Sunday, February 14, 2016

ስለ አሜን ባሻገር የተሰጠ አስተያየት (በአበበ ተድላ)

ስለ ከአሜን ባሻገር ብዙ ሰው አስተያየቱን እንደሰጠ ድጋፍም ተቃውሞም እንደቀረበበት አውቃለው። እኔም ከዚህ በፊት ትርጉም ላይ አንድን ገፅ ብቻ ይዤ ያልተስማማውበትን መፃፌን አስታውሳለው። ዛሬ ግን ሙሉ መፅሃፉን ስላነበበኩ ሙሉ መፅሃፉ ላይ አስተያየቴን ሰጣለው። እኔ የምቦጫጭረውን ያየ ሰው መቼስ ያው በአማርኛ ሃሳቤን መግለፅ መቻሌን እንጂ በስነፅሁፍ ደጅ ዝር እንዳላልኩ የነጠላ ሰረዝ እና ድርብ ሰረዝ ወዘተ የአጠቃቀም ድክመቴን ያየ ማንም ይረዳል። ስለዚህ ስለስነፅሁፉ ብስለት ሳይሆን ስለ ሃሳቡ ብቻ መናገር እንደምፈልግ ተረዱልኝ። ስለስነጽሁፉ ብስለት ለባለሙያዎች ትቻለው።አንተ ማነህ እንዳትሉኝ የሱን ፅሁፍ ለመገምገም። ማንም ልሁን ማን እውነትን እኔም ባነበብኩት ባለኝ እውቀት የተሰማኝን ስለእውነት የምፅፍ ተራ ኢትዮጵያዊ ነኝ። 
በነገራችን ላይ በአማራ የመጣ ማንም ይሁን ማን በአይኔ የመጣ ስለሆነ አማራን ያለአግባብ ለሚወነጅል መፅሃፍ ገንዘብ አላወጣም ባልኩት መሰረት መፅሃፉን ለማንበብ የተዋስኩት መጽሃፉን ከገዛ ወዳጄ ነው። በአማራነቴ እና በኢትዮጵያዊነቴ የመጣ በአይኔ የመጣ ነው። 
ወደኔ አስተያየት ልግባና መፅሃፉን ችግሩን ብቻ መፃፍ አልፈልግም፤ ምንም እንከን እንደሌለበት አድርጌ እንዳንዳዶችም ያለሂስ አላዳንቅም። ስለሆነም ጥንካሬው እና ድክመቱ ብዬ ከፋፍዬ መፃፍን መረጥኩ። 
የመፅሃፉ ጥንካሬዎች
1. መፅሃፉ እንዲህ በይድረስ ይድረስ የተፃፈ ሳይሆን ረጅም ጊዜ የወሰደና በመረጃ የተደገፈ እንጂ በስሚ ስሚ በለው ያለመሆኑ ትልቅ ጠንካራ ጎኑ ነው። በመረጃ ሃሳብን መሞገቱን በጣም የሚያኮራ ቢሆንም ሲተረጉም ለተፈጠረው ነገር እንደድክመት ከስር መጣበታለው። በእውቀቱን ከድሮ ጀምሮ ስራውን ስለምከታተል በዚህ መፅሃፍ ላይም ያሳየው ወጣ ያለው አስተሳሰቡን እና ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ማየቱን ነው ደግሞ ያረጋገጠልኝ። ይሄንን ችሎታውን አሁንም ያስመሰከረ ቢሆንም ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ መሆን ሲገባው በእግዚአብሄር ማመንን የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሄርን መፍራት ነው የሚለውን ቢተውም ያደገበት የኦርቶዶክስ ተዋጅዶ እምነት ላይ ብቻ ከሌሎች እምነቶች የጠነከረ ሂስ ማቅረቡን እንደድክመት ከስር አቀርበዋለው። (አማራን በትርጓሜ ስህተት ባይወነጅል እና ከሃይማኖቶች ለይቶ የሚያውቃትን ያደገበትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስታና ሃይማኖት ላይ ቢቻ ሂስ ማተኮሩን ባያስከፋኝ ገንዘብ አውጥቼ እንጂ ተውሼ አላነበውም ነበር)። 
2. የመፅሃፉ ትልቅ ጥንካሬ ብዬ በግሌ የማስበው ከማንም በላይ ህዝብን ከጥቂት ከውስጣቸው ከወጡ ጠባቦች እና ድርጅቶቻቸው ለያይቶ ማየቱ ነው። መቼስ በጥላቻ የተለወሱ ጠባቦችን እንዴት አፈር እንዳስጋጣቸውና አንጀቴ እንደራሰ አትጠይቁኝ። ብዙ ጊዜ ችግራችን አንድ ወይንም ጥቂቶች ከአንድ ህብረተሰብ ስለወጡ እና እነኛ ጥቂቶች ላጠፉት የዛን ህብረተሰብ ሙሉ ተወቃሽ ማድረግ ተገቢ አይደለም። ይሄ ማለት ግን አሁን በህይወት አብረን እያለን ስላለው ትግሬው ራሱ ወጥቶ ትህነግ አይወክለኝም ሳይል ትግሬ ትህነግን አይወክልም እያለ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሊከራከርለት ይገባል ማለቴ ግን