“ሲ ዋን” - የግንቦት ልባቦት
በንፍታሌም
የመጽሐፉ የመጀመሪያ ህትመት ለአንባቢያን የቀረበው በሀገረ-አሜሪካ ነው፡- ከወር በፊት፡፡ እነሆ በወርሃ ሕዳር የመጨረሻ ሳምንት ለሀገር ቤት ተደራሲያንም ይዳረስ ዘንድ ለገበያ ቀረበና እጄ ገባ፡፡
ዳጎስ ያለ መጽሐፍ ነው፡፡ “ሲ ዋን” የሚል ርዕስ ተሰጥቶታል፡፡ የመፅሐፉ ሽፋን በአብዛኛው ጭልጥ ባለ የባህር ምስል ለብሷል፡፡ በጉልህ ከተፃፈው ርዕስ ሥር እስከ አንገታቸው ድረስ በውሃ የተዘፈቁ፤ እርስበርስ ተሸካክመው፣ ተደጋግፈውና ተቃቅፈው የሚጓዙ ሰዎች ይታያሉ፡፡ በመፅሃፉ ሽፋን ግርጌ ደረቅ መሬት ላይ ኩርምትምት ብለው ተቀምጠው ወደሰፊው ባህር የሚመለከቱ በርካታ ሰዎች ተኮልኩለዋል፡፡ ከርዕሱ በላይ (አናት) እንክትክቱ የወጣ ተራ ጀልባ እና ግዙፍ መርከብ፣ እንዲሁም ከባህሩ ማዕበል ጋር ትንቅንቅ የገጠሙ በርካታ ሰዎች ምስል ይታያል፡፡ የባህሩ መጨረሻና ሠማይ የተገጣጠመ ይመስላል፡፡ ሽፋኑ ላይ የሚታዩት ምስሎች የመፅሐፉን ውስጣዊ ይዘት የሚያሳብቁ ዓይነት ናቸው፡፡ እንዲያም ይሁን እንጂ ርዕሱ ሥሜት የሚሰጥ አልሆነልኝም፡፡
ቢሆንም ወደውስጥ ዘልቄ ታሪኩን ማንበብ አለብኝ፡፡ ጥቂት ገፆች እንኳ መግፋት አልቻልኩም፡፡ ደራሲው ወደዋናው ታሪክ ከመዝለቁ በፊት በፃፈው “መግቢያ” መፅሐፉን በማስታወሻነት ያበረከተላቸውን ሰዎች እያሰብኩ እንባ ተናነቀኝ፡፡ አብዛኞቹን በአካል አውቃቸዋለሁ፡፡ የሙያ አጋሮቼ ነበሩ፡- የነፃው ፕሬስ ጋዜጠኞች፡፡ ከሙያ አጋርነት ባሻገር የሕይወት ግጥምጥሞሽ ያቆራኘን፣ የእስር ቤትን የመከራ ጠበል (ላብ) አብረን የተራጨን፣ መራራውን መከራ በቀልድ እያዋዛን በገጠመን ችግር የተሳለቅን፣ በተረብ የተሞሸላለቅን…ጓደኛሞች ነበርን፡፡ ጥቂቶቹ በአስጨናቂ ሁኔታ ራሳቸውን ለማጥፋት (ለመሞት) የተገደዱ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ሳይወዱ በግድ በእግርም በጢያራም ከሀገር የተሰደዱ ናቸው፡፡ እናም በህይወት ያሉትንም የሌሉትንም አንድ በአንድ አስታወስኳቸው፡፡
“ሲ ዋን” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ለአንባቢያን ያበረከተውጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ከሀገራቸው ከተሰደዱት የቀድሞው ነፃ ፕሬስ አባላቶች አንዱ ነው፡፡ መፅሐፉን አንብቤ የጨረስኩት በጥልቅ ሐዘን ተውጬ ነው፡፡ የመጽሐፉን የመጨረሻ ገፅ ሳጥፍ ደግሞ ደጋግሞ ወደ ህሊናዬ የመጣው የሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን “የቴዎድሮስ ስንብት በመቅደላ” የሚለው ግጥም ነው፡፡ የሚከተለው፡-
“…ታዲያ እንግዲህ አንቺ ኢትዮጵያ እኛስ ልጆችሽ ምንድነን
አመንኩሽ ማለት የማንችል ፍቅራችን የሚያስነውረን
ዕዳችን የሚያስፎክረን
ግፋችን የሚያስከብረን
ቅንነት የሚያሳፍረን ቂማችን የሚያስደስተን፡፡
ኧረ ምንድነን? ምንድነን?
