Sunday, October 28, 2012

የ“አዲሱ መንግስት” ተግዳሮት እና የአቶ ኃይለማሪያም አጣብቂኝ

ዘሪሁን ተስፋዬ
(የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ባልደረባ)
አዲስ ታይምስ
 
mስከረም 2፤ 2005 ዓ.ም ሎንዶን። ከእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ የተወከሉ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል ከሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ጋዜጠኞች እና የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ተወካይ ግለሰቦች ጋር ለውይይት ተቀምጠዋል። ወቅቱ የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ማን ይተካ ይኾን የሚለው ጉዳይ የሚብሰለሰልበት ነበር። በርግጥ ለእንግሊዝ ተወካዮች የሚያብሰለስል ጉዳይ አልነበረም፤ ምስጢራቸውን በልባቸው ሸሽገው ከባለሞያዎቹ ተጨማሪ ሃሳቦችን ይሰበስባሉ። ሁሉም ባለድርሻ የሚመስለውን እና ጥናቱ ያመላከተውን ሐሳብ ሰነዘረ። ተንታኞችን በሚያስማማ መልኩ የአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ተተኪነት አነጋጋሪ አልነበረም። በጠቅላይ ሚኒስትር ተተኪ ማንነት ላይ ላይ ጥርጣሬ የነበረው ማንም አልነበረም። የድሕረ መለስ የፖለቲካ ኹኔታ እንዲሁ ትኩረት ያገኘ ነበር።የ“አዲሱ መንግስት” ተግዳሮት እና የአቶ ኃይለማሪያም አጣብቂኝ
የተለየ ጉዳይ የተከሰተው ግን ተሳታፊዎች ውይይታቸውን አጠናቀው በሻይ ሰዓት የግል ጭውውት ሲያደርጉ ነበር። የውጭ ጉዳይ ተወካዮቹ የያዟትን ምስጢር ለመተንፈስ እድል ያገኙ መሰለ። ከእንግሊዝ ተወካዮች መካከል አንዱ የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ አብጠርጥሮ ያውቃል ብለው ወደገመቱት የፖለቲካ ባለሞያ ቀረብ ብለው “ስለ ደመቀ መኮንን የምታውቀውን ንገረኝ?” አሉት። ለዓመታት የምሥራቅ አፍሪካን የፖለቲካ ግለት ሲለካ ለነበረው ባለሞያ ጥያቄው ዱብ ዕዳ ብቻ ሳይኾን፤ በአዲስ አበባ ከተማ በአንድ ቀበሌ ስለሚኖር አንድ ተራ ግለሰብ ዝርዝር ጉዳይ የመጠየቅ ጉዳይ ኾኖ ተሰማው። ስለአቶ ደመቀ የሚያውቀው ጉዳይ ቢኖርም ለበሰለ የፖለቲካ ተዋስዖ የሚበቃ አልነበረም። መረጃ በሌለው ጉዳይ ላይ ዝምታን ቢመርጥም ጉዳዩ ከንክኖት ስለነበር በተራው ጠያቂ ኾነ፤ “ደመቀን በተመለከተ ምን አዲስ ነገር አለ?” ምላሹም በዲፕሎማሲያዊ ቃና የታሸ ነበር። “ [ደመቀ] ቦታ ሳይያዝለት አልቀረም”- አጠር ምጥን ያለ ምላሽ።
ባለሞያው ተጨማሪ ማብራሪያ አላሻውም። ይልቁንም ነገሮች ከጠበቀው ውጪ እየተራመዱ እንደኾኑ ይበልጥ ግልጽ ኾነው ታዩት። በእርግጥም የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንደወትሮው ሁሉ ከግምት ውጪ የኾኑ ክስተቶችን እያስተናገደ ነበር። አቶ ደመቀን እንዲህ ላለ ከፍተኛ ስልጣን ማንም የገመተ አልነበረም። በአብዛኛው የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ ከሕወሓት ወይም ከኦሕዴድ እጅ ያመልጣል የሚል ግምት አልነበረም። በተለይ ለአመታት ‹‹ከስልጣኑ ስገለል ኖሪያለሁ›› የሚለው ኦሕዴድ ከስልጣን ቅብብሎሹ ተጋሪ ይኾናል የሚል ዕምነት በብዙዎች ዘንድ ነበር።