አይደለም። ከዚህ አኳያ በተለይ በጣም ደስ ያለኝ በተለይ ስለድሮ ጥፋት ሲሆን አማራ ላይ መደፍደፍ ሆኖም ግን መልካም ነገር ሲሆን የውሸት መረጃ እያጠቀሱ እከሌ አማራ አይደለም የማለት እና ወደራሳቸው ብሄር ለመውስ,ድ የሚያደርጉትን ጥረት እና የራሳቸው ብሄርን የታሪክ ጥፋት ሰምቶ እንዳልሰማ የሚደረግ የጠባቦችን የጥፋት ፖለቲካ ውድቅ ያደረገበት አቀራረብ የልጁን ብስለት ያሳያል። ስለብሄር እይታው በግሌ የተሰማኝን አለበት የምለውን ድክመት ከስር ድክመት ላይ በዝርዝር መጣበታለው። 
3. አፄ ምኒሊክን ማንም ውርጋጥ በጥላቻ እና በዝቅተኝነት ስሜት ተነስቶ ታላቁን ንጉስ ከሞቱ በኃላ ስማቸውን ሊያቆሽሹ የሚሞክሩትን በመረጃ ከማንም በላይ ግልፅልፅ አድርጎ መሞገቱ አንጀቴን አርሶታል። ስለነጎበና ዳጬና ሌሎችም ጀግና ኢትዮጵያዊያን በመረጃ ማስረዳቱ እንዴት ደስ እንዳሰኘኝ አጠይቁኝ። ሆኖም ግን በዚህ መጽሃፍ ኦሮሞን ለማግነን ብዙ ርቀት እንደሄደ ድክመቱን ከስር መጣበታለው። በበሬ ወለደ ታሪክ እንዴት ታላቁን የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም የአፍሪካን ንጉስ ሊያጥላሉ የሚሞክሩ ትንንሽ ሰዎችን ከገባቸው በመረጃ አፈር ድቤ አስግጧቸዋል፣ ጆሮ ያለው ይስማ። በተለይ አፄ ምኒሊክን አማራ ተወካይ ብቻ አድርገው ለሚቆጥሩ ምን ያህል ዙሪያቸው ትግሬን ጨምሮ ሁሉም ብሄር አማካሪያቸውና ወታደሮቻቸው እንደነበሩ በተለይም ኦሮሞዎች ቀኝ እጃቸው እንደነበሩ የምናውቀውን ግን ሊካድ የተሞከረውን ታሪክ አስረግጦ አስረድቷል። ንጉሱ ከዘመናቸው ሰዎች ሁሉ ምን ያህል አስተዋይ እና ብልህ እንደነበሩ አሳይቷል። ይሄ 5 ሚሊዮን ኦሮሞ አለቀ፤ ያልነበረ ጡት ተቆረጠ የሚሉትን እቃቃ ጨዋታ አቤት እንዴት አፈር ድቤ እንዳስጋጠልኝ፤ በመረጃ በስሚ ስሚ አይደለም። በተለይ ደስ ያለኝ የትህነግ ወዳጆች ኦነግና ኦህዴድ አፄ ምኒሊክን በጦርነት ላይ ለሞቱት ኦሮሞዎች አጋነው እየጮሁ ለምን አፄ ዮሃንስ ወሎ ጦርነት ያልገጠማቸውን እስላም ነህ ብለው የተገደሉ ኦሮሞዎች ትዝ እንደማይሏቸው ሁሌ ይነሳ ነበርና በመረጃ ልክ ልካቸውን ለጠባቦቹ እና ተንኮለኞቹ በደንብ መንገሩ ነው። ትህነጎች አፄ ዮሃንስ ስንት ግፍ ፈጽመው ስማቸውን ምንም በደል እንዳልፈፀሙ እንደቅዱስ እየጠሩልን በአፄ ምኒሊክ ዘመንም ሰው በጦርነት የሞተ ቢሆንም ከአጼ ዮሃንስ የተሻለ አስተዋይ እና እልቂት የቀነሱ ስለሆኑ ፤ስማቸውን ሊያጠፉ የሞከሩበትንም ፉርሽ አድርጎ በመረጃ አስረድቷል። ስለ አፄ ቴዎድሮስ፤ ስለ ልኡል አለማየሁ እና ስለ በላይ ዘለቀ በፃፈው ላይ ያለኝን ቅሬታ ድክመት ላይ ከስር ዘረዝራለው። 
4. ሌላው አንጀቴን ቅቤ ያጠጣው ነገር ይሄንን ዲያቢሎስ ተስፋዬ ገብረእባብ በደንብ ተንኮሉን ተረድቶ ምን ያህል በፈጠራ በህዝብ መሃከል ጥላቻ የዘራና ሊዘራ የሚሰራ እንደሆነ በደንብ አስረግጦ በመረጃ አሳይቷል። ይሄ እባብ በተለይ ለአማራ እና ለኢትዮጵያ ያለውን ጥላቻ በስነ ፅሁፍ ችሎታው ተጠቅሞ ስንት መርዝ እንደረጨና አንዳንዴም ተሳክቶለት ሃውልት እስኪቆም ልብወለድ የፃፈ ክፉ አውሬ መሆኑን በመረጃ አሳይቷል። የሚገርማቹ በቅርቡ “አንዳርጋቸው በምናቤ” ብሎ የፃፈውን ፅሁፍ በጣም አስተዋይ ያልኳቸው ጭምር ልክ እንደ ደህና ፅሁፍ አንዳርጋቸውን ያመሰገነ መስሏቸው በየድህረገጹ ሲለቁ ነበር። የዛ ፅሁፍ አላማ እነ አረጋዊ እና ጓደኞቹ ሲነጋገሩ በሚል አስታኮ አማራ ድሮ ስልጣን ላይ እንደነበረ አድርጎ መናገር እና ልክ ድሮ ኦሮሞ ስልጣን ይዞ እንደማያውቅ በማስመሰል ኦሮሞው የበለጠ ተገፍቼ ነበር ወደሚል ሃሳብ በመግፋት በህዝብ መካከል ቁርሾን ያነገበ ፅሁፍ እንደነበረ ሰዎች አለማስተዋላቸው ነው። ከእባብ እንቁላል እርግብ አትጠብቁ ስንል እንደነበረው የገብረእባብን ተንከሲስነት በመረጃ ማሳየቱ አንጀቴን አርሶታል።
