Saturday, December 8, 2012

የርሳቸው ነፍስ… (አጭር ልቦለድ)


የርሳቸው ነፍስ… (አጭር ልቦለድ)፣ አቢ ቶኪቻው 

በህይወታቸው እንዲህ ያለ ማጭበርበር አጭበርብረው አያውቁም። እንደምንም ብለው የሰማይ ቤት ጥብቃ ሰራተኞችን፤ አሳምነው ወደ ምድር ተመልሰው መጡ። በርቀት ሲመለከቷቸው የነበሩ ኢትዮጵያዊ ነፍሶች፤ “ድሮም ሰውዬው የማሳመን እና የማሳመም ችሎታቸው እኮ ቀላል አይደለም” እያሉ አደነቋቸው።
ከሰማየ ሰማያት ወደ ምድር ሲመጡ መጀመሪያ በቀጥታ የሄዱት የብራሰልሱ ሃኪማቸው ዘንድ ነበር። አገኙት። ሊጨብጡት እጃቸውን መዘርጋት ፈልገው፤ ለካስ እጅ የላቸውም። ለካስ መላ ስጋቸው ግባ ተመሬት ተብሏል።
“የምረዳዎት አለ…?” አላቸው ዶክተሩ ማን እንደሆኑም እንደረሳቸው የገባቸው ይሄኔ ነበር። “በቃ ሰዉ በራዬን ካላየ አያውቀኝም ማለት ነው…?” ሲሉ እያንሰላሰሉ፤  “ከዚህ በፊት አንተ ዘንድ ታክሜ ሞቼ ነበር። አሁን በስንት ትግል መሰለህ ከሰማይ ቤት የመጣሁት፤ እባክህን የመጨረሻ እድል ሞክርልኝ እና ከህመሜ አድነኝ…!” አሉት። ሃኪሙ ግር እያለው። “ስጋዎን እኮ አልያዙትም” አላቸው…! ይሄኔ “ስጋቸው የት እንዳለ ማሰብ ጀመሩ…
ይህንን እያሰቡ ወደ ቴሌቪዥኑ ዘወር ሲሉ እርሳቸውን “የተኩዋቸው” አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ ተመለከቱ። መጀመሪያ  “ውይ ይሄንን ሰውዬ ጠቅላይ ሚኒስትር አደረጉት ማለት ነው…?” ብለው ደነገጡ። ወድያውም ታዛዥነታቸውን አይተው ምክትል ሲያደርጓቸው ስተት እንደሰሩ ገባቸው። ያልገባቸው አሁን አቶ ሃይለማሪያም ከአልጀዚራ ጋር እያደረጉ ያለው ቃለ ምልልስ ነው፤
“ወደ አስመራ ሄጄ መደራደር እፈልጋለሁ። መለስም ከሃምሳ ጊዜ በላይ ወደ አስመራ ተመላልሶ ለመታረቅ ሙከራ አድርጓል…” ጆሯቸውን ማመን አቃታቸው። ድሮስ የተቀበረ ጆሮ ምኑ ይታመናል!?  “እንደውም ስሜ አያምርም፤ ይሄ ሰውዬ ጭራሽ ሊያስጠምደኝ ሃምሳ ጊዜ ተመላልሷል ይላል እንዴ…! ወይ አነ ግዲ…” ብለው ተበሳጩ ይሄኔ አንድ ወደላይ ቢያስተኩሶ ወይ ደግሞ ራሳቸው አንድ ሮዝማን ቢለኩሱ ደስ ይላቸው ነበር። ነገር ግን ድሮ እንጂ አሁን ምንም የላቸውም እና ራሳቸውን ወደ አዲሳባ ተኮሱ…!
አዲሳባ ሲደርሱ ከተማው በሙሉ በርሳቸው ምስል ተዥጎርጉሯል። ግራ ገባቸው፤ “አልሞትኩም እንዴ…!?” ብለውም አሰቡ። ግን ሞተዋል። ባይሞቱ ኖሮ ስጋ በላያቸው ላይ ይኖር ነበር። ስጋዬን አገኘው ይሆን…? ራሳቸውን ጠየቁ… “የት ይሆን የቀበሩኝ…!? መቼም ቤተክርስቲያን እሺ ብለው አይቀብሩኝም…” አሉ ሰማይ ቤት የተከሰሱባቸው  በክርስቲያኖች ላይ የሰሩት ሸፍጦች ቁልጭ ብለው ታዩዋቸው…! መስጂድም አይቀብሩኝም አሉ… አሁንም የሰማይ ቤቱ የክስ ቻርጅ ትዝ እያላቸው። ጫካ ወርውረውኝ ይሆን…? ብለው አስበው ሳይጨርሱ “ምናልባት ቤተ መንግስቱ ውስጥ ተቀብሬ ይሆናል…” ሲሉ ገመቱ እና ወደዛው ገሰገሱ!
ቤተ መንግስት ከመድረሳቸው በፊት ፓርላማ አካባቢ አባላቱን በርከትከት ብለው ተመለከቷቸው። ይሄኔ የፓርላማ ስብሰባው ትዝ አላቸው ቁጣቸው ራሳቸውን አስደነገጣቸው፤ ቀልዳቸም አሳቃቸው። “ኮሚክ እኮ ነበርኩ” ብለው በሆዳቸው ሊያስቡ ሲቃጡ… (ለካስ ሆዳቸው የለም!)
ፓርላማው አካባቢ የሚያዩዋቸው አባላት በሙሉ እርሳቸውን ነው የሚመስሉት። ግር አላቸው፤ እንዴት ነው ነገሩ…! ቆይ ቆይ… ብለው የተለያዩ ባለስልጣናት ቢሮ ሄደው ጎብኘት ጎብኘት ማድረግ አሰኛቸው… ሁሉም ባለስልጣናት እርሳቸውን የሚመስል ነገር በላያቸው ላይ ለጥፈዋል።
የት ነው የተቀበርኩት…? ብለው ሲጨነቁ፤ ለካስ አልቀበሯቸውም። ስጋቸውን ቆራርጠው ተከፋፍለው ሁሉም ባለስልጣኖች እርሳቸውን ለመመስል እያሰፉ ለብሰውታል። “ወይ አነ ግዲ…” በጣም አዘኑ…!
ሀሳባቸው ስጋቸውን ካለበት አውጥተው ብራሰልስ ወስደው ሀኪሙን እባክህ ድጋሚ ገጣጥምና ሞክረኝ… ብለው ሊለምኑት ነበር። ነገር ግን በየት በኩል… ያመኗቸው ባለስልጣናት ተከፋፍለው ስጋቸውን ለብሰውታል። ምናለ የራሳቸውን ስጋ ቢለብሱ!? ሲሉ በጣም ተበሳጩባቸው!
ባለስልጣናቱን ሰብስበው ሊጮሁባቸው ፈለጉ ግን በምን አፍ… “አፌ ማን ጋ ይሆን…” ብለው እያሰቡ እያለ… አንዳች ነገር ወደላይ ሲጎትታቸው ታወቃቸው። የሰማይ ቤቱ ጥበቃ ክፍል ባልደረባ ነው። ጎትቶ ከመጡበት የሰማይ ክፍል ሲያደርሳቸው ኢትዮጵያውያን ነፍሶች አንድ ተረት በዜማ አሉላቸው
“ዶሮ በረጅሙ ሲያሰሯት የለቀቋት መሰላት!”

No comments:

Post a Comment