Monday, December 3, 2012
ጀኔራል መሐመድ ሲነሱ፣ ጀኔራል ሞላ ተመለሱ
ጀኔራል መሐመድ ሲነሱ፣ ጀኔራል ሞላ ተመለሱ
(እየሩሳሌም አርአያ)
ባለፈው ወር ከአየር ሃይል አዛዥነታቸው የተነሱት ጄ/ል ሞላ ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንደተመለሱ ምንጮች ገለፁ። ጄ/ል ሞላን እንዲተኩ
ተደርገው ለሶስት ሳምንት አየር ሃይሉን በዋና አዛዥነት ሲመሩ የሰነበቱት ጄ/ል መሓመድ እንደነበሩ
ያረጋገጡት ምንጮች አክለውም ጄ/ል ሞላ ወደ አዛዥነት በመመለሳቸው ጄ/ል መሓመድ ይዘውት
ከሰነበቱት ሃላፊነት እንዲነሱ መደረጉን ገልፀዋል። ጄ/ል መሓመድ የአግዚ ክፍለ ጦር ዋና አዛዥ እንደሆኑ
ሲታወቅ፤ በተጨማሪ የሕወሓት ታጋይ እንደነበሩ ተጠቁሞዋል። አየር ሃይልን ለመምራት የሚያስችል ምንም
እውቀት እንደሌላቸው ምንጮቹ ገልፀዋል።
ጄ/ል ሞላ ከሃላፊነት እንዲነሱ የተደረገው ከጄ/ል ሳሞራ ጋር በተፈጠረ የከረረ ቅራኔ መሆኑን ምንጮቹ
ሳይጠቁሙ አላለፉም። ሳሞራ በመሩት ስብሰባ ላይ ጄ/ል ሞላ ካቀረቡዋቸው ተቃውሞዎች መካከል ከጥቂት
ወራት በፊት ለከፍተኛ መኮንኖች የተሰጠው የጄነራልነት ማዕረግ ዕድገት በተመለከተ ያቀረቡት ሲጠቀስ፤
ለአንዳንድ መኮንኖች የተሰጠው የጄኔራልነት ማዕረግ ጨርሶ ተገቢ ያልሆነ በማለት እንደተቃወሙ ምንጮች
ገልፀዋል። በተጨማሪ « ከእኔ እውቅና ውጭ አዳዲስ ከፍተኛ መኮንኖች እየተመደቡ ነው፤ ይህ የማልቀበለው
ነው። ሕጉን በመተላለፍ በማን አለብኝነት እየፈፀምክ ያለኅው ሳሞራ ነሕ።፡» በማለት ጄ/ል ሞላ በሃይለ ቃል
ጭምር መናገራቸውን ገልፀዋል።
ስብሰባው ካለመግባባት በተጠናቀቀ ማግስት ጄ/ል ሳሞራ ለአየር ሃይል ከፍተኛ መኮንኖች፦ « ከእንግዲህ በሁዋላ አየር ሃይሉን
የሚመራው ጄ/ል መሓመድ ነው፤ » በማለት በቃል መግለፃቸውን ያረጋገጡት ምንጮች አክለውም ጄ/ል ሞላ እንደተነሱ የተነገራቸው
በስልክ መሆኑን ጠቁመዋል።
በጄ/ል ሞላ እና በጄ/ል ሳሞራ መካከል ስር የሰደደ ቅራኔና ልዩነት የፈጠረው ጉዳይ በስብሰባ ላይ የተገለፀው እንዳልሆነና ከዚህ ውዝግብ
ጀርባ ፦ ጐራ ለይተው የተፋጠጡትን ሁለት የፖለቲካ ሃይሎች በመደገፍ ጄኔራሎቹ በየፊናቸው አቁዋም በመያዛቸው እንደሆነ ምንጮቹ
ያሰምሩበታል። ለዚሁ ማረጋገጫው ጄ/ል ሞላ እንዲመለሱ የተደረገው በጄ/ል ሳሞራ ፍቃድ ሳይሆን.. የነስብሃት ቡድን ባደረገው ጫናና
ይህን ቡድን በሚደግፉ ጄኔራሎች ጥያቄ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ በመቀሌ በተካሔደው የሕወሓት ስብሰባ ላይ ከፍተኛ የጦር አዛዦች ተሳታፊ እንደነበሩ ምንጮች ገለፁ።
በሕገ መንግስቱ ድንጋጌ መከላከያ ሰራዊት ከየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ያልወገነ ገለልተኛ ነው፤ ቢልም በተደጋጋሚ ይሕ ድንጋጌ ሲጣስ