5. ጸረ ሽብር የሚባለውን ህግ እንዴት አድርጎ አብጠልጥሎ እንደጻፈው የስነፅሁፍ ችሎታውን ያሳያል። ነገር ግን በ አሜሪካ ህዝብ ድምፅ ቃለ መጠይቅ ሲሰጥ “የኢትዮጵያ ህዝብ” ሳይሆን ልክ እንደትህነግ እና አጋሮቹ “የኢትዮጵያ ህዝቦች” ማለቱ እና በዚህ መጽሃፉ ህገ መንግስት ሳይሆን ህገ አራዊት ስለሆነው ህገመንግስት ተብዬው ችግሮች አለመጥቀሱ ገርሞኛል። እንግዲህ የገነት ዘውዴ ልጅ ስለሆነ አልታየውም እንዳልል፤ በጣም አስተዋይ እና ነገሮችን አርቆ የሚያይ እንደሆነ ከሚፅፈው መረዳት ይቻላል። ስለዚህ ወይ እንደነ ትህነግን እና ዋለልኝ መኮንን ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እስርቤት ናት ብሎ ያምናል ስለዚህም የኢትዮጵያ ህዝቦች አለ ወይንም ስለዚህ ርእስ መንካት አልፈለገም። ለማንኛውም ስለኢትዮጵያዊነት የጻፈውን ባደንቅም ስለኢትዮጵያዊነት ያለውን አመለካከት አንዳንድ ግልፅ ያላደረጋቸው ነገሮች እንዳሉ ይሰማኛል። ሌላው ቢቀር በዚህ ህገመንግስት ተብዬው ላይ ኢትዮጵያ እንደሃገር ድንበር እንዲኖራት ሳይሆን ሳይሆን የክልል ድንበር ብቻ እንዲኖራት መደረጉና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜግነት ለማግኘት ካንዱ ክልል ተብዬ ጋር መተሳሰር ግድ መሆኑ እንደሱ ላሉ የተቀላቀሉ ነገዶች አገር እንደሚያሳጣ ቢጠቅስ እና ልክ እንዳልሆነ ቢያስረዳ ምንኛ ፅሁፉ ሙሉ በሆነ ነበር። እንደዚህም ሆኖ በመረጃ የተደገፈ ጠባብ ብሄርተኞችን አፈርድቤ ያስጋጠ መፅሃፍ ነው ። አበዛህው አንተ ምንም ሳትሞክር ትችት አበዛህ እንዳትሉኝ የተሰማኝን ሃሳብ ነው እየገለጽኩ ያለው ፤ደሞም የስነ ጽሁፍ ችሎታ የለኝም ብያለው። 
6. የዘመኑን ትውልድ በተለይ የመሃል ሃገሩን ሰው ትህነግ ለምን በሱስ የደነዘዘና በወሲብ ሴሰኝነት ተጠምዶ እንዲኖር እንዳደረገው ያቀረበው ትንተናም ተመችቶኛል። ትህነግ የራሱን ወገኖች እና ተላላኪዎቹን እያስተማረ ሌላውን በመድሃኒት እና በዝሙት አደንዝዞ፤ በበሽታ ጨርሶ የወደፊት ህልም የሌለው ታሪኩን የማያውቅ እንደከብት በነዱት የሚሄድ ትውልድ ለመፍጠር የሚያደርገውን ሴራ በደንብ ገልፆታል። ትግራይ ብለው የከለሉት ውስጥ ግን ሱሰኝነት በወጣቱ ውስጥ እንዳይጠናከር ስንት ጥብቅ ህግ እንዳለና ልዩ ልዩ ትምህርት ቤት እየከፈቱ ውጪ እያስተማሩ እየሰሩ ያለውን የራሳቸው የሚሉትን በከፍተኛ ደረጃ አስተምረው ሌሎችን በተለይ አማራውን እንዴት ወደመቀመቅ እየከተቱ እንደሆነ ቢዘረዝረው ደስ ባለን ነበር ግን ይሄንንም ሰዉ ብዙም ያላስተዋለውን ደባ ስለፃፈ እግዚአብሄር ይስጠው። 
የመፅሃፉ ድክመቶች
ድክመቶች ብዬ ከመዘርዘሬ በፊት እሱ ሲፅፍና እኔ ሳነብ ያለንን ልዩነት እና ተመሳሳይነት ያልኩትን ላስረዳ። ከሚያመሳስለን ነገር አገር የጋራ ነች ልዩነት አግነን ለሁላችንም የማትሆን አገር ከምትሆን፤ተመሳሳይ የሆነ ነገራችንን አግንነን የሁላችንም ሃጋር ይኑረን ባለው አንድ ነን። ህዝብን ከጥቂቶች ሰዎች እና ድርጅቶቻቸው ወይንም እነኛ ጥቂቶች ከመሰረቱት መንግስት ተብዬ ስርአት ለይተን እንድናይ ባቀረበው ሃሳብ እስማማለው። የምንለያየው ያልኩት ደሞ በኔ ግምገማ ምንም እንኳን ኦሮሞን ጠባብ አስተሳሰብ አራማጆች ከሆኑ ኦሮሞዎች መለየቱን ብስማማም በዚህ መፅሃፍ እሱ ለኦሮሞ ትኩረት ሲሰጥ እና ኦርቶዶክስ ላይ ጠንከር ያሉ ሂሶች ሲያቀርብ፤ እኔ ደግሞ መጽሃፉን ኦርቶዶክስን እና አማራ ላይ የማይሆን ነገር የፃፈ የመሰለኝ ሁኔታዎች ላይ አተኩሬ ነው ያነበብኩት። አማራን ነክቶ ኢትዮጵያ ትኖራለች ብዬ ስለማላምን በኢትዮጵያዊነት እሳቤው ብንስማማም አማራን ከነካ መጣላታችን አይቀርምና።
