Tuesday, August 5, 2014

“ስለእኔ አታልቅሱ!”(ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

“ስለእኔ አታልቅሱ!”(ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )



“ዋይ ዋይ ከሚሉና ሙሾ ከሚያወጡ ሴቶችና ከሕዝቡ እጅግ ብዙዎች ተከተሉት፡፡ ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፡- እናንተ የኢየሩሳሌም ልጆች ለእኔስ አታልቅሱልኝ፤ ዳሩ ግን፡- መካኖችና ያልወለዱ ማኀፀኖች፣ ያላጠቡ ጡቶችም ብፁአን ናቸው የሚሉበት ጊዜ እነሆ ይመጣልና ለራሳችሁና ለልጆቻችሁ አልቅሱ፡፡” (የሉቃስ ወንጌል ም. 23 ቁ. 27-30) ከቅዱስ መጽሐፉ ይህን የመሲሁ የመጨረሻ ምክር የመረጥኩት (ምንም እንኳ ረቢው የተናገረው ስለመለኮታዊው ትምህርት ቢሆንም) ዓለማዊው ፍች የኢትዮጵያችንን የወቅቱን መንፈስ ለመረዳት ከማስቻሉም በዘለለ፤ በየጊዜው እያየን፣ እየሰማን ያለነውን የፖለቲካ ተቃውሞው የጥምዝምዞሽ መንገድ በአርምሞ ለመመርመር መልካም ምሳሌ ይሆናል በሚል እሳቤም ነው፡፡

የሠላማዊ ትግሉ መቀልበሻ ስልቶች

እፍኝ በማይሞሉ ፋኖዎች ከአርባ ዓመታት በፊት “ደደቢት” በተሰኘ የሰሜን በርሃ የተመሰረተው ህወሓት ከተራዘመ የትግል ጉዙ በኋላ፤ ታጋይ ሕላዊ ዮሴፍ “እልፍ ሆነናል” እንዲል፤ ራሱን አጠናክሮ “እልፍ” በመሆን ሥልጣን ይዞ፣ የሀገሪቷን አንጡራ-ሀብት አመራሩ መምነሽነሺያው ካደረገ፣ እነሆ ሃያ ሶስት ዓመታት እንደዘበት ነጎዱ፡፡ ርግጥ ነው ይህች የዳንኪራ እና ፌሽታ ዘመን እውን ትሆን ዘንድ፣ የቡድኑ ዋና ዋና መሪዎችም ሆኑ መላው ታጋይ (የበረከቱ ተቋዳሽ ባይሆንም) በቃላት ሊገለፅ የማይችል የመከራ ዓመታትን በቆራጥነት ማሳለፋቸው የሚስተባበል ታሪክ አይደለም፡፡ ሥልጣን እጃቸው ከገባ በኋላም የአገር ጥቅም መገበርን ጨምሮ እየገደሉ፣ እያሰሩና እያሰደዱ… በሕዝብ ላይ ወደር የለሽ ጭካኔን በመፈፀም ዘላቂነቱን እንዲህ ስለማስረገጣቸውም ተወርቶ የተዘጋ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ይሁንና ከዕለት ዕለት እየመረረና እየከፋ የመጣው ይህ ኩነት፣ ምድሪቷ የአንድ እውነት መዝጊያና የአዲስ ዓመት ምዕራፍ መክፈቻ ላይ መድረሷን ስለማመላከቱ ለመመስከር ጠቢብነትን አይጠይቅም፤ የዘመኑ መንፈስ እያሰማን ያለው “ፋኖ ተሰማራ”ም የሶስተኛው አብዮት ደውል ስለመሆኑ ለመረዳት የቀደሙ ነብያቶችን ትንበያ መጠበቅ አያሻም፡፡

ገዥዎቻችን፣ መግደልና ማሰርን ሱፍ ለብሶ፣ ከረባት አስሮ፤ ጠዋት ወደ ቢሮ ተገብቶ፣ ማታ የሚወጣበት መደበኛ ሥራ ከማድረጋቸውም ባለፈ፣ የሥልጣን ግዛታቸውን እንዲህ ነቅተው (ታጥበውና ታጥነው) ባይጠብቁት ኖሮ፣ ለሃያ ሶስት ዓመት ቀርቶ፣ ለሃያ ሶስት ሰዓት እንኳን በቤተ-መንግስቱ መቆየት እንደማይችሉ አብጠርጥረው ያውቁታል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ፍሬ-ሃሳብም በዚህ መልኩ የሥልጣን ዕድሜውን ገና የማቱሳላን ያህል ማራዘም የሚፈልገው ኢህአዴግ፣ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚያቀነቅኑት የሠላማዊ ትግል አቅጣጫን የሚቀይስበትን እና የሚወስንበትን የሴራ ፖለቲካ፣ ለውጥ ፈላጊው ኢትዮጵያዊ ነቅቶ እንዲያከሽፈው መቀስቀስ ነው፡፡

ዛሬ በርካቶች በቁጭት እንደሚብሰለሰሉት ኢህአዴግ በመንበሩ ላይ ከሁለት አስርታት በላይ ተደላድሎ የመቆየቱ ምስጢር በውስጣዊ ጥንካሬው፣ አሊያም ሲቪል ጀግኖች በመጥፋታቸው ሳቢያ አይደለም (ወላድ በድባብ ትሂድና፤ ሀገሪቱ የሚሞትላት ጀግና ትውልድ ከመፍጠር መክና አታውቅም)፡፡ የግንባሩ ዋነኛ የጥንካሬ ምንጭ የተቃዋሚውንም ወገን የቤት ሥራ ጠቅልሎ እየሰራ በመሆኑ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ወደኋላ ሄደን በአደረጃጀትም ሆነ በድጋፍ መሰረታቸው ‹‹የተሻሉ›› ሊባሉ የሚችሉ ተቀናቃኝ ፓርቲዎችን ሂደት ብንመረምር፣ መራራውን እውነታ እየጎመዘዘንም ቢሆን መጋታችን አያጠራጥርም፡፡ ለማሳያ ያህልም በአገዛዙ የማስቀየሻ እርምጃ ተጠልፈው ከከሸፉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎች መካከል ጥቂቶቹን በአዲስ መስመር እንመልከት፡፡

ኦነግ

የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር፣ መለስ ዜናዊና ጓዶቹ ቆንጥረው ከሰጡት የሽግግር መንግስት ሥልጣኑ ተገፍቶ ከወጣ በኋላ ወደለመደው በርሃ በገባበት ወቅት፣ በአንፃራዊነት ቀድሞ መገንባት ከቻለው ጥንካሬ ባሻገር፣ በኦሮምኛ ተናጋሪው ማሕበረሰብ ዘንድ የሚሊዮኖችን ልብ ይበልጥ ማማለል ችሎ እንደነበረ የአደባባይ ሐቅ ነው፡፡ ወቅታዊውን የኃይል አሰላለፍ ጠንቅቆ የተረዳው “አባ መላ”ው ኢህአዴግም የጠብ-መንጃ ግብግቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ፣ ከተማውን ለቆ ያልወጣውን የአመራር አባሉን ኢብሳ ጉተማን ወደ እስር ቤት ወረወረ፤ ይህንን ተከትሎም ኦነግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በእልህና በቁጭት ተነሳስቶ አርሲና ሐረርን አስተባብሮ፣ ወለጋን በታንክ አቋርጦ፣ ባቱ ተራራን በመድፍ ጩኸት አንቀጥቅጦ፣ በባሌ ተሻግሮ ፊንፊኔ ላይ በድል ሊንጎማለል ነው ተብሎ ሲጠበቅ፤ በግልባጩ ዋና ፀሀፊው ሌንጮ ለታ እና የተወሰኑ መሪዎቹ በቦሌ በኩል በመመለስ “ወይ እኛንም አብራችሁ እሰሩን፤ አሊያም ጓደኛችንን መልሱልን?” በማለት ከመረጡት የኃይል ትግል ጋር የማይጣጣም ስልት ተግብረው አረፉት፤ በዚህም የልብ ልብ የተሰማው ኢህአዴግ፣ የድርጅቱን አባላትም ሆነ ኦሮምኛ ተናጋሪውን በጅምላ በ “ስመ-ኦነግ” እየወነጀለ ለአስከፊ እስር መዳረጉ፣ በክልሉ ላይ ከባድ ፍርሃት አነበረ፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ስህተትም ለዛሬው ሽንፈቱ ዋነኛ ተጠቃሽ ሲሆን፤ የተቃውሞ ጎራ ትግሉንም ከሥርዓት ለውጥ ወደ እስረኛ ማስፈታት ያወረደ ቀዳሚ ኩነት ሆኖ በታሪክ ተከትቧል፡፡

መአሕድ

የፕ/ር አስራት ወልደየስ የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ውድቀትም ከኦነግ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ መአሕድ በምስረታው ማግስት ያገኘው መጠነ-ሰፊ የሕዝብ ድጋፍ፣ ህወሓት/ኢህአዴግ በ17 ዓመታት ከሰበሰበው ሁሉ ይልቅ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡ ይህ አይነቱ ፈጣን ግስጋሴም ሊያስከትለው የሚችለውን የቁጣ ናዳ አስቀድሞ የተረዳው ‹‹ብልጣ-ብልጡ›› ኢህአዴግ፣ ሊቀ-መንበሩን ጉምቱ የሕክምና ሊቅ ጨምሮ ጥቂት የአመራር አባላቱን እስር ቤት ወረወረ፡፡ ከዚያማ ድርጅቱ ‹‹እታገልለታለሁ›› የሚለውን የፖለቲካ ሥልጣን የመቆጣጠር ዓላማውን ‹‹መሪዎቻችን ይፈቱ!›› ወደሚል አኮስሶ ባለበት ሲረግጥና ሲዳክር ለ13 ዓመታት ከቆየ በኋላ፣ በስተመጨረሻ ህላዊነቱ አክትሞ ወደ ሕብረ-ብሔር (መኢአድ) ድርጅትነት መሸጋገሩ ታወጀ፡፡ ክስተቱም አብዮታዊው ግንባሩ የተቃውሞ ጎራውን እንቅስቃሴ ወደፈለገው አቅጣጫ መዘወሩን በሚገባ እንደተካነበት ያስረገጠ ሆኖ አልፏል፡፡

ቅንጅት

ዛሬ ዛሬ እንደ ንግስት ሳባ ዘመን የሩቅ ጊዜ ታሪክ ያህል ይሰማኝ የጀመረው ምርጫ 97ም ሌላኛው የነገረ-አውዱ አስረጂ ነው፡፡ በጥቂት ወራት ውስጥ ከጫፍ ጫፍ ሀገራዊ ንቅናቄ መፍጠር የቻለው ግዙፉ ቅንጅት በአብዛኞቹ የምርጫ ጣቢያዎች በይበልጥ ደግሞ በገጠር አካባቢዎች አሸናፊ መሆኑ በተለያዩ አጣሪ አካላት በመረጋገጡ፤ የኢህአዴግን‹‹መንግስት ለመመስረት የሚያስችለኝ ድምፅ አግኝቻለሁ›› ጨዋታን ከውስጥም ከውጭም አምኖ የተቀበለ አንድም እንኳ አልነበረም፡፡ በአዲስ አበባ አንዳንድ አካባቢዎች ይህንንዓይን ያወጣ ስርቆት በሠላማዊ መንገድ ለመቃወም በሞከሩ ዜጎች ላይ በተወሰደው ርህራሄ አልባ የኃይል እርምጃ በርካታ ንፁሀን ለህልፈት እና ለአካል ጉዳት ሲዳረጉ፣ በተወሰኑየክልል ከተሞች ደግሞ ከፍተኛ ሕዝባዊ ማጉረምረም ተፈጥሮ እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ግና፣ ‹‹ብልሆቹ›› የኢህአዴግ ኤጲስ ቆጶሳት በተካኑት ስልት የቅንጅቱን መሪዎች ከያሉበትሰብስበው እስር ቤት ከተቱ፤ ትግሉም ከተነሳበት ‹‹የገጠሩ ወገኖቻችን ድምፅ ይመለስ!›› ወደ ‹‹መሪዎቻችን ይፈቱ!›› ቀኝ ኋላ ዞሮ፣ የሥርዓቱ ዕድሜ እንዲቀጥል ስለመፍቀዱ የእኔ ትውልድ የአይን ምስክር መሆኑ ርግጥ ነው፡፡

ሕዝበ-ሙስሊሙ

ለሶስት ዓመት ተመንፈቅ (ከ‹‹እፎይታ ጊዜ››ው በቀር) ካለማቋረጥ በተቀጣጠለው የሙስሊሙ ኃይማኖታዊ ነፃነትን የማስከበር ትግልም፣ የንቅናቄው አስተባባሪዎች ‹ቃሊቲ የታጎሩትን መሪዎች የማስፈታት ዓላማ በአራተኛነት የተያዘ ነው› ቢሉም (‹‹አህባሽን በግዴታ ማጥመቅ ይቁም››፣ ‹‹መጅሊሱ ወደ ሕዝቡ ይመለስ›› እና ‹‹ነፃ ሕዝባዊ ምርጫ ይካሄድ›› የሚሉት ሶስቱ መሪ ጥያቄዎች የተቃውሞ መነሾ እንደሆኑ ልብ ይሏል)፤ የሕዝበ-ሙስሊሙ በተለይም የቅርብ ጊዜዎቹ የመስጂዶቹ እምቢ-ባይነቶች፣ ሥርዓቱ ለማደነቃቀፍ (ዓላማውን ለማስቀየስ) ባዘጋጀው የ‹‹ይፈቱ›› ማዕቀፍ ስር የተገደበ የመምሰል አዝማሚያው ነው በዚህ አውድ እንድጠቅሰው ያስገደደኝ፡፡ በርግጥ የሁለት አስርታቱን የተቃውሞ ልምድ በቅጡ የመረመሩ የሚመስሉት የ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ወጣቶች፣ በዚህ የተለመደ የትግል ቅልበሳ ላለመጠለፍ የሚያደርጉት ብርቱ ሙከራ እንዳለ ብገነዘብም፣ ከቀደመው ‹‹ጥቁር ሽብር›› ወዲህ በቀጣይ በሚኖሩት የትግል ወቅቶች ዋነኛ የትግል ጥያቄያቸውን ነፃነታቸውን በማስከበር ማዕቀፍ ስር እንደሚያደራጁት አምናለሁ፡፡

ማልቀስስ ለማን?

በ1983ቱ የመንግስት ለውጥ ዓለም አቀፋዊው አውድ፣ ለሽፍቶቹ ስብስብ እርግማንም በረከትም ይዞ ነበር፡፡ እርግማኑ፣ በቀደመ-ፖለቲካዊ ዝማሜያቸው ዝግ ሶሻሊስት ሥርዓት መመስረት አለመቻላቸው ሲሆን፤ በረከቱ ደግሞ በረዥሙ የእርስ በእርስ ጦርነት ክፉኛ የተመታችውን አገር በተለይም ተቋሞቿን ለመገንባት ከሚያስፈልገው ጊዜ አኳያ የምዕራባውያኑን ‹‹ዕድል እንስጣቸው›› የድጋፍ ልብ ማግኘታቸው ነው፡፡ በእነ ሳሙኤል ሀንቲንግተን ‹‹መድበለ-ፓርቲ ሥርዓትን እርሱት፤ አውራ ፓርቲነት ያዋጣችኋል›› ምክረ- ሐሳብ አማካኝነት የወቅቱ ምዕራባውያን አለቆቻቸውን መንፈስ መረዳታቸውን ወደኋላ ስንገነዘብ፤ ቢያንስ እስከ 97 ድህረ-ምርጫ ውጥንቅጥ ድረስ በተጓዙበት የአምባ-ገነንነት መንገድ በጥብቅ አለመወገዛቸውን እንረዳለን፡፡ በአናቱም በህወሓትና መሰል ነፍጥ አንጋቢ የድህረ-ቀዝቃዛው ጦርነት ቡድኖች ላይ ተስፋ የነበራቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ምሁራንም ዘግይተውም ቢሆን ቡድኖቹ ወደ ቋሚ ሽፍትነት መቀየራቸውን ከመመልከት አልዳኑም፡፡ የዚህ አይነት ስብስብ ቋሚ መለዮ፣ በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ ሙሉ ሀገራዊ ሀብት ማፍሰስ ነው፤ መግፍኤውም ግልፅ ነው፤ የሕብረተሰቡ የአምራችነት ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ አቅም ሲጎለብት፣ እነርሱም የሚያግበሰብሱት ሀብት እየሰፋና እየበዛ እንዲሄድ የማስቻሉ ሀቅ ነው፤ እንደ ህወሓት ያሉ የነፃ-አውጪነት የኋላ ታሪክ ያላቸው ገዢ ቡድኖች፣ በምርጫ ፖለቲካ የማይነቀነቁባቸው ምክንያቶችም ከዚሁ ጋር ይተሳሰራል፤ ከሰላማዊ ሕዝባዊ ዓመፅ ውጪ ይህን ነውረኛ ቡድን ማስቆም እንደማይቻል በ‹‹ሕዳሴ አብዮት›› ርዕሰ-ጉዳይ ለመከራከር የሞከርኩትም ለዚሁ ነው፡፡ እንግዲህ ከእስክንድር ነጋ እስከ ርዕዮት አለሙ፤ ከውብሸት ታዬ እስከ የሱፍ ጌታቸው፤ ከአንዱአለም አራጌ እስከ በቀለ ገርባ፤ ከጦማሪያኑ እስከ እነ ሐብታሙ አያሌው… ድረስ ዘርዝረን የማንጨርሳቸው የእልፍ አእላፍ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን መታሰር አሳዛኝ ቢሆንም፤ ለእነርሱም ሆነ ለሀገር የሚበጀው ‹‹ታጋይ እንጂ ትግል አይሞትም!›› የሚለውን የጊዜውን አስገዳጅ ሕዝባዊ ጥሪ በመቀበል አደባባዩን በቁጣ ማጥለቅለቅ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ዛሬ እያየነው እንዳለው የግፉአኑን መፈክር አንግቦ መነሳትን ገሸሽ አድርጎ፣ የ‹‹ይፈቱ›› ጥያቄ የትግሉን መንፈስ ይመራው ዘንድ መፍቀድ ሂደቱን ለሥርዓቱ ሴራ አሳልፎ እንደመስጠት የሚቆጠር ይመስለኛል፡፡

መግቢያዬ ላይ የጠቀስኩት የመምህሩ ቃል የሚነግረንም ለእነሱ ከማልቀስ ይልቅ፣ የአምባ-ገነኑን ሥርዓት ቀንበር ተሸክመን በአሳረ-ፍዳ ኑሮአችንን ስለምንገፋው ስለራሳችን ብናለቅስ የተሻለ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም አብዝተን ነፃነታቸውን የምንሻላቸው ጀግኖቻችን እንደምኞታችን ቢፈቱና መፃኢ ዕድላቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ራሳችንን ብንጠይቅ፣ የምንፋጠጠው ‹ተመልሰው በኢህአዴግ የብረት ጫማ ስር ለጥ-ሰጥ ብሎ ማደር› ከሚል እውነታ ጋር ብቻ ነው፡፡የተለመደውን ‹‹የይቅርታ ቃጭል›› አጥልቀው፣ በተሰበረ መንፈስ ከትግሉ ርቀው አንደበታቸውን ሸብበው አሊያም ከሀገር ወጥተው ቀሪውን ህይወታቸውን በስደት እንዲያሳልፉ ከማድረግ ያለፈ የምንፈጥርላቸው ወይም የምናመቻችላቸው ምንም ነገር አለመኖሩ ርግጥ ነውና፡፡ ያውም ብርቱካን ሜደቅሳን ለቅቆ፤ ርእዮት ዓለሙን የሚያስርበትን የቆየ የፖለቲካ ጨዋታውን ሳንዘነጋ፡፡ ይህም ነው ሕዝብን የማዳመጥ አንዳችም ልምድ ለሌለው ሥርዓት ‹‹ይፈቱ!››፣ ‹‹ይለቀቁ!›› እያልን ከመጮኽ በመቆጠብ፣ ታሳሪዎቹ ስለተዋደቁባቸው የነፃነት እሴቶች መተግበር መታገልን ግድ ያደርገው፡፡

