መስከረም ፲፭ (አስራ አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ኢትዮጵያን ለ 21 ዓመታት የገዙዋት አቶ መለስ ዜናዊ በህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት ሲለዩ እርሳቸውን የተኩዋቸው አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ ትሁት፣ ቅንና ደግ ቢሆኑም፣ የህወሀት ባለስልጣናትን ተጋፍተው ለውጥ የሚያመጡ ሰው አለመሆናቸውን እርሳቸውን በቅርብ የሚያውቁና አብረዋቸው የሰሩ ሰው ለኢሳት ተናግረዋል። አቶ ሀይለማርያም ተሿሚዎቻቸውን እንደፈለጉ ለማሽከርከር ለሚፈልጉ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የተመቸ ጠባይ እንዳላቸው የገለጡት ከእርሳቸው ጋር በአንድ ወቅት አብረዋቸው የሰሩት በአሁኑ ጊዜ የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ የአመራር አባልና የደቡብ ክልል ተወካይ የሆኑት አቶ ዳንኤል ሺበሺ ለኢሳት ገልጠዋል።
ከአቶ ሀይለማርያም ጋር የቀረበ ግንኙነት የነበራቸው አቶ ዳንኤል በቤተሰብም ሆነ በግል ባህሪያቸው እጅግ የተመሰገኑ ሰው መሆናቸውን ተናግረዋል::
አቶ ሀይለማርያም ጥሩ የግል ስብእና ቢኖራቸውም ሰብአዊ መብቶችን በመጣስ ከሚወገዘው ኢህአዴግ ጋር አብረው መስራታቸው አድርባይ ተደርገው እንዲተቹ መንገድ እንደከፈተና እርሳቸውም እንዲህ አይነቱን አስተሳሰብ እንደሚጋሩት አቶ ዳንኤል ተናግረዋል::
አቶ ሀይለማርያም በሚቀጥሉት የስልጣን ጊዜያቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ ያመጣሉ ብለው እንደማያስቡ አቶ ዳንኤል ሽበሺ ይናገራሉ::
አቶ ዳንኤል አቶ ሀይለማርያም እንደ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደፋር እርምጃ በመውሰድ ለለውጥ እንዲነሱም ጥሪ አቅርበዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የህወሀት ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ስዩም መስፍን የአቶ ሀይለማርያምን እና የአቶ ደመቀ መኮንንን ሹመት የህወሀት ኢህአዴግ አባላትና አንዳንድ የአመራሩ አካላት ተቃውመውት እንደነበር አምነዋል። ነባር የኢህአዴግ አባላት ይች አገር ብዙ ውስብስብ ችግሮች ያሉባት መሆኑዋን እያወቃችሁ እንዴት ምንም ልምድ ለሌላቸው ሰዎች ታስረክባላችሁ በማለት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ተናግረዋል። አቶ ስዩም መስፍን አዲሱ አመራር ብቻውን የሚንቀሳቀስ ሳይሆን እስከመጨረሻው በነባሩ አመራር ድጋፍ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ ግልጽ አድርገዋል::
የአቶ ስዩም ንግግር በኢህአዴግ ውስጥ የቡድን አመራር መፈጠሩን የሚያመላክት ብቻ ሳይሆን አዲሱ አመራር ራሱን ችሎ ለማስተዳደር ሀላፊነት እንዳልተሰጠው የፖለቲካ ተቺዎች የሚያቀርቡትን ትችት የሚያጠናክር ተደርጎ ታይቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢህአዴግ ውስጥ አሁንም የስልጣን ፍትጊያው እንደቀጠለ መሆኑን የሚደርሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኢህዴዶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ስልጣን እንኳን ይገባናል በማለት ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ ህወሀቶች በበኩላቸው ከመከላከያ፣ ደህንነትና ፖሊስ ተቋማት በተጨማሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታ ይገባናል እያሉ ነው።
አቶ ሀይለማርያም አዲሱን መንግስታቸውን ሳያዋቅሩና ሚኒስትሮቻቸውን ሳይሾሙ በ67ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላይ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ወደ ኒዮርክ ማምራታቸው አስገራሚ መሆኑን የአዲስ አበባው ዘገባ ገልጧል።
አቶ ሀይለማርያም ደሳለኝ እውነተኛ ስልጣን ቢኖራቸው ኖሮ ወደ ኒውዮርክ ከማምራት ይልቅ ሌሎች አጣዳፊ ስራዎችን መስራት ነበረባቸው ያለው ዘጋቢያችን፣ ማንኛውም አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያደርገው ካቢኔያቸውን አዋቅረው እና ለህዝብ አሳውቀው ራእያቸውን ወደ መትግበር በቀጥታ መግባት እንጅ ውጤት ወደ ሌለው የኒዮርኩ አመታዊ ጉባኤ ማምራት አልነበረባቸው ብሎአል።
No comments:
Post a Comment