1. በዚህ መጽሃፍ ላይ እንደፃፈው በእግዚአብሄር ያለማመን መብቱ የተጠበቀ ሆኖ ሳለ በኦርቶዶክስ እምነት ላይ በውስጡ ስላደገ ብቻ እስልምናን ጨምሮ አንድም ሌላ ሃይማኖት ሳይነካ የኦርቶዶክስ እምነት ላይ ብቻ ማተኮሩ አላስደሰተኝም (ቢን ላደንን ከፂም ጋር አያይዞ ፂማም ሳይ አሸባሪ አልኩ አለ እንጂ ስለ እስልምና ምንም አላለም ጂሃድ ፈርቶ ከሆነ አላውቅም)። ሌላ ምን ያውቃል ኦርቶዶክስ ሆኖ ስላደገ ብትሉኝ አልስማማም፤ ምክንያቱም በአለም እይታ እናብጠልጥል ከተባለ ክርስትናም እስልምናም ማብጠልጠል ይቻላል እና። ግን የደፈረው በክርስትና ጂሃድ ስለማይታወጅበት ብቻ በየምሳሌው ሲያቀርብ የነበረው እና ያብጠለጠለው ኦርቶድክስን ብቻ መሆኑ ቅር አሰኝቶኛል። ወይ ሃይማኖት አለመንካት ነው፤ በሃይማኖት አላምን ካለ ግን ምሳር የበዛባትን ግን ያሳደገቸውን በእውቀት የኮተኮተችውን ሃይማኖት ኦርቶዶክስን ብቻ ህፀፅ ለማውጣት መሞከር ግን ያስተዛዝባል። ከዚህ በፊትም አቡነ ተክለሃይማኖትን ስንት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ከእግዚአብሄር ያማልዱኛል ብሎ እያመነ የማይሆን ነገር ተናግሮ ችግር እንደደረሰበት ልብ ይለዋል። እስልምናን ቢነካማ ምን እንደሚጠብቀው ስለሚያውቅ አይነካም። ለነገሩ ፈሪ ለናቱ የሚል መርህ እንዳለው ስለተመስገን በጻፈው ላይ መረዳት ትችላላቹ። ለምን ፈራ አይደለም መብቱ ነው ጨዋታዬ ከፈራ ሁሉንም ይፍራ ነው። ተመስገን ግን አንድ ለናቱ ጀግና ሆኖ በር ተዘግቶበት መኖሩ እንደእግር እሳት እንደሚያንገበግበኝ ሳልጠቅስ አላልፍም። አንዳንዴ ህዝቡ ዝም እስካለ ድረስ እንደ ሌላው ተልመስምሶ መኖር ሲችሉ ነፃ ህሊና ስላላቸው ብቻ እስር ቤት የገቡትን ሳስብ ምንም እኳን ህሊናቸው ነጻ ቢሆንም የሚደርስባቸውን ጉስቁልና በደል ሳስብ ግን ያመኛል ።እውነት እንነጋገር ከተባለ መታሰርህን ለሚረሳህ ህዝብ ይሄንን አይነት መስዋእትነት መክፈል ያስፈልጋል ወይ የሚል ሃሳብ አንዳንዴ ውስጤ ይገባል። 
2. ከላይ እንዳልኩት የአባቴ ወገን ኦሮሞ ነው ስላለ ይሁን አላውቅም፤ ስለሴት እየተከራከርኩ ነው እያለ ነውር የተባሉ መሻፈድ ምናምን ቃላትን እየተጠቀመ እየፃፈ፤ ቁላ ብሎ እየፃፈ፤ ወላይታ መጠራት በማይፈልግበት ወላሞ እያለ (ስለ ወላሞ ስያሜ አሰጣጥ አፄ ምኒሊክ ያወጣላቸው ስም እንዳልሆነ ታሪኩን ማስረዳቱን እንደጥንካሬ ይያዝልኝ) ልክ የአባቱ ወገን ሲሆን ግን ጋላ ተብሎ ባደባባይ ሲፃፍ የነበረውን እሱ ግን ደግሞ ደጋግሞ ጋ* እያለ ሲፅፍ ማየቴ እንዳልኩት ሲጀመር እስኪጨርስ ኦሮሞነቱን ለመደገፍ ያለውን ሃሳብ ያሳያል። በቃ ኦሮሞ በስህተት ጋላ እንደሆነ ተደርጎ የተወሰደው ስድብ ነው ይቅር ስለተባለ ጋ* ብሎ ከጻፈ፤ ምነው ታዲያ ስድብ ነው ተብሎ የቀረው ወላሞን ወ* ብሎ አልገለፀውም ምክንያቱም ስህተት ነው ተብሎ ወላይታ ብቻ ነው የሚባሉትና ባሁኑ ጊዜ። ለጃንጀሮም እንዲሁ ማድረግ ነበረበት። ረሳው እንጂ አማራን ለመወንጀል ትህነጎች ትግሬ የሚለው አማራ ተእግሬ ስር ለማለት የተፈለገው ነው እየተባለ ትግሬ እንዳትሉን ማለታቸውን ቢያነሳም ኖሮ እንዴት ደስ ባለኝ ነበር ምክንያቱም የፈረደበት አማራን የሚወነጅሉ በርካታ ናቸውና። 