እንደሚታይ ምንጮቹ ሳይጠቁሙ አላለፉም። በ1993 እና በ1997ዓ.ም በፓርቲው ዙሪያ ቀውስ በተፈጠረ ጊዜ የመከላከያ ጦር አዛዦች
ከሕወሓት/ኢሕአዴግ ጋር በመወገን ያካሔዱት ስብሰባና የወሰዱት አቁዋም በቂ ማሳያ እንደሆነ እነዚህ ወገኖች ያስታውሳሉ።
በ1993ዓ.ም ሕወሓት ለሁለት ሲሰነጠቅ አቶ መለስ ከፍተኛ ጄ/ል መኰንኖችን ስብሰባ በጠሩበት ወቅት ብ/ጄ/ል ታደሰ (ጋውና)
ባቀረቡት ተቃውሞ፦ « ሕገ መንግስቱን እየጣስክ ነው፤ መከላከያ ሰራዊት ገለልተኛ ተብሎ በግልፅ ተቀምጦዋል። ዛሬ አንተ ከሰበሰብከን
ነገ ደግሞ የትኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ስብሰባ ከጠራን < ሕግና አዋጁ አይፈቅድም > ሊባል ነው? ሕጉ በአንዱ የሚጣስበት፡ ለሌላው
ደግሞ የሚከለከልበት ምንም አይነት አግባብ የለም። አቶ መለስ እኛን ሰብስበህ ስለ ሕወሓት ቀውስ መስበክ አትችልም። ሕጉ ይከበር!
በበኩሌ ሕግን ጥሶ በሚካሄድ ስብሰባ መቀጠል አልፈልግም።» በማለት ረግጠው እንደወጡ ያስታውሳሉ።
በተጨማሪ በ1997ዓ.ም ሰኔ 2 እና 3 ቀን ከፍተኛ መኮንኖችን ስብሰባ የጠሩት ጄ/ል ሳሞራ ፦ « ሕገ መንግስቱን ለመናድ የተነሳውን
ቅንጅት በማጥፋት ሕጋዊውን መንግስት ከአደጋ ማትረፍ አለብን» እንዳሉ እነዚህ ወገኖች ያወሳሉ።
አሁን ደግሞ ጄኔራሎች በመቀሌው ስብሰባ መገኘታቸው ሕገ መንግስቱን የጣሰ ከመሆኑ ባሻገር ፖለቲካዊ ቀውሱ እየሰፋ መሆኑን
የሚያሳይ ነው ብለዋል። በስብሰባው ጄ/ል ሰዓረ፡ሳሞራ፡ ወዲ መድህን፡ ተስፋዬ፡ወዲ ዘውዴ፡ ሞላ….ከተገኙት የጦር አዛዦች መካከል
ይጠቀሳሉ።
ጀ/ል ሞላ ኃ/ማርያም በሌላም በኩል ሶስት ከፍተኛ ጄኔራሎችን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ ባለ-ማዕረግተኞች መታገዳቸውን ምንጮች ጠቆሙ። በተለይ
ጄኔራሎቹ ምንም አይነት ትዕዛዝ እንዳይሰጡ የእገዳ ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። ውሳኔው በደብዳቤ ያልተገለፀ መሆኑ አነጋጋሪ ሆኖዋል። ቢሮ
ገብተው ክመፈረም ውጭ መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ እንዳልሆነ ምንጮች አረጋግጠዋል። በቅርቡ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ
እንደሚጠበቅ ያመለከቱት ምንጮቹ፤ መባረራቸውን በሚደግፉና በሚቃወሙ የጦር አዛዦችና የፖለቲካ ቡድን ጐራዎች መካከል
ውዝግቡ ተካሮ እንደቀጠለ አያይዘው ገልፀዋል። ( የታገዱት ከፍተኛ መኮንኖች ማንነት እና ዝርዝር ሒደት በተመለከተ ከውሳኔው
በሁዋላ እንመለስበታለን)
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment