Friday, December 28, 2012

እናት ዓለም ደረስኩልሽ ግጥም በወሰን ሰገድ ገብረ ኪዳን

እናትዓለም ደረስኩልሽ(ወሰን ስግድ ገብረ ኪዳን)
የዕድሜሽ ጀምበር ሲያዘቀዝቅ - እኔ ልጅሽ ደረስኩልሽ፡፡
ደረስኩልሽ እኔ ልጅሽ
ለዘመናት ከተጣባሽ - ማጣት መንጣት ልታደግሽ
ጥገኝነት ከተባለ - ክፉ ደዌ ልፈውስሽ
ከሰው እኩል ሰው ላደርግሽ 
ላንቺም ሥራ ፈጠርኩልሽ፡፡
መራር ህይወት ያዛለውን - ጉልበትሽን ‘ማይፈትን
እንደልምድሽ ‘ሚያኖርሽ - ከአቅምሽ ጋር ‘ሚመጠን
ፈጠርኩልሽ መልካም ሥራ
እንኳን አንቺን ሀገርሽን ‘ሚያኮራ፡፡
የልብ አውቃው እኔ ልጅሽ
የማታ ጣ‘ይ ሳይጠልቅብሽ
ከመጦር ጦር ልታደግሽ
እንደራስሽ ‘ሚያኖርሽ
መልካም ሥራ ዘየድኩልሽ
የሀገሪቱን እድፍ ጉድፍ - ማፅዳት መቼም አያቅትሽ፡፡
አየሽ እናት እኔ ልጅሽ
ጥንቱኑ እንዴት እንደማቅ‘ሽ
ከሰው እኩል ሰው ላደርግሽ
በፍፃሜው ደረስኩልሽ፡፡
አስቀድሞም ደንዳና ነው - ድድር ነው ያንቺ ትከሻ
እንኳንስ ተራ ውዳቂ - እንኳንስ የቤት ቆሻሻ
የመንደር የጎጡን ሁሉ - የሀገሩን የሰው ልቃሚ
ከመቻል በላይ ችለሻል - ኖረሻል ስትሸከሚ፡፡
እናም እናት ይኸውልሽ - ጥቃቅኗን ሥራ ሰርተሽ
ከጥቃቅን ጉስቁልና - ከመመፅወት ወዲያ ርቀሽ
እንድትኖሪ በእጅሽ ፍሬ - እንድትኮሪ በዕድሜሽ ማምሻ
ላንቺም ሥራ ፈጠርኩልሽ - እኔ ልጅሽ አባ-ግርሻ፡፡
አየሽ እናት እኔ ልጅሽ - ያንቺን ህይወት አልረሳሁም
ወትሮም ቢሆን ቁርጠኛ ነሽ
ከፍትፍቱ ፊቱ ‘ሚሉት - አጉል ተረት አይገባሽም
ማዕዱ ሳለ ተዘርግቶ - ሰው የሰው ፊት ምን አሳየው
ነገን በነግ የሚያኖረው - ዋናው ነገር ፍትፍቱ ነው
እናም እናት ቅን አላሚው - እኔ ልጅሽ ዘየድኩልሽ
ፍትፍት ሥራ ፈጠርኩልሽ
እርግጥ ነው አልዘነጋሁም - የኑሮ ጣጣ ፈንጣጣ
አሳሩን አስጨምቆሻል - የቀና ቀን ላያመጣ
የመከራሽን መከር - እያጨድሽ እንዳመጣጡ
ጧሪ ቀባሪ እንዳታጪ - ፀልየሽ ነበር በቁርጡ
ነገር ግን አንቺ ያልታየሽ - በዚህ ዘመናይ ዓለም
ክፋትና ክርፋት ሞልቶት - ቀባሪ እንጂ ጧሪ የለም፡፡
ስለዚህ ዕድሜሽ ቢገፋም - ጉልበትሽን ምን ቢያልምም
የሀገር ቆሻሻ ለማንሳት - ለመጠራረግ አታንሺም፡፡
አየሽ እናት እኔ ልጅሽ - የሞት ጥላ ሳይጋርድሽ
የእጅሽን ጣ‘ም አጣጥምሽ - አንቺው ባንቺ ተመክተሽ
እንድታልፊ ከዚህ ዓለም
ያላለምኩት ነገር የለም፡፡
ባስብ ባስብ - ባስብ ባስብ - ላንቺ ሚሆን ምጥን ሥራ
የለም ጭራሽ በዚች ሀገር - ችግር ገዝፏል ከተራራ፡፡
ይህቺ ምስኪን ቀደምት ሀገር ከዓለም በፊት የነበረች
የገናኖች ገናን ሆና - የሥልጣኔን ያሳተማረች
ቁልቁል ወርዳ ተፍገምግማ
መክሊቶቿን ከእጇ ጥላ በድህነት ተለጉማ
የዓለም ጭራ የሆነችው
ለምን እንደሁ ሳሰላስል - ምስጢሩን ሳብሰለሰልው
እውነቱን ገልጨ ሳየው
አንቺን ባለዕዳ ያረገው
ቆሻሻዋን ከሥር ከሥር - ጠርጋ ባለመጣሏ 'ኮነው፡፡
እናም እናት እኔ ልጅሽ
በስተኋላ ደረስኩልሽ
ከሰው እኩል ሰው ላ'ረግሽ
ላንቺም ሥራ ፈጠርኩልሽ
የሃገሪቷን እድፍ ጉድፍ - ማፅዳት መቼም አያቅትሽ፡፡
አስቀድሞም ደንዳና ነው - ድድር ነው ያንቺ ትከሻ
እንኳንስ ተራ ውዳቂ - እንኳንስ የቤት ቆሻሻ
የመንደር የጎጡን ሁሉ - የሀገሩን የሰው ልቃሚ
ከመቻል በላይ ችለሻል - ኖረሻል ስትሸከሚ፡፡
ጥረጊው - ጥረጊውና - የሃገሩን ሁሉ ቆሻሻ
ላንቺም እንጀራ ይውጣልሽ - ለእኔም ይሁን እጅ መንሻ፡፡


No comments:

Post a Comment