Sunday, October 7, 2012

ከፖለቲካ ፍጥጫው በስተጀርባ (ከኢየሩሳሌም አርአያ)


ከኢየሩሳሌም አርአያ
በገዢው ሰፈር ጎራ ለይቶ ከተለኮሰው የቡድን ፖለቲካዊ ፍጥጫ እና ሴራ ጀርባ አገር እና ህዝብን የሚጎዳ አደገኛ ተግባር በግልጽ እና በስውር እየተካሄደ እንዳለ ከተለያዩPolitical cries inside Ethiopian ruling party የፓርቲው ምንጮች የተገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በተለይ በብአዴን እና በህወሃት ቱባ አመራሮች መካከል ስር ሰዶ የቆየው እና የአቶ መለስን ህልፈት ተከትሎ ያገረሸው የውስጥ ሽኩቻ ሁለት ቡድኖች የሃይል አሰላለፋቸውን ለማጠናከር «ይረዱናል » የሚሏቸውን የሌሎች ፓርቲ ሹማምንት እና የመከላከያ የጦር አዛዦች ከጎን የማሰለፉን ተግባር ቀጥለውበታል።ለግንዛቤ እንዲረዳ የሃይል አሰላለፉን በጥቂቱ በመዳሰስ ወደ ዋናው ነጥብ እናምራ።
ከበረከት እና ዓዜብ ጎን በመሰለፍ ቀዳሚ የሆኑት አቶ ተፈራ ዋልዋ እና አዲሱ ለገሰ ናቸው።አቶ አዲሱ በይፋ ከሚታወቀው የአየር መንገድ የቦርድ ሃላፊነታቸው ባሻገር ኮተቤ መስመር በሚገኘው እና «የአቢዮታዊ ዲሞክራሲ ማኔጅመንት ት/ቤት »ተብሎ በተከፈተው ተቋም ዋና ሃላፊ እና ለባለስልጣናት እንዲሁም ካድሬዎች መምህር ጭምር ናቸው። ከመለስ መታመም ወዲህ የህወሃት ካድሬ ላልሆኑ በአቶ አዲሱ እየተሰጠ ያለው ፖለቲካዊ ትምህርት ሳይሆን የበረከትን አቋም የሚያቀነቅን እና ህወሃትን የሚያጥላላ ቅስቀሳ ሆኖአል።
በሌላ በኩል ዓዜብ ከጎኗ ማሰለፍ የቻለችው ጄነራል ሰአረ መኮንን እና እንዲሁም በእርሳቸው የሚመራውን ጦር ነው ።በተጨማሪም ቴዎድሮስ ሃጎስ ይገኛሉ ።የዓዜብ አስገራሚ “አቋም” በሶፊያን አህመድም ላይ ተንጸባርቋል።”ለኤርትራ ካሳ “በሚል 2.1 ቢሊዮን ብር ለሻብያ በሚስጥር እንዲሰጥ በፊርማቸው ጭምር ከወሰኑት መካከል አቶ መለስ ዜናዊ፣ሙሉጌታ አለም ሰገድ ፣ሟቹ አቃቤ ህግ መስፍን እና ሶፊያን አህመድ ይገኙበታል።ዓዜብ ከዚህ በመነሳት “መለስን የማይክዱ ታማኝ “ካለቻቸው አንዱ ሶፊያን ናቸው ።
በተቃራኒው በነስብሃት በኩል ያለው የሃይል አሰላለፍ ለየት የሚያደርገው በነ በረከት ቂም የቋጠሩ “ተገፊ እና አድፋጭ”አመራሮችን እያቀፈ መቀጠሉ ነው ።ስዩም መስፍን ፣ሃይለኪሮስ ገሰሰ፣አባዲ ዘሞ ፣ቢተው በላይ . . . .. .በከፊል ይጠቀሳሉ ።
