Saturday, September 1, 2012


የሕዝባዊ ከያኒ ያለህ !


የዛሬው ‘ የጽናት’ ሬድዮ ጋዜጠኛ የቀድሞው አቀንቃኝ ሰለሞን ተካልኝ ‘ቅንድባሙ መሪ’ የሚለውን ዘፈኑን ወደ ሸገር ዘልቆ ካስባረካና ከስርዐቱም ጋር እርቅ ካደረገ በሁዋላ የመጀመሪያ ልምጩን ያሳረፈው የሙያ ወዳጁ አቀንቃኝ ነዋይ ደበበ ላይ ነበር። ( አቀንቃኝ ሲያረጅ ኮሚቴ ይሆናል መሰል ነዋይ ደበበ የልቅሶ ኮሜቴ አመራር ውስጥ ይህን ጽሁፍ ሳዘጋጅ ሰማሁ ሹመት ያዳብር ብለናል ነዋይ ) የሰለሞንን እርቅና እርሱን ተከትሎ አውራ ወያኔ ለመሆን መሻቱን ካልወደዱለት መሃል ነዋይ አንዱ ሳይሆን አልቀረምና ሰለሞን እንዲህ ሲል የወረፈው ዛሬ ድረስ ፈገግ ያሰኘኛል፡
ፍየል ቅጠል እንጂ አትበላም እንጉዳይ
በጥርሷ ሰላሳ በአይኗ መቶ ገዳይ
የሚለውን የነዋይ ዘፈን አዜሞ ሲያበቃ ከመቼ ወዲህ ነው ፍየል በጥርሷ መቶ ስትገድል ነዋይ ያየው ሲል አድማጮቹን በተሳልቆ ድምጸት ጠየቀ። ሰለሞን በዚህም አላበቃም ነዋይ በሶስተኛ ወገኖች በኩል ወደ ሀገሩ ለመግባት ‘ድርድር’ ላይ እንደሆነ እንደሚያውቅ ሁሉ ለሬዲዮ አድማጮቹ ጠቅሶ አላርፍ ካልክ ‘ ብዙ እናውቃለን’ ሊለው ቃጥቶት ነበር። (ምናልባትም ሁለቱንም ልማታዊ አቀንቃኝ ይሆኑ ዘንድ ከስርዓቱ ጋር የሚያደራድሯዋቸው ሰዎች መረጃ እየሸላለሙ ያቃርኑዋቸውም ይሆናል) ዛሬ ነዋይ ደበበም ሰለሞንም የስርዓቱ ልማታዊ አቀንቃኞች ናቸው። ምን አልባትም ቀድሞ ለሰለሞን ያልታየው የፍየሊቱ አይነ ገዳይነት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ጸበል ሲጠመቅ ይገባው ይሆናል። አልያም ነዋይ ሂስ ውጦ የፍየሊቱ ጉዳይ ትምክህተኛ አመለካከት እንደሆነ ያምንም ይሆናል ። ከዚህ ባለፈ ግን የእነርሱ እንካ ሰላንታ ፤ የእነርሱ ትላንት ሰበታ ነገ ወላይታ መገኘት እኪነት አካባቢ ምን እየሆነ ነው ወደሚለው ጨዋታ ይወስደናል። የአቶ መለስ ዜናዊ እረፍት ተከትሎ የታዘብነው ደግሞ ምነው በዚህ ዕድሜ ፤ ምነው ምነው ፕርፌሰር እገሌ ፤ ምነው አትሌት እገሌ ፤ ምነው ዶፍተር እንቶኔ ደግሞ ደጋግሞ አሰኝቶናል። ምንም እንኳን ያለፉት ጥቂት ቀናት የአርቲስቶቻችንን ብዛት ከሺዎች ከፍ አድርጎት ፌዲራል ፓሊሱም፤ አትሌቱም፤ ዶክተሩም፤ ካድሬውም ፤ የዪኒቨርሲቲ መምህራን ሳይቀሩ ተሰጥዖዋቸውን ካሜራ ፊት ያሳዩበት ቢሆንም ማህበረሰባችን አልቦ የኪነት ሰው መሆኑን ያሳየበት ሁነት ይበልጥ ገኖ ተስተውሏል።
በቅርቡ የማውቀው አንደ ሰው መቼ ይሆን ሀገራችን ህዝባዊ ከያኒ የሚኖራት ሲል የሞገተኝ ጉዳይ እነዚህን ለቅሶ ተኮር ክስተቶች ካስተዋልኩ በሁዋል ይበልጥ ይከነክነኝ ገባ።ይህ ሀሳብ የብዙዎች እንደሚሆንም እገምታለሁ። ከያኒዎቻችን በተለይም አቀንቃኞቹ ‘ የአዝማሪነት’ ዘመን እንዳበቃና አዲስ የአብርሆተ ከያኒነት ጊዜ እንደባተ በተደጋጋሚ ሲነግሩን ነበር የቆዩት አንዳንድ አጉል ጊዜ እየመጣ ሲሸሹት ከኖሩት ‘ የአዝማሪነት’ ምግባር አሁንም አንዳልወጡ ባያሳብቅባቸውም። ለጨዋታችን መስመር ሲባል የአቀንቃኞቹን ጉዳይ እፊት ረድፍ አስቀመጥኩት እንጂ የሌላውም የኪነት ዘርፍ ( ስነ ስዕሉም ፤ ተውኔቱም ፤ የፊልም ጥበቡም ፤ ድርሰቱም ) ከእነርሱ ቢብስ እንጂ የተሻለ አይሆንም። የደራሲያን ማህበር መሪ አቶ መለስ በህይወት ሳሉ የወርቅ እስኪርቢቶ ሸልሞአቸው ሲያበቃ የማህበሩ አባል እንዲሆኑ ለጠየቃቸው አስብበታለሁ ያሉትን ይዞ ሲቃ እየተናነቀው ደስታውን ለካሜራ ሙያተኛው ሲያጋራውና ሰውየው መጽሀፍ ትራሱ መሆናቸውን ሲናገር ቤተ መንግስት ነው እንዴ የሚኖረው ስንል እርሳችንን ከጠየቅን አመት አይሞላም። እንዲህ አይነቱ ገጠመኝ ጉዳዩ ሐገራዊ ወረርሽኝ እንደሆነ ፍንትው አድርጎ ያሰያል። አንዳንዴ በአንክሮ ላስተዋለ ባለቅኔ ጸጋዬ ገ/መድህንም ይኽኛውም አደግዳጊ እኩል ደራሲ መሰኘታቸው ግርምትን የግድ መጫሩ አይቀርም። ኢትዮጵያ መቼም የፍቅረ አዲስ ነቅአ ጥበብን ‘ የሀሙሱ ፈረስንም’ የጻፈውም እንደ በዓሉ ግርማም አይነቱ ምጡቅና ደፋር ደራሲ አንድ አግዳሚ የሚቀመጡባት ሐገር ነችና አንዳንድ የቁጩ ደራሲ ነኝ ባይ ሲያጋጥምም ወይ ነዶ ከማለት ውጪ ማለት ምን ይባላል ? በተለይም የኋለኛው ልማታዊ ደራሲ ከሆነ ከግንድ የሚያጋጭ አባት አጋር ሲኖረው !
ጉዳዩ ከተነሳ አይቀር ጥቂት ስለ ‘ህዝባዊ ከያኒ’ ሀሳብ መጨዋወቱ የሚሻል ሳይሆን አይቀርም። በመጀመሪአይ ሕዝባዊ ኪነት ካልሆነው እንጀምር። ሕዝባዊ ከያኒ የዚህኛውን ወይም ያኛውን የፓለቲካ ቡድን የሙጥኝ ብሎ ‘ እምበር ተጋዳላይ’ አልያም ‘ጀግናን ይወዳል ልቤ’ የሚል ማለት አይደለም። ብዙዎች እንደሚስማሙበትም ወይ ደረቱ ፤ ወይ ሽንጧም ሲል ዘወትር ለፍትወት ንሸጣም የሚያሸረግድም አይደለም። ሕዝባዊ ከያኒ እንደ ኢትዮጵያ ባለ ዘርፈ ብዙ ማህበራዊ፤ ፓለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ችግሮች ባለበት ሐገር ዘወትር ለምን እያለ የሚጠይቅ፤ ጊዜ ከሞላላቸው ሚሊዮኖች ይልቅ ቀን የጎደላባቸውን ጥቂቶች ለቅሶ የሚያስተጋባ ድምድ ነው። በአጭሩ የሕዝባዊ ከያኒ ወገንተኝነቱ ከግፉአን እና ምንዱባን ዘንድ እንጂ ከባለጊዚዎች ጋር አይደለም። ሕዝባዊ ከያኒ የጥበብ ስራውን ለእውነት ባለው ቅርበት የሚመትር እንጂ በንዋያዊ ፍይዳውንና በአድናቂው ብዛት የማይለካ የጥበብ ሰውም ነው። ሕዝባዊ ከያኒ እውነተኛዋ ኪነ ጥበብ አንገት የምታስቀስፍ እንጂ ቤተ መንግስት የምታደገድግ አለመሆኗንንም ጠንቅቆ ያውቃል። ሕዝባዊ ከያኒ ‘ሕዝባዊ’ ነው ብንልም የብዙኋኑን ጉድፍ ለመንቀስና ለመሄስ ወዳ ኋላም አይልም እንዲያውም በተቃራኒው ሕዝብ በመንገኝነት አስተሳሰብና ልማድ የሚሄድበትን የዘወትር መንገድ ‘አይሆንም’ የጥፋት መንገድ ነው እያለ የተሻለ የመሰለውን ሀሳብ የሚጠቁም ነው።