ይኹንና የቅርብ ተንታኞችም ኾኑ የአገሬው ዜጋ ሳይሰማ የብአዴን ተወካይ አቶ ደመቀ ትልቁን የሥልጣን እርከን እንደሚቆጣጠሩ እንግሊዞች “ደርሰውበት” ኖሯል። ከቀናት በኋላም የኾነው ይህ ነበር። በእዛው ሣምንት ቅዳሜ ምሽት ኢህአዴግ አቶ ደመቀን የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ “መረጠ”። በእለቱ የተሰራጨው ዜና ለብዙሃኑ የፖለቲካው ነፋስ አቅጣጫ ተንባዮች እና ዜጎች አዲስ ቢኾንም ቀመሩን ለሠሩት ለአሜሪካ፣ ለእንግሊዝ፣ ለአቶ ስዩም መስፍን እና ለአቶ በረከት ስምዖን ግን የቤት ሥራው በወጉ መጠናቀቁን “የሚያበስር” ነበር። “ቦታ ሳይያዝለት አልቀረም” የምትለዋ ዲፕሎማሲያዊ ሐረግም ፍቺዋን አገኘች።
ምስጢራዊነት ትልቁ የፖለቲካው ማቀንቀኛ መድረኩ የኾነ የፖለቲካ አመራር ሥፍራውን በተቆጣጠረበት አገር ግምቶች ሁሉ ፉርሽ ናቸው። ኢህአዴግ እና ምስጢረኝነት ደግሞ የዘመናት ቁርኝት አላቸው። ግንባሩ በትጥቅ ትግል ወቅት ስኬታማ ከኾነባቸው መንገዶች አንዱ የኾነውን ጥብቅ የምስጢር ጠባቂነት ወግ የመንግሥት ሥልጣንንም በእጁ ካስገባባት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሙጥኝ ብሎ ይዟል። የሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አልጋ ላይ መዋልን ተከትሎም በተለያዩ የብዙሐን መገናኛ ዘዴዎች ሲወራ የነበረውን “ዜና እረፍት” በዚሁ የምስጢረኝነት ጠባዩ በመጽናት እስከመጨረሻዋ ሰዓት ድረስ ሲያስተባብል ቆይቷል። በማስተባበሉ ሂደትም ግንባሩ የሥልጣን ሽግግሩን ጉዳይ አፍኖ ቢይዝም ውስጥ ውስጡን ግን ከለጋሽ አገራት በተለይም ከእንግሊዝ እና አሜሪካ ጋር በመኾን ቀመሩን ሲያሰላ ነበር።
ምስጢራዊነቱ የተዋጣለት ለተባለ ግምት በሩን የከፈተ ስላልነበርም የቀመሩ ስሌት የሕ.ወ.ሓ.ትን የዓመታት የበላይነት ያስወገደ በሚመስል ሁኔታ ለአደባባይ ወሬ በቃ። የደ.ሕ.ዴ.ን ሊቀመንበር ኃይለማሪያም ደሳለኝን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም ፍጹም ቦታ አይኖረውም ተብሎ ተግመቶ የነበረው ብ.አ.ዴ.ን አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በማሾም ቀመሩ የ.ሕወ.ሓ.ትን የበላይነት አደብዝዞ አሳየ። ይህም የተጭበረበረ ምስል የአንድ ብሔር ልሂቃን የበላይነት ለዘመናት ሠፍኖባት ለነበረባት አገር የፖለቲካውን አቅጣጫ ይለውጠው ይኾናል የሚል እምነት በነበራቸው ዜጎች እና በለጋሽ አገራት ዘንድ ትልቅ ስኬት ተደርጎ ተወሰደ። በርግጥም የበርካታ ቋንቋ ተናጋሪዎች ስብስብ የኾነው የደቡብ ክልል የሥልጣን ተቋዳሽ መኾኑ፤ እንዲሁም በሥልጣን ክፍፍሉ “ምንም ዓይነት” ሽራፊ ስልጣን ላይኖረው ይችላል ተብሎ ተገምቶ የነበረው የአማራ ክልል “ትልቁን” ድርሻ ማንሳቱ የስልጣን ሽግግሩ ከተገቢ ለውጥ ጋር ተካሂዷል ለሚሉት ሰዎች ማሳያ ሊኾን ይችላል።
