Sunday, January 24, 2016

“እኔም ሆድ ሲብሰኝ እንደዚያ ያልኩባቸው ቀናት አይጠፉም” – ቃለምልልስ ከያሬድ ጥበቡ ጋር | በኦሮሚያ፣ በሁመራ፣ በቅማንት ጉዳዮች ላይ ይናገራሉ | የቀለም ቀንድ ጋዜጣ

አቶ ያሬድ ጥበቡ ይህን ቃለምልልስ ያደረጉት ሃገር ቤት ከሚታተመው የቀለም ቀንድ ጋዜጣ ነው:: በተለይ ውጭ ሃገር ለሚገኘው አንባቢ ግንዛቤ በሚል እንደወረደ አቅርበነዋል:: 
እንደሚያውቁት ብአዴን በቅርቡ የ35ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በተለያዩ ፕሮግራሞች ሲያከብር ቆይቷል። ከድርጅቱ መሥራቶች አንዱ ነዎትና የድርጅቱን ስኬቶችና ድክመቶች በአጠቃላይ የ35 ዓመቱን ትርፍና ኪሳራዎች እንዴት ነው የሚገመግሟቸው? ድርጅቱ ማድረግ ሲገባው ያላደረጋቸውን ነገሮች እና ወደፊት ቢሠሩ መልካም ነው የሚሏቸውን ተግባራት ጨምረው ቢገልጹልን።
የብአዴንን የ35ኛ ዓመት ምሥረታ በዓል ፕሮግራሞች ለማየት ዕድል አልገጠመኝም። የበረከትን ቃለ ምልልስ ብቻ ነው ያየሁት። የገረመኝ የሕወሓት ደጋፊዎች በመሆናቸው የሚታወቁት ወጣት ጋዜጠኞችና ጦማሪያን፣ ብአዴን በትጥቅ ትግሉ ውስጥ ተሳትፌያለሁ ማለቱ ጨርቃቸውን አስጥሎ እንደማበድ ሲያደርጋቸው ማየቴ ነበር። ጀብደኝነት ለትግሬዎች ብቻ የተሰጠ ማዕረግ አድርገው የወሰዱት ይመስላሉ። ይህን በተመጻደቁ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያ ክልል ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ ትጥቅ ሳያስፈልጋቸው እንኳ መጀገን እንደሚቻል አስተማሯቸው። ጦማሪያኑ ልብ ይገዛሉ ብዬ አስባለሁ። ወደ ጥያቄህ ስመልስ፣ የኢሕዴን/ ብአዴን 35 ዓመታት ትርፍና ኪሳራ እንዲህ በቀላሉ በቃለ ምልልስ የሚያልቅ አይመስለኝም። ሆኖም ልሞክር። ትልቁ ስኬት የሚመስለኝ፣ ኢሕአፓን ከሚያህል ትልቅ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የወጣ ኢምንት ኃይል፣ ያን የጨለማ ዘመን አልፎ የሥልጣን ተጋሪ ለመሆን መቻሉ ነው። የሥልጣን ተጋሪ ስል የማይመቻቸው ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። የወያኔ አሽከር መሆን ምን ያኮራል የሚሉ አሉ። እኔም ሆድ ሲብሰኝ እንደዚያ ያልኩባቸው ቀናት አይጠፉም። ሆኖም በእኔ ውሱን መረጃና ዕውቀት መሠረት፣ ባለፉት 25 ዓመታት በዘጠኙ ክልሎች ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ላስተዋለ፣ የተሻለ አስተዳደር ያለው የሚመስለኝ በብአዴን ሥር ያለው የአማራ ክልል የተሰኘው አስተዳደር ነው። ከሕዝቡ ጋር የተሻለ ቅርበት ያላቸው ካድሬዎች ያሉበት ክልል ሆኖ ይሰማኛል። በሙስና ደረጃም ከሌሎቹ ያነሰ ንቅዘት ያለበት ክልል እንደሆነ ነው የምሰማው። ንቅናቄውን ስንጀምር ያደረግናቸው የአምስት ወራት ውይይቶችና፣
በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበረን ጥብቅ ሥነ ምግባርና ከኢሕአፓም ሰንቀን ያመጣናቸው ሕዝብና አገር ወዳድ ስሜቶች ገና ተመንዝረው ስላላለቁ ይመስለኛል።
ሌላው የኢሕዴን/ብአዴን አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሕወሓትን ጠባብ ብሔረተኝነት እየታገለ፣ ‹‹አይዞን ይቻላል›› እያለና እያደፋፈረ፣ ነጻ የትግራይ ሪፐብሊክ ከመመሥረት፣ በአጠቃላይ ደርግን ወደመገርሰስ ትግሉ እንዲሸጋገር ያደረገው አስተዋጽኦ ይመስለኛል። በዚህም ላይ ‹‹መሃል አገር መጥተው ከሚያምሱን ቢገነጠሉ ይሻለን ነበር›› የሚሉ ድምጾች መኖራቸው ጠፍቶኝ አይደለም። ግን ትግራይና ኤርትራ ተገንጥለው ደርግን ቢተውት፣ ደርጉ፣ ደቡቡንና መሃል አገሩን እያደራጀ እንቅልፍ ይነሳቸው ስለነበር፣ ባይወዱ እንኳ ተገደው የሱማሌና ኦሮሞ አማጺያንን ወደማጠናከርና የኢትዮጵያን መበታተን ግፊት ያደርጉ ነበር። ስለሆነም የኢሕዴን መኖር ሕወሓት ተደፋፍሮ ወደመሃል አገር እንዲመጣና የአገሪቱም አንድነት እንዲጠበቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ይመስለኛል።