ጥያቄው ታዲያ ምነው የእኛ ምድር ለምን ሚሊዮን አዝማሪዎች ግፋ ካለም ጥቂት ‘ልማታዊ’ ከያንያን ብቻ በዙባት ነው። የኢንቨስትመንት መሬታቸውን ጉልበተኛ ሲነጥቃቸው ግጥምና ዜማ ለመሬታቸው የሚያወጡ ዘፋኞች፤ አምባገነኖችን በቁማቸው ‘ ንጉሱ እርቃኑን ነው’ ሊሉ ሲገባቸው ለአስከሬናቸው ‘ የሙሴ በትርን’ የሚቀኙ (ቅኔ ከተባለ)፤ የቲያትር ድርሰታቸው ለተቃዋሚ ሀሳብ ያዘማል ተብሎ ከመድረክ በታገደባቸው ሳምንት ‘ ልማቲው ቲያትር’ ሊያሰተምሩ ባህር ዳርና ጎንደር የሚረግጡ ባጠቃላይ ዝለል ሲባሉ የት ድረስ እንጂ ለምን የማይሉ ‘አርቲስቶች’ ብቻ ያች ምድር ስታፈራ የኪነ ጥበብ ግዝትና እርግማን ይኖርብን ይሆን አሰኝቶ ጥያቄ ውስጥ መክተቱ አይቀርም።
ለማንኛውም ብቁ የፓለቲካ ሰዎችን የመፍጠሩ ነገር የእኛው ጉዳይ እንደመሆኑ እውነተኛ ከያኒያንን የመውለዱም ነገር የጋራ ፈተናችን መሆኑን ልብ ማለት ይገባል። አቀንቃኞቻችን ‘ ፍየል ቅጠል እንጂ …’ ባሉ ቁጥር ቁጭ ብድግ ማለታችን የትም እንዳላደረሰን ጊዜ አስተምሮናል። ለፍትሕ የሚሟገቱ ሕዝቦች ቀድሞም አሁንም እንደሚያደርጉት ቅድሚያው የሕዝብ ጉዳይ መሆኑን አስተውለን ከያኒዎቻችንን አንቱ ከማለታችን በፊት ሚዛን ላይ ማስቀመጡና የሀሳባቸውንና አቋማቸውን ጥንካሬ መመርመሩ ግድ የሚል ይመስላል። በየስደቱ ሐገሩም በሀገር ቤትም ‘አቧራ’ የሸፈናቸውን ሕዝባዊ ከያንያን ማበረታታቱ አዲስ መጪዎቹንም ከአገልጋይነት መነፈስ ወጥተው እውነትን፤ ፍቅርንና ፍትህን የሚሹ ይሆኑ ዘንድ መንገድ ማሳየቱ ተገቢ ተግባር ነው። እንደተለመደው ደግሞ ትልቁ ሀብታችን ‘ ተዓቅቦ’ ነውና አፍቃሪ ወያኔ አቀንቃኞች እነ ‘ ወይ ደረቱን’ ይዘው ኪሳችሁን እንለባችሁ ሲሉ ወግዱም ማለት ትልቅ ነገር ነው። የመሀመድ አላሙዲንን ማባባል ያሸነፈ ትውልድ የፍቅረ አዲስንና የማዲንጎን ‘እሪ በል ጎንደር’ ፈረንጅ ብላ ለማለት ብዙም አይከብደውም።
የቃላት መፍቻ ፡
አዝማሪ ፡ ከቤቱ ጥቂት ግጥም መሰንቆና ድምጹን ይዞ የሚወጣ ሰዎች ሊወዱት ይችላሉ የሚለውን ዘፈን በተከፈለው መጠን ሕዝብ እተሰበሰበበት ስፍራ የሚጫወት ሰው ማለት ነው። የአዝማሪ መነሻው ኑሮን ማሸነፍ በመሆኑ በተቸረው ገንዘብ መጠን መላጣውን ጎፈሬ ፤
ልማታዊ ከያኒ ፡ ይኅኛው ዘመናዊ አዝማሪ ሊባል የሚችል ነገር ግን ደጓሚው መንግስት አልያም ልማታዊ ባለ ሀበት ነው። በፈጠራ ችሎታው የአዝማሪን ያህል እንኳን ክህሎት የሌለው ፤ የመንግስትን የልማት ውሽከታ በግጥምና ዜማ መልክ ከሽኖ ሀገሪቱ ማርና ወተት የሚፈስባት ናት ካላመናችሁ በረከት ስምዖንን ጠይቁ የሚል ነው።
ቸር እንሰንብት
ወልደ ገብራኤል – ስዊትዘርላንድ

No comments:

Post a Comment