ስዩም ከስልጣን ተነስተው የቻይና አምባሳደር መሆናቸው ከተገለጸ በኋላ በውጭ ጉዳይ ቢሮ የተመደቡ ሰባት አባላት በሂልተን ሆቴል የምሳ ግብዣ አድርገውላቸው የነበረ ሲሆን በወቅቱም “ከስልጣን እንደምነሳ ምንም የማውቀው አልነበረም።አስቀድሜ ባውቅ ኖሮ ለእናንተም ብዙ ነገር አደርግ ነበር፤ አዝናለሁ። የበረከት ፣መለስ እና አዜብ ስራ ነው “ብለው ስዩም በቁጭት እንደነገሯቸው በስፍራው ከነበሩ ማወቅ ተችሏል። በሌላም በኩል ሃይለኪሮስ ለበረከት ከፍተኛ ቂም አላቸው ።ከቻይና ቀጥሎ የሱዳን አምባሳደር ተደርገው ነበር ።በኋላም በቃኝ ብለው ከፓርቲው በመውጣት የግል ንግድ ውስጥ ተሰማርተው ቆይተዋል ።አሁን ደግሞ ለበቀል ሲሉ የስብሃትን ቡድን ተቀላቅለዋል ።እንዲሁም በመለስ/በረከት የማይወደዱት እና ሃይለኪሮስን ተክተው በሱዳን አምባሳደር እንዲሆኑ የተመደቡት አባዲ ዘሞ ሌላው የፍልሚያው ተሳታፊ ናቸው ።ድፍረት የተሞላበት የተቃውሞ ሃሳብ በመሰንዘር እና መለስን ጭምር በመጋፈጥ የሚታወቁት ብቸኛው አባዲ ከዚህ በተጨማሪ በህወሃት ካሉ ባለስልጣናት ሙስና ውስጥ ካልገቡ ሁለት ሰዎች አንዱ ናቸው በማለት ምንጮች ይመሰክራሉ ።ሁለተኛው ደግሞ አባይ ወልዱ ናቸው ሲሉ ያክላሉ ። ከህወሃት የተባረሩት አምባሳደር አውአሎም ወልዱ ወንድም ናቸው አቶ አባይ ወልዱ ።ቢሆንም አባይ በጣም ደረቅ እና አምባገነናዊ ስብእናም እንዳላቸው ምንጮቹ አልሸሸጉም።
በዚሁ ወደ ዋናዎቹ ሁለት ርእሰ ጉዳዮች እናምራ፤ የበረከት እና ስብሃት ጎራዎች አንዱ የሆነው የልዩነት ፍጥጫ የአቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ እና የአቶ ደመቀ መኮንን ሹመት ይገኝበታል። ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያምን በተመለከተ የተገኙ ተጨባጭ መረጃዎችን ለጊዜው እናቆያቸው ፤ትችት እና ወቀሳውንም እንዲሁ።ነገር ግን አቶ መለስ ማንኛውንም የፓርቲ አመራር ሲመለምሉ እና ሲያስመለምሉ የጀርባ ታሪኩን የሚያራምደውን አቋም . . . .መነሾ በማድረግ እንደሆነ የሚጠቁሙት ምንጮቹ አያይዘውም ፤ ተምሯል ፣ለሃገር እና ህዝብ ይሰራል. . .ወ.ዘ.ተ የሚለው በጭራሽ መስፈርት ሆኖ አይገባም ይላሉ ።የምልመላው ጥናት ቀንደኛ ተሳታፊ በረከት ሲሆኑ በመቀጠል የህወሃት አመራሮችም ይካፈላሉ ።ህወሃት ከበረሃ አንስቶ የተማረ አይወድም ፣ጠላቱ ነው ሲሉ የፓርቲው ምንጮች ያሰምሩበታል።
አቶ ሃይለማርያም ገና በጠዋት ለፓርቲው የተመለምሉበት የነመለስ-በረከት “መስፈርት”እንደተጠበቀ ሆኖ የመለመላቸው ተ/ማርቆስ ተ/ማርያም የተባለ እና አሁንም ድረስ ከጀርባ ሆኖ የደቡብ ክልል ባለስልጣናትን እንዲሁም መስተዳድሩን እያሽከረከረ ያለ ካድሬ ነው።ተ/ማርቆስ በደርግ ዘመን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ ምሩቅ የነበረ እና በአስተማሪነት የተመደበ ፣እንዲሁም ወደ አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተዛውሮ ሲሰራ ከቆየ በኋላ በ1982 አመተ ምህረት ገደማ የተባረረ ነው። ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ሲመጣ በአቶ ቢተው በላይ አማካይነት ተመለሰ ።ከዚያም በይፋ ያልተገለጸ ቁልፍ ስልጣን እንዲጨብጥ ተደረገ ፤በአጭሩ ሃይለማርያም ዛሬ ለደረሱበት የስልጣን ደረጃ ተ/ማርቆስ ለአቶ መለስ ያደረሰው የስለላ-ጥናት ውጤት ሲሆን ከዚሁ ጎን የባለቤታቸው ወ/ሮ ሮማን አቋም በነ መለስ “መስፈርት “ አሟልተው በመገኘታቸው ጭምር ነው ። በተመሳሳይ የበረከት ምልምል የሆኑት ደመቀ መኮንን በኢሰፓ አባልነት ይታማሉ ።
እነ ስብሃት ራሳቸው ሲከተሉት እና ሲያስፈጽሙት የነበረ በመሆኑ የሃ/ማርያም እና የደመቀ ሹመት በበረከት በኩል መከወኑ እጅግ አበሳጭቶአቸዋል።የጠቅላይ ሚንስትሩ ቀጣይ “አቋም” ይቀየራል ? ወይስ ከአሁኑ ማንጸባረቅ በጀመሩት የመለስ/በረከት አጥፊ መስመር ጉዞ ይቀጥላሉ ?የሚለው በተለያዩ ወገኖች ድብልቅልቅ ስሜት ፈጥሮአል ፡፤ለምሳሌ በቅርቡ በሰጡት መግለጫ ላይ “ቀይ መስመር፣ሰላማዊ እና ህጋዊ ባርኔጣ” በማለት ንጹሃን የህሊና እስረኛ ጋዜጠኞችን እና በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በማድረጋቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ ወገኖችን ያለ ሃፍረት በጅምላ ወንጅለዋል።በዚህ ሳያበቁ “ከሻብያ ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ መነጋገር እንፈልጋለን “ሲሉ የመለስ ፣በረከት እና ስብሃት… አቋም ቃል በቃል አንጸባርቀዋል።በረከት፣መለስን የተኩት የህወሃት ሊቀመንበር አባይ ወልዱ “ከተቃዋሚዎች ጋር ድርድር የማይታሰብ ነው “እያሉ በጥላቻ የታጠረ አቋማቸውን ሲገፉበት በሚስተዋልበት ተጨባጭ ሁኔታ ዛሬም ሻእቢያ እግር ስር በመደፋት ልምምጥ እና ልመናው መቀጠሉ ፣በአንጻሩ በአገር ውስጥ እና በውጭ ያሉ የተቃዋሚ ሃይሎች የድርድር ጥያቄ መገፋቱ እና አፈናው ተጠናክሮ መቀጠሉ ሲታይ ፦በእርግጥም ከሃ/ማርያም ጀርባ ያለው “ሹፌር”ለኢትዮጵያ እና ህዝቧ ጥቅም ምንም ግድ የሌለው እንደሆነ በቀላሉ ያሳያል ይላሉ እነዚሁ ወገኖች ።
ወደተከታዩ ነጥብ ስንሻገር በአስደንጋጭ ሁኔታ በሃገሪቱ ተጠናክሮ የቀጠለውን የሙስና ዘመቻ እናገኛለን ። በግልጽ እና በስፋት የሙስናውን መንደር ከተቀላቀሉት እና “ተከታይዋ ወይም ግልገሏ አዜብ”የሚል ቅጽል የወጣላቸው የበረከት ስምኦን ባለቤት አሰፉ በቀዳሚነት ትጠቀሳለች ።በረከት “አሲ”እያሉ በቁልምጫ የሚጠሯት አሰፉን ጨምሮ 6 የቤተሰብ አባላት በፓርቲው አባላት “ደቂ ማዘር” በሚል መጠሪያ ይታወቃሉ ።የታምራት ላይኔ ባለቤት የዚሁ ቤተሰብ አባል ስትሆን ከብአዴን የወጣችው (ከ6ቱ)እሷ ብቻ ናት ።የታደሰ ጥንቅሹ ባለቤት እንዲሁ የአሰፉ ቤተሰብ አካል ናት ።