የኢሕዴን/ብአዴን ድክመቶቹ ከዚሁ በመሃል አገር ሥልጣን ከመያዝ ጋር የተቆላለፉ ናቸው። በሁለት ደረጃ ነው ድክመቶቹ የሚታዩኝ። አንደኛው፣ በአመዛኙ የአርሶ አደር ድርጅት ስለነበርና፣ መሃል አገር ከደረሰም በኋላ ሊቀላቀለው ይችል የነበረው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ በጥርጣሬ እንዲያየው ስለተገደደ፣ ቶሎ ብሎ የልሂቁን ድጋፍ ማግኘት አልቻለም። በአንጻሩ ሕወሓት ፊደል የቆጠረውን ትግሬ ሙሉ (መቶ በመቶ ባይሆንም) ድጋፍ ማግኘቱ፣ ቢሮክራሲውን፣ ፋይናንሱን፣ መሬቱን ፈጥኖ እንዲቆጣጠር ረድቶታል። በወቅቱ በደቡብ የአገራችን ክፍሎች፣ በተለይ በኦሮሞ ክልል በአማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ይካሄድ የነበረውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመቃወም መአሕድ መቋቋሙና፣ መአሕድንም በዋነኛነት የመታገሉ ተልዕኮ ለኢሕዴን በመሰጠቱ፣ ድርጅቱ ከኅብረ ብሔራዊነቱ አሽቆልቁሎ፣ መኖሩ እንኳ አጠራጠሪ የሆነ፣ የአማራ ብሔርተኛነት ወኪልነትን ለራሱ መረጠ ወይም በሕወሓት አስገዳጅነት ተቀበለ። አመራር አባላቱ ከኤርትራ እስከ ሲዳማ የሚጣቀሱ ኢትዮጵያውያን
ያሉበት ድርጅት፣ አማራ ነኝ ሲል ‹‹ቱሪስት ብላ›› ከመባሉ ባሻገር፣ ከክልሉ ውጪ ዜጎች አማራ ናችሁ በመባል በሚደርስባቸው የንብረትና ሕይወት እጦት ሊደርስላቸው የሚችል ድርጅት ሊሆን ስላለቻለ (ቢያንስ ተቃውሞውን በመድረክ የሚያሰማ)፣ የአማራ ብሔርተኝነቱ ስማዊ (አፋዊ) ከመሆን አልፎ፣ በግድያውና መፈናቀሉ ተባባሪነት ስሙን የሚያጎድፍ ሊሆን በቅቷል። በተለይ እንደ ታምራት ላይኔ፣ ዳዊት ዮሐንስና ተፈራ ዋልዋን የመሳሰሉት መሪዎቹ የጠዋት ማታ የውግዘት መፈክራቸው ነፍጠኛ ብለው የሚጠሩት አማርኛ ተናጋሪ ሕዝብ መሆኑ፣ ለድርጅቱ መጠላትና መገለል የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል።
በሁለተኛ ደረጃ፣ ምንም እንኳን ኢሕዴን ወደአማራ ክልል አስተዳዳሪነት ቢወሰንምና፣ ከክልሉ ውጪ ባሉ አማርኛ ተናጋሪዎች ላይ ለሚደርሰው ጥቃት ተከላካይ ሆኖ ባይገኝም፣ አሁን ላይ ሆኜ ሳየው፣ ድርጅቱን የወያኔ አሽከር አድርጎ ኮንኖ የዳር ተመልካች ሆኖ ከመቀመጥ፣ ኢትዮጵያዊው ብሔርተኛው ኃይል ቢቀላቀለው ይሻል ነበር ብዬ የማስብባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም። ፖለቲካ ውስጥ ኩርፊያ መሣሪያ መሆን የሚችል አይመስለኝም። የመሃል አገሩ ሰው ከማኩረፍ ይልቅ፣ በእጁ ያለውን ይዞ (ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል አይደል የሚባለው)፣ ብአዴንን ተቀላቅሎ ቢሮክራሲውንም፣ የባንክ ብድሩንም፣ የመሬት ቅርምቱንም እየተሻማ ቢቀጥል ይሻል ነበር ወይ ብዬ ያሰብኩባቸው ጊዜያት ብዙ ናቸው። የመሃል አገሩ ሰው ይህን ሲያደርግ፣ ኦሮሞው ደግሞ በኦነግ ዙሪያ ተመሳሳይ ተሳትፎ አድርጎ ቢሆን ኖሮ፣ ዛሬ የምናየውን የትግራይ ኤሊት እብለላ (ጥጋብ) (በትግርኛ dominance ለማለት ይጠቀሙበታል) ባላስከተለ ነበር።
ሌላው የኢሕዴን/ብአዴን ችግር ከመጀመሪያው ጀምሮ በአገውነታቸው ወይም ትግሬነታቸው ማንነት ላይ ግልጽ አቋም መያዝ ያልቻሉ ግለሰቦች በውስጡ ያሉበት መሆኑ ነው። በአመራሩ ደረጃ ታደሰ ካሳና (ጥንቅሹ)፣ ካሳ ተክለብርሃን ያ ችግር ያለባቸው ሰዎች ይመስሉኛል። ሸሪፎ (ካሳ ተ/ብርሃን)፣ ኋላ የተቀላቀለን ትንሽ ልጅ ስለነበር ብዙም አላስታውሰውም። ጥንቅሹን
ፖለቲካ ገና አልገባንም ነበር። ዓላማ፣ መስዋዕትነት፣ ቅንነት፣ ሕዝብን ማገልገል ወዘተ. ነበር አዕምሯችንን የሞላው። በችርቻሮ ደረጃ አስፈላጊ የሆነው የፖለቲካ ሀ…ሁ ገና አልገባንም ነበር። ስለሆነም ቅንነታችን ብቻውን ሊረዳን አልቻለም። የወዲ ዜናዊ ፖለቲካዊ ቁማር መመከቻ ብልሃት አልነበረንም። ስለሆነም ተበለጥን።
ከኤርትራ ሁለት ወራት የሚሞላ ጉብኝት በኋላ ወደሰቆጣ ስመለስ፣ ታደሰ ከሻዕብያ የተረከብናቸውን 300 ምርኮኞችና (ኋላ 7 ዓመታት ኢሕዴን ውስጥ ከታገሉ በኋላ ኦሕዴድን እንዲመሠርቱ የተደረጉት ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን) መሣሪያና ገንዘብ ተረክቦ እንዲመጣ ኤርትራ ጥዬው ተመለስኩ። እግረ መንገዴን ወዲ ዜናዊ የነበረበት ወርኢ ቤዝ-አምባ ስደርስ ሊጣላኝ ነገር የሚፈልግ መለስን አገኝሁት። ከታደሰ የሬዲዮ መልዕክት ስለደረሰው ነው ብዬ አልጠረጠርኩም ነበር። ከዓመታት በኋላ ነው ታደሰና ታምራት ከወዲ ዜናዊ ጋር በድብቅ የሚገናኙበት የሬዲዮ ኮድ እንደነበራቸው ያወቅነው። ኋላ አዲስ አበባ ላይ ሥልጣን እንደያዙ የወያኔን ኤፈርት የሚኮርጅ ድርጅት ለአማራው ክልል ሲያቆሙ ታደሰን የጥረት ዋና ኃላፊ አደረጉት። በራሱ በታደሰ እምነት እንኳ ዛሬ ጥረት ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ይቆጣጠራል። የሚገርመው ግን ኤፈርት የእንግሊዘኛው (EFFORT – Endowment Fund For Rehabilitation of Tigray – የትግራይ መልሶ መቋቋም ፈንድ (ድርጅት)) ምህጻረ ቃል ሲሆን፣ ጥረት ግን የእንግሊዘኛው ኤፈርት ቀጥተኛ ትርጉም ነው። ጥረት የማን ነው የሚለውንና ብዙ የኢሕዴን ታጋዮች በየጊዜው ከድርጅቱ የተባረሩበትን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል። የወያኔ አመራር አባላት እነርሱ በቸሩት 40 ሚሊዮን ብር የተቋቋመ ድርጅት መሆኑን ነግረውናል። ግን ታደሰ ጥንቅሹ ከላይ ተቀምጦ፣ ጥረት የሚያስገባውን ገንዘብ ለማን ነው አሳልፎ የሚሰጠው? የድርጅቱ የቁጥጥር ኮሚሸን ገቢ ወጪ ሒሳቡን ይቆጣጠረዋልን? የአማራ ክልል ፈንድ ነው ከተባለ መቼ ነው ሌጀሩን የአማራ ክልል ኦዲተር ፈትሾት የሚያውቀው? ጥያቄዎቹ ብዙ ናቸው።
የታደሰ ካሳንና የካሳ ተክለብርሃንን ጉዳይ የማነሳው  ያለምክንያት አይደለም። በብአዴን ውስጥ መሽገው፣ የወያኔ የአማራን ክልል ግፊት አስፈጻሚ ሆነው በመገኘታቸው ነው። በተለይ ከወልቃይት/ጠገዴና ሁመራ ጋር በተያያዘው የመሬት ጥያቄና፣ በቅማንት የማንነት ጉዳይ የክልሉን አመራሮች በማስጨነቅ፣ ከበረከት ቀጥሎ ጠንካራ ሚና የሚጫወቱት ሁለቱ መሆናቸውን በተደጋጋሚ እሰማለሁ። በተለይ ካሳ ተክለብርሃን ባለፉት ዓመታት ይዞት የቆየውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤነት ሥልጣን በመጠቀም፣ የወያኔ ጥቅም አስከባሪ በመሆን፣ ከአዲስ አበባ ስልክ በመደወል እንደሚያስፈራራቸው ነው ድርጅቱ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ካድሬዎች የሚነግሩኝ። ለመሆኑ ሕወሓት በታሪክ አጋጣሚ ባገኘው ወታደራዊ የበላይነት በኃይል የያዘውን የወልቃይት ጠገዴን ለም መሬት ሕዝብ እየገደለና እያሰረ ይዞ የሚቆው እስከመቼ ነው? ለመሆኑ በረጅም የታሪክ መስተጋብር ቋንቋውንም ሆነ ሃይማኖቱን ለውጦ ከሌላው አማርኛ ተናጋሪ ጎንደሬ ጋር የተዋሐደውን ቅማንቴ የተለየ ማንነት ጥያቄ እንዲያነሳ ለምንድን ነው ግፊት የሚደረገው? በእኔ ግምት በሰሜን ምዕራብ በኩል የትግራይ ክልል አምባገነኖች ተፈጥሯዊውን የተከዜ ወሰን ጥሰው እስከ መሃል ወገራ መጥተው ግጨው እንደደረሱ ነው የምሰማው። በእነርሱ ትንሽ ስሌት የአርማጨሆ በረሃ ብዙም ሰው ስለሌለው፣ ቀሰ በቀስ የትግራይን ችግረኛ እያሰፈሩበት ሰንብተው፣ ትግሬ የሰፈረበት መሬት ሁሉ የትግራይ ነው በሚለው አይዲዮሎጂያቸው ድጋፍ እስከ አይከል ያለውን መሬት ወደትግራይ ክልል ያጠቃልላሉ። ከዚያ ራስ ገዝ አስተዳደር የተሰጠው የቅማንት ሕዝብ ሕዝበ-ውሳኔ በማድረግ ከትግራይ ጋር መቀላቀልን ይመርጣል። አንዲት ጥይት ሳይተኮስ ጎንደር ከተማ በር ላይ ከች አሉ ማለት ነው። በነርሱ ትንሽ አእምሮ ያሰሉት እንዲህ ይመስለኛል። በትዕግስትና ፍርሃት መሃል ያለው ልዩነት የገባቸው አይመስለኝም። ቆስቁሰው ቆስቁሰው ጎንደር ብረቱን ይዞ እንዲወጣ አስገድደውታል። ይሄኛው ትውልድ ያባቶቹን ርስት ማስመለስ ባይችል ጥያቄውንና ትግሉን ለቀጣዩ ትውልድ አውርሶ ያልፋል እንጂ ጥያቄው ከቶም አይሞትም። ያልገባቸው ይህ የመሬት ምዝበራ ጦስ፣ በአዲስ አበባ ካካሄዱት ነቀላና፣ በክልሎች ከሚያካሂዱት የመሬት ነጠቃ ጋር ተዳብሎ፣ የመጨረሻቸው መጀመሪያ ሊሆን መቻሉን ነው። እንደዚያ ግን የግድ መሆን አልነበረበትም።
አፐታይታቸውን ቀነስ አድርገው፣ የሕዝቡን ዋይታ የማድመጥ አማራጭ አላቸው። ዛሬ የሚመኩበት ደህንነትና መከላከያ የቁርጡ ቀን ሲመጣና መግደል ሲሰለቸው፣ አሁንስ አብሬያችሁ አልወድቅም በማለት አፈሙዙን እንደሚያዞርባቸው ወይም እንደሚበታተን መረዳት አለባቸው። ሩቅ መሄድ የለባቸውም፤ 1966ንና የራሳቸውን 1983 ሁኔታ መለስ ብለው ማየት ነው። በወታደራዊ ኃይል ስላሸነፉ ብቻ ሳይሆን (ከደብረ ታቦር ውጊያ በኋላ ትግራይ ነጻ ከወጣ ለምንድን ነው ለሌላው የምንሞተው ወደአገራችን መልሱን ብሎ የከዳቸውን 30ሺህ ጦር ልብ ይሏል)፣ የደርጉ ወታደር ሊከላከላቸው ፈቃደኛ ስላልሆነም ጭምር መሆኑን ያውቁቱል። የቱ ጋ ነው የ‹‹ዲየን ቢየን ፉ››ን የመሰለ ወሳኝ ውጊያ ማድረግ የተገደዱት?