በተለይ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የሥልጣን ሽግግሩን በአዎንታዊ መልኩ እንዲወስድ ያስገደደው ብሔርን ያማከለው ፌዴራሊዝም አዳዲስ ፊቶችን ከተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ማካተቱ ነው። ይኹንና የተለያየ የፖለቲካ ስብዕና የተላበሱ አመራሮች ወደ ሥልጣን መምጣታቸው እና የኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ የሥልጣን ሽግግር ሰላማዊ መኾን የአገዛዙን መሠረታዊ መለያ ጠባያት የለወጠ አይደለም። ይልቁንም በግልጽ የሚታይ የአመራር ክፍተት እና ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር የተወረሱ ሕጸጾች የፖለቲካው መለያ ጠባያት ኾነው እንዲቀጥሉ አድርጓል። አቶ ሃይለማሪያምም በቀላሉ ለመፍታት ከሚቸግሯቸው ተግዳሮቶች ጋር መፋጠጣቸው የግድ ነው።
ስንኩል አመራር
የአቶ ኃይለማርያም አስተዳደር ከሚገመተው በላይ በጣም ደካማ ነው። ከመነሻውም ቢኾን የቀድሞ ዋነኛ የሕ.ወ.ሓ.ት እንዲሁም የኢሕአዴግ አመራር አባላትን ይኹንታ ያላገኙት የደቡቡ ሰው፤ ከስሙ በስተቀር የአመራር ብቃታቸውን የሚያሳዩበትን ስልጣን ከእጃቸው አላስገቡም። አቶ መለስ ዜናዊ ሞት ባይቀድማቸው ቃል እንደገቡት በቀጣዩ ምርጫ ሥልጣናቸውን የማስረከብ ዕድል ቢኖራቸው ኖሮ ምንአልባት ከሕወሓት አፈና መጠነኛ የኾነ መተንፈሻ ያገኙ እንደነበር የተነገረላቸው አቶ ኃይለማሪያም ነጻ የመኾንን ዕድል ተነፍገዋል። የደህንነት፣ የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የአገሪቷን የደህንነት እና ስለላ ሥራ የሚያግዘው የቴሊኮሙኒኬሽን ክፍል አሁንም በሕወሓት እጅ የተያዙ እና ከአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቁጥጥር ውጪ የኾኑ ናቸው።
በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ እንዲሁም የኢኮኖሚ የአማካሪነት ሥፍራዎች ዋነኛ እና ጠንካራ ትግራዋይነትን በሚያቀነቅኑ የሕወሓት አባላት አሁንም የተያዙ ናቸው። በጉምሩክ፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ቢሮዎች እና በመካከለኛ የሥልጣን ዕርከን በፌዴራል ቢሮዎች የሚሠሩ የፖለቲካ ሹመኞች በብዛት የሕወሓት አባላት ሲኾኑ የማይገሰስ የበላይነትን ያሰፈኑ ናቸው። ብዙዎቹም ሥርዓቱ የፈጠረላቸውን አጋጣሚ ተጠቅመው አግባብ ያልኾነ ሐብት ያካበቱ በመኾናቸው በቀላሉ ሥፋራውን ለአዲሱ አመራር ለመልቀቅ የተዘጋጁ አይደሉም። ከዚህም ባሻገር በአቶ መለስ ቀጥታ አመራር ሥር የነበረው እና ሙሉ ለሙሉ የሕወሓት ቅርጽ እና መልክ የተላበሰው አምስት ሺህ የሚገመተው አግዓዚ ኮማንዶ እጣው ፈንታው ያለየ ሌላው የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራስምታት ነው። ይህም የአቶ ኃይለማሪያም መንግሥት አሁንም የሕወሓት የበላይነት የሰፈነበትን የፖለቲካ ሥርዓት ከለላ በመኾን ዕድሜ ከማራዘም ተሻግሮ ይህ ነው የሚባል ፋይዳ እንዳያስመዘግብ እንቅፋት ይኾናል።
