 ዓ.ም ቅኝ ገዢዎች በነበሩት እንግሊዞች አስተናባሪነት፣ ዩጋንዳዊያን የኦውንን ግድብ በአንድ ሜትር ከፍ ቢያደርጉ፣ ግብጽ ለዩጋንዳ አንድ ሚሊዮን ስተርሊንግ ፓውንድ (£1,000,000) እንደምትከፍል ተስማምታለች። ክፍያውም ያንዴ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት እንደሚኖረው ተዋውለዋል። ግብጽ ይህን ውል የተዋዋለችበት ምክንያት፣ በሱዳንና በግብጽ በረሃ በትነት የሚባክነውን ውሀ ለመቀነስ፣ ማለትም የቪክቶሪያን ሀይቅ እንደ ውሀ ማጠራቀሚያ ገንዳ አርጋ ለመጠቀም ስለፈለገች ነው። የዩጋንዳ ምድር አብዛኛው ከዓመት እስከ ዓመት በቂ የዝናም መጠን የሚያገኝ ስለሆነ ዩጋንዳዎች የዐባይን ውሀ ለመስኖ ስራ አይጠቀሙበትም፣ አይፈልጉትም። ስለዚህ ከዐባይ የሚያጡት ጥቅም የለም። በዚህም ምክንያት ዩጋንዳዊያን ዐባይን በተመለከተ (ከግብጽና ከሱዳን መገላገያ ለማግኘት ያህል አንዳንዴ ከሚያንገራግሩ በስተቀር) ብዙውን ጊዜ ገለልተኞች ናቸው። 
3. ኬንያ፡ ከኬንያ ምእራባዊ ከፍተኛ ቦታዎች (Western Highlands) ተነስተው ወደ ቪክቶሪያ ሀይቅ የሚገቡ አጫጭር ወንዞች አሉ። እነዚህ ወንዞች የረባ የኤሌትሪክ ኃይል ሊያመነጩ የሚችሉ አይደሉም። በነዚህ ወንዞች ምክንያትም ኬንያዊያን ቀረብን የሚሉት ጥቅም የለም። ይሁን እንጂ የቪክቶሪያ ሀይቅ እሩቡ (1/4th) ያህል በኬንያ ክልል/ድምበር ውስጥ ነውና፣ ከቪክቶሪያ ሀይቅ ውሀ ጠልፈን ለመስኖ መጠቀም እንፈልጋለን ብለው ሱዳንንና ግብጽን፣ ዩጋንዳንም ጭምር ማስፈራራት ይችላሉ። ዩጋንዳ የምትፈራበት ምክንያት የውሀ ኃይል የምታመነጭበት ግድብ ውሀው የቪክቶሪያ ሀይቅ ስለሆነ፣ የቪክቶሪያ ሀይቅ ሲቀንስ የግድቡ ውሀ ስለሚቀንስባት ነው። ያም ሆነ ይህ እስካሁን እንደታየው ኬንያዊያን በሽምግልና ከሚሰለፉ በስተቀር የዐባይ ውሀ አጠቃቀም እምብዛም ደንታ አይሰጣቸውም።
4. ሩዋንዳና ቡሩንዲ፡ ከሩዋንዳና ከቡሩንዲ ተራራማ ቦታዎች ተነስተው ወደቪክቶሪያ ሀይቅ የሚገቡ ወንዞች አሉ። ወደቪክቶሪያ ሀይቅ ከሚገቡት ወንዞች መካከል ትልቁ ከሩዋንዳ ከፍተኛ ቦታዎች የሚነሳው ካጌራ (Kagera River) የሚባለው ወንዝ ነው። ሩዋንዳና ቡሩንዲ ካመት እስካመት በቂ ዝናም የሚያገኙ ሀገሮች ስለሆኑ የካጌራንና የሌሎቹንም ወንዞች ለመስኖ የመጠቀም ፍላጐት የላቸውም። ይሁን እንጂ ኃይል ለማመንጨት የካጌራን ወንዝ ለመገደብ የተጠና ጥናት አላቸው። ገንዘቡ ተገኝቶ የካጌራ ወንዝ ለኃይል ማመንጫ ቢገደብም ሱዳንንና ግብጽን ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም። ምክንያቱም፣ ሀ) የኃይል ማመንጫ ግድብ ስለሆነ ወደቪክቶሪያ ሀይቅ የሚገባውን የውሀ መጠን አይለውጠውም፣ ለ) የኃይል ማመንጫው ግድብ በዝናማማውና በደጋማው አካባቢ ስለሆነ (ወደ ሱዳንና ወደ ግብጽ ሲደርስ) በትነት መልክ የሚባክነውን ውሀ ይቆጥባል። ሩዋንዳና ቡሩንዲም በዐባይ ውሀ ክፍፍል ላይ ከመነታረክ ይልቅ፣ የካጌራን ወንዝ ለመጠቀም ከሌሎች አጐራባች ሀገሮች ጋር በጣምራ መስራት ይሻላል በሚል ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቡሩንዲና ዩጋንዳ በአባልነት የሚገኙበት የካጌራ ሸለቆ ድርጅት (Kagera Basin Organization) የተሰኘ ድርጅት አቋቁመው የድርጅቱ አባል ሀገሮች የጋራ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ብልሀት በማፈላለግ ላይ ናቸው። ስለዚህ የግብጽን እብሪት ለመግታት ከኢትዮጵያና ከሌሎቹ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ጋር ህብረት ለመፍጠር የሚገፋፋቸው ችግር የለም።
5. ታንዛኒያ፡ አብዛኛው (2/3 ያህል) የቪክቶሪያ ሀይቅ በታንዛኒያ ክልል ውስጥ ነው። ታንዛኒያ (የጀርመን ቅኝ ግዛት በነበረችበት ጊዜ) በቅኝ ገዢዎቿ አማካይነት የቪክቶሪያን ሀይቅ ውሀ ጠልፋ በቦይ (canal) ወደ መሀል ታንዛኒያ በመውሰድ የመስኖ እርሻ ለማስፋፋት አቅዳ ነበር። ግብጽም ያንን የድሮ ቅኝ ገዢዎች ጅምር ስለምታውቅ፣ በንቃት በዓይነ ቁራኛ የምትከታተለው (ከኢትዮጵያ ቀጥላ) ታንዛኒያን ነው። ያንን የቅኝ ገዢዎች ውጥን እገፋበታለሁ ካለች፣ የቪክቶሪያን ሀይቅ ውሀ፣ ብሎም ወደ ዐባይ የሚገባውን ውሀ በጣም የሚቀንስ/የሚያዛባ ስለሚሆን፣ የግብጽን ብቻ ሳይሆን የነጭ ዐባይን ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ ቀልብ የሚስብ ይሆናል። እስካሁን ግን የግብጽን ትዕቢትና ለትብብር አለመዘጋጀት እያስተዋለች ግብጽን ከምትተች በስተቀር፣ ግብጽን ስጋት ላይ የሚጥል ፕሮጀክት አልወጠነችም። የጥንቱን ውጥኗንም አልቀሰቀሰችም።
6. የቪክቶሪያ ገበቴ ሀገሮች ተሰባስበው
የቪክቶሪያ ገበቴ ቡድን (Lake Victoria Basin Group) የተሰኘ ድርጅት አቋቁመዋል። የተቋቋመው ቡድን አትኩሮቱ በሀይቁ አጠቃቀምና አጠባበቅ ላይ እንጂ፣ ከሱዳንና ከግብጽ ጋር በቀጥታ የሚያነካካ አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ ቡድኑ የሚያተኩረው በቪክቶሪያ ሀይቅ ላይ በሚንሳፈፈው ቅጠል/አረም (water hyacinth)፣ በሀይቁ ብክለት (pollution)፣ በሀይቁ ላይ ስለሚካሄደው የአሳ ማጥመድ ጉዳይና በሀይቁ የመጓጓዣ ጉዳይ ላይ ነው። 
ባጭሩ ለማጠቃለል ያህል የምስራቅ አፍሪካ (የዐባይ ተፋሰስ) ሀገሮች በግብጽና በሱዳን የውሀ ድርሻ ላይ ህብረት/ግምባር የሚያስፈጥር ጥብቅ ችግር የለባቸውም ማለት ይቻላል። ፊታቸውን ወደ ሶቪየት ኅብረት ያዞሩትን የግብጹን ገማል አብደል ናስርንና የሱዳኑን ጀኔራል አቡድን ቂም ለመወጣት ብለው፣ እንግሊዞች (ከ1959 ዓ.ም እስከ 1961 ዓ.ም ድረስ) የምስራቅ አፍሪካ የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ግምባር (ኅብረት) እንዲፈጥሩ ለማስተባበር ሞክረው ነበር፣ ግን አልተሳካላቸውም። ከእንግሊዞቹ ጅምር በመነሳት የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ያለባቸውን ትንሽ የመቆጨት አዝማሚያ በመጠቀም ግምባር እንዲፈጥሩ በማግባባቱ፣ በመቀስቀሱና በመጐትጐቱ በኩል መታገል የነበረባት ኢትዮጵያ ነበረች። አቅም (የኢኮኖሚም ሆነ የተማረና የሰለጠነ ሰው) የላትምና፣ በአቅመቢስነቷም የተነሳ ተደማጭነት የላትምና አላደረገቺውም። ኢትዮጵያ የማስተባበር አቅም እንደሌላትም ግብጾች ጠንቅቀው የሚያውቁ ይመስለኛል። 
ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት እነዚህ የምስራቅ አፍሪካ/የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች፣ ሀ) ለግብጽ ዓይን የማይሞሉ (በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በጦር ኃይል) ደካሞች ናቸው። የዐባይን ችግር በሰላማዊ መልክ በድርድር ካልፈታሁ፣ ያለኔ ተሳትፎ የራሳቸውን እርምጃ ይወስዳሉ የሚባሉ አይደሉም። ለ) አብዛኞቻቸው የዐባይ ወንዝ ውሀ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ ስለማይነካቸው አይቆረቁራቸውም። ከግብጽና ከሱዳን ጋር የሚያፋጥጥ ጉዳት አልደረሰባቸውም። 
በግብጽ በኩልም ሲታይ፣ እነዚህ ሁሉ ሀገሮች ተደማምረው ለግብጽ ከሚደርሰው የዐባይ ውሀ ከ5% እስከ 14% ብቻ ነው አስተዋጽኦ የሚያደርጉት። ስለዚህ ግብጽ ከምስራቅ አፍሪካ (የዐባይ ተፋሰስ) ሀገሮች የምታገኘው የውሀ ድርሻ ከፍ እንዲልላት፣ ወዳጅነት እየፈጠረች (ለምሳሌ፣ የዩጋንዳዎችን ግድብ ከፍታ በመጨመር፣ የአልበርትን ሀይቅ በማስገደብ፣ ወደ ሱድ ረግረግ የሚሄደውን የነጭ ዐባይ ውሀ እንደ ጆንገሌይ ቦይ በመሳሰሉት) ከነጭ ዐባይ ተጨማሪ ውሀ ለማግኘት ከምትጥር በስተቀር፣ በቀንደኛ ባለጋራነት የምትሰለፍበት ጉዳይ የላትም።  