ስለሆነም፣ ወታደራዊ ትምክህቱን ትተው የሕዝቡን ልቦና ማድመጡን ቢመርጡ ይሻላል ባይ ነኝ። ከነዚህ የሕዝብ ጥያቄዎች ሁለቱ፣ የትግራይን ክልል ወሰን ከተከዜ ወንዝ በስተምሥራቅና በስተሰሜን መወሰንና፣ የኢትዮጵያን አርሶ አደሮች ከመንግሥት ጭሰኝነት አላቆ የመሬት ባለቤትነታቸውን ማረጋገጥ ቀዳሚዎቹ መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች ይመስሉኛል። የቅማንት ራስ- ገዝ አስተዳደር ለመመሥረትም ከሚያደርጉት ሙከራ ቢቆጠቡ ውጥረቱን ያረግበው ይመስለኛል። ብዙሃኑ ሕዝብ ያለፈውን የጋራ ታሪክና የነገውን ሁኔታ አርቆ አስቦና ገምግሞ አሰላለፉን ከወገኑ ጋር ያደረገ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ በሕወሓት ተደነባብረውና በጊዜያዊ ጥቅም ተለክፈው ሕዝቡን ለመከፋፈል የሚሠሩት ወገኖች ስላሉ እነዚህ አካላት አቋማቸውን መልሰው መላልሰው መመርመር አለባቸው። ሕወሓት የትግራይ ሪፐብሊክ ለማቆም ዕቅድ በነበረው ወቅት ከሱዳን የሚያዋስነው መሬት ሲፈልግ ተገጥሮአዊውን የተከዜ ወንዝ ተሻግሮ የጎንደርን መሬት የኔ ነው ብሎ ወረረ። አሁን ወልቃይቴዎች ትግሬ አይደለንም አማሮች ነን ሲሉ የግድ ትግሬ ትደረጋላችሁ የሚል የዕብሪት ፖሊሲ ከሚከተል፣ የወልቃይትን ጎንደሬነት ተቀብሎ አስተዳደሩን ለጎንደር ቢለቅ ተገቢ ነው። ከዚህም አልፎ ሄዶ፣ አንድ ቀን ሕወሓት ሲከፋው ይጠቀምበታል ተብሎ የተቀመጠውን የመገንጠል መብት ከሕገ መንግሥቱ ሰርዞ አገሬው ኢትዮጵያዊመቱን ተቀብሎ እንዲረጋጋ ማድረግ አላስፈላጊ ከሆኑ የማንነት ጥያቄዎች መነሳትና ያን ለማብረድ ግድያ ከመፈጸም ያድነዋል። የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ምሬት እየበዛ፣ ጥያቄውም እየገፋና እየተጠነከረ መጥቷልና እንደከዚህ ቀደሙ በግድያና በእስር እንፈታዋለን ማለቱ ውድ ዋጋ ያስከፍላል። በተጨማሪም፣ ሕወሓት ባለፉት 30 ዓመታት የወልቃይት መዘጋ ወይም ቆላ ላይ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ትግራውያን ስላሰፈረ፣ በጉልበት አልያዝኩም ብትፈልጉ በሕዝብ ድምጸ ውሳኔ ወይም ሪፍረንደም ቢል ወልቃይቴው መቀበል አይኖርበትም።
ማነው በሕዝበ ውሳኔው የሚሳተፈው? ማንስ ነው በፍትሐዊ መንገድ መካሄዱን የሚያየው የሚል ጥያቄ ማንሳት ይኖርባቸዋል። ፍትሐዊ ድምጸ ውሳኔ ከመደረጉ በፊት በጉልበት የገቡት የሕወሓት ካድሬዎች ወደትግራይ ተመልሰው አስተዳደሩ ወደ ጎንደር መካለል ይኖርበታል። ለተወሰኑ ዓመታት የማረጋጋት ሥራ ከተካሄደ በሁዋላ ብቻ ነው አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የሪፍረንደም ጥያቄ ሊነሳ የሚችለው። አሁን አይደለም።
ወደፊት ቢሠሩ መልካም ነው ከምላቸው፣ ቀዳሚው የሚመስለኝ፣ ኢሕአዴግ በውስጡ የሐሳብ ድርቀት የሚያጠቃው ድርጅት እየሆነ ስለመጣ፣ ሐሳብ ከውጪ ለመቀበል የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርበታል። አንዱ መንገድ ፕሮፌሽናል መደቡንና ካድሬውን መለየት፣ መንግሥትንና ፓርቲውን መለየት የግድ ይመስለኛል። መንግሥት የሁሉም ዜጎች የጋራ ተቋም መሆኑን በመረዳትም (መንግስት የሚቆመው በሕዝቡ አሥራት ወይም ታክስ እንጂ በፓርቲ አባላት መዋጮ ስላልሆነ)፣ የመንግሥት ሥራ ለሁሉም ዜጎች ክፍት የሆነና፣ ሥራ ለማግኘት የፓርቲ አባልነት አላስፈላጊ መሆኑን በመቀበል፣ በ1997 ዓመተ ምህረቱ ምርጫ ተደናብረው የገቡበትን የማንአለብኝነትና የወመኔ አሠራር መቀየር ይኖርባቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ማድረግ መቻል አለባቸው ወይም ይህን መሠረታዊ ጉዳይ ማስፈጸም ካልቻሉ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ቢለቁ መልካም ነው እላለሁ። አንባቢዎችህን እንዳላሰለች እዚህ ላይ ላቁም።
ኢሕአዴግ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔራዊ መግባባት እና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ተፈጥሯል ይላል። አገዛዙ ይህን ይበል እንጂ ደግሞ በሕዝቦች መካከል ከፍተኛ የሆነ አለመተማመንና ጥርጣሬ ነው ያለው። በብዙ አካባቢዎች የብሔረሰብ ግጭቶች አሉ፤ ዜጎች በተለይ አማሮች በሰፊው ይፈናቀላሉ። በእርስዎ ግምገማ ሁኔታው ወደ አደገኛ የዘር ፍጅት እንዳያመራና የኢትዮጵያን ህልውና እንዳይፈታተን መደረግ አለበት የሚሉት የመፍትሔ ሐሳብ ምንድነው? ብሔራዊ መግባባትና አንድነት ሊመጣ የሚችለውስ እንዴት ነው?