ከግለሰብ አምባገነንነት ወደ ቡድን አምባገነንነት
አቶ መለስ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወዲህ ሕወሓት የሚታወቅበትን “ዴሞክራሲያው ማዕከላዊነትን” አፈር አልብሰው ሲያበቁ በብቸኝነት አመራሩን ተቆናጠው ኖረዋል። ጠያቂ በሌለበት እንዳሻቸውም ገዝተዋል። ከትልቁ የፖለቲካ ሥልጣን እስከ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ያለው የሥልጣን ተዋረድ ከእርሳቸው ቁጥጥር ውጭ አልነበረም። ይህም ታዛዥ እና ተገዢ እንጂ በራሱ የሚተማመን አመራርን ለኢሕአዴግ አልፈጠረም። ከዚህም ባሻገር ሁሉም የኢሕአዴግ አመራር አባላት በሚባል ደረጃ የሕዝብ ተቀባይነት የሌላቸው ሲኾኑ አንዳንዶቹም መርጦናል ብለው ለሚደሰኩሩለት ማኅበረሰብ ባዕድ ናቸው።
አቶ መለስም ጥለው የሄዱት ኢሕአዴግ ገና ወደ ፖለቲካው መድረክ እንደተቀላቀለ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ በመዳህ ላይ ያለ ነው። ይህ ኹኔታም አደገኛ መዘዝን ይዞ ነው የመጣው። ለዘመናት በአንድ ግለሰብ አምባገነንነት ከሚመራ ግንባር የሥልጣን ሽኩቻ ወደበዛበት እና የግለሰቦች ፉክክር ወዳየለበት የአንጃዎች ጥርቅም የግንባሩን ቅርጽ ይለውጠዋል። “እኔ ከማን አንሼ” የሚለው የፉክክር መንፈስ የፖለቲካውን መድረክ ይቆጣጠረዋል። ይህ ዓይነቱ ለውጥ የግል ወይም የብሄር ጥቅማቸው ያስተሳሰራቸው በአንድነት ጥላ ሥር የተሰባሰቡ አባላት ብዛት መገለጫው ይኾናል። ግንባሩም የይስሙላ “አንድነት” ቢኖረውም ልል እና አማካይ የአመራር ሥፍራ እንዳይኖረው ያደርገዋል።
አማካይ ሥፍራ የሌለው አመራር ተጠያቂነትን የሚያዳፍን እና የቡድን አምባገነንነትን የሚያሰፍን ነው። አቶ ኃለማሪያምም እንዲተውኑ የተሰጣቸውን “ሥልጣን” በአንድ እርምጃ ለማራመድ ቁርጠኝነቱን ለማሳየት እስካሁን አልደፈሩም። ለመጥቀስ ያህል ሕገ መንግሥቱ የፈቀደላቸውን በቤተ መንግሥት የመኖር መብት እንኳ ለመጠየቅ ድፍረቱን አላገኙም። ከርሳቸው ይልቅ ከወይዘሮ አዜብ መስፍን ጋር ቅሬታ አላቸው የሚባሉት የሕወሓት አባላት እና አቶ በረከት ስምዖን እመቤቲቱን ለማስወጣት ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላሉ። አቶ ኃይለማሪያም ለውሳኔ በዘገዩ እና የተተበተቡበትን ሠንሠለት ለመበጣጠስ በአቅማሙ እና በዘገዩ ቁጥር የአንጃዎቹ መበርታት የያዙትንም ቦታ ሊያሳጣቸው ይችላል።
በሌላ በኩል የግንባሩ መፍረክረክ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ባለበት አገር እንደ መልካም አጋጣሚ የሚቆጠር ነው። የተሻለ ታክቲክ በመንደፍ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ አመቺ ነው። ይኹንና አሁን ባለው ኹኔታ በጥንካሬ የሚጠቀስ ተቃዋሚ በአገር ውስጥ የለም። የአማራጭ ሃይሎች በፖለቲካው መድረክ አለመታየት ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ ውስጥ ከሚታየው የሥልጣን ሽኩቻ ጋር ተደማምሮ አጠቃላይ አገራዊ የአመራር ቀውስ ሊፈጥር ይችላል።
ኦ.ሕ.ዴ.ድ- “ሲሞቅ በማንኪያ . . .”