በጥቅሉ በመከራው ዳገት ላይ ያሉት ወገኖቻችን የገጠማቸውን ሁነት ያስነሳው፣ ማናችንም በነፃነትና በእኩልነት ልንኖርባት የምትገባዋን አገር የመናፈቅ እንደሆነ ከተስማማን ዘንዳ፣ በየእስር እርምጃው የተፈጠሩትን ክፍተቶች እየደፈንን፣ የነፃነቱን ቀን ለማቅረብ መታተር የወቅቱ አስገዳጅ ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በቀድሞው የቅንጅት አመራሮች የገፍ እስር ማግስት፣ የከተሞቹን ንቅናቄዎች ከ‹‹ይፈቱልን›› ይልቅ፣ ‹‹ድምፃችን ይመለስልን!›› በሚለው መሠረታዊ ጥያቄ አጥብቀን ይዘን ትግላችንን ብናራዝመው ኖሮ፣ ፖለቲካዊ ለውጦችን መጨበጥ እንችል እንደነበር ማናችንም ብንሆን የምንጠራጠር አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አኳያም የሚያስማማን ዋነኛ ጭብጥ፣ ቢያንስ የ2002ቱ ምርጫ በተካሄደበት አስቂኝ ድራማ ልክ ተከናውኖ እና ተቀልዶብን የማለፉ ዕድል እጅጉን ያነሰ የመሆኑ ጉዳይ ነበር፡፡

ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ ያየናቸው የጦማሪያኑና የሶስቱ ፓርቲዎች ወጣት አመራሮች እስር፣ በተለመደው የ‹‹ይፈቱ›› ደካማ የትግል ስልት የመሄድ ዳርዳርታውን ገርተን፣ ከአደባባዩ መራቃቸውን ተከትሎ እየተፈጠረ ያለ የሚመስለውን (ከማሕበራዊ ድረ-ገፆች እስከ የዕለት ተዕለት የፓርቲዎቹ እንቅስቃሴ ድረስ) ክፍተት መሻገሩ፣ የተሻለ ብቻም ሳይሆን ገዢዎቻችን እንድንሰምጥበት ከሚሹት የሽንፈት ማጥ ውስጥ ከመነከርም የሚገታ አማራጭ ነው፡፡

እነሆም ለማንስ ማልቀስ ይገባል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚያስፈልገን እንግዲህ በዚህ ከባድ ወቅት ላይ ነው፡፡ …እንደየተነሱበት አውድ ለሚያምኑባቸው ክቡድ ዕሴቶች ዘብጥያ ለተጣሉት ዜጎች መብሰልሰልን በመምረጥ ከጎናቸው መሰለፍን ላንገራገርነው ለኛ ማዘን የበለጠ የተገባ ነውና፣ እነርሱ ድርሻቸውን ስለመወጣታቸው እያመሰገንን፣ ፍትሃዊ አቋሞቻቸውን በገዘፈ ጉልበት ወደፊት መውሰድ ብቸኛው ምርጫችን መሆን ይኖርበታል፡፡ የ‹‹ሕዳሴው አብዮት›› ተግባሮትም አስፈላጊው ሥነ-ልቦና ይኸው ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ድል ለግፉአን ኢትዮጵያውያን

No comments:

Post a Comment