አማሮች ይፈናቀላሉ ላልከው እርግጠኛ አይደለሁም። አማርኛ ተናሪዎች ማለቱ ሳይሻል አይቀርም። ትላልቆቹ፣ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና መስፍን ወልደማርያም ያሉ ሰዎች የአማራ ብሔርን መኖር ሲጠይቁ ማድመጡ የተሻለ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ጎንደሬዎች፣ ጎጃሞች፣ ወሎዬዎች ናቸው የሚታዩኝ። አማሮች ገና ከስንት አበሳና የመሬት ግፊት በኋላ የሚፈጠሩ ነው የሚመስለው። እንደ ትልቅ ፍጻሜ ካየነው፣ አማራነት ከወያኔ ምሬት የተረገዘና ገና በጽንስ ላይ ያለ መስሎ ነው የሚሰማኝ። ወደፊት መወለዱንም እርግጠኛ አይደለሁም። ምነው ሸዋን ረሳኸው ብትለኝ፣ ሸዋ አማርኛና ኦሮሞኛ ተናጋሪ ከመሆኑም በላይ፣ እርስ በርሱ በጣም የተዳቀለ፣ በባርነት ይዟቸው ከነበሩ የቤት አገልጋዮቹ ጋርም የተዋለደ በመሆኑ፣ የዘመናዊት ኢትዮጵያ ጦረኛ ስለነበር ቀዳሚ ማንነቱ ኢትዮጵያዊ ይመስለኛል። አማራ ነህ ብትለው ይከፋዋል፤ አይቀበለውም። ከአማራ ክልል ውጪ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ ግን በየዕለቱ ግፍ የሚወርድበት አማራ ነህ ተብሎ ስለሆነ፣ ሳይወድ በግዱ አማራ እየተደረገ ሳይሆን አይቀርም። ራሱን ለመከላከል ሲልም፣ ሕይወቱን ጠብቆ ለማቆየት እንደ አማራ መሰባሰብ ይገደድ ይሆናል። ምናልባት የአማራ ብሔርተኝነት የሚወለደው፣ ከክልሉ ውጪ ባሉት የቋንቋው ተናጋሪዎች ሊሆን ይችላል። መገፋት የወለደው ብሔርተኝነት።
ለአማርኛ ተናጋሪዎች በየክልሉ ተጠቂ መሆን ትልቁን አስተዋጽኦ የሚያደርገው ሥርዓቱ ዘር ተኮር ቅኝት ያለው በመሆኑ የማንነት ጥያቄ እንዲጎላና፣ ኢትዮጵያዊ ማንነት ሁለተኛ ደረጃና ከዚያም ያነሰ መገለጫ እንዲሆን ለ25 ዓመታት ያደረገው ግፊት ውጤት ነው። ከትግራይ ቤዛቸው ብዙ ርቀው ስለመጡና ቁጥራቸውም አነስተኛ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያዊነትን በማዳከምና ብሔረሰባዊ ማንነት እንዲጎለብት አገሬውን ሁሉ በማነሳሳት፣ በተለይ ኢትዮጵያዊነትና የኦሮሞ ብሔርተኝነት ተገዳዳሪ ኃይሎች መስለው እንዲቀርቡ በማድረግና፣ ኢትዮጵያዊነትን እንደ አማራ ትምክህት በማንቋሸሽ የፈጠሩት የአገዛዝ ዘይቤ ነው በጥያቄህ ያነሳኸውን የርስ በርስ የመተላለቅ አደጋ የጋበዘው። ትልቁም መፍትሔ መንግሥትና ገዢው የፖለቲካና ቢዝነስ ኤሊት የያዙት መንገድ ወደጥፋት የሚወስዳቸው መሆኑን አውቀው፣ እስካሁን የመጡበት መንገድ ያደረሳቸውን የገደል አፋፍ ማየት ነው። በዚሁ መቀጠል ከፈለጉ ከማይፈሩት ገደል ውስጥ መውደቃቸው አይቀርም። ብቻቸውን የሚወድቁ ቢሆን ባልከፋ ነበር። ሆኖም አገራችንን ጭምር ይዘው ስለሚወድቁ አብረን መምከር የግድ ነው። አብሮ ለመምከርም እስካሁን ከሚያሳዩት የማፊያ ዝንባሌ መታቀብ አለባቸው። እኛ ከወደቅን ትበታተናላችሁ ስለሆነም ሰጥ ለጥ ብላችሁ ተገዙ ከሚለው ሟርታቸው ተቆጥበው፣ እንዴት ነው ለሁላችን የምትመች አገር መገንባት የምንችለው የሚል መድረክ መክፈትና ሕዝቡንና በተለይ ምሁሩን ማወያየት ይኖርባቸው ይመስለኛል። በር ዘግተው የሚደርጉት የፓርቲ ጉባኤ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል የደረሱበት አፋፍ ሊያሰተምራቸው ይገባል እላለሁ። ከኢሕአዴግ ውጪ ያለውን ድምጽ ማድመጥ ይገባቸዋል።
እንደሚታወቀው ባለፈው ብሔራዊ ምርጫ ኢሕአዴግና አጋሮቹ መቶ በመቶ አሸነፍኩ ማለቱንና የፖለቲካ ከባቢው ከጊዜወደ ጊዜ እየጠበበ መምጣቱን ተከትሎ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አልቆለታል፤ ከዚህ በኋላ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው በኢሕአዴግ ውስጥ ሊፈጠር በሚችል ችግር/ክፍፍል ብቻ ነው የሚሉ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርብ እንደሚከታተል አንጋፋ ፖለቲከኛ የአገራችንን የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይገመግሙታል? ኢትዮጵያ ከዚህ አረንቋ ልትወጣ የምትችለውስ እንዴት ነው?