5. የግብጽ አትኩሮት በኢትዮጵያ ላይ ከሁሉም የተፋሰሱ ሀገሮች የበለጠ ግብጽ እምታተኩረው ኢትዮጵያ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከላይ ከዘረዘርኳቸው የምስራቅና የመካከለኛው አፍሪካ (የዐባይ ተፋሰስ) ሀገሮች በጣም የተለየ ነው። ኢትዮጵያ እንደሌሎቹ የዐባይ (ላይኛው) ተፋሰስ ሀገሮች ሁሉ አቅመ ደካማ ብትሆንም፣ ለግብጽና ለሱዳን የምታበረክተው የውሀ መጠን በጣም ብዙ ነው። ከሀገራችን ጠቅላላ ስፋት 32%9 (ወይም 365,449 km2) የሚሆነው ለግብጽ ውሀ የሚያቀብል ነው። ከዚህ ሰፊ መሬት (365,449 km2) ላይ የሚዘንመው የዝናም ውሀ ሁሉ በጥቃቅን ገባር ወንዞች አማካይነት ወደ ጥቁር ዐባይ፣ ወደ አኮቦ-ባሮና ወደ ተከዜ ተቀላቅሎ በመጨረሻ ወደዋናው ዐባይ10 የሚገባ ነው። ሦስቱ ትልልቅ ተፋሰሶች ከነስፋታቸው እንደሚከተለው ቀርበዋል። 
 የተፋሰስ ስፋት (km2)  የተፋሰስ ስም      በኢትዮጵያ ድምበር ውስጥ 
1. የጥቁር ዐባይ ተፋሰስ      201,346 2. የባሮና ያኮቦ ተፋሰስ (የሶባት ተፋሰስ)    74,102 3. የተከዜ (ያትበራ) ተፋሰስ      90,001    ድምር       365,449 
ዩጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲና ከስምጥ ሸለቆ በስተምእራብ የሚገኘው የኬንያ ክፍል ባንድ ላይ ቢደመሩ ጠቅላላ ስፋታቸው ከነዚህ ሦስት ተፋሰሶች ስፋት አይደርስም። ይህን ያህል ስፋት ባለው መሬት ላይ ነው ኢትዮጵያ ውሀ ነክ ልማት እንዳታካሂድ ግብጽ የምትቃወመው። 
እነዚህ ተፋሰሶች ግብጽ ከሚደርሰው የዋናው ዐባይ ውሀ ከ86% እስከ 95% የሚሆን አስተዋጽዖ ያደርጋሉ። ሦስቱ ተፋሰሶቻችን በያመቱና በክረምት ወራት ግብጽ ለሚደርሰው የዐባይ ውሀ የሚያደርጉት አማካይ አስተዋጽኦ ከነጭ ዐባይ ጋር ሲነጻጸር (ግምታዊ አሀዙ/estimate) በሚከተለው ሰንጠረዢ ላይ የሚታየውን ይመስላል።  
የተፋሰሶች ስም
   ግብጽ ለሚደርሰው የዐባይ ውሀ    የሚያደርጉት አስተዋጽዖ በ(%)  
ጥቁር ዐባይ 
ያመት አስተዋጽዖ
የክረምት (የዝናም) ወራት አስተዋጽዖ 59 68 ባሮና አኮቦ (ሶባት) 14 5 ተከዜ (አትበራ) 13 22
የኢትዮጵያ አስተዋጽዖ በጠቅላላ/ድምር  86 95
ነጭ ዐባይ 14 5 Source:   Waterbury, J. (2002) The Nile Basin: National Determinants of Collective Action, Yale University Press, London.  
ሰንጠረዡ እንደሚያሳየው የነጭ ዐባይ አስተዋጽዖ (ከባሮና ካኮቦ ያልተሻለ) አንስተኛ ነው። በተለይ በክረምት ወራት ግብጽ ለሚደርሰው የዐባይ ውሀ፣ የነጭ ዐባይ አስተዋጽዖ 5% ብቻ ነው። ስለዚህ ነው የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ተባበሩም አልተባበሩም፣ የግድብና የመስኖ ፕሮጀክቶች ሰሩም አልሰሩም ለግብጾች አሳሳቢ እማይሆነው። ኢትዮጵያ ግን ካመት እስካመት ግብጽ ከሚደርሰው የዐባይ ውሀ ባማካይ 86%ቱን የምትሰጥ የግብጽ ህልውና የተመሰረተባት ናት። በክረምት ወቅት ደግሞ (በተለይ በነሐሴና በመስከረም) ግብጽ ከሚደርሰው የዐባይ ውሀ ከመቶ ዘጠና አምስቱ እጅ (95%) ከኢትዮጵያ የሚሄድ ነው። ከሦስቱ የኢትዮጵያ ተፋሰሶች ውስጥ አብዛኛውን (ያመቱ 59%፣ የክረምቱ 68%) ውሀ ለግብጾች የሚወስድላቸው ጥቁር ዐባይ ነው (ሰንጠረዡን ይመልከቱ)። ግብጾችም ከሁሉም አብልጠው አይናቸውን አፍጥጠው በንቃት የሚጠብቁት ይህንኑ ጥቁር ዐባይን ነው። 
ከነዚህ ሦስት ተፋሰሶች እየተነሳ ወደግብጽ የሚሄደው ውሀ በርካታ ሁኖ ሳለ፣ በተፋሰሶቹ ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ግን በተደጋጋሚ የድርቅ ሰለባ ይሆናል። እነዚህ ሦስት ተፋሰሶች የአማራን ክልል፣ የጋምቤላን ክልል፣ የቤኒሻንጉል-ጉሙዝን ክልል እና የትግራይን ክልል ከሞላ ጐደል ይሸፍናሉ ብንል (በ2012 ዓ.ም በተገመተው የሕዝብ ብዛት መሠረት) ወደ ሀያ ሦስት ሚሊዮን (22, 508, 807) የሚጠጋ ሕዝብ ይገኝባቸዋል። ይህም ከጠቅላላው (ከ92 ሚሊዮን) የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 25% ይሆናል። በአማራና በትግራይ ክልል ባማካይ በያንዳንዱ ኪሎሜትር ካሬ መሬት ከ105 እስከ 115 የሚሆን ሕዝብ ይኖርበታል። የትግሬውና የአማራው ክልል ባመዛኙ የመሬቱ አምራቺነት በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ እያንዳንዱ ኪሎ ሜትር ካሬ ከ105 እስከ 115 የሚሆን ሕዝብ የመያዝ አቅም የለውም። የመሬቱ አምራችነት ዝቅተኛ በሆነው አካባቢ የሚኖረው ሕዝብ በተቀናጀ ሁኔታ ወደ ደልዳላው አካባቢ ሂዶ በመስኖ እንዳይጠቀም ያለግብጽ ፈቃድ የረባ የመስኖ ስራ መስራት አይቻልም። (አለመቻሉን በ1996 ዓ.ም ግብጽ ለኢሕአዴግ የሰፈራ እቅድ የሰጠቺውን ምላሽ ዝቅ ብለው ያነቡታል)። 
በግምት ወደ ሰማኒያ አምስት በመቶ (85%) የሚሆነው የሦስቱ ተፋሰሶች ነዋሪ በግብርናና በከብት እርባታ የሚተዳደር ነው። ግብርናውም ከብት እርባታውም በዝናም ውሀ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው። ይህ ሕዝብ በነዚህ ሰፊ ተፋሰሶች ውስጥ ከሚያልፉት ወንዞች የረባ የኤሌትሪክ ኃይልም ሆነ የመስኖ አገልግሎት ሳያገኝባቸው አልፈውት ወደግብጽ ይወርዳሉ። 
የዐባይን ውሀ ለመስኖ ባለመጠቀሟ ኢትዮጵያ ባጉረመረመች ቁጥር ከግብጾችና ከደጋፊዎቻቸው ከሚሰነዘሩት መልሶች አንዱ “ኢትዮጵያ አማራጭ አላት” የሚል ነው። አማራጭ የተባለው “ዝናም” ነው። ኢትዮጵያ ዝናም ይዘንምላታል፣ የዝናም ወቅት እየጠበቀች ስታመርት የኖረች ነች፣ ያንኑ የዝናም አጠቃቀም ዘዴ እያሻሻለች ትቀጥል ለማለት ነው። ነገር ግን የኢትዮጵያ ዝናም እንደ ኮንጐ፣ እንደ ሩዋንዳ፣ እንደ ቡሩንዲ፣ እንደ ዩጋንዳና እንደ ምእራብ ኬንያ አይደለም። ቀደም ብየ እንደገለጽኩት እነዚህ የምስራቅ አፍሪካ (የዐባይ ተፋሰስ) ሀገሮች በጅዖግራፊያዊ አቀማመጣቸው የተነሳ ካመት እስካመት በመጠንም፣ በስርጭትም በቂና አስተማማኝ የሆነ ዝናም ያገኛሉ። የዝናሙ ውሀ በቂ ስለሆነ የወንዞቻቸውን ውሀ ለመስኖ አይፈልጉትም። ስለዚህም ነው ወደ ነጭ ዐባይ የሚፈሰው የወንዞቻቸው ውሀ ደንታ እማይሰጣቸው። 
የኢትዮጵያ ዝናም መጠን፣ ጸባይና ስርጭት ግን ከዚህ በላይ ከጠቀስኳቸው ሀገሮች በጣም የተለየ ነው። ከባሮ ተፋሰስ በስተቀር በሌሎቹ ተፋሰሶች የሚዘንመው ዝናም አስተማማኝ አይደለም። በቂ ዝናም በማይገኝበት ጊዜና አንዳንዴም ጨርሶ በሚጠፋበት ጊዜ ከእጅ-ወደ አፍ ኑሮ የሚኖረው አርሶ-አደርና አርብቶ-አደር ሕዝብ ለርሀብና ለስደት ይጋለጣል። በተፋሰሶቹ አካባቢ የሚዘንመው ዝናም ተለዋዋጭ ነው። ያለወቅቱ ይመጣል፣ ያለወቅቱ ይሄዳል(ያቋርጣል)። አንዴ ያንሳል፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከመጠን በላይ ይበዛና አፈሩ፣ ቡቃያው፣ እንስሳው፣ ሰው ከነንብረቱ ለጐርፍ ይጋለጣል። አርሶ አደሩ ሕዝብ ይህንን የማያስተማምን ዝናም እየጠበቀ የሚያመርተው ምርት ለዓመት ቀለቡ አይበቃም። ስለዚህ ኢትዮጵያን በተመለከተ ዝናምን የመስኖ ምትክ ወይም አማራጭ አርጐ ማቅረብ ዓይን ያወጣ ብልጣ ብልጥነት ነው። 
ሕዝባችን ለዝናም እጥረት መደጐሚያ እንኳን የሚሆን የመስኖ ውሀ (supplemental irrigation) የለውም። ድርቅ በሚሆንበት ጊዜ፣ ወይም ዝናሙ በቂ በማይሆንበት ጊዜ እንዲጠቅም ተብሎ በማሟያነትና በመጠባበቂያነት የተቀደደ፣ በሀገርና በክልል ደረጃ ቀርቶ በወረዳና በቀበሌ ደረጃ እንኳን የሚታወቅ ዘመናዊ ቦይ የለም። በዝናም ብቻ ተማምነን የምንኖር በመሆናችንም የተነሳ በ1970ዎቹና በ1984-85 ዓ.ም በዐባይና በተከዜ ተፋሰሶች ውስጥ11 በርሀብ ያለቀውን በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ እናስታውሳለን። አሁንም ቢሆን በነዚህ ተፋሰሶች ውስጥ የሚኖረው (ከጠቅላላው የሀገሪቱ ሕዝብ 25%) ኢትዮጵያዊ አብዛኛው በድህነትና በችግር የሚቆላ ነው። በየጊዜው ከውጭ በሚመጣ የምግብ ምጽዋት እየተደጐመ የሚኖር ሕዝብ ነው። የሀገሪቱን የምግብ ፍላጐት ለማሟላት በመስኖ ሊለማ የሚችለውን መሬት፣ አቅም ያላቸው ዜጐችና ድርጅቶች አልምተው ለገበያ ለማቅረብ ይችሉ ነበር። ዳሩ ግን ወንዞቻችን ከሱዳንና ከግብጽ ጋር ስላቆራኙን፣ በልበ-ሙሉነት/በድፍረት በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ በውሀ ላይ የተመሠረተ የረባ ወይም ከቁጥር የሚገባ የመስኖ ልማት ስራ የሚጀምርና የሚያካሂድ የለም። ከጐረቤቶቻችን ጋር ለሚያነካኩን ወንዞች ጀርባችን እየሰጠን፣ እስካሁን ድረስ ስንረባረብ የቆየነው በአዋሽ ወንዝ ላይ ብቻ ነው። 
በመስኖ ሊለማና ችግራችን ሊቀርፍ የሚችል ምን ያህል መሬት ያለጥቅም እንደተቀመጠ በግልጽ እንዲታያችሁ አንዳንድ ምንጮች የሚሉትን አጠር አጠር አድርጌ ልዘርዝርላችሁ። 
 ዋተርበሪ/Waterbury (2002) የኢትዮጵያ አንድ ሦስተኛ (ወደ 33 ሚሊዮን ሄክታር) የሚሆን በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት አላት ይላሉ።    የማእከላዊ ፕላን ብሔራዊ ኮሚቴ (1990) 3.5 ሚሊዮን ሄክታር ለመስኖ የሚያመች መሬት እንዳለን ይገልጻል። በመስኖ የለማው ግን 200,000 ሄክታር ወይም ወደ ስድስት በመቶ (5.7%) ብቻ መሆኑን ይኸው ብሔራዊ ኮሚቴ ያብራራል። 
 የአሜሪካ ጠፍ-አቅኚ? ቢሮ (US Bureau of Reclamation) በ1964 ዓ.ም ያቀረበው የጥናት ሪፓርት የሚከተለውን በመስኖ ሊለማ የሚችል ግምታዊ (estimate) የመሬት ስፋት ያሳየናል።
1) ከዲንደር ወንዝ እስከ ተከዜ ወንዝ ድረስ 230,000 ሄክታር መሬት በመስኖ  ሊለማ ይችላል። (ከዲንደር ወንዝ በስተደቡብ የሚገኘው የበለስ ወንዝ ተፋሰስ እስከ ወለጋ ድምበር ያለው ደልዳላ መሬትና የተፋሰሱ ላይኛ ክፍል እዚህ ግምገማ ውስጥ አለመግባቱን ያስተውሉ)። 
2) በአንገረብ ተፋሰስና በተከዜ ተፋሰስ ውስጥ 300,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ ይችላል።(ይህ አካባቢ እነሰቲት ሁመራንም ይጨምራል)። 
3) ይኸው ያሜሪካ (ጠፍ-አቅኚ) ቢሮ ባኮቦ-ባሮ ተፋሰስ ውስጥ 335,000 ሄክታር ለመስኖ ሊውል የሚችል መሬት አለ ሲል፣ ታምስ-ኡልግ (TAMS-ULG) የተሰኘ ቡድን ግን በ1995 ዓ.ም ባካሄደው ግምገማ በዚሁ (ባኮቦ-ባሮ) ተፋሰስ ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ ይችላል ይላል። 
እነዚህ የተለያዩ ቡድኖች የሰጡት ቁጥር ቢለያይም፣ የተጠኑት አካባቢዎች ምናልባት ሊደራረቡ (overlap) ቢችሉም፣ የሁሉም ግምገማ በማያሻማ ሁኔታ የሚያሳየን በመስኖ ሊለማ የሚችል፣ ገና ያልነካነው ሰፊ መሬት ያለን መሆኑን ነው። 
ከሌሎች ምንጮች ደጋግመን እንደምናገኘው ከተፋሰሶቻችን ሁሉ የሚበልጥ12 (በግምት ከ760,000 ሄክታር በላይ የሆነ) ሰፊ ለመስኖ የሚውል መሬት ያለው ተፋሰስ ጥቁር ዐባይ ነው። በግብጽ እብሪትና በኛ/በራሳችን አቅመቢስነት የተነሳ ወንዞቻችንም ሆነ ለመስኖ የሚሆነውን መሬታችን ለመጠቀም አልቻልንም። “እያዩ ማዘን” ማለት ይህ አይደለም? ውሀና መሬት ይዘን አርሰን የማንጠቀም፣ ከንፈራችን እማይወዛ ጦም አዳሪዎች፣ የግብጽን ጡንቻ እያየን፣ ወንዞቻችን የመጠቀም መብታችን ተገፍፈን ተሸማቅቀን የምንኖር ደካሞች ነን።  
ግብጽም የምትፈልገው ደካማነታችን እንዲቀጥል ነው። ትንሽ ጠንከር ካልን ወንዞቻችን ካሁኑ በተሻለ ሁኔታ መጠቀማችን እማይቀር ነው። ትንሽ ጠንከር ካልን ግብጾችን በተለያዩ መድረኮችም ሆነ በወታደራዊ ኃይል እንቋቋማለን ማለታችን እማይቀር ነው። ይህ እንዳይሆን ግብጾች በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያደርጋሉ። የተለያየ ዘዴ እየፈጠሩ በስውርም በግልጽም ይወጉናል፣ ያዳክሙናል። 
ብዙዎቻችን “ጦርነት እንከፍታለን” የሚለውን የግብጾችን ማስፈራሪያ ደጋግመን ስለምንሰማ፣ ብዙውን ጊዜ ሀሳባችን እሚያዘነብለውና እሚያተኩረው ወደ ወታደራዊ አቅማችን ነው። ስጋታችን የግብጽን ወታደራዊ ኃይል የሚመጥን ወታደራዊ ዝግጅት ይኖረን ይሆን? የሚል ነው። አዎ! ተገቢ ስጋት ነው። እኔ በበኩሌ ግብጽን የሚቋቋም ወታደራዊ ድርጅት አለን ብየ አላምንም። ግብጽም የለመደቺውንና ወደፊትም ለመጠቀም ያቀደቺውን የውሀ መጠን የሚቀንስ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ብትጀምር (ሌላ የምትፈራው የኢትዮጵያ ተገን/patron ካልኖረ በስተቀር) ግብጽ ጦር ከማስነሳት ትቆጠባለች ብየ አላምንም። ትልቁና ግብጽ ስትጠቀምበት የኖረቺውና ወደፊትም የምትጠቀምበት የጦርነት ዘዴ ግን በተለያዩ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች/መድረኮች ውስጥ የምታካሂድብን ጦርነት ነው። በአቅመ ደካማነታችን ላይ የዲፕሎማሲና የሞራል ተጽእኖ ከታከለበት ይበልጥ እየደከምን፣ ይበልጥ አቅም እያጣን፣ ይበልጥ አድማጭና ሰሚ እያጣን፣ ይበልጥ ለጥቃት እየተጋለጥን እንሄዳለን። 
ግብጽ በተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዩ ቅርንጫፍ ድርጅቶች (FAO, UNDP, UNEP, ECA, WMO, WHO, UNESCO, etc.)፣ በዓለም ባንክ፣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF)፣ በሌሎችም ትልልቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ፣ በአህጉራዊ ልማት ባንኮች ውስጥ ስር የሰደዱ፣ ቁልፍ ቁልፍ ቦታ ይዘው የሚሰሩ ዜጐች አሏት (Waterbury 2002, 11)። እነዚህ በተለያየ የትምህርት መስክ የሰለጠኑ ታላላቅ ግብጻዊያን፣ ተናግረው የሚያሳምኑ፣ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ ሊያደርጉ የሚችሉ፣ ውለታ ላደረገላቸው ውለታውን መመለስ የሚችሉ፣ ውሳኔ ሊያስቀይሩ የሚችሉ ዜጐች ናቸው (እንደላይኛው)። በተለይ በውሃ ጥናት መስክ (hydrological studies) የነጠሩና በብዙ ትልልቅ ድርጅቶች ውስጥ ባማካሪነት የሚሰሩ የግብጽ ባለሙያዎች አሉ (እንደላይኛው)። እነዚህ በየቦታው የተሰገሰጉ ግብጻዊያን የኢትዮጵያ አቤቱታና ጩኸት እንዳይሰማ ግልጽ ባልሆነ መንገድ መሰናክል ሊፈጥሩ ይችላሉ። 
በኢትዮጵያ ተረ(ቅ)ቆ የሚቀርብ ፕሮጀክት ቢኖር ውድቅ እንዲሆን ሊያደርጉ ይችላሉ። ለቀረበው ፕሮጀክት ብድር ሊያስከለክሉ ይችላሉ። የትልልቅ ውሀ ፕሮጀክት ተቋራጮች እንዲሸሹ ሊያደርጉ ይችላሉ። የሕግ አማካሪዎችንና ባለሙያዎችን ሊያግባቡ ይችላሉ። በውሀ ክፍፍል ስምምነቶችና ውሳኔዎች ላይ ኢትዮጵያ እንድትገለል ሊያደርጉ ይችላሉ። በዐባይ ውሀ ላይ ኢትዮጵያን የማግለሉ ጉዳይ ከዚህ በፊት በ1989 ዓ.ም. በማያሻማ ሁኔታ ተከስቷል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) እና የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን (ECA) በ1989 ዓ.ም ያቋቋሙት፣ ሮጀር በርተሎት (Roger Berthelot) በተባለ ሰብሳቢ የተመራ አጥኚ ቡድን (fact finding mission) ኢትዮጵያን በጥናቱ ሳያስገባ፣ በቪክቶሪያ ሀይቅ ዙሪያ በሚገኙት የዐባይ ተፋሰስ ሀገሮች ብቻ በመመርኮዝ የዐባይ ውሀ አጠቃቀም ባለበት እንዲቀጥል ወስኗል። ይህም ማለት “እንደ ድሮዋ ኢትዮጵያ የዐባይን ውሀ ሳትጠቀም ትቀጥል” ማለት ነው። ይህ የጥናት ቡድን የሱዳንንና የግብጽን ጥቅም ላምስጠበቅ የተሰለፈ ሁኖ መታየቱን ወተርበሪ (Waterbury, 2002) ይገልጻሉ13። 