3. ይሄንን የመሰለ መጽሃፍ ፅፎ በትርጓሜ ስህተት ይሁን አማራን ምንም ብል ማን ይነካኛል ብሎ አቢሲኒያ የሚለውን በአማራ መተካቱ በጣም ሁሉን ነገር በዜሮ አባዝቶብኛል። እርግጥ ነው ለአማራ ተከራክሯል። አማራ ባልበደለ መወንጀሉን፤ ከሚኖርበት መፈናቀሉን ተቃውሟል እግዚአብሄር ይስጥህ። ይሄንን ለአማራ የተከራከረበትን ጻፈ ማለት ግን የማይሆን ቦታ ላይ አቢሲኒያ በሚለው ቦታ አማራን ማስገባቱ ከሂስ አያድነውም። ልብ በሉ ከትርጋሜው ቀደም ብሎ ሁሉም ብሄር በተለይ ከጦርነት በኃላ ሲያሸንፉ የመስለብ ባህል እንደነበረው ይገልፃል። የተወሰኑት ብሄሮች ደሞ በደህና ቀንም ጀግና ብለው ለመቆጠር እንደሚሰልቡ ፅፏል። ሌላው ደግሞ ጋላ ኦሮሞ ማለት እንዳልሆነ ራሱ በመጽሃፉ አንዳንድ ኦሮሞዎች ራሳቸውን ኦሮሞ እያሉ ሌላውን ጋላ ይላሉ ብሎ ጠቅሷል። በምን ሂሳብ እንደሆነ አላውቅም አቢሲኒያን አማራ ያለበት እና ጋላን ኦሮሞ ያለበት አሁንም አልገባኝም እና በኔ ምዘና ስህተት ነው። አንድ ምእራፍ ላይ ዊንተር የሚለው በቀጥታ መተርጎም ሲያስቸግረው ዊንተርን ለምን ክረምት እንዳላለ እና በቀጥታ ዊንተር የሚለውን ቃሉን ለምን እንደተጠቀመ በመጽሃፉ ላይ ጠቅሷል። ታዲያ እዚህ ቦታ ላይም ፍቺው ያምታታል ብሎ ካሰበ በደፈናው ለምን አቢሲኒያ እና ጋላ ብሎ በቃ ያኔ በነበረው ሁኔታ መስለብ አሎ ብሎ አያልፍም ነበር? ምክንያቱም የዛ ቦታ የፅሁፉ አላማ አፄ ምኒሊክ እንዲህ ያለ ነገርን ለማስቆም መስራታቸውን ለማሳየት እንጂ እከሌ ብሄር ይሰልባል አይሰልብም ለማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። መፅሃፉ ከወጣ በኃላ መልስ ሲሰጥ አቢሲኒያ የሚለውን አበሻ ብለው አበሻ ብዙዎቻችንን ስለሚወክል ውዝግብ ያስነሳል ብዬ ጸሃፊው (ተሳስቶ መሆኑን ያውቀዋል) አቢሲኒያ ማለት አማራ ነው በሚል ስለፃፈው አማራ ብዬ ተረጎምኩት አለን። እንግዲህ ልብ በሉ አንዴ ሁሉም ብሄር ቁላ ይቆርጣል ይልና አበሻ ካልኩት ብዙ ሰው ስለሚያስቆጣ አማራ አልኩት ማለት አማራ አይቆጣም ማን ይነካኛል ይመስለበታል። እናም ይቺ አረፍተ ነገር በመጽሃፉ ላይ ትልቅ ጥቁር ነጥብ ጥላብኛለች። ይሄንን የመሰለ ስራ ሰርቶ አቢሲኒያ የሚለውንም ይሁን ጋላ የሚለውን እንዳለ ጸሃፊው እንደተሳሳተው ቃል በቃል በተረጎመ ይሻል ነበር ምክንያቱም አቢሲኒያ ከሚባሉትም ውስጥ ኦሮሞች፤ጉራጌዎችም አማራም ነበሩበት እና የሰጠው ትርጉም ከሱ አይጠበቅም። 
4. ሌላው እንደ ድክመት ያየሁት የገነት ዘውዴ ልጅ ስለሆነ ነው መሰል ብሄሮች መቀላቀላቸውን በተለይ ደሞ አማራው እና አገው የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን ረስቶ ትልቅ ድንበር በመሃላቸው ይሰራል። ለዘመናት አብሮ ከመኖር ቅማንት፤ አገው፤ወይጦ፤ አማራ ወዘተ አንድም ሁለትም ናቸው። በነኚህ ህዝቦች መካከል ትህነግ አማራውን ለመከፋፈል ጥረት እንደሚያደርገው የተለያዩ ያልተዋሃዱ አይነት አድርጎ አንዳንዴ መሳሉ ትንሽ ቅር አሰኝቶኛል። ስለ ላሊበላ ሲፅፍ እዛ ቦታ አማራ የሚባል ነገድ ያለም አይመስልም እና ፣ተመልሼ እንደገና እንደአዲስ ታሪክ ማገላበጥ ግዴታ ሆኖብኝ ነበር፣ አማራ የሚባል ህዝብ መቼ ነው መኖር የጀመረው እንድል። እና አማራና አገውን ባትለያይ መልካም ነው አንድም ሁለትም ናቸው። እነኚህ እርጉም ትህነጎች መጥተው ነው እንጂ ትግሬና አማራም እንዲሁ ብዙ የሚያመሳስል ነገር ነበረን ግን በቃ ደም አቃቡን። 