አሜኬላ የሚያብብን
ፍግ የሚለመልምብን፡፡…..”
አዎ “ሲ ዋን” መፅሐፍ እንዲህ ያሰኛል፡፡ የዚህች ምሰኪን ሀገር ምስኪን ልጆች መከራ የሚያበቃው መቼ ነው? ያሰኛል፡፡ ደራሲው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ለበርካታ ዓመታት በ“ሞገድ” ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነት ያገለገለ ነው፡፡ በሌሎች የቀድሞ ነፃ ፕሬስ የሕትመት ውጤቶች (ጋዜጦችና መፅሔቶች) በአምደኝነትና በሪፖርተርነት ሠርቷል፡፡ በ1997 ዓም ምርጫ በተከሰተው ሁኔታ ነው ሃገሩን ጥሎ ለመሰደድ የተገደደው፡፡
“ቅድመ ስደት” በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር ባሰፈረው ምጥን ሀተታ “…እስራትን፣ መጋዝን፣ ያለአግባብ መቁሰል፣ መድማትን ለዓመታት ኖሬበታለሁ” ይላል ዳንኤል፡፡ በዚህም የተነሳ ያንገፈገፈውን መከራ ለመሸሽ ሲል “ካሳለፍኳቸው መከራዎች የባሰ ወደሚመረው ስደት ለመግባት ተገድድኩ፡፡” ሲል በአፅንኦት ይገልፃል፡፡ እናም ከሬት መራርነት በላይ የሚጎፈንነውን የሥደት ህይወት በ279 ገፆች ይተርክልናል፡፡
ዳንኤል ታሪኩን በአራት ክፍሎች (ምዕራፎች) ከፋፍሎታል፡፡ ከአዲስ አበባ - ትልቁ አውቶብስ ተራ ተነስቶ የሥደት ጉዞውን ይጀምራል፡፡ ጉዞውን ለየት የሚያደርገው መውጫ መንገዶች ሁሉ ታጥረውበት ሥደትን መምረጡ ነው፡፡ በመርፌ ቀዳዳ እንደመሹለክ ዓይነት የሥደት ምርጫ፡፡ ከአ/አበባ ጅጅጋ፣ ከጅጅጋ ቦሳሶ ሶማሊያ፣ ከቦሳሶ የመን፣ በየመን ደግሞ ሌላ የስደት መከራ…የነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ትረካው ይቀጥላል፡፡ በርሃ ለበርሃ በእግር ጉዞ እያቆራረጠ፣ በባህር ብቅ ጥልቅ እያለ፣ እየሰመጠ፣ የገፋውን የሥደት ህይወት እያንገሸገሸው ይነግረናል፡፡
ጋዜጠኛ ተስፋዬ ገ/አብ የዳንኤልን ታሪክ አንብቦ ከመፅሐፉ ጀርባ ያሰፈረው አስተያየት ሁኔታውን ጠቅለል ባለ መልኩ ቅልብጭ አድርጎ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ እነሆ የተስፋዬ ገ/አብ አስተያየት፡-
“…ዳንኤል ገዛኸኝ ትረካውን ሲጀምር ‘ብታምኑም ባታምኑም እኔ ከሞት ጋር ተያይቻለሁ፤ ሞትን ተመልክቻለሁ’ ይላል፡፡ ፊት ለፊት ብቻ ሳይሆን፣ መልዓከ ሞት እና ጋዜጠኛው ዳንኤል የህይወት ቁማር እየቆመሩ አብረው ሰንብተዋል፡፡ በምድርም በባህርም አብረው ተጉዘዋል፡፡ ሆኖም ተራኪው ጋዜጠኛ ከሞት ጋር ጉሮሮ ለጉሮሮ ተናንቆ አሸንፎ ለመውጣት ችሏል፡፡ ከሶማሊያ ወደየመን በተራ ኮንትሮባንድ ጀልባ ስለመጓዝ አስባችሁ ታውቃላችሁ? ዳንኤል ፈፅሞታል፡፡ እንደተደነቅሁና ልቤ እንደተሰቀለ፤ ሕንድ ውቅያኖስ ላይ በማዕበል ከምትንገላታው ከርካሳ ጀልባ ጋር እኔም አብሬ እየተንገላታሁ ታሪኩን አንብቤ ጨሻለሁ፡፡ ‘ሰው ብርቱ - ድመት ጠንካራ’ የሚባለው እውነት ኖሯል?...”