የተለያዩ ሰበብ አስባቦችን (መረጃ አልተሟላም ማለትን ጨምሮ) በመጠቀም ውሳኔ በማዘግየት (በማጉላላት) ተስፋ እሚያስቆርጥ ሁኔታ ላይ ሊጥሉ ይችላሉ። ባንጻሩ ለግብጽ ሁኔታዎችን ሁሉ ሊያመቻቹ፣ ቅድሚያ ሊሰጡና ሊያሰጡ ይችላሉ። ይህ ጦርነት በውሀዎች አጠቃቀም ዙሪያ ብቻ የሚያካሂዱት ጦርነት ሳይሆን፣ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ጠንካራ ሀገር እንዳትሆን በሌሎች መስኮች ሁሉ ሊከፍቱብን የሚችሉት ጦርነት ነው። ይህ በየቢሮውና በየመድረኩ የሚካሄደው ስውር ጦርነት ሲካሄድ የኖረ ነው፣ አሁንም በመካሄድ ላይ ነው። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊም በግብጽ የሚካሄደው ኢትዮጵያን ለዘለቄታው በኢኮኖሚ ደካማ የማድረግ አሻጥር ገብቷቸው ነበር። ያቶ መለስን አባባል በግርጌ ያንብቡ14። 
ታዲያ ይህን የመሰለውን ጦርነት ለመቋቋም ኢትዮጵያ ምን ይህል ዝግጁ ነች? በኔ ግምት ሀገራችን በኢኮኖሚም፣ በተማረ ሰው ኃይልም ገና እንደ ሕፃን የምታንቧችር ሀገር ነች። ከግብጽ ደረጃ ለመድረስ ብዙ ይቀራታል። ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በወታደራዊ ድርጅት ግብጽን የሚመጥን አቅም እንደሌላት ሁሉ፣ በተማረና በሰለጠነ የሰው ኃይልም አቅም የላትም። 
በኢትዮጵያ ላይ ከሚሸረበው ደባና አሻጥር በተጨማሪ ሀገራችን አቅም በማጣቷ የተነሳ ስንት ውጥኖች ተወጥነው፣ ፍጻሜ ላይ ሳይደርሱ መክነው ቀርተዋል። እነዚህ በውጥን የቀሩ የልማት ፕሮጀክቶች የአቅመ-ደካማነታችንና የተጠቂነታችን ነጸብራቆች ናቸው። ጥቂቶቹን ልዘርዝርላችሁ።   
6. በዐባይ ተፋሰስ መክነው የቀሩ ውጥኖች (በከፊል) የአሜሪካ ጠፍ-አቅኚ ቢሮ (US Bureau of Reclamation, Department of the Interior) ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም ድረስ በዐባይ ተፋሰስ ላይ ያጠናው ጥናት፣ በ1964 ዓ.ም በ17 ቅጾች ታትሞ ወጥቷል። በዚህ የጥናት ሪፓርት እንደሚታየው፣ ከጣና ሀይቅ ጀምሮ እስከ ሱዳን ጠረፍ ድረስ ባለው 900 ኪሎ ሜትር እርቀት ውስጥ፣ ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ ሊውሉ የሚችሉ 26 ግድቦች (reservoirs)  ሊገደቡ እንደሚችሉ ይገልጻል። ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው። 
ሀ) ሜጀር (በኋላ ኮሎኔል) ችዝማን (Cheesman) የተባሉ እንግሊዛዊ? በ1930 ዓ.ም ጣና-በለስ የተሰኘ፣ ጥናቱ የተጠናቀቀ የልማት ፕሮጀክት እንደነበር ይገልጻሉ። ከጣና ደቡባዊ ምእራብ በኩል ስፋቱ 5 ኪሎ ሜትር ብቻ የሆነውን ሸንተረር ቀ(ድ)ዶ/በስቶ (tunnel) የጣናን ውሀ ከበለስ ወንዝ ጋር አቀላቅሎ፣ ውሀው ለኃይል ማመንጫ አገልግሎት ከዋለ በኋላ በበለስ ወንዝ አማካይነት ወደ ዐባይ ወንዝ እንዲገባ ለማድረግ ታቅዶ ነበር ይላሉ። ይህ የጣና-በለስ እቅድ ኃይል ለማመንጨትና 65,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት የታቀደ ነበር። ከዚሁ እቅድ ጋር አያይዘው አሜሪካኖቹም በዚሁ በበለስ ወንዝ ተፋሰስ ሌላ ለኃይል ማመንጫ የሚውል ጥናት አጥንተው ነበር። 
በ1982 ዓ.ም የኢትዮጵያ መብራትና ኃይል ባለስልጣን ይህንን የጣና-በለስ ፕሮጀክት ከዲዴሳ ፕሮጀክት ጋር ቀላቅሎ ይከታተለው ነበር። በ1986 ዓ.ም ወደ በለስ የሚወሰደውን ውሀ መጠን ለመቆጣጠር የሚያስችለው ስራ ጣና ላይ ተጠናቅቆ ነበር። በ1990 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሸለቆዎች ባለስልጣን (EVDSA-WAPCOS) በበለስ ሸለቆ/ተፋሰስ ብቻ 5 ግድቦችን ቀስ በቀስ መገደብ እንደሚቻል አምኖበት ነበር። በ1990 ዓ.ም ይህንኑ የጣና በለስ ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ የደርግ መንግሥት ቸሊኒ (Celini) ከተባለ የጣሊያን ተቋራጭ ኩባንያ ጋር ተዋውሎ፣ ተቋራጩም ለእቃው ማመላለሻ  የሚያገለግል ያየር ማረፊያ ከጠረገ/ካዘጋጀ በኋላ ስራው (ባልታወቀ ምክንያት) በውጥን/ተቋርጦ ቀርቷል። በደርግ የተጀመረው የጣና-በለስ ፕሮጀክት በድርቅ የተጐዳውን ሕዝብ በምእራብ ኢትዮጵያ አስፍሮ 150,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ነበር። 
ለ) የአሜሪካ ጠፍ-አቅኚ ቢሮ ከጣና ሀይቅ ሰሜናዊ ምስራቅ በኩል የሚገኝ የመገጭ ልማት (Megech Scheme) በተሰኘ፣ 25,000 ሄክታር መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻል ታምኖበት እንደነበር ይገልጻል።
ሐ) ይኸው የአሜሪካ ጠፍ-አቅኚ ቢሮ ዲዴሳ ወንዝ ላይ 4 ግድቦችን መገደብ እንደሚቻልና ከወንዙ በታች በኩል ከሚሰራው ግድብ ላይ ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል አጥንቶ ነበር። 
መ) ዲንደርና ረሀድ በተሰኙት ወንዞች ከሱዳን ጋር የሚዋሰነውን የጐንደርና የሰሜናዊ-ምእራብ ጐጃምን ደልዳላ መሬት በመስኖ ማልማት እንደሚቻልና የውሀ ኃይልም ማመንጨት እንደሚቻል አሜሪካኖቹ ሪፓርት አድርገዋል። 
ሰ) ካራዶቢ (Karadobi) የተሰኘ ጉደር ወንዝና የዐባይ ወንዝ ከሚገናኙበት ትንሽ ከፍ ብሎ እንዲገነባ የተጠና ትልቅ የኃይል ማመንጫ ግድብ ነበር። ይህ ቦታ ትልቅ የኃይል ማመንጫ ግድብ ለመገደብ በጣም አመቺ መሆኑንና በትነት ብዙ ውሀ እንደማያባክንም ገልጸዋል። 
ረ) የድምበር ግድብ (Border Dam) የተሰኘ፣ ከሱዳን ድምበር ወደ ኢትዮጵያ 21 ኪሎ ሜትር ያህል ገባ ብሎ ከሚገኝ ቦታ ላይ፣ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ሊይዝ የሚችል፣ 6.2 ሚሊዮን ኪሎዋት አወርስ (KWh) የሚሆን ኃይል ማመንጨት የሚችል ግድብ እንዲሰራ ሀሳብ ቀርቦ ነበር። ይህ ግድብ ምናልባት አሁን “ሕዳሴ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው ይመስለኛል። 
ከዚህ ሁሉ የተጠና ፕሮጀክት ውስጥ፣ ጭስ ዐባይ ላይ ካለቺው አንስተኛ የኃይል ማመንጫና መጠነኛ ከሆነው የፊንጫ የኃይል ማመንጫ በስተቀር በተግባር የተተረጐመ የልማት ስራ የለም። አሜሪካኖቹ በዘመኑ አሉ በተባሉት ሳይንሳዊ የጥናት ዘዴዎች ተመርኩዘው ካገኙዋቸው 26 የግድብ ቦታዎች መካከል ሃያ አራቱ (24) መክነው የቀሩ ናቸው። 
የፊንጫ ግድብ ስራ በተጀመረበትም ጊዜ ግብጽ ተቃውሞ አቅርባ በስንት ውጣ ውረድ (ባሜሪካኖች ተጽእኖ) ከዓለም ባንክ መጠነኛ-ከፊል ብድር ተገኝቶ ሊሰራ ችሏል። የፊንጫ (ፊንጫ-አማሪቲ ፕሮጀክት) ግድብ የተጠናው ለመስኖና ለኃይል ማመንጫ ቢሆንም፣ የሆነ ያልሆነ ምክንያት በመፍጠር፣ ዛሬ ነገ በማለት፣ ግድቡ እስካሁን ድረስ ለመስኖ ስራ እንዲያገለግል አልተደረገም። ከግድቡ የሚወጣው ውሀ ለመስኖ አገልግሎት ሳይውል ሙሉ በሙሉ ወደ ዐባይ ወንዝ የሚቀላቀል ነው። የመስኖው ስራ ያልተካሄደበትና ያልተስፋፋበት ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? ከጥርጣሬ በስተቀር ማስረጃ ስለሌለኝ አንባቢዎች ማስረጃ ካላችሁ አካፍሉን። ያለዚያ ግን ሴራ ስታሴርብን የኖረችና የምትኖር ሀገር ነችና ግብጽን በመጠርጠር አጅቡኝ። 