የበረከት ባለቤት አሰፉ የመንግስት ስራ በመተው ወደ ከፍተኛ ንግድ መግባቷ ምንጮቹ አረጋግጠዋል። በአስመጭና ላኪ ንግድ የተሰማራችው አሰፉ በተለይ ወደ ዱባይ እና ሳኡዲ የተዘጋጁ የከብት ስጋ እና ቡና በመላክ እንዲሁም ከዱባይ እና ቻይና የሞባይል ቀፎዎችን የመኪና መለዋወጫ እቃዎችን እና የተለያየ ይዘት ያላቸውን ጄነረተሮች በማስመጣት ንግዷን አጧጡፋለች ።አብዛኞቹ ቀረጥ ሳይከፈልባቸው በጉምሩክ ሰትት ብለው እንደሚያልፉ ሲታወቅ የአዜብ ቀጥተኛ ድጋፍ እና ትእዛዝ እንዳለበት ተጠቁሞአል። አብዛኛውን ጊዜ ሁለቱም አብረው እንደሚያሳልፉ ምንጮቹ ገልጸዋል። በአስር ሚሊዮኖች የሚገመት ዶላር በመዛቅ ላይ የምትገኘው የበረከት ሚስት አሰፉ ለህወሃት ስር የሰደደ ጥላቻ እንዳላት የገለጹት እነዚህ ወገኖች በተደጋጋሚ ይህን አቋሟን በይፋ ስታንጸባርቅ መታየቷን አስታውቀዋል።
በሌላም በኩል አባይ ፀሃዬ ለበርካታ ባለሃብቶች በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ብድር በመፍቀድ በቅርብ ስጋ ዘመዶቻቸው በኩል ሃብት እንዳካበቱ ታውቆአል ። ቀደም ሲል የነበራቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሃላፊነት ተገን አድርገው የፈጸሙት ዘረፋ ነው።የሙስናው ተዋናዮች አምስት የአባይ ጸሃይዬ የቅርብ ዘመዶች ናቸው ። ባለሃብቶችን በማግባባት ደላላ ሆነው እየቀረቡ በተፈለገው መጠን የገንዘብ ብድር ማሰጠት እንደሚችሉ ከገለጹ በኋላ ያለምንም ውጣ ውረድ አባይ ጸሃዬ እንዲፈቅዱ ይደረጋል። ከብድሩ እስከ 50 ሚሊዮን ኮሚሽን ይወስዱ እንደነበር ተጠቁሞአል ።ተመሳሳይ ተግባር አቶ ግርማ ብሩ ይፈጽሙ እንደነበር ምንጮቹ አያይዘው ገልጸዋል። በተለይ “ራዲሰን”የተባለው እና ካዛንችስ አካባቢ የተገነባው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ለግንባታ ተብሎ የተፈቀደለት 400 ሚሊዮን የብድር ገንዘብ እንደሆነ ሲረጋገጥ ከዚህ ገንዘብ ባለስልጣናቱ በኮሚሽን መልክ 150 ሚሊዮን ኪሳቸው እንደከተቱ ተረጋግጦአል። በጣም የሚገርመው ሸራተን ሆቴል እንኳን በአንድ መቶ ሰባ ሚሊዮን እንደ ተገነባ በይፋ እየተነገረ ለዚህኛው ሆቴል ግን ሁለት እጥፍ በብድር ስም ተፈቅዶ ሲመዘበር አቶ መለስ ጭምር ያውቁ ነበር ።በማያያዝም በባንክ ብድር የተሰራው ሸራተን ላለፉት 15 አመታት ብድሩን ያለመክፈሉና ባለፈው አመት ባንኩ የመሰረተው ክስ እንዲቆም መደረጉ አስገራሚ ሆኖአል ።