Wednesday, January 16, 2013

የሀገር ጩኸት እና የታሳሪ ልጆች… አውደ-ዓመት


የሀገር ጩኸት እና የታሳሪ ልጆች… አውደ-ዓመት
አጀንዳ- ፩
ለምን ይጮኸል?
መልሱ፣ ለምን አይጮኸም ይሆን? …በጠመንጃ አስገዳጅነት፣ ለማይጨበጥ፣ ለማይታይ ‹‹ራዕይ›› ሀገርን፣
ዘመንን፣ ትውልድን፣ እምነትን… ‹‹ገብር›› ሲባል ማን ነው የማይጮኸው? ... የመንግስት ሰራተኛው
ይጮኸል፣ የግል ተቀጣሪው ይጮኸል፣ ቀጣሪው ይጮኸል፣ ስራ እጡ ይጮኸል፣ ነጋዴው ይጮኸል፣ ሸማቹ
ይጮኸል፣ ሰራዊቱ ይጮኸል፣ ሙስሊሙ ይጮኸል፣ ክርስቲያኑ ይጮኸል፣ ጠንቋዩ ይጮኸል፣ እምነት
የሌለው ይጮኸል፣ የተደራጀው ይጮኸል፣ ያልተደራጀው ይጮኸል፣ የጠገበው ይጮኸል፣ የራበው
ይጮኸል፣ ፍትህ ያጣው ይጮኸል፣ እስረኛው ይጮኸል፣ እስረኛ ጠባቂው ይጮኸል፣ ታሪክ
ይጮኸል….ሰሚ አልባ ጩኸት! እሪ በከንቱ!!
ለዚህ ሁሉ ጩኸት ኃላፊነት መውሰድ አለበት የሚባለው መንግስት ‹‹መናገር እንጂ መስማት ተስኖታል›› በሚል ድምዳሜ መዝገቡ
ከተዘጋ ፀሀይ ጠልቃለች፡፡ በእርግጥ ያለፉት ስርዓታት መስማት የተሳናቸው ስለነበሩ ታሪክ ሆነው የመቅረት ዕጣ ገጥሟቸዋል፡፡ አፄ
ኃይለሥላሴ ‹‹ህዝባችን…›› እያሉ ያንቆለጳጵሱት የነበረውን ህዝብ አንድም ቀን አድምጠውት አያውቁም ነበር፡፡ ኮሎኔል መንግስቱም
የስልጣናቸው ምንጭ ‹‹ሰፊው ህዝብ እና ታሪክ የጣለባቸው አደራ›› እንደሆነ በየአደባባዩ ቢደሰኩሩም ከአፄው ያለመስማት ታሪክ
አልተማሩምና ከውድቀት ሊያመልጡ አልቻሉም፡፡ አቶ መለስ ዜናዊም ቤተ-መንግስት የገቡት ለ17 ዓመት በዱር በገደሉ በመታገላቸው
ሳይሆን፣ ብሔር ብሔረሰቦች ስለመረጧቸው መሆኑን ደግመው ደጋግመው መግለፃቸው የሚታወቅ ቢሆንም‹‹መረጡኝ›› ያሏቸውን
‹‹ብሄር ብሄረሰቦች›› ሲያደምጡ ታይተው አያውቁም፡፡ ተተኪዎቻቸውም ቢሆኑ የተለየ ድምፅ፣ የተለየ ሃሳብ ለማድመጥ አልተዘጋጁም፡፡
… ለዚህም ነው ዛሬም እሪ በከንቱው የቀጠለው (ያውም ‹‹የሚሰማው እከሌ ነው›› ተብሎ ጣት ሊጠቆምበት የሚችል መሪ በሌለበት
ሀገር)
የሆነ ሆኖ እንደ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ወድቆ መነሳትን ችሎ ለለውጥ የታገለ ህዝብ ያለ አይመስለኝም፤ ተረኛውን ጨቋኝ ገዥ
(ብሔርንና ሀይማኖትን ሳይለይ) ታግሏል፤ እየታገለም ነው፡፡ ከስንት አንዴ በለስ ቀንቶት ማሸነፉ የተሳካለት እንደሆነም፣ ድሉን ጥቂት