ይህንኑ ጀምሮ የመተው ልማዳችን የታዘበው “የድምበር ዘለል ወንዞች ድርጅት” (International Rivers Network) በቅርብ ጊዜ በሕዳሴ ግድብ ገምጋሚዎች (Panel of International Experts) ከቀረበው የግምገማ ሪፓርት ተነስቶ ሲጽፍ፣ ------ በተፋሰሶች ውስጥ ታቅደው ተግባራዊ ያልሆኑ ፕሮጀክቶች ዘይንተረፍ ናቸው ሲል በኛ ላይ የቀረብ ሽሙጥ ሁኖ ይሰማኛል። የሕዳሴ ግድብ ጥናት የሚጐድለው የችኮላ ስራ ነውና በግድቡና ግድቡ በሚያስከትለው አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጨማሪ ጥናት ይካሄድበት ማለቱም፣ (ነገር ጠምዛዥ አትበሉኝ እንጂ) የግብጾችን ልማዳዊ የማሰናከያ ዘዴ የሚያንጸባርቅ የመልእክተኛ አነጋገር ሁኖ ይሰማኛል። 
ተጨማሪ መረጃና ተጨማሪ ጥናት መጠየቅን ግብጽ የማሰናከያ ዘዴ አድርጋ የምትጠቀምበት መሆኑን ለማሳየት ያህል፣ ገና የሽግግር መንግሥት በነበረበት ጊዜ (በ1993 ሐምሌ ወር) ከግብጽ ወይም ከሙባረክ ጋር የወዳጅነት ፊርማ በተፈራረመው በዚህ (በኢሕአዴግ ወይም በአቶ መለስ) መንግሥት ላይ የሆነውን ላስታውሳችሁ። 
ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ የበተነውን የኢትዮጵያ ሠራዊት/ወታደር፣ ከራሱ (ከኢሕአዴግ) ጋር የመጡትንና ከስራ የተባረሩትን ሽምቅ ተዋጊዎች፣ በድርቅና በጦርነት ምክንያት ካካባቢያቸው ተፈናቀለው መተዳደሪያ ያጡትን ኢትዮጵያዊያን (በተለይ የትግራይ ተፈናቃይዎችን) በግብርና ስራ ለማሰማራት አንድ ፕሮጀክት ነድፎ ነበር። በዚያ ፕሮጀክት በዐባይ ተፋሰስና በተከዜ ተፋሰስ ውስጥ 10, 000 (አስር ሺህ) ሄክታር መሬት ለማረስ ታስቦ ነበር (Waterbury 2002, 83)። ከአስሩ ሽህ ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ሦስተኛው (ወደ 3,333 ሄክታር የሚሆን መሬት) ከዐባይና ከተከዜ ተፋሰሶች ውሀ ተጠልፎ በመስኖ እንዲታረስ ነበር የታሰበው። ከሁለቱ ተፋሰሶች ለመስኖ የሚጠለፈው ውሀ ባመት 37 ሚሊዮን ሜትር ኩብ እንደሚሆን ተገምቶ ነበር። ያ ውሀ ከጠቅላላው አማካይ የዐባይ ውሀ 0.004% እንደሚሆን ነበር የተሰላው። 
ይህንን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ “መልሶ ማቋቋምና ማህበራዊ ተሀድሶ?”15 (Ethiopian Relief and Social Rehabilitation Fund) የተሰኘ ገንዘብ አሰባሳቢ ድርጅት ተቋቁሞ ከዓለም ባንክ ገንዘብ ተጠየቀ። የዓለም ባንክም በፕሮጀክቱ አምኖበት ለፕሮጀክቱ ስራ የሚውል $70 ሚሊዮን ዶላር መደበ። በዓለም ባንክ ሕግ መሠረት በድምበር አቋራጭ ወንዞች ላይኛ ክፍል ላይ ያለ ሀገር ፕሮጀክት ሲወጥን፣ የሚመለከተውን የታችኛ የተፋሰስ ሀገር ማሳወቅ ግዴታ ነውና፣ ኢትዮጵያ ያቀደቺውን የሰፈራ ፕሮጀክት ለግብጽ እንድታሳውቅ የዓለም ባንክ ጠየቀ። በዓለም ባንክ ጥያቄ መሠረት ኢትዮጵያ ለግብጽ ስታሳውቅ ግብጽ ፕሮጀክቱን ልታውቅ/ልትቀበል አልፈለገችም። 
የግብጽ ምላሽ “ተጨማሪ ጥናት ይደረግበት”፣ “ተጨማሪ መረጃ ይሰጠን” የሚል ነበር። በዚህም የተነሳ ፕሮጀክቱ በተግባር ላይ ሳይውል ረዢም ጊዜ ወሰደ። የዓለም ባንክም የግብጽን መልስ ሲጠብቅ ለፕሮጀክቱ የመደበውን $70 ሚሊዮን ዶላር ሳይለቅ እስከ 1997 ዓ.ም ድረስ ቆየ። በመጨረሻ ግን (ምናልባት በአሜሪካና በእንግሊዞች አግባቢነት?) የዓለም ባንክ ለዚህ ፕሮጀክት የመደበውን $70 ሚሊዮን ዶላር በ1997 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ለቀቀ። ግብጽም ማቋረጫ የሌለውን የመረጃና የጥናት ጥያቄ እንደቀጠለች ፕሮጀክቱን ሳታውቅ/ሳትቀበል ቀረች። የዓለም ባንክ በማን/በነማን አግባቢነትና ተጽእኖ ለኢትዮጵያ ገንዘብ ለመስጠት እንደወሰነ ግብጽ ባትረዳ ኑሮ ብዙ ጩኸት፣ ብዙ ማስፈራሪያ ታሰማ ነበር። የኢሕአዴግ ፕሮጀክትም ዓለም ሁሉ በንቃት የሚከታተለው ትልቅ መነጋገሪያ ዜና ይሆን እንደነበር እገምታለሁ። ያም ሆነ ይህ በእቅድ የተያዘው፣ ወደ 3,333 ሄክታር መሬት በመስኖ የማልማት ጉዳይ ተግባራዊ የሆነ አልመሰለኝም። የዓለም ባንክ የሰጠው $70 ሚሊዮን ዶላርም ለታሰበላቸው ሰዎች እንዴት እንደተሰጣቸው አላውቅም። ዋናው ላስተላልፈው የፈለግሁት መልእክት ኢትዮጵያ በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የመስኖም ሆነ የኃይል ማመንጫ ስራ ስትወጥን፣ ተጨማሪ ጥናትና ተጨማሪ መረጃ መጠየቅ የግብጽ የማደናቀፊያ ዘዴ መሆኑን ነው።  
ይህንን ታሪክ ያመጣሁት የሕዳሴን ግድብ አስመልክቶ የ‘ድምበር ዘለል ወንዞች ድርጅት’ (International Rivers Network) ተጨማሪ ጥናትና ተጨማሪ መረጃ እየጠየቁ የልማት ፕሮጀክቶችን ማወሳሰብና ተጨናግፈው እንዲቀሩ ማድረግ ከግብጽ የተዋሰው አሰራር መስሎ ስለታየኝ ነው። 
7. ወሳኝ አቋም በሕዳሴ ግድብ ላይ  ስለሕዳሴ ግድብ ዝርዝር መረጃ የለኝም። ሂጀም አልጐበኘሁትም። ትልቅ ግድብ መሆኑን እሰማለሁ። ለሌሎች ሀገሮች የሚሸጥ የውሀ ኃይል (hydro-electric power) እንዲያመነጭ መታቀዱን ሰምቻለሁ። ከሱዳን ድምበር 20 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ገባ ብሎ በኢትዮጵያ መሬት (በቤኒሻንጉል-ጉሙዝ ክልል) ውስጥ፣ በዐባይ ወንዝ ላይ መጀመሩን አውቃለሁ። 
ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም በአሜሪካኖች በተካሄደው የዐባይ ተፋሰስ ጥናት እዚሁ አካባቢ፣ ማለትም ከሱዳን ድምበር 21 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ገባ ብሎ 11 ቢሊዮን ሜትር ኩብ ውሀ ሊይዝ የሚችል፣ ቆቃን ሰባት ጊዜ የሚበልጥ፣ የግብጾችን አስዋን ግድብ ሁለት ሦስተኛ የሆነ (⅔) ትልቅ ግድብ እንዲገደብ በአሜሪካኖቹ አጥኚ ቡድን ሀሳብ ቀርቦ እንደነበር አንብቤአለሁ።  
ኢትዮጵያ ወደ ኮሚዩኒስቱ ዓለም ጭልጥ ብላ ገብታ በነበረበት ጊዜ፣ በ1984 ዓ.ም ምእራብ-ዘመም (pro-west) በነበሩት የሱዳን መሪ ጃፋር አልኒሜሪ (Ja’afar al-Nimeiry) የሱዳንን የኤሌትሪክ ኃይል ችግርና የመስኖ ችግር እንዲያጠና ያሜሪካ ጠፍ-አቅኚ ቢሮ (US Bureau of Reclamation) ተጋብዞ ነበር። ይህ የአሜሪካ አጥኚ ቡድን ሱዳን ውስጥ ጥናት ሲያካሂድ፣ ቀደም ሲል (ከ1958 ዓ.ም እስከ 1963 ዓ.ም) ኢትዮጵያ ውስጥ ካጠናቸው ግድቦች አንዱን (ከሱዳን ድምበር 21 ኪሎ ሜትር እርቆ ኢትዮጵያ ውስጥ ተጠንቶ የነበረውን) ግድብ (Border Dam) ለኒሜሪ አንስቶላቸው ነበር። 
የድምበር ግድብ (Border Dam) የተባለውን ሱዳን መጠቀም ብትችል፣ የካርቱምን፣ የዋዲመዳኔን፣ የአትበራን ከተሞች የኤሌትሪክ ኃይል ፍላጐት በቀላሉ ማሟላት እንደምትችል፣ የሮሲየርስን ግድብ (Roseires Dam) የውሀ ከፍታ መጨመር እንደምትችል፣ ከሶባት ወንዝ ጀምሮ በኢትዮጵያና በነጭ ዐባይ መካከል ያለውን የተንጣለለ ሰፊ የሱዳን መሬት እስከ አትበራ ድረስ ያለምንም ችግር ካመት እስካመት በመስኖ ልታለማ እንደምትችል የአሜሪካው አጥኚ ቡድን ለኒሜሪ ገልጾላቸዋል። የድምበር ግድብ (Border Dam) የተባለው፣ ሮሲየርስ ግድብ (Roseires Dam)፣ ስናር ግድብ (Sennar Dam) እና ካሽም- አል-ጊርባ ግድብ (Khashm al-Girba) የተባሉት ሦስት የሱዳን ግድቦች የሚይይዙትን የውሀ መጠን ባምስት እጥፍ እንደሚበልጥ አብራርቶላቸዋል። በዚያን ጊዜ (በ1984 ዓ.ም) ሱዳንና ኢትዮጵያ በምእራቡና በምስራቁ ጐራ የተለያዩና ጨርሶ እማይጣጣሙ ሀገሮች ስለነበሩ፣ የሱዳን ባለስልጣኖችና የኢትዮጵያ ባለስልጣኖች ባንድ ላይ ተወያይተው፣ የተጠናውን የድምበር ግድብ ገድበው፣ በጋራ ተጠቃሚ ለመሆን አልቻሉም/አልበቁም። የዐባይን ወንዝ አጠቃቀም በተመለከተ ሁልጊዜ ከግብጽ ጐን በመሰለፍ የምትታወቀው ሱዳን፣ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ ከግብጽ ተለይታ የሕዳሴ ግድብ ደጋፊ የሆነችበት ዓይነተኛ ምክንያት ይህንኑ (በ1984 ዓ.ም) ያመለጠ እድል ለመጠቀም ፈልጋ ይመስለኛል። 