5. ስለ አፄ ቴዎድሮስ እና ስለ ልኡል አለማየሁ እንዲሁም ስለ በላይ ዘለቀ የፃፍከው በእውነት አሳዝኖኛል። ስለ አበበ ቢቂላም የፃፍከው ያስተዛዝባል። እንዴ አፄ ቴዎድሮስን እነ ዳንኤል ክብረት ሆሉ አፋቸውን ይከፍቱባቸው ጀመር። ጀግና ከሞተ በኃላ ነው ለካስ የሚጠቃው በህይወቱ እያለማ ጀግና ነው ማን ሊደፍረው። በቀደምት አባቶችህ ድል ባግባቡ እስከተጠቀምክበት የሚኖረውን የስነ ልቦና ጥቅም ላንተ ማስረዳት ለቀባሪው አረዱት ነው የሚሆንብኝ። አሸናፊ ወገኖችህን ስታስብ የስነልቡና የበላይነት ይሰማሃል ያደሞ ለትልቅ ድል ያበቃል። በደፈናው በድሮ እየተኩራራን የራሳችንን ታሪክ ሳንሰራ አንሙት ጥሩ መልእክት ነው ፤ግን በጀግኖች አባቶቻቹ አትኩሩ አያስኬድም። ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ተገዝታ አታውቅም የሚለው ዛሬ ላይ ስታስበው ምንም ጥቅም ያለው ላይመስልህ ይችላል። ነገር ግን አንድ ሌላ ጥቁር አፍሪካዊ ጋር ወይንም ነጭ ጋር ሆነህ ይሄንን ስትወያይ ምን አይነት ስነልቦና እንዳሚሰማህ ካላየህው ላስረዳህ አልችልም። ነገር ግን ትህነግ የኋሊት ጠፍንጎ አስሮ እየገረፈው የባርነት ኑሮ እየገፋን ዝም ብላቹ አትፎክሩ ተደራጁና ጠላትን አሸንፉ ከሆነ መልእክትህ እንስማማለን። አለበለዚያ ለስነልቡና የአባቶቻችንን ድል መጠቀም የለባቹም ማለት ልክ አይመስለኝም። ግን ይሄንን በበላይ ዘለቀ መፎከር እንዲሁ ሳይሆን ጠላታችንን ትህነጎችን እና ወዳጆቻቸውን ለመታገል ለመቀስቀስ ይሁን በሚል ከሆነ እስማማለው። ትህነግ አንገትህ ላይ ቆሞ መተንፈስ ሳትችል ምንም ሳትሰራ አገር ሰላም እንደሆነ አትፎክር ከሆነ መልእክትህ በዛ እስማማለው። የአፄ ቴዎድሮስ ልጅ የልኡል አለማየሁን ምንም ማለት ስላልሆነ መቃብሩን ማየት አያስፈልግም ያልከው ደሞ ሌላው አሳዛኝ ነው። ተው ሌላው ቢቀር በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ታሪክ ያለው የንጉስ ልጅ የነበረ በበደል ከሃገሩ ወጥቶ ተንከራትቶ የሞተ ወገንህ እንዴት ምንም ፋይዳ ስለሌለው አላይም ትላለህ? ይሄ ያስተዛዝባል። በመጨረሻም እውነት ለመናገር ቓራ የሃገር ስም እንጂ በቓራ የሚጠራ ብሄር እንደነበረ አላስታውስም። አፄ ቴዎድሮስም ጠላቶቻቸው እንደሚሉት ሳይሆን ተብሎ ከሰሎምን ዳይናስቲ የዘር ሃረጋቸውን የሚያጣቅስ አንብቢያለው እና ይሄ ጉዳይ ቓራ የተባለው ብሄር በየት በኩል ከሰለሞኒክ ዳይናስቲ ውስጥ እንደተቆጠረ አጣራለው። አማራ አይደሉም ለማለት አንድ አንቀፅ ከአንድ መፅሃፍ ጠቅሰህ አማራ አይደሉም ላልከው ምላሽ የታሪክ ተመራማሪዎች ቢሰጡህ ብዬ ትቼዋለው። በኔ ግምት ያ የኮሶ ሻጭ ልጅ እያሉ ሲያጥላሉት የነበረው አይነት፤ ከዘመኑ ወጣ ያለው አስተሳሰብ ስለነበራቸው ንጉሱ ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት ጋር መጋጨታቸው ያስነሳባቸው አይነት ተቃውሞ የፈጠረው ውዥንብር አይነት የፈጠረውን መረጃ የተከተልክ ይመስለኛል። ስለዚህ ጉዳይ በደንብ አንብቤ ወደፊት ምላሽ ሰጣለው ወይ ስለንጉሱ ትውልድ ዘር በደንብ መረጃ ያለው እና ቓረኛ የሚባል ህዝብም ከአማራ ተለይቶ ከነበረ (ሆነም ቀረም አሁን ሁሉም አማራ ነው ብዬ አስባለው)ልክ እንዳንተ ታሪክን መረጃ አድርጎ ያስረዳሃል ብዬ አስባለው። ግን አፄ ቴዎድሮስ አሳዘኑኝ አማራ አይደሉም ለማለት ስንት ብሄር ላያቸው ላይ ተለጠፈ ከሞቱ ከስንት አመታት በኃላ። መረሳት የሌለበት ግን ከለገሰ ዜናዊ በፊት የነበሩ የትኛውም የኢትዮጵያ መሪዎች ኢትዮጵያዊነታቸውን እንጂ ብሄራቸውን ስለማይጠሩ ይሄ ጉዳይ የጠባቦች ችግር እንጂ ሌሎችን አያሳስብም። ነገር ግን ያለ በቂ መረጃ አንተ ራሱ እንዳልከው መጥፎ ሲሆን አማራ የሰራው እየተባለ መልካም ታሪክ ሲሆን ደሞ ከአማራ ለመንጠቅ የሚደረገው ይቁም ስል አሳስባለው። 