በእርግጥም ተስፋዬ ገ/አብ እንዳለው፣ ደራሲው ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ ሞትን ከአንድም ሁለት ሶስት ጊዜ ተጋፍጦታል፤ ተናንቆታል፡፡ “በሰሜን ሶማሊያ ዲሽሽ” በሚለው ርዕስ ሥር ያሰፈረውን ታሪክ ለአብነት እንኳ ብንጠቅስ ስቅቅ ይለናል፡፡ በዚያ ቅልጥ ባለ ነዲድ በርሃ ውስጥ፣ የውሃ ጠብታ ማግኘት እንደፅድቅ በሚቆጠርበት በዚያ ምድረበዳ፣ በርካታ ስደተኞች በቡድን በቡድን ሆነው እየተጓዙ ሳለ በአጋጣሚ ምንጭ አጠገብ ደረሱ፡፡ በዚያ በርሃ ድንገት ከየቁጥቋጦ ውስጥ ብቅ በሚሉ የሶማሊያ ታጣቂዎች ያላቸውን ሁሉ እየተነጠቁ ባዶ እጃቸውን የሚንከላወሱት ስደተኞች በሰቆቃ እያዘገሙ ሳለ፣ ከንፈራቸውን ለማርጠብ እየቋመጡ ሳለ አምስት ታጣቂዎች ከየት መጡ ሳይባል ከበቧቸው፡፡ ያ ምንጭ “በአቅራቢያው ከሚገኝ መስጊድ የሚመጡ ሙስሊሞች ከስግደት በፊት ‹ውዱ› የሚያደርጉበት (የሚጠቀሙበት) እንጂ የማንም ካፊር የሚያረክሰው አይደለም” አሏቸው፡- በቁጣ ክላሽ እየወደሩባቸው፡፡
ከስደተኞቹ መሃል የእስልምና ኃይማኖት ተከታይ የሆነው ወጣት በተሳሰረ አንደበት ሙስሊም መሆኑን እየነገራቸው ተማፀናቸው፡፡ በአላህ ስም እንዲምል አፋጠጡት፡፡ አላመኑትም፡፡ ዋሽተሃል ብለው ጮሁበት፡፡ በአረብኛ ቋንቋ በእስልምና ኃይማኖት መባል ያለበትን አለላቸው፡፡ ይህ ግን የአንዱን ታጣቂ ጣት ቃታ ከመሳብ የሚገታው አልሆነም፡፡
“…አሸሃዱ አላ…ህ … የጀመረውን ቃል ሳይጨርስ ልጁ አንገቱን መቆጣጠር ተስኖት ወደ መሬት ድፍት አለ፡፡… ከእሱ ሰውነት ጎርፎ እየሰራ የወረደው ደም እኔን ማራስ ጀምሯል፡፡…ተጠራጠርኩ፤ እኔንም የጥይቱ አረር የነደለኝ መሰለኝ፡፡…የዚያ ልጅ ደም የለበስኩትን ጃኬትና የውስጥ ልብሴን አርሶታል፡፡ …የትኛውን የአካሌን ክፍል ነድሎት ይሆን?” ይላል ጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ በትረካው፡፡ (ገፅ 106 - 114)