ይህ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀዘንና ሮሮ ሲያሰማበት በኖረው በዐባይ ተፋሰስ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረ ግድብ ነው። አቅም ከተገኘ ወይም ጊዜያዊ አቅም የሚሰጥ ተገን/ከለላ16 ከተገኘ፣ ኢትዮጵያዊያን ሊቀበሉትና ሊደግፉት የሚገባ ጅምር ይመስለኛል።
ይህ ግድብ ለኢትዮጵያዊያ የኢኮኖሚ እድገት አስተዋጽኦ ያደርጋል በሚል እምነት የተጀመረ ግድብ ነው። ኢትዮጵያዊያንን ይጠቅማል ተብሎ የታሰበ የልማት ስራ ስለሆነ፣ ሀሳቡን በበጐ ዓይን ማየቱ የሚበጅ ይመስለኛል። 
በዚህ ጽሑፍ ሰፋ አድርጌ ለማሳየት እንደሞከርኩት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በዐባይ ተፋሰስ ላይ የሚጀመርን ፕሮጀክት የምትጠላ፣ የምትቃወምና የምታደናቅፍ ግብጽ ብቻ ናት። በዚሁ ተፋሰስ ላይ የተጀመረውን የልማት ፕሮጀክት (የሕዳሴን ግድብ) ብንቃወም፣ ተቃውሟችን የግብጽ አጋር እሚያደርገን ይመስለኛል። 
ምንጊዜም አቅመ ደካሞች ነንና (ለአቅመ ደካማነታችንም ዋናዎቹ ተጠያቂዎች፣ ካለፈው ትውልድ ጭምር፣ ራሳችን ነን) በገንዘብ አቅም የተነሳም ሆነ በሌላ ምክንያት የግድቡ ስራ ሊጠናቀቅም ላይጠናቀቅም ይችላል። ፍጻሜውንና ወደፊት የሚሆነውን ማናችንም በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ሀሳቡና ጅምሩ ግን ለተራው ጦም-አዳሪ ኢትዮጵያዊ ለእለት ችግሩ አይደርስም እንጂ፣ በሀገር ደረጃ ረዘምና ሰፋ አድርጐ ለሚያስብ ሰው፣ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ ያቅም ግምባታ ጉዳይ ለሚያስብ ሰው፣ የግድቡ በጐ ጐን ጐልቶ እንደሚታየው እገምታለሁ። በመግቢያዬ ላይ እንደገለጽኩት ዐባይን ጥቅም ላይ ማዋል የኢትዮጵያ ሕዝብ ሲናፍቅ ኖሯልና፣ ለሕዳሴ ግድብ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥ አምናለሁ። ይህ እምነቴ እውነት ወይም ትክክል ከሆነ፣ የሕዳሴን ግድብ የምንቃወም ሁሉ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየንና የተገነጠልን እንሆናለን ማለት ነው። አንዳንድ የኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓለቲከኞች ሲናገሩ እንደምሰማው “ግድቡን ኢሕአዴግ የጀመረው በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን/ድጋፍን ለማትረፍ ነው” ይላሉ። ይህንን ጅምር ሕዝብ እንደሚወደው ተረድተዋል ማለት ነው። 
የሕዳሴን ግድብ አንደግፍም ወይም እንቃወማለን ከሚሉ (በጽሑፍም ሆነ በገጽ ካጋጠሙኝ) ፖለቲከኞች መካከል፣ እስካሁን ድረስ አንድም አጥጋቢ የሆነ ፍሬ ነገር አላገኘሁም። ካጋጠሙኝ ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው። 
7.1. የሕዳሴን አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ በሚመለከት፣  ግድቡ የሚያስከትለው አካባቢያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጽእኖ “በቂ ጥናት አልተደረገበትም” የሚል ትችት ይሰንዝራሉ። በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ያካባቢ እንክብካቤ ጉዳይ (environmental conservation) አሳሳቢ ሁኖ አይቆጠርም ነበርና፣ ያሜሪካኖቹ የጥናት ቡድን፣ ግድቡ ባካባቢው ላይ የሚያስከትለውን ተጽእኖ በጥናቱ ውስጥ ሳያስገባው ቢቀር አያስደንቅም። ባሁኑ ጊዜ ግን እንኳን ይህን ያህል የብዙ ቢሊዮን ዶላር ትልቅ ፕሮጀክት፣ የትኛውም ዓይነት አንስተኛ ፕሮጀክት ሲሰራ ባካባቢውና በነዋሪው ሕዝብ ላይ የሚያስከትለው ተጽእኖ ሳይጠና አይጀመርም። ይህን ያህል ግዙፍ ግድብ ሲገደብ በነዋሪው ሕዝብ፣ በእጽዋቱና በእንስሳቱ፣ እንዲሁም በተፈጥሮ መኖሪያቸው ላይ ለውጥ እንደሚያስከትል የሚያጠያይቅ አይደለም። ግን ግድቡ ያስገኛል ተብሎ ከታሰበው ጥቅምና ከሚያስከትለው ጉዳት የትኛው ይበልጣል? ይህን ዓይነቱን ጥያቄ ለመመለስ ነው፣ ግድብ ሲታሰብ ከሚጠኑት ብዙ ጥናቶች መካከል አንዱ የሆነው “cost-benefit analyses” የሚባለው ጥናት የሚካሄደው።  
ይህ ግድብ በተጀመረበት አካባቢ ይከሰታል ተብሎ የተፈራውን ያካባቢ ቀውስ የግድቡ ተቃዋሚዎች ተጨባጭ በሆነ መልክ ቢገልጹልን ኖሮ ሁላችንም ትምህርት እናገኝበት ነበር። ግድቡም ይቅርብን ለማለት ያስችለን ነበር። ግን አልገለጹልንም። 
ይህ ግድብ የተጀመረው በቤኒ-ሻንጉል-ጉሙዝ ክልል፣ በድሮው አጠራር በመተከል አውራጃ ውስጥ ነው። የቤኒ-ሻንጉል- ጉሙዝ ክልል የሕዝብ ብዛት ባማካይ በየኪሎ ሜትር ካሬው ከ10 እስከ 13 ሰው የሚገኝበት ነው። ተራርቆና ተበታትኖ የሚኖር ሕዝብ ነው። ወደ መተከል ደርግ አዝምቷችሁ የነበራችሁ ሁሉ ያካባቢው አጠቃላይ ስዕል እስካሁን ባእምሯችሁ ውስጥ እንደተቀረጸ ይገኝ ይሆናል ብየ እገምታለሁ። ምን ያህል መንደር አይታችኋል? እያንዳንዱ ያያችሁት መንደር ምን ያህል ሕዝብ የሚኖርበት ነበር? መንደሮቹ ምን ያህል ይራራቁ ነበር? የሕዳሴ ግድብ ይሰራበታል የሚባለው አጠቃላይ ገጽታው እናንተ በዐይናችሁ ካያችሁት የተለየ አይደለም። 
ያ ያያችሁት ደልዳላ መሬት እስከ ሱዳን ነጭ ዐባይ፣ ካርቱም ድረስ የሚደርስ ሰፊ ደልዳላ መሬት ነው። የቤኒ-ሻንጉል-ጉሙዝ ሕዝብ ባመዛኙ አዳኝና ከብት አርቢ በመሆኑ፣ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር ነው። መንደሩም ከጥቂቶቹ በስተቀር አብዛኛው ጊዜያዊ ነው። እንደ ደገኛው ሕዝብ ጠንካራና እድሜያማ ቤት አይሰራም። ስለዚህ  በግድቡ የተነሳ ከቀየው/ከመንደሩ የሚፈናቀለው የሰው ቁጥር ብዙ አይሆንም። 
በተፈናቃዩ ሕዝብ ላይ ይደርሳል ተብሎ የሚገመተው ጉዳትና ግድቡ ለሀገር ያስገኛል ተብሎ የታመነበትን ጥቅም አነጻጽሮ ማየት ያስፈልጋል። ያም ሆነ ይህ የከብት ማሰማሪያ መሬቱና የአደን መሬቱ ግድቡ በሚፈጥረው ሀይቅ ስለሚዋጥበት፣ የለመደው የአኗኗር ዘይቤ መዛባቱ የማይቀር ነውና ላካባቢው ሕዝብ ተገቢው ካሳ ሊከፈለው ይገባል። በግድቡ የሚነካው ሕዝብ ብዛት ስለማይኖረው፣ የሚከፈለው ካሳ ካቅም በላይ የሚሆን አይመስለኝም። በሕዝብ መፈናቀል ሰበብ ግድቡን ከመቃወም ይልቅ፣ ለነዚህ በግድቡ የተነሳ ኑሯቸው ለሚዛባባቸው ሰዎች መንግሥት ተገቢውን ካሳ መክፈል አለመክፈሉን መከታተልና በተፈናቃዮቹ ጐን መሰለፍ ያስፈልጋል። 
የተፈጥሮ ሚዛንን በመለወጥ በኩል፣ ግድቡ የሚፈጥረው ባሕር በቅርብ የሚገኘውን የባሕሩን አካባቢ የማቀዝቀዝ ጸባይ ይኖረዋል። ሙቀት የለመዱ እጽዋትና እንስሳት (አዲሱን አካባቢ የመቋቋም ችሎታ ካልኖራቸው በስተቀር) ግድቡ ከሚያቀዘቅዘው አካባቢ ይጠፉና/ይሸሹና አዲሱን የአየር ንብረት የሚወዱ ሌሎች እጽዋትና እንስሳት ይተኩ ይሆናል። ይህ ግን ከቁጥር የማይገባ ጥቃቅን ለውጥ ነው። ግድቡ በተፈጥሮ ሚዛን ላይ የሚያስከትለው አስጊ ተጽእኖ ቢኖርማ ኑሮ ከኢትዮጵያ ይልቅ ስጋት ላይ የምትወድቀው፣ ከግድቡ በታች ሰፋፊ የመስኖ እርሻ መሬት እያለማች የምትኖረውና በርካታ ከብት አርቢ ሕዝብ ያላት ሱዳን ነበረች። ሱዳን ግን ከግድቡ የምታገኘውን ጥቅምና ጉዳት አመዛዝና ግድቡን ደግፋለች።  