6. አንዳንድ አስተሳሰባቸው የወረደ ድሮም አሁንም አንድን ህዝብ አስተሳሰቡ ዝቅ ያለ አድርገው የሚናገሩትን መገሰፅህ እሰየው የሚያስብል ነው። አይደለም ህዝብን ግለሰብን የሚንቅ ራሱ መጀመሪያ የተናቀ ነው። በዛው ልክ ደሞ ልክ ኦሮሞ ከሌላው ህዝብ የበለጠ ብሩህ ነው ብሎ ማቅረብም ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ አይነት ነገር ነው የሆነብኝ። ማንም ህዝብ ከማንም ህዝብ አያንስም አይበልጥም። አጋጣሚ ያገኘ ሁሉም ጤነኛ ሰው ብሩህ አእምሮ አለው። ጥቂቶች ደሞ ከሁሉም ሰዎች መካከል አስተሳሰባቸው ላቅ ይላል። ያ ማለት ግን ብሄሩ ተለይቶ ላቅ ያለ አስተሳሰብ አለው አያስብልም። ለዚህ ምሳሌም ስለ እናራያ ስልጣኔ መፅሃፍት ጠቅሶ ሲያወራ ሌላ ቦታ ምንም እደጥበብ ያልነበረ አድርጎ የፀሃፊውን ግነት መጠቀሙ በእውቀቱንም የአባቱን ወገን ለማግነን የሞከረ አስመሰለው። እዚህ ፅሁፍ ላይ እናራያ በኦሮሞ ከመያዙ በፊት ስለነበሩ ህዝቦች ብዙም ካለመጥቀሱ በተጨማሪ ብዙ ቦታ ታሪክን ከወደ ቅርብ ብቻ የመጀመር ሁኔታ አይቼበታለው በተለይ ኦሮሞዎች በ16ኛው ክፍለዘመን ብዙ ቦታ ወርረው መያዛቸውን ብዙ ሳይናገር ማለፉን አስተውያለው። ለዚህም ነው እኔ አማራን እንዳይነካ እየጠበኩ ሳነብ እሱ ደሞ ኦሮሞን ከጠባቦች ክፋት አስተሳሰብ ቢለይም ኦሮሞን ከሌላ በተለየ መልኩ ለማግነን የተወሰነ ርቀት የሄደ የመሰለኝ። 
7. እየተነገረውም የአባትህ አባት ስለሞቱ እና ግማሽ የአባትህ ወንድም ስላሳደጓቸው ነው በዳዳ ወደ ስዩም የተቀየረ ቢባልም የአያቴ ስም የኦሮሞ ስም ስለሆነ ሊሆን ይችላል የተቀየረው ብሎ ለማጣራት የሄደው ርቀት ሌላው የትህነግ ዘመን ወጣት መሆኑን የሚያሳይ ነው። የዮናታን ተስፋዬ ረጋሳ አማራን ሲያንጓጥጥ ደጋፊው የነበረበት ምክንያት የገባኝ አሁን ነው። እናቴም አባቴም ወላጆቻቸው እያሉ ባሳደጓቸው አባት ነው የሚጠሩት አዲስ ነገር ስላልሆነ ማንም ስራዬ ብሎ ስለዚህ አይነሳም። አማራውም እኮ ከተማ ሲመጣ የገጠር ስም እየተባለ ስሙ ይቀየራል በቓንቓውም ድሮ አይደለም ይሀው ዛሬም ድረስ በተለያዩ ድራማዎች እና ተውኔቶቶች (ምሳሌ ቤቶች ድራማ) ይቀለድበታል። እነኚህን ድራማዎች በሌላ መልኩ በደንብ ጥፋታቸውን አቅርበሃል ግን አማራ ላይ እያላገጡ መሆኑን ግን ዘለልከው። ምነው ይሄ በአማራ ዛሬም ድረስ በአደባባይ መቀለዱ ሳያንገበግባቸው ድሮ ከተማ ሲመጡ ሰዎች ስማቸው ተቀይርዋል የሚለው ክርክር በዝቶ ይሰማል። ዛሬ ስንቱ የአማራ ሴት ነው ትህነግ ገረድ አድርጎ እያሰቃያቸው ያሉ የገጠር ስማቸውን ትተው ሊሊ ኪኪ እያሉ ስማቸውን የቀየሩ። ታዲያ ምነው ይሄንን አላስተዋልክም ወንድሜ? በእውቀቱ አማራ ላይ ብዙ ነገሮች እንደሚደርሱ ያውቃል ነገር ግን ጥቂቶቹን ብቻ አንስቶ ብዙ ያለፋቸው አሉ። ቢያንስ ግን አለ አግባብ መወንጀሉን እና አለአግባብ መፈናቀሉን መናገሩ ደስ ያሰኛል። በእውቀቱ እዚህ ጋር በከተማ ውስጥ በከተሜነት የሚመጣ የባህል ግጭት ችግርና በብሄር ወይንም ቓንቓ ተፅእኖ የሚመጣ ነገር ያምታታ ይመስለኛል። ወደገጠር ብትሄዱ ማንም አማራ፤ትግሬ፣ወላይታ፤አሮሞ ወዘተ ስሙን አይቀይርም። ከተማ ደሞ ሁሉም ብሄር ያለበት ላይ አማራም ኦሮሞም ትግሬም ሌላውም በየጊዜው ከወቅቱ ጋር እንዲሄድ ብለው ለልጆቻቸው የሚመርጡት ስያሜ አለና የአፄ ሃይለስላሴ ወይንም የአማርኛ ቓንቓ ወይንም የአማራ ተፅእኖ አይነት አድርጎ ያቀረበው አልተመቸኝም። አሁን አሁንማ ሁሉም ብሄር በተለይ ከተማ ውስጥ ወይ የመፅሃፍ ቅዱስ ወይንም