ጨካኞች ይቀለብሱትና ታግሎ ወደ ጣለው ስርዓት ይመለስ ዘንድ ያስገድዱታል፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ልጅ እያሱን ታግለዋል፡፡ ‹‹ከስራ
ይልቅ ጨዋታና ፈንጠዚያ ያበዛሉ››፣ ‹‹ብዙውን ጊዜ ‹ችሎት›ስለማይሰየሙ አቤት ባይን ያንገላታሉ››፣ ‹‹የኢትዮጵያን መሰረት ሊንዱት
ነው››… የሚሉ ቅሬታዎችን በማራገብ መኳንንቱን አስነስተውባቸው ከስልጣን ካባረሯቸው በኋላ፣ ለአራት አስርት ዓመታት ሀገሪቱን
ያስተዳደሩት ከልጅ እያሱም በከፋ የጭቆናን ቀንበር በማሻከም ነበር፡፡
ከተማሪ እና አስተማሪ ጋር ተባብሮ አፄውን ‹‹ጨቋኝ››በሚል ከዙፋን የገለበጠው ደርግስ ቢሆን ስልጣን በእጁ ሲገባ ምንድር ነው
ያደረገው? ሰቆቃን፣ ሽብርን፣ እልቂትን፣ ድህነትን… በጅምላ ማከፋፈል ነበር፡፡ ደርጉን ‹‹ፋሽስት፣ ጨፍጫፊ›› በሚል የታገለው
ኢህአዴግስ ከድል በኋላ መንበረ ስልጣኑን ሲያደላድል ወዴት ተመለሰ? ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ ‹‹የቀንድ አውጣ ኑሮ›› በሚል ርዕስ
ባሳተመው የግጥም መድብል ላይ የገለፀው አይነት ነው የሆነው፡-
‹‹…አቶ እርገጤ ሄደው፣ አቶ እርገጤ መጡ፣
ከቀንድ አውጣ ዛጎል ላይ የሚቀመጡ፣
ነገደ ቀንድ አውጣ እንቅልፍህን ለጥልጥ፣
እንቀሳቀስ ብለህ ሰው እንዳትገለብጥ፣
ዛጎልህ ምቹ ነው፣ ከላይ ብሎ ጎበጥ፣
  ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝሺህ ዓመት ቢቀመጡት መቼም አይጎረብጥ፡፡›› …ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት የስርዓቱ የማይገሰስ፣ የማይከሰስ አለቃ የነበሩት አቶ መለስ
ካለፉ በኋላም ቢሆን የተተኪዎቹን አካሄድ ለመግለፅ የዚህች ግጥም የመጨረሻ መስመሮች በልክ የተሰፋሠፉ ይመስላሉ፡-
‹‹አዋጅ 104…
አበሻ አበሻ ቀንድ አውጣ፣ ቀንድ አውጣ
በአቶ እርገጤ ማለፍ እንዳትቀናጣ
ሲከተል የኖረ ያንን ጫማቸውን አርጎት እንዳይመጣ›› እናስ! የአቶ እርገጤ ጫማ ተመልሶ አልመጣምን? …ወይስ የመኢሶን ሰዎች
‹‹የየካቲቱ ገጣሚ›› እያሉ የሚያሞካሹት ታላቁ ባለቅኔ ዮሀንስ አድማሱ፡-
‹‹አሉ ቁጢጥ፣ ቁጢጥ፣ በሰማይ ደመና፣
ከእንግዲህ ቀረች እንቅልፍና ጤና፣
መንግስት ብረት እንጂ አይገዛም ልቦና፡፡› ሲል የተቀኘው ይሆን የኃይለማርያምን አስተዳደር የሚገልፀው?
በጥቅሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመለወጥ ያለ ማቋረጥ እየተደረገ ያለው ትግል ግማሽ ክፍለ ዘመን ያስቆጠረ ቢሆንም፣ ዛሬም በአጭር ጊዜ
ውስጥ የተሻለ ለውጥ ይመጣል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት አልሆነም። ከስረ- ምክንያቶቹም አንዱ ‹‹ህዝባዊ ትግሉን እንመራለን›› በሚል
የሚመሰረቱ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ከፖለቲካ አጀንዳቸው ይልቅ ግለሰባዊነታቸው ጎልቶ ስለሚወጣ መሆኑ በአደባባይ የታዘብነው ሀቅ ነው፡
፡ ይህም ሁኔታ ፓርቲዎቹን ከማዳከሙና ከማፈራረሱ በተጨማሪ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ዘላቂ ህብረት ፈጥረው እንዳይጠናከሩ አግዶ
ይዟቸዋል፡፡ በእርግጥም ችግሩ ምን ያህል አስከፊ እንደሆነ የሚገባን በኢትዮጵያ‹‹የድርጅት ፖለቲካ›› (የፖለቲካ ፓርቲ) ፅንሰ-ሀሳብ
መሬት ከወረደበት ከ1960ዎቹ አንስቶ፣ እዚህኛው ዘመን ድረስ እንደ መታገያ ድርጅት ህልው መሆን የቻሉ ፓርቲዎች በሙሉ
ስለአንድነታቸውና ስለጓዳዊ ግንኙነታቸው የሰበኩትን ያህል፣ በጥቂት ወራት ወይም በጥቂት ዓመታት ልዩነት ደግሞ በ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ››
ተከፋፍለው መወጋገዛቸውን ስናስተውል ነው (‹‹ኢህአፓ-ሀ››፣‹‹ኢህአፓ-ለ››፤ ‹‹መኢሶን-ሀ››፣ ‹‹መኢሶን-ለ››፤ ‹‹መኢአድ-ሀ››፣
‹‹መኢአድ-ለ››፤ ‹‹ኢዴፓ-ሀ››፣‹‹ኢዴፓ-ለ››፤ ‹‹ኦህኮ-ሀ››፣ ‹‹ኦህኮ-ለ››፤ ‹‹አንድነት-ሀ››፣ ‹‹አንድነት-ለ››… በሚል ጎራ ተከፍለው
እርስ በእርስ ያደርጉት የነበረው እሰጥ-አገባ ከፖለቲካ ፓርቲዎቹ ድክመቶች ከብዙ በጥቂቱ ማሳያ መሆን ይችላል፡፡ ችግሩ በቀጣይም
መከሰቱ አይቀሬ ለመሆኑ የሚጠቁመው ‹‹መድርክ››ን ሊሸፍነው እየተቃረበ ያለውን ‹‹ጭጋግ›› መመልከታችን ነው፡፡ እናም የመድረኩ
አባል ፓርቲዎች በሆደ-ሰፊነትና በአስተዋይነት ጭጋጉን ካላመለጡት በቀር? በጣም በቅርቡ መድረኩ በ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ታሪክ ከመዘከር
የሚታደገው ተአምር ከየትም ሊመጣ አይችልም)
ሌላኛው ድክመት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ድርጅቶቹ ‹‹የምርጫ ሰሞን ፓርቲ›› መሆናቸው ነው፡፡ በተለይም አብዛኛው አባላት
በምርጫ ወቅት እንደ ሰርገኛ ታድሞ፣ ከሰርጉ በኋላ እንደግሪሳ ‹‹እዚህ ነኝ›› ሳይል የሚበታተን ነው፡፡ እንዲሁም የገዢው ፓርቲ ጫና
መረር ሲል ትግል ጥሎ መሄድ፣ ለዘብ ሲል የትግሉ ዋና አጋፋሪ መሆን በፓርቲዎቹ እንደ አሰራር መለመዱ ተጨማሪ ችግር ነው ብዬ
አስባለሁ፡፡ ይህ አይነቱ ትግል ወንዝ አያሻግርም፡፡ ካለ ጥብቅ ትግልእና መስዋእትነት መልካም አስተዳደርም ሆነ ዴሞክራሲ እንደ ‹‹መና››
ከሰማይ ሊዘንቡ አይችላቸውም፡፡
የሆነ ሆኖ የ‹‹እሪ በከንቱ››ውን ምዕራፍ ዳግም እንዳይመለስ አድርጎ ይዘጋል ተብሎ ተስፋ የሚጣልበት አማራጭ በቅርብ የለንም፡፡
‹‹የለውጥ መሳሪያ›› የሚባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ዛሬም እንደ ትላንቱ ቢሮአቸውን ከውስጥ ቆልፈው በ‹‹ጋዜጣዊ መግለጫ
ትግል››ሰጥመዋል፡፡ በአቶ መለስ የተተካው አዲሱ መንግስትም የተሻለ የፖለቲካ ስርዓት ለመፍጠር እንደማይጨነቅ በገደምዳሜ
አውጇል፡፡ ነፃ ፕሬስን፣ ሰብዓዊ መብትን፣ ዴሞክራሲን፣ ለአስተማማኝ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ነው የሚባለውን ‹‹የተረጋጋ የግብይት
ስርዓት››ን፣ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን የመሳሰሉ የመጪውን ትውልድ ህልሞች ማደላደያ መንገዶችን አርቆ ሰቅሏቸዋል፡፡ በግልባጩም
ጩኸትን በማፈን እና ተቃውሞን በመደፍጠጥ፤ እንዲሁም በአቶ መለስ ‹‹ስርዝ ድልዝ-