አገዛዞች ሁሉ የሚወድቁት ራሳቸውን ለማረም ፈቃደኛ ስላልሆኑ ነው። ያልተገደበ ሥልጣን ስላላቸው፣ በአገሪቱ ውስጥ የፍርሃት ጥላ እንዲያጠላ ያደርጋሉ። ስለሆነም የሕዝቡን ተስፋ፣ ፍርሃትና ተቃውሞ የሚያውቁበት መንገድ የለም። ካድሬ ባጦዘው ሪፖርት ነው አገሩን የሚያዩት። በዚህ ላይ ተገዢው ሕዝብ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ሕዝብ ዓይነት የሺህ ዓመታት አገዛዝን የመሸከም የደነደነ ጫንቃ ያለው ሕዝብ ሲሆን ገዢዎቹ ይሰክራሉ። የሕዝብ ድጋፍ አለን ብለው ራሳቸውን እስኪያሳምኑ ድረስ ተላላ ይሆናሉ። በአንጻሩ፣ ቢጠይቁት እንኳ እውነቱን የማይነግራቸው ሕዝብ ግን ወደውስጥ እያቄመ ነው። አድብቶ ምቹ ጊዜ ነው የሚጠብቅላቸው። ቀኑ ሲደርስ ‹‹የሰከረ አሳ አመለጠህ፣ በለው!›› ይልና ከቀፎው እንደተለቀቀ ንብ መናደፍ ይጀምራል። አይጣል ነው። እንዲህ ዓይነት ሕዝብ ገዢዎቹን የሚያዘናጋውን ያህል፣ ሊመሩት የሚችሉትንም ልጆቹንም ተስፋ ያስቆርጣል። በመሆኑም ሁሌም፣ ተገቢው አመራርና ድርጅት ስለማይኖረው፣ ‹‹ሆ!›› ብሎ በተነሳበት ቅጽበት የሚከፍለው መስዋዕትነት ትልቅ ቢሆንም፣ ውጤት አልባ ለመሆን ይገደዳል። ወጣት ልጆቹን ገብሮ፣ ያነባው እንባ ሳይደርቅ፣ በአዲስ መልክ ሊገዙት የሚሸነግሉትን አዲስ ገዢዎችን ይፈለፍላል። ስለሆነም፣ የፍትሕና ነጻነት ቀን ትርቅበታለች። ይህ ሁኔታ ካልተለወጠ የኢትዮጵያ የነጻነት ብርሃን እንደራቀን ይኖራል።
በተራዘመ ሠላማዊ ትግል ልምድና ድርጅት ያካበተ ሕዝብ፣ አገዛዝን የመቋቋም አቅም ይገነባል። በመጨረሻም በማያዳግም መንገድ ማንበርከክ ይችላል። በአንጻሩ በጥቂት ጀግኖችና የጎበዝ አለቆች (ለነርሱ ያለኝ አክብሮት እንደተጠበቀ ሆኖ) የሚተማመን ሕዝብ ግን፣ የጎበዝ አለቆቹ ጭፍራ ከመሆን ላይድን ተረግሟል። ኢትዮጵያችንንም ሰንጎ የያዛት፣ ለውጥ የማምጣቱ ኃላፊነት ለጥቂቶች ምርጦች የተተወ በመሆኑ ነው። እነዚህ ጥቂቶች ግን ምን መልአክነት የደረሰ ንጽሕና ቢኖራቸው፣ በአንድ በኩል ቁጭ ብሎ የሚጠብቅ ሕዝብ፣ በሌላ በኩል የሙስናና ንቅዘት ልምድ ያካበተ ነጋዴና ባለሀብት መደብ ባለበት ሁኔታ፣ ሚዛኑ ሁሌም ወደኋለኞቹ ማድላቱና፣ መልአክነት የሚጠበቅባቸው መሪዎችም ፈጥነው የሚዘቅጡበት አደጋ ሰፊ ነው። ደርጉንና ኢሕአዴግን ማየት ነው። ታዲያ ምን ይሻላል? የጨነቀ ነገር ነው።
እርግጥ ነው ኢሕአዴግ ውስጥ ያለ ክፍፍል ሊረዳ ይችላል። ሆኖም የገዢው ኃይል ለመከፋፈል በመጀመሪያ በሕዝብ ትግል የተንገላታ መሆን አለበት። ሥልጣናችንን በምን መንገድ እናስቀጥል በሚል ጉዳይ ላይ ነው ገዢዎች የሚከፋፈሉት። ይህ የሚሆነው ደግሞ የሕዝቡ ሰላማዊ ትግል ፋታ የማይሰጥ፣ አጣዳፊ ምላሽ የሚጠይቅና የሚያስፈራ ሲሆን ነው። ይህ ከግብታዊ የሕዝብ ሰላማዊ አመጽ ሊገኝ የመቻሉን ያህል (ቱኒዚያን ማየት ነው)፣ በአብዛኛው ግን ውጤቱ ቀደም ብዬ ለማሳየት አንደሞከርኩት፣ አንዱን አገዛዝ በሌላ ከመተካት ውጪ አቅም አይኖረውም (ግብጽን