7.2. የግድቡን ትልቅነት በሚመለከት የሚቀርቡ ተቃውሞዎች የሕዳሴን ግድብ ከሚቃወሙ ፓለቲከኞች የምሰማው ሌላው ነቀፋ፣ “ግድቡ ትልቅ ነው፣ በአፍሪካ የተገደቡ ትልልቅ ግድቦች ለተራው ሕዝብ አልጠቀሙም። ይህ ትልቅ ግድብም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጠቀሜታ አይኖረውም። ለኢሕአዴግ ስም መጠሪያ ብቻ የሚሆን ነው” የሚል ነው። ይህ አባባል ታላላቅ ግድቦች የሚወቀሱበትን ምክንያት በደምብ ሳያጤኑ የሚሰነዘር የጅምላ አባባል ሆነ እንጂ እውነትነት አለው። አባባላቸውንም ባንዳንድ ማስረጃዎች መደገፍ ይችላሉ። ትክክለኛው የአፍሪካ ታላላቅ ግድቦች ታሪክ ባጭሩ የሚከተለውን ይመስላል። 
አንዳንድ የሕዳሴ ግድብ ተቃዋሚዎች እንደሚሉት ሁሉ፣ በአፍሪካ ውስጥ የታላላቅ ግድቦች ታሪክ አብዛኛው አኩሪ አይደለም። በ1950ዎቹ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጠናቀቀበትና አሜሪካ የምእራባዊው ዓለም መሪ ሁና የወጣችበት ዘመን ነበር። ያ ዘመን (ከ1950ዎቹ እስከ 1960ዎቹ) ባልሳሳት ፓርቱጋል ከገዛቻቸው ከሞዛምቢክና ከአንጐላ በስተቀር፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች ከቅኝ ግዛት ነጻ የወጡበት ዘመን ነበር። እነዚህን ነፃ የወጡ ሀገሮች በጐናቸው ለማሰለፍ (to bring them under their sphere of influence) የምስራቁ ዓለም (በተለይም ሶቪየት ዩኒዬን) እና የምእራቡ ዓለም (በአሜሪካ መሪነት) የሚፎካከሩበት፣ ቀዝቃዛው ጦርነት የተጧጧፈበት ዘመን ነበር። 
በዚህ የምስራቁ ዓለምና የምእራቡ ዓለም ውድድር ወይም በቀዝቃዛው ጦርነት የተነሳ፣ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት ሀገሮች ገንዘብ እንደልብ ይፈ(ስ)ስላቸው ነበር። ያንን (በእርዳታም በብድርም) እንደልብ ያገኙት የነበረውን የማባበያ ገንዘብ፣ የመስኖ እርሻን በማስፋፋት ርሀብንና ድህነትን እናጠፋበታለን በሚል ትልልቅ ግድብ ለመገደብ ቆርጠው ተነሱ። ከ1950ዎቹ እስከ 1960ዎቹ ድረስ ይገደቡ የነበሩት ታላላቅ ግድቦች “አረንጓዴው አቢዮት” (Green Revolution) በመባል የሚታወቀው እንቅስቃሴ አካል ናቸው። ከእርሻው መስክ በተጨማሪ ለፋብሪካዎች ማንቀሳቀሻ ፔትሮሊየም በውድ ከመግዛት ይልቅ፣ ግድቦቹ በሚያመነጩት ርካሽ የውሀ ኃይል (hydro-electric power) ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ይቻላል የሚል እምነት ነበር። 
እነዚያ ታላላቅ ግድቦች ሲገደቡ ብዙ ሕዝብ ከሰፈረበት መንደር ተፈናቅሏል17። የተራ ገበሬዎች እርሻዎች በግድቡ ውሀ ተውጠዋል/ተጥለቅልቀዋል። የተፈናቀለው ሕዝብ ካሳ ተቀብሎ እንዲሰፍርበት በተሰጠው አዲስ አካባቢ ሊለምድ ባለመቻሉ ከመቶ ሃምሳ እጁ (50%) ያህል ወደ ከተማ እየተሰደደ ባዝኖ ቀርቷል። በግድቡ አካባቢ እንዲሰፍር የተደረገውም ሕዝብ የሰፋፊዎቹ የመስኖ እርሻዎች የቀን ወዛደር ሁኗል። 
ታዲያ ተራው ሕዝብ ያን ያህል ከፍተኛ ዋጋ/መስዋእትነት ከከፈለ በኋላ፣ የመስኖው እርሻ በተራው ገበሬ የማይታረስ፣ ለጥቃቅን እርሻዎች የማይመች ሆነ። የተንጣለለ ሰፊ መሬት ሊያርሱ የሚችሉ ቱጃር ግለሰቦች፣ ቡድኖች ወይም ኩባንያዎች ብቻ በዘመናዊ መሳሪያ የሚያርሱት ሆነ። ያም አልበቃ ብሎ (ለሀገር ውስጥ የምግብ እህል ማምረቱ ለቱጃሮቹ ብዙ ትርፍ ስለማያስገኝላቸው) ወደውጭ የሚላኩ ምርቶች (export crops) የሚመረቱበት፣ የተራውን ሕዝብ ርሀብና ችግር የማይቀርፍ ሆነ። የሕዝቡን ርሀብና ችግር ለማስወገድ የታቀደው የታላላቅ ግድብ ፕሮጀክት ዓላማውን ሳተ። ሕዝቡ ከድህነትና ከጦም አዳሪነት ሳይላቀቅ ቀረ። ከዚህም በተጨማሪ ሰፊ የመስኖ እርሻ ሊያካሂዱ የሚችሉ ሀብታም አፍሪካዊያን ጥቂት ስለነበሩ፣ አብዛኛው ሰፋፊ የመስኖ እርሻ የውጭ ቱጃሮችና ኩባንያዎች መዋእለ ንዋያቸውን እያፈሰሱ የሚያካሂዱትና የሚጠቀሙበት የእጅ-አዙር ቅኝ አገዛዝ የሚንጸባረቅበት ሆነ። 
ከታላላቆቹ ግድቦች በርካሽ ይገኛል የተባለውም (ከውሀ የሚመነጭ) የኤሌትሪክ ኃይል በከተሞች ለሚገኙ (ባመዛኙ) በውጭ ዜጐች ለተያዙ ፋብሪካዎች መጠቀሚያ ሆነ። አፍሪካዊያን እነዚያን ግድቦች በመስኖም ሆነ በኢንዱስትሪ ልማት ለመጠቀም (በገንዘብ፣ በዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎች፣ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ ወ.ዘ.ተ.) ዝግጁ ስላልነበሩ ግድቦቹ የጥቂት ሀብታሞችና የውጭ ዜጐች መጠቀሚያ ሆኑ።  
ያም ሆኖ ግን እነዚያ ግድቦች ለተራው ዜጋ አልጠቀሙም እንጂ፣ ለመንግሥት በሚያስገቡት ግብርና ቀረጥ ለአጠቃላይ የሀገር ገቢ አስተዋጽኦ አላደረጉም አይባልም። በጋና(አኮሶምቦ ግድብ)፣ በናይጀሪያ(ካይንጂ ግድብ)፣ በኮንጐ(ኢንጋ ግድብ)፣ በዚምባቡዬና በዛምቢያ (ካሪባ ግድብ) እስካሁን ድረስ በመብራትና በኃይል አመንጭነት፣ በፋብሪካና በመጠጥ ውሀ አቅርቦት፣ በመስኖ አገልግሎት፣ በአሳ ማጥመጃነትና በመጓጓዣነት ለየሀገራቸው ከፍተኛ አገልግሎት እየሰጡ ነው። እሚወቀሱበት ምክንያት መጀመሪያ የታቀዱበትን (የሕዝቡን ድህነት የመቅረፍ) ዓላማ በመሳታቸው ነው። ስለዚህ ነው እነዚያ ታላላቅ ግድቦች የታሰበላቸውን (ሕዝብን ከድህነት የማላቀቅ) ግብ የሳቱ፣ የሀገር መሪዎች ስም መጠሪያ ብቻ ሁነው የቀሩ ናቸው እየተባሉ ሲተቹ እሚኖሩት። 
የሕዳሴ ግድብ ግን ትልቅ ከመሆኑ በስተቀር ለየት ላለ ዓላማ የታቀደ ግድብ ነው። የግድቡ ዓላማ በመስኖ አርሶ የሕዝቡን የምግብ ፍላጐት ለማርካት ሳይሆን፣ የውሀ ኤሌትሪክ ኃይል አመንጭቶ፣ ኃይሉን ለሌሎች ሀገሮች ሽጦ ለሀገር ገቢ ለማስገኘት ነው። የሕዳሴ ግድብ የተራውን ሕዝብ ያጭር ጊዜ (የምግብ) ችግር ለመፍታት እንዳልተወጠነ በግልጽ የተነገረና የታወቀ ነው። ጥቅሙ (ወደፊት) ለሀገር በሚያስገኘው ገቢ የሚለካ ነው የሚሆነው። 
የሕዳሴ ግድብ ገቢ አስገኝቶ የሀገራችን አቅም (ኢኮኖሚይዊ፣ ወታደራዊ፣ የተማረና የሰለጠነ የሰው ኃይል) ለመገንባት የሚጠቅም ከሆነ፣ ትልቅ በመሆኑ ብቻ ልንቃወመው አይገባም። በትልቅነት ብቻ ግድብን የምንቃወም ከሆነማ ለግብጾች ሁለንተናቸው የሆነውን የአስዋን ግድብም መቃወም ሊኖርብን ነው ማለት ነው። አናቶሊያ የተሰኘው በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከሚደነቁት ታላላቅ ግድቦች አንዱ የሆነው የቱርኮች ግድብም መወገዝ አለበት ማለት ነው። ታላላቅ ግድቦች ጠቃሚ በመሆናቸው እስካሁን በመሰራት ላይ ናቸው። የቻይናዎቹን  ታላቅ ግድብ (the Three Gorges Dam) እንደምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። 
አንዳንድ ተቺዎች፣ ብዙ ቢሊዮን ብር አውጥቶ አንድ ትልቅ ግድብ ከመስራት ይልቅ፣ በዚያው ገንዘብ ከተለያየ ቦታ ላይ አንስተኛ የሆኑ ግድቦች ቢገደቡ ይሻላል፣ ‘ለሕዝብም የሚጠቅሙት አንስተኞቹ ግድቦች ናቸው’ ይላሉ። ይህ አባባል የመነጨው ከላይ የጠቃቀስኳቸው ታላላቅ ግድቦች የተገደቡበትን (የሕዝቡን ርሀብና ችግር የመፍታት) ኢላማ በመሳታቸው ነው። “ትልልቁ ግድብ ለሕዝቡ ችግር መፍትሄ ካልሰጠ፣ መለስተኛና አንስተኛ ግድቦች ይገደቡና ይሞከሩ” ከሚል አስተሳሰብ የመነጨ ነው። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ግለሰቦች ተጨባጭ ማስረጃ ሳይኖራቸው “ለሕዝብ የሚጠቅሙት መለስተኞቹና አንስተኞቹ ግድቦች ናቸው” በማለት የትልልቅ ግድብ ተቃዋሚ ይሆናሉ። 