ከሞት ጋር የገጠመው ፍጥጫ በዚህ አያበቃም፡፡ ከኢትዮጵያ ጠረፍ አንስቶ እስከ ሶማሊያ ጠረፍ፣ ብሎም በባህር ላይ በርካታ ጊዜ ከሞት ጋር ተያይቷል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን በየበርሃው ወድቀው መነሳት አቅቷቸው አሸዋ ስር ተቀብረዋል፡፡ በዚህ የመከራ ስደት ያልተሸነፉት የመጨረሻ አቅማቸውን አሟጠው ባህር ለመሻገር መቧቸር ቀጥለዋል፡፡ በመቶ የሚቆጠሩ ከሰው ተራ የወጡ ኢትዮጵያውያን በአንዲት ከርካሳ መርከብ ተፋፍገው ወደ የመን ለመሻገር ጉዞ ጀምረዋል፡፡ ጉዞው ቀንና ለሊት ነው፡፡ ካለእረፍት በውሃ ላይ እየጋለቡ በውሃ ጥም የተቃጠሉ ኢትዮጵያውያን ውሃ ከያዙ ወገኖቻቸው በኮዳ ክዳን ውሃ በ50 ብር ለመግዛት ለምነው አጥተዋል፡፡ አየር እንኳ መሳብ ያቃታቸው ተጓዥ ስደተኞች በሞትና በሕይወት መሃከል በጣር እየቃተቱ ጉዞው ቀጥሏል፡፡ ወገን ለወገን መተጋገዝ፣ መረዳዳት እንኳ በዘር፣ በብሔርና በቋንቋ ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላ ያለውን ቃል በቃል ከመፅሐፉ ትረካ እንቋደስ፡-
“…ከጉድጓድ መሳይዋ የጀልባ ክፍል ውስጥ ያሉ ልጆች ጩኸት በረከተ፡፡ ሳሚ ነገሩን ለናኩዳዎች (ለባህር አስተላላፊዎች) አስተረጎመ፡፡ እኔ ግን ማየት አልቻልኩም፤ አቃተኝ፡፡ …ጨፈንኳቸው፡፡ ወዲያው የዘጋኋቸውን ዓይኖቼን ገለጥኳቸው፡፡ ልጆቹን ከውስጥ ተረዳድተው አውጥተው ወደ ባህሩ ወረወሯቸው፡፡ ጣሰው ‹አለ፤ አለ…አንደኛው አልሞተም፤ ነፍሱ አልወጣችም፤ ሩሁ ገና ነች›” አለ፡፡ የሚሰማው አልነበረም፡፡ ልጁ (ወደ ባህሩ የተወረወረው) ዓይኖቹ እንደተከፈቱ ናቸው፡፡…ከሁሉ በላይ የሚያስፈራው ሞት አይደል እንዴ? ሕዝባችንን እንዴት ጨካኝ ሆነ?...” (ገፅ 163) ይላል ዳንኤል በትረካው፡፡ ዳንኤል ሕዝባችን እንዴት ጨካኝ ሆነ ሲል የሚጠይቀው ነፍሱ ከስጋው ያልተላቀቀችውን ሰው ወደባህር የሚወረውሩት ኢትዮጵያ ወገኖቹ በመሆናቸው ነው፡፡፡
ከዚህ በላይ ሞትን መጋፈጥ ከዚህ፤ በላይ የሞት ሞት ምን አለ? በዚያ የሥደት የጣዕር የስደት ጉዞ ውስጥ አንዲት ኢትዮጵያዊ ወጣት ከአንድም በሁለት ሶማሊያውያን የባህር አስተላላፊዎች ፊት ለፊታቸው ስትደፈር ማየቱን ይነግረናል፡፡ ይህንን ማየት በራሱ የሞት ሞት አይደል እንዴ? ከዚህ በላይ ኢትዮጵያዊ ስብዕናን ማጣት፣ ከዚህ በላይ ውርደት ምን አለ? ይህንን ሁሉ ግፍ እና መከራ የምንጋትበት ምክንያት ምንድነው?