ይህ እዳ ሳይከፈል በባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አቶ በረከት ስምኦን ትእዛዝ 942 ሚሊዮን ብር ለሼሁ ድርጅቶች መፈቀዱ እና በቅርቡ ደግሞ ታግዶአል መባሉ እንቆቅልሽ ከመሆኑም ባሻገር ምን ያክል የተበላሸ እና ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ስርአት አልበኝነት በሃገሪቱ መንገሱ አመላካች ነው ተብሎአል ።በነገራችን ላይ አቶ በረከት ወደ ደቡብ አፍሪካ በሼሁ ቻርተር አውሮፕላኖች እንደሚመላለሱ ምንጮቹ አረጋግጠዋል።
በሌላም በኩል በቃሊቲ- አቃቂ በ7 ቢሊዮን የተቋቋመው ግዙፍ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ ሲጠቀስ ከጀርባ የአንበሳው ድርሻ ባለቤቶች ስዩም መስፍን እና አዲሱ ለገሰ ይገኛሉ ። ከዚህ በማስከተል በተለያዩ ባለስልጣናት የተገነቡ እና እየተገነቡ ያሉ የሙስና ውጤቶች እንመልክት ።በትግራይ መቀሌ ከተማ “ለአካባቢ የአየር ጥበቃ “በሚል ተተክሎ የነበረውን ደን በመጨፍጨፍ መሬቱን የተቀራመቱት ስብሃት ነጋ ፣ቴዎድሮስ ሃጎስ ፣ሃለቃ ጸጋይ፣ጎበዛይ ፣ኪሮስ ቢተው፣ተክለወይኒ፣… ዋና ዋናዎቹ ናቸው ።”አፓርታይድ መንደር”በሚል በነዋሪው በተሰየመው በዚህ ቦታ የተደረገው የአደባባይ የመሬት ቅርምት የተቃወመ የማዘጋጃቤት ሃላፊ ከስልጣን ተነስቶ እስካሁን የደረሰበትም አይታወቅም ።የተጠቀሱት የህወሃት ሹማምንት እጅግ ምርጥ እና ዘመናዊ ቪላ በጥድፊያ እያስገነቡ እንዳሉ ሲታወቅ ባለ ሁለት እና ሶስት ፎቅ የሆኑት ቪላዎች ከአስር ሚሊዮን ብር በላይ ለእያንዳንዱ ቤት ግንባታ መድበው ስራውን ወደ ማጠናቀቅ መድረሳቸውን ማረጋገጥ ተችሎአል ። በስምንት ሚሊዮን ብር የተገነባው የኪሮስ ቢተው ዘመናዊ ባለ ሁለት ቪላ ግንባታው በቅርቡ እንደተጠናቀቀ ታውቆአል።
ሽማግሌው ስብሃት በቀድሞው የአየር ሃይል ም/አዛዥ ጄነራል ሰለሞን እና በአሜሪካ በሲያትል እና በዋሽንግተን ዲሲ በሚኖሩ ስምንት የስብሃት የአጎት እና የአክስት ልጆች ስም በአክሲዮን ሽፋን የከፈቱት “ሉሲ አካዳሚ”ከሙስና የተገኘ ትልቅ የገቢ “ዘረፋ” ምንጭ ሆኖአል ።አካዳሚው በገርጂ እና ሳር ቤት – ባለ ስድስት ፎቅ ህንጻ አቅፎአል። የፌደራል ፖሊስ ም/ኮሚሽነር ሃሰን ሺፋ በቦሌ ያስገነቡት ባለሁለት ቤት ቪላ ተጠናቆ በየወሩ 25 ሺህ ብር መከራየት ጀምሮአል። የጄነራል ሳሞራ ቪላ ከለንደን ካፌ ፊት ለፊት ሲገኝ ከ1997 አመተ ምህረት ጀምሮ በየወሩ 30 ሺህ ብር ይከራያል። ባለ ሶስት ፎቅ የአባዱላ ቪላ ከሳሞራ ቪላ ቀጥሎ ሲገኝ ከሚያዚያ 97 አመተ ምህረት ጀምሮ በየወሩ 4 ሺህ ዶላር ለነጮች ይከራያል። ቦሌ ኤርፖርት መግቢያ ከኖክ ማደያ ጀርባ የብርሃነ ገ/ክርስቶስ እና የአዲስአለም ባሌማ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ባለሶስት ፎቅ ምርጥ ቪላዎች ይገኛሉ።