ማየት ነው)። ይህም ቢሆን ግን፣ ተሞክሮው ሕዝቡን አስተምሮት የሚሄደው ልምድ ትልቅ ስለሆነ፣ ዝም ብሎ ከመገዛት በግብታዊነት አምፆ የወደቀ ሕዝብ ይሻላል። የሚያስተሳሰረው የጋራ ተግባርና የሚኮራበት የመስዋዕትነት ታሪክ ይኖረዋል። ብዙ ወጣቶች ይሞቱ ይሆናል፣ ግን በጫት ደንዝዘው፣ በድህነት ተቆራምደው፣ ወይም ይህን ሲሸሹ አሳ ነባሪና ‹‹አይሲስ›› የሚባል አውሬ ከሚበላቸው፣ ታሪክ ለመሥራት ሕይወታቸውን የገበሩ ወጣቶች ለቤተሰባቸውም ሆነ ለአገራቸው የሚያኮሩ ናቸው። ለዚህ ተገቢውን ክብር ለመስጠት ግን የታደልን መስሎ አይሰማኝም።
ለምን ይሆን በድህነት፣ በበሽታ፣ በረኀብ፣ በሥራ አጥነት መሞትን ለሕዝብ ፍትሕ ሲባል ከተከፈለ መስዋዕትነት አብልጠን የምናየው? አንዱ ችግር የሚመስለኝ፣ ለኔ ትውልድ መስዋዕትነት የሚሰጠው ትርጉም ነው። የየካቲት 66 ወጣቶችና ምሁራን ደም እንደ ደመ-ከልብ ነው የታየው። አዲሱን ሥርዓት ማዋለድ ሲያቅተን አሮጌውን መመኘት ያዝን። ስለሆነም፣ አሮጌውን ያፈረሱትን በጠላትነት አየናቸው። በተለይ በደርግ ዘመን ያደገው ወጣት፣ ታላላቅ ወንድሞቹን ከመኮነን ከማላዘን ውጪ ወይ የኔ የሚለው ሐሳብም ሆነ ተግባር የለው፣ ወይ ተሸናፊነቱን ተቀብሎ አርፎ አይቀመጥ፣ የተደረገውን ትግል ሲያንቋሽሽ ራሱ ወደ አርባዎቹ መጨረሻና ሐምሳዎቹ መጀመሪያ እየደረሰ ነው። ደስ የሚለውና ተስፋ የሚሰጠው ግን በኢሕአዴግ ዘመን የተወለዱትና ያደጉት ወጣቶች የኔን ዘመን ወጣቶች ታታሪነትና ጀግንነት የሚስተካከል ብስለት ማሳየት ጀምረዋል። የዞን ዘጠኝ ጦማሪያንን፣ የሚዲያ ጀግኖቻችንን፣ እንዲሁም ከተመክሮ ማነስ የሚፈጠሩት ስህተቶች እንደተጠበቁ ሆነው የሰማያዊ ፓርቲ ወጣቶችን እና በሰሞኑ የኦሮሚያ ክልል በመሬት ባለቤትነት ጉዳይ ላይ በሰላማዊ ትግል አገር ያናወጡትን ወጣቶች ማየት ነው። ጽናታቸው፣ ቁርጠኝነታቸው ተስፋ የሚሰጥ ነው። ማሸነፍ ሲችሉ ተስፋ ቆርጠው አገር ጥለው ለመሰደድ እንዳይከጅሉ የኢትዮጵያ አምላክ ልበ ብርሃን ይስጣቸው። ከተሰደዱ ግን ይህ ሁሉ ድካምና እንግልት ውኃ ሊበላው ነው። በአገር ውስጥ ቆይተው ሰላማዊ ትግሉን ከዳር ያደርሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ወደ አዲስ አበባ ጉዳይ እንምጣ። አገዛዙ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ሁሉንም አካባቢዎች በጋራ ለማልማት እንዲጠቅም ሆኖ መዘጋጀቱን ሲገልጽ፤ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ማስተር ፕላኑን ይቃወሙታል። ብዙ አዲስ አበባን እድገት የሚፈልጉና የሚደግፉ ኃይሎች በአንጻሩ የኢሕአዴግን የመሬት ዝርፊያና አርሶ አደሮችን መፈናቀል ቢቃወሙም አርሶ አደሮች የሚቋቋሙበት መንገድ ተፈልጎ አዲስ አበባ ተፈጥሯዊ እድገቷን መቀጠል አለባት ይላሉ። በእርስዎ አስተያየት የአካባቢውን አርሶ አደሮች ሳይጎዳ የአዲስ አበባ እድገትና ዘላቂ ልማት ሊቀጥል የሚችለው እንዴት ነው?
ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ በዚህ ሰሞን የሰጡትን ቃለ ምልልስ አድምጠህ ከሆነ፣ ውብና ቀለል ባለ ቋንቋ ነው ችግሩን ያቀረቡት። የከተማ ክልል ሰፍቶ ወደገጠር ቀበሌዎች ሲቃረብ የአርሶ አደሩ እልልታ ከሩቅ ይሰማል፤ ምክንያቱም በጋሻና በሔክታር እየተለካ ይሸጥ የነበረው መሬቱ በሜትርና በስንዝር እየተለካ ስለሚሸጥ አርሶ አደሩ ሀብታም ይሆናልና ነው። ስለሆነም የከተማውን መስፋፋት በዙሪያው ያለው አርሶ አደር በናፍቆት የሚጠብቀው ነገር ነው። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮች መርሐ ግብሩን የተቃወሙት ከመሬታቸው ይነቀላሉ እንጂ የሽያጩ ተጠቃሚ ስለማይሆኑ ነው። ስለሆነም ጥያቄያቸው ተገቢና የሚደገፍ ነው ነበር ያሉት ታላቁ ምሁር። የኔም አስተሳሰብ ተመሳሳይ ነው። የሰሞኑ የሕዝብ ተቃውሞ እምብርት ጥያቄ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ነው።
የምጨምረው ነገር ቢኖር ይህን የመሬት ጥያቄ ከማንነት ጥያቄ ጋር ማቆላለፍ የሚፈልጉት የኦሮሞ ብሔርተኞች ሁሉ የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት መብት አይቀበሉም። ልክ እንደ ኢሕአዴግ ሁሉ፣ እነርሱም አርሶ አደሩ የመሬቱ ባለቤት ከተደረገ፣ በርካሽ ቸብችቦ ይደኸያል ብለው ይፈራሉ። የኦሮሞ አርሶ አደር መሬት አልባ ሆኖ ይደኸያል ብቻም ሳይሆን፣ የአማራ ሀብታም ይገዛዋል ብለውም ይፈራሉ። የአማራ ሀብታም የተደመሰሰ መሆኑ አይታያቸውም። በደርጉም ሆነ በኢሕአዴግ 40 ዓመታት ሙሉ አበሳውን ያየ በመሆኑ የሚፈሩት የሌለ ነገርን ነው። ዘመኑም ተቀይሯል። ዕድሜ ለእሌኒ ገብረመድህንና ለሴልፎን ቴክኖሎጂ፣ እንኳንስ በአዲስአበባዙሪያያለአርሶደር፣ባሌጠረፍላይያለ እንኳ በቆሎውን ለመሸጥ፣ ‹‹ሃሎ አዲስ አበባ!›› ብሎ የገበያውን ዋጋ አጣርቶ እንደሚሸጥ ነው በተደጋጋሚ የምሰማው። ስለሆነም፣ አርሶ አደሩ ጥቅሙን አያውቅም፣ መሬቱን በርካሽ ዋጋ ሸጦ ይደኸያል የሚለው ስጋት ቦታ ሊኖረው አይገባም።
በተግባር እንደምናየው አርሶ አደሩ የመሬቱ ባለቤት ሳይሆን ሲቀር ብቻ ነው፣ የደላሎችና የመንግሥት ባለሥልጣን ሸሪኮቻቸው መጫወቻ ሆኖ ፍጹም ድህነት ውስጥ የሚወድቀው። የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ግን ከአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ባሻገር የፍትሕና ነጻነትም በር ከፋች ነው። ሕዝቡን ሌላ መተዳደሪያ ክህሎት ሲያጣ ካድሬ በመሆን፣ ለባለሥልጣናት ጭራውን እየቆላ ሕዝቡን አበሳ ከሚያሳየው የፓርቲ አባል ፍርሃትና ጭቆና ነጻ ያወጣዋል። አርሶ አደሩ ከመሬት ባለቤትነቱ ጋር ሰብዕናውም ብቻ ሳይሆን፣ በሕይወቱ ላይ አዛዥ ናዛዥ መሆኑን ይረዳል። ስለሆነም፣ ኃላፊነትንና ዜግነትን፣ ከዚህ ጋርም በተጣመረ ለቤተሰቡና ለአገሩ መቆርቆርን መሰዋትን ያመጣል። የተጠባባቂነትን ባህል በማስወገድ፣ በሌላ የማላከክን ደካማነት በማጥፋት ለጠፋውም ሆነ ለለማው የግል ተጠያቂነትን ያዳብራል። የመንግሥት ባለሥልጣናትም በቀላሉ የማያስደነብሩት ዜጋ ይሆናል። ይህ ዜጋ ሲፈጠር ብቻ ነው ስለ ዴሞክራሲና የሕግ ልዕልና ማውራት የምንችለው። ስለሆነም ከመሬት ባለቤትነት ጋር የተቆራኙትን መልከ ብዙ አገራዊ ፋይዳዎች በማየት፣ የኦሮሞ ብሔርተኞች በዚህ ማዕከላዊ ጥያቄ ላይ ከገዢው ፓርቲ የተለየ አቋም እንዲይዙ፣ ሕዝቡም ፓርቲዎቹ ይህን አቋም እንዲይዙ ግፊት እንዲያደርግባቸው ጥሪ ማድረግ እወዳለሁ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወጣት ጃዋር መሐመድን የመሰሉ የኦሮሞ ብሔርተኞች፣ የአዲስ አበባን መስፋፋት አንቃወምም፤ ሆኖም አርሶ አደሩ ተገቢውን ካሳ ማግኘት አለበት ማለት መጀመራቸው የአስተሳሰብ እድገት ነው እላለሁ። ግን ከካሳ ባሻገር የአርሶ አደሩን ቀጥተኛ ተጠቃሚነት የሚያጠናክረውን የመሬት ባለቤትነቱን መብት ቢቀበሉና ትግሉን ቢያጠናክሩ የነጻነት ቀን የበለጠ የሚቀርብ ይመስለኛል። በተመሳሳይ መንገድ ባለፉት 25 ዓመታት አዲስ አበባ ውስጥም ከይዞታው እየተፈናቀለ በከተማው ዳር ወዳሉ ቀበሌዎች የተወረወረውን የአዲስ አበባ ነዋሪ ትግሉን እንዲቀላቀል የሚያስተባብረው ይሆናል። የመሬት ባለቤትነት ጥያቄው ተሰልቦ የማንነት ጉዳይ ተደርጎ ሲቀርብ ግን፣ ለፍርሃትና ለጥርጣሬ ቦታውን በመተው፣ የትግል ኅብረት እንዳይኖር ያግዳል። ይህን ማየት ለምንድን ነው የሚከብደው?
ይህ ጽሁፍ የተገኘው ከዘ-ሐበሻ ድህረ ገጽ ነው።

No comments:

Post a Comment