ደራሲው ጋዜጠኛ ዳንኤል በመፅሐፉ ውስጥ የሚተርከው ወደ 500 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን የሥደት ሥቃይ ነው፡፡ መነሻው የእሱና የሙያ ጓደኞቹ የሥደት ጉዞ ቢሆንም፤ አጠቃላይ ይዘቱ የኢትዮጵያውንን መከራ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
የሞተው ሞቶ፣ የተረፈው ተርፎ የየመንን ምድር ከረገጡ በኋላ የሊገጥማቸው ሥቃይ ከሬት በላይ የሚጎመዝዝ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሃገር ጥለው በሥደት የመከራ ሕይወት ውስጥ የሚቃትቱት ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት ተቧድነው እርስ በር መጠላለፋቸው ነው ይበልጥ የሚያሳዝነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ማነን? በመከራ ሰዓት እንኳ የማንስማማ ምንድነን? ምን ዓይነት ልክፍት ነው የተጣባን የሚያሰኝ ነው፡- “ሲ ዋን” መፅሐፍ፡፡
በነገራችን ላይ ደራሲው ለመፅሐፉ የሰጠው “ሲ ዋን” የሚለው ርዕስ ከዕብራይስጥ ቋንቋ የተወሰደ ሲሆን፣ ትርጉሙ ግንቦት የሚል እንደሆነ በመግቢያው ተጠቅሷል፡፡ ይህ የርዕስ ሥያሜ ግን ለዚህ ዳሰሳዊ ፅሁፍ ጦማሪ አልተዋጠለትም፡፡ የመፅሐፉን የመነበብ ዕድል በእጅጉ የሚያኮሰምን የርዕስ አመራረጥ ነው ብሎ ያምናል፡፡ በውስጡ ከያዘው መራር ዕውነት አኳያ ርዕሱ ገላጭነት የለውም ብሎ ያምናል፡፡
እንደ እኔ እንደእኔ የመፅሐፉ ርዕስ “የግንቦት ልባቦት” ቢባል የበለጠና የተሻለ ትኩረት ይሰጥ ነበር ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ዳንኤልና የሙያ ጓደኞቹ የስደት ምክንያት በወርሃ ግንቦት ተካሄዶ የነበረው ምርጫ ነው፡፡ ግንቦት ለእነዳንኤል ስደት ምክንያት የሆነው የኢህአዴግ መንግስት ስልጣን የተቆናጠጠበት ወር ነው፡፡ ግንቦት ከወራት ሁሉ እጅግ ሞቃታማ ወር መሆኑን “ልባቦት” የሚገልፀው ቃል ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በመፅሐፉ ውስጥ የተካተቱት ትርክቶች ሁሉ የግንቦት ወር ፖለቲካዊ ሙቀት የፈጠራቸው ተግዳሮቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ “የግንቦት ልባቦት” ቢባል የበለጠ ገላጭ ርዕስ በሆነ ነበር ብዬ አምናለሁ፡- ያውም ከነኢትዮጵያዊ የቋንቋ ለዛና ኃያልነት ጋር፡፡
ከዚህ ውጭ የጋዜጠኛ ዳንኤል ገዛኸኝ “ሲ ዋን” መፅሐፍ በ279 ገፆች የያዛቸው ጉዳዮች የኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያዊነትን ተግዳሮቶች ነቅሶ የሚያሳይ፤ ራሳችንን እንድንፈትሽና እንድንመረመር ግድ የሚል፤ መርመረንም መፍትሄ እናበጅለት ዘንድ የሚሞግት የተዋጣለት ሥራ መሆኑን መመስከር ግድ ነው፡፡ ለዛሬው በዚሁ እንሰነባበት፡፡ ቸር ክራሞት!!
No comments:
Post a Comment