በ1988 አመተ ምህረት የተገነቡት የሁለቱ ቪላ ሁለት የአሜሪካ ከፍተኛ መኮንኖች እያንዳንዳቸው በአራት አራት ሺህ ዶልር ተከራይተውታል። ከኢምፔሪያል ሆቴል አጠገብ የተገነባው እና በሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ የተሰራው የተፈራ ዋልዋ ባለ ሦስት ፎቅ ቪላ በወር 30 ሺህ ብር መከራየት የጀመረው በ97 አመተ ምህረት መጨረሻ ነበር።የሙስናው ዝርዝር እና ስፋት በጣም ሰፊ ነው ።ወደ ውጭ እየሸሸ የሚገኘው የሃገር እና ህዝብ ሃብት ሳይካተት ማለት ነው ።
በዚህ አጋጣሚ ሳይጠቀስ የማይታለፈው በታይላንድ ባንኮክ የሚጸመው አሳዛኝ የሙስና ድራማ ነው። በርካታ የህወሃት ጄነራሎች እና ሌሎች ባለስልጣናት ከራሳቸው አልፈው የቅርብ ዘመዶቻቸውን እና ውሽሞቻቸውን ጭምር በከፍተኛ ወጭ ማሳከምን ተያይዘውታል። ከህወሃት ጀነራሎች መካከል ጄነራል ሰአረ እና ጀነራል ተስፋዬ በዋናነት ይጠቀሳሉ ።የሆስፒታሉ የህክምና ወጭ እንዲሁም የሚያርፉባቸው ባለ5 ኮከብ ሆቴሎች (ኢንተር ኮንቲኔታል እና ቻል ዲፖሎ )ናቸው ። በየሶስት ወሩ በሚቀርበው የክፍያ ዝርዝር ሪፖርት ከሰባት እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፈል የቅርብ እማኞች ያስረዳሉ።
ከፍተኛ ክፍያ የተፈጸመው ለአባዱላ ገመዳ ልጅ ነው ።የሶስት አመቷ ህጻን ዲቦራ አባዱላ ስትወለድ የአንጀት ፣የሳምባ እና የአእምሮ ችግር ነበረባት ።ለሁለት አመት ተከታታይ ህክምና ተደረገላት ።የአባዱላ ባለቤት ራሄል ልጇን ያን ያክል ጊዜ ስታስታምም ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ቪላ ተከራይታ ነበር ።የሁለት አመት የተከፈለው አጠቃላይ ወጪ 2.5 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ተረጋግጦአል። በአሁኑ ወቅት አባዱላ ሼሁን ተገን አድርገው ከበረከት ጎን ተሰልፈዋል።
በመጨረሻም አዜብ መስፍንን ከኤፈርት ለማስነሳት ሰፊ ዘመቻ በህወሃት አመራር ውስጥ መከፈቱን ለማወቅ ተችሎአል። የፓርቲው ሰዎች “የአዜብ ጸሃይ እየጠለቀች ነው “ብለዋል ።በቅርቡ አሜሪካ የቀሩት የአዜብ ምክትል ጌታቸው በላይ ለሽማግሌው ስብሃት ነጋ የቅርብ ዘመድ ሲሆኑ ከአቶ መለስ ጋር ደግሞ አብሮ አደግ ጎረቤቶች እንደነበሩ ታውቆአል። በኤፈርት የአዜብ ፈላጭ ቆራጭነት ያስመርራቸው እንደነበር ሲታወቅ ከነበራቸው የሚንስትርነት ስልጣን ወደታች መንሸራተታቸው ቅሬታ አሳድሮባቸው እንደቆየ የቅርብ ምንጮች ጠቁመዋል ። የሙስናው ጉዳይ እንዲጣራ አንድ ፖለቲከኛ ጥቆማ ስጥተዋል።

No comments:

Post a Comment