የአቶ መለስ ዜናዊ አልጋ ላይ መዋልን ተከትሎ ከበሮ ይመታባቸው ከነበሩ ሥፍራዎች ሁለቱ ተጠቃሽ ናቸው- ጎረቤት ሶማሊያ እና የግንሩ አጋር ድርጅት ኦ.ሕ.ዴ.ድ። በተለይ የሶማሊያ ታጣቂዎች (ሽብርተኛውን አል-ሻባብን ጨምሮ) የመለስን መሞት በጉጉት ይጠብቁ ነበር። ከተለያዩ የሚዲያ ባለሞያዎች መረጃ ለመሰብሰብ የሚያደርጉትን ያላሰለሰ ጥረት የተመለከተ ጠባቸው ከአቶ መለስ ጋር ብቻ የኾነ ያህል እንዲሰማው ያደርጋል። የኦ.ሕ.ዴ.ድ ከበሮ ግን የአል-ሻባብን ያህል ባይደምቅም አጋጣሚውን ተጠቅሞ ሥልጣን ለመጋራት ያለውን ፍላጎት ያሳይ ነበር።
ከሁለት ወራት በፊት የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረገው በኦሮሚያ ክልል ተቀባይነት አላቸው የሚባሉትን አቶ አባ ዱላ ገመዳን ለድርጅቱ ሊቀመንበርነት በማጨት ነበር። ወትሮውኑም ቀድሞ የነበራቸው ወጣ ያለ ተሳትፎ በኢሕዴግ ያልተወደደላቸው አባ ዱላ አፈ ጉባዔነቱን እንዲይዙ የተደረገው ኾን ተብሎ ከኦሮሚያ ክልል ለማራቅ መኾኑን ማንም አላጣውም። በወቅቱም ድርጅቱ እርሳቸውን ወደፊት ለማምጣት ፍላጎቱን ሲያሳይ ከፍተኛ ተቃውሞ የመጣው ከ.ሕ.ወ.ሓ.ት ነበር።
ኦ.ሕ.ዴ.ድ ለሕ.ወ.ሓ.ት “ቀኑን የሚጠብቅ ኦ.ነ.ግ” ማለት ነው። እምነት ሊጥሉበት አልቻሉም። ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የኦ.ነ.ግ አባላት መሰግሰጊያ ነው ሲሉ ይሟገታሉ። በመኾኑም ድርጅቱ በተሻለ ሰው እንዳይወከል የመንግሥት ከፍተኛ አመራር አካላት ሌት ተቀን ደክመዋል። ለዚህም ይመስላል በቅርቡ ድርጅቱ ባደረገው ስብሰባ አቶ አለማየሁ አቶምሳን ለድርጅቱ በከፍተኛ ሥልጣን ደረጃ አለመወከል ተጠያቂ በማድረግ የህወሓትን ሴራ ለማደፋፈን እየተሞከረ ያለው። “አቶ አለማየሁ ሁለቱንም ሥልጣን ደርቦ በመያዝ ኦሮሚያ ከፍተኛ ሥልጣን በፌደራል መንግሥቱ እንዳይኖረው አድርጓል” የሚል ወቀሳ ከአባሎቻቸው የደረሰባቸው። ነገሩ ግን ግልጽ ነው። የአቶ በረከት እና መሰሎቻቸው ሴራን ለመሸፈን እና ችግሩን ወደ ድርጅቱ ለማምጣት ነው።
ከኦሕዴድ ጋር ያለው ትግል በአጭሩ የሚቋጭ አይመስልም። በቀጣይ ከፍተኛ ሹም ሽር ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል። በርካታ የድርጅቱ አባላት ጥርስ የተነከሰባቸው እና በቅርቡ ከፓርቲው የሚሰናበቱ ናቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን የሕወሓት ሙሉ ተሳትፎ እንጂ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ከቀጥጥራቸው ውጪ የኾኑ ነገሮች እየተካሄዱ ነው። ከሁሉ በላይ ግን ኦሕዴድን ከከፍተኛ ሥልጣን ማግለሉ የአቶ ኃይለማሪያምን የሥልጣን ዘመን ተጨማሪ ፈተና ይሰጠዋል።
ከላይ የተጠቀሱት አንኳር ነጥቦች እና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች ወሳኝ አመራርን የሚጠይቁ ጉዳዮች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለትክክለኛ ለውጥ የቆሙ ከኾነ ከፊታቸው የተጋረዱትን ፈተናዎች በብልሃት እና በትዕግስት መፍታት ይኖርባቸዋል። አዳዲስ ሰዎችን ወደ ሥልጣን ማምጣት፣ ለተቃዋሚዎች መድረኩን መክፈት፣ ለነጻው ፕሬስ አመቺ ሁኔታን መፍጠር እንዲሁም የፖለቲካ እሰረኞችን መፍታት የተግባሮቻቸው ሁሉ መጀመሪያ ሊኾኑ ይገባል።

No comments:

Post a Comment