ደሞ የቁራን ስም ነው የሚወጣው። ይሄንንስ ያካሄዱት አፄ ሃይለስላሴ ይሆኑ ወይንስ አማራ አይንስ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን? ከተሳሳትኩ እታረማለው ግን በፍፁም ከተማነት አማራንም ኦሮሞንም ሌላውን ስሙን ወደከተማነት ወዳለው ይስማማል ወዳሉት አንዳንዶችን እንዲቀይሩ አደረገ እንጂ በአዋጅ ማንነትን ለመዋጥ የተካሄደ ቢሆን ገጠርም ይሄንን ተፅእኖ ባየን ነበር። የከተማ ህዝብ ደሞ ከኢትዮጵያ ስንት % እንደሆነ አይጠፋህም ብዬ አስባለው። 
መደምደሚያ፦ አዎን ልክ ነው በእውቀቱ ስዩም በዳዳ ውሸቶችን ዝም ብሎ መቀበል ጥሩ አይደለም። በዛው ልክ ደሞ ተሳስቶ ትርጉም መስጠት አይቻልም በተለይ ተከራካሪ ያጣውን አማራን መወንጀል አይቻልም። አቢሲኒያ ማለት መቼም አማራ ማለት ሆኖ አያውቅም። ጠባብ ኦሮሞዎች ጋላ የሚለውን ኦሮሞ ማለትህን ሳይሆን የሚቃወሙህ በውሸት ህዝብን ከህዝብ ለማጣላት የሚያደርጉትን የውሸት ፕሮፓጋንዳ በመረጃ ስላጋለጥክባቸው ነው። ጋላ ማለት ኦሮሞ ነው ቢባልማ ጠባቦቹ ኦሮሞዎች ይፈልጋሉ ምክንያቱም ጥላቻ ለመንዛት ይመቻልና። እስቲ እግዚአብሄር ያሳይህ ያሁሉ የኦሮሞ ጦር እያላቸው ኦሮሞ ደም እያላቸው ኦሮሞ እና ጋላ አንድ ቢሆን ኖሮ አፄ ምኒሊክ “ሰውን አትግደሉ ጋላም ቢሆን” እንዴት ይላሉ? አየህ ሆን ተብሎ በህዝብ መሃል ጠላትነት ለመፍጠር የተስፋፋ እንጂ በምንም ሁኔታ ጋላ ማለት ኦሮሞ ነው ማለት አይሆንም የቃሉን ትርጉም በደንብ አጥናው ማን ጋላ እንደሚባል እንደነበረ ታውቃለህ። በ እግዚአብሄር አለማመን መብትህ ነው በጊዜው ከእግዚአብሄር ጋር ትጠያየቃለህ ነገር ግን የሌሎችን ሃይማኖት መንካት ልክ አይደለም ከነኩም ደሞ ጎበዝ ከሆኑ ሁሉንም ነክተው የመጣውን መጋፈጥ እንጂ አንዱን ሃይማኖት በኢትዮጵያ ላይ ይሄንን ይሄንን ተፅእኖ አደረሰ እያሉ እየተዘባበቱ ሌላውን ዝም ብሎ ማለፍ ያስተዛዝባል። ወይ ሁሉንም ዝም ወይ ሁሉንም መተቸት። ወንድም በእውቀቱ ትርጓሜ ከመስጠትህ በፊት እንደሁሌህ አስብ። መተርጎም ከተቸገርክ ልክ ዊንተርን ክረምት ሳይሆን በቀጥታ ቃሉ ዊንተር እንዳልከው አቢሲኒያን ፤አቢሲኒያ ፤ጋላን ፣ጋላ እንጂ አቢሲኒያን፣ አማራ ፣ጋላን፤ ኦሮሞ ባትለው ከትልቅ ስህተት በዳንክ ነበር። በተረፈ በጣም አስተዋይ ነህ። ጊዜ ሰጥተህ በመረጃ የፃፍከው ትልቅ መፅሃፍ ነው። በተለይ ጠባቦች ለስልጣን ሲሉ በውሸት ላይ ተንተርሰው ህዝብን ለማጋጨት የሚሰሩትን በመረጃ ማክሸፍህ ሊያስመሰግንህ ይገባል። የተሳሳትከው ነገር የዘመኑ አማራን የማቃለል ፈሊጥ ሆኖ ይቅር የማልለው ስህተት ሆኖብኝ እንጂ መጽሃፉን እንዴት ባመሰገንኩልህ ነበር። አማራን እየተሳደቡ በፖለቲካ ማደግም ሆነ መጽሃፍ ሸጦ ገንዘብ መስራት መቆሚያው ጊዜ ስለሆነ መልካሙን ስራህን ለአማራ ወገኔ ስል ከመተቸት አልመለስም። በተረፈ እንግዲህ የጥበብ መጀመሪያ እግዜአብሄርን መፍራት ነው ስለሚል የእግዚአብሄርን መፍራት ሰጥቶህ የበለጠ ጥበብ ሰጥቶህ ቀጣፊዎችን በመረጃ ማጋለጡን ቀጥል እላለው። ሰው ነህ ትሳሳታለህ ግን ስህተት ላለመድገም ሞክር ዋናው መማርህ ነውና። 
አመሰግናለው።
ያነበብነውን በልቦናችን ያሳድር። በውሸት ህዝብን አጣልተው የስልጣን እና የገንዘብ ጥማታቸውን ለማርካት የሚሞክሩትን ህሊና ይስጣቸው። ካላስተዋሉም ሃይለኛ የገባው ህዝብ ይዘዝባቸው እና ከሁሉ ያጡ ያድርጋቸው። 
አማራ ወገኔ ሆይ እንዲህ ተከላካይ አጥተህ አጋጣሚ ያገኘ ሁሉ ሲያጠቃህ ሲሰድብህ ብረሳህ ቀኜ ይርሳኝ!
አበበ ተድላ
የካቲት 2008

No comments:

Post a Comment