ግድቦች መለስተኞችና ትንንሾች ስለሆኑ ብቻ ለሕዝብ ይጠቅማሉ ማለት ስህተት ነው። በነፊንጫ፣ በነመልካ ዋከና፣ በነቆቃ የትኛው ሕዝብ ሲጠቀም አይታችኋል? በነዚህ መለስተኛ ግድቦች የተነሳ ችግሩ የተቀረፈለት የትኛው ተራ ኢትዮጵያዊ ነው? እኔ እማውቀው በተቃራኒው ነው። ከ1960 ዓ.ም እስከ 1971 ዓ.ም ድረስ በየተራ በተሰሩት በቆቃ፣ በአዋሽ ሁለትና በአዋሽ ሦስት ግድቦች በሚካሄደው የመስኖ ልማት የተነሳ የአርሲ ኢቱ ከብት አርቢዎች የከብት ማሰማሪያቸው ተወስዶባቸው ተስድደዋል (ካካባቢው ጠፍተዋል)። የአፋርና ኢሳ ከብት አርቢዎች በተንዳሆ የልማት ስራ የተነሳ የግጦሽ መሬታቸውን አጥተዋል። ያውም ያለካሳ። እነዚህ መለስተኛ ግድቦች በተራው ሕዝብ ላይ ያስከተሉት ችግር መጠኑ ከማነሱ በስተቀር፣ በአፈናቃይነታቸውና ባካባቢያዊ ተጽእኗቸው ከታላላቆቹ ግድቦች በምን ይለያሉ? ስለዚህ ትንንሾቹ ግድቦችም ቢሆኑ ካንዳንድ መሠረታዊ ለውጦች ጋር የተቀናጁ ካልሆኑ በስተቀር ለተራው ሕዝብ እርባና የላቸውም። አይጠቅሙም። ለተራው ሕዝብ አልጠቀሙም ተብሎ ግን ባጠቃላይ ለሀገር የሚሰጡት አገልግሎት ሊካድ አይችልም። እነዚህ መለስተኛ ግድቦች የሚሰጡትን ጥቅም ስለምታውቁት ከኔ መስማቱ እሚያስፈልጋችሁ አይመስለኝም። ስለዚህ ባጭር ጊዜ የተራውን ሕዝብ አለመጠቀም ምክንያት አድርገን የሕዳሴን ግድብ በትልቅነቱ ብቻ ልንቃወመው አይገባም እላለሁ። 
ይህ ግዙፍ ግድብ የግብጽን ዓይን ይስባል፣ ስለዚህ መለስተኛና አንስተኛ ግድቦች ቢሰሩ ይሻላል የሚሉ ካሉ፣ ግብጽ ግድቡን የምትቃወመው በትልቅነቱ አለመሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ግድቦቹ አንስተኛም ቢሆኑ በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚገደቡ እሰከሆኑ ድረስ ግብጽ ከመቃወም አትታቀብም። ግብጽ በዐባይ ተፋሰስ ላይ ምንም ዓይነት ልማት አትፈቅድም። ቀደም ብዬ እንደ ገለጽኩላችሁ አቶ መለስ በ1993 ዓ.ም ከግብጽ ጋር የወዳጅነት ውል ተፈራርሜያለሁ ብለው፣ በ1996 ዓ.ም በተከዜና በዐባይ ተፋሰስ ለማሰፍረው ሰፋሪ ወደ 3,333 ሄክታር መሬት በመስኖ እንዳለማ እወቁልኝ ሲሏቸው፣ ተጨማሪ መረጃና ተጨማሪ ጥናት እየጠየቁ ፈቃደኝነታቸውን ሳይገልጹ ቀርተዋል። ከዚህ ያነሰ ፕሮጀክት ምን አለ?  
7.3. ታላላቅ ግድቦች የመሪዎች ስም መጠሪያ ስለመሆናቸው፣ ታላላቅ ግድቦች የመሪዎች መጠሪያ ናቸው የሚለው ትክክል ነው። የሕዳሴ ግድብ የአቶ መለስ ወይም የኢሕአዴግ መጠሪያ ሆነ አልሆነ በኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር ላይ እሚጨምረውም እሚቀንሰውም ነገር የለም። አንድ መንግስት አንድ ትልቅ ስራ ሲሰራ፣ ስራው መጠሪያው እንደሚሆን እሙን ነው። ኢሕአዴግ ስሙን እሚያስጠራበት ስራ አልገደደውም።  ኢትዮጵያን በር-አልባ አድርጓልና ሲጠራበት ይኖራል።  የልማት ስራን (መንገድን፣ ሕንጻን) በተመለከተ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከጣሊያን ቀጥሎ ተወዳዳሪ የለውምና ሲጠራበት ይኖራል።  ኢትዮጵያን በቋንቋና በጐሳ አስተዳደር ለያይቶ የገዛ ነውና ሲጠራበት ይኖራል።  ሕዳሴንም ከገደበ ስራው ነውና ሲጠራበት ይኖራል። 
ስራ የሰሪው መጠሪያ ነውና አዲስ ሊሆንብን አይገባም።
8. ማጠቃለያ በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት የሞከርኩት በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ በመስኖ ሊለማ የሚችል መሬት እንደልብ ሁኖ ሳለ በአቅመ- ደካማነታችን የተነሳ ልንጠቀምበት አለመቻላችን ነው። ከኛ ተነስቶ በሚሄደው ውሀ ግብጽ በብዙ ሚሊዮን ሄክታር የሚሰፈር መሬት በመስኖ እያለማች የምግብ ፍላጐቷን ስታሟላ፣ እኛ በትንሹ እንኳን እንዳንጠቀም መከልከላችን ጥቃት ሁኖ ይሰማኛል። በጽሑፌ ውስጥ እንዳሳየሁት ስንትና ስንት የልማት ጥናቶች ተጠንተው በተግባር ሳይተረጐሙ መክነው መቅረታቸው፣ የአቅመ-ደካማነታችን፣ የተጠቂነታችን ግዙፍ ማስረጃዎች ናቸው። መሬት ጾሙን እያደረ የእርሻ መሬት የገደደው፣ በመስኖ ጥሩ ምርት ማምረት ሲችል በድርቅ የሚጠቃ፣ መጥገብ ሲገባው የሚራብ፣ እንደ ዐባይ ተፋሰስ ሕዝብ ያለ የለም። ይህ ያሳዝናል። 
የውሀ አጠቃቀም ከተፋሰስ በላይ ወይም በታች በኩል በመገኘት አይደለም። በደጋ ወይም በቆላ በመገኘት አይደለም። በጽሁፌ ደጋግሜ እንዳሳየሁት የውሀ አጠቃቀም ከአቅም ወይም ከኃይል ሚዛን ጋር የሚሄድ ነው። ስለዚህ የዐባይን ውሀ ለመጠቀም ከፈለግን የዘለቄታው መፍትሄ (ኢኮኖሚያዊ፣ ወታደራዊና የተማረ-የሰለጠነ የሰው ኃይል) አቅማችን መገንባትና ከባላጋራዎቻችን ጋር አቻ ሁነን መገኘት ነው። ዓለም አቀፍ ያገር-አቋራጭ ወንዞች አጠቃቀም ሕግጋት ሊረዱን/ሊደግፉን የሚችሉት አቅም/ኃይል/ጡንቻ ለማሳየት ስንችል ብቻ ነው። በየትኛውም መድረክ እየተገኘን ያለ የሌለ ተቃውሞ ብናሰማ ያላቅም አድማጭ አይኖረንም። ዐባይን ያላቅም ልንጠቀምበት አንችልም። 
በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የሚወጠን የልማት ውጥን፣ ትርፍና ኪሳራ፣ ጥቅምና ጉዳት የሚሰላበት ብቻ ሳይሆን፣ የጥቃት መወጫና የመብት ማረጋገጫ ሁኖ መታየት ያለበት ይመስለኛል። ስለዚህም ነው በዐባይ ተፋሰስ ውስጥ የተጀመረውን “ሕዳሴን” የምደግፈው። የሕዳሴ ጥቅም ገና ወደፊት የሚታይ ይሆናል። የጥቃት መወጫና የመብት ማስከበሪያ ምልክትነቱን ግን እወደዋለሁ። 
ዐባይ ከጭቃና ከፖለቲካ አይጠራም። ዐባይ ከፖለቲካ እማይጠራ መሆኑ የሚታመንበት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አቋሟን ማጠናከር ይኖርባታል። በተለያዩ ዓለም አቀፋዊ መድረኮች የሚወክሏት፣ የሚከራከሩላት፣ እንደ ግብጾች ተደማጭነትና ክብደት ያላቸው ፖለቲከኞች/ዲፕሎማቶች ያስፈልጓታል። እነዚህንና እነዚህን የመሳሰሉ ሰዎች ለማፍራት አሁንም የኢኮኖሚ ጥንካሬ/አቅም ወሳኝ ነው። በደካማ ኢኮኖሚ የነጠረና ልምድ ያካበተ የሰው ኃይል ማፍራት አይቻልም። 
የሕዳሴ ግድብ መነጋገሪያ ከሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ በተለያዩ የሕዝብ መገናኛ ዘዴዎች አልፎ አልፎ እንደዋዛ የሚሰነዘሩ አነጋገሮች ይሰማሉ። እነዚህ አነጋገሮች፣ አንደኛው “ውሀው እሚያመነጨው የኤሌትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ፣ ውሀው ለግብጽ” የሚል ነው። ሁለተኛው ደግሞ “ኢትዮጵያ የዐባይ ወንዝ ባለመብትነቴ ይከበርልኝ ስትል፣ በወንዙ ላይ አንድ ወይም ሁለት ግድብ ልገድብ ማለቷ ነው” የሚል ነው። ይህ ወጥመድ ውስጥ እሚያስገባ አባባል ስለሆነ፣ ከወዲሁ መጠንቀቅ ይገባል። ኢትዮጵያ ከውሀ የሚመነጭ ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ ለመስኖ ልማት የሚውል ከዐባይ የውሀ ድርሻ እንዲኖራት ትፈልጋለችና ይህን ግልጽ አድርጐ በሚገኘው መድረክ ሁሉ ማሳወቅ የሚጠቅም ይመስለኛል።
አንባቢዎች፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ያሉ መረጃዎች ሁሉ የተወሰዱት ከሚከተለው መጽሐፍ ነው። ዐባይን በሚመለከት ብዙ ቁምነገሮችን ያካተተ መጽሐፍ ነው። ጽሐፊው ግብጽ ውስጥ ብዙ የቆዩ፣ ካይሮ ዩኒቨርሲቲ ያስተማሩ፣  የተፋሰሱን ሀገሮች ተዘዋውረው ያዩና ባለስልጣኖችን ያነጋገሩ አሜሪካዊ ናቸው። አንብቡት። John Waterbury (2002) The Nile Basin: National Determinants of Collective Action; Yale University Press, London.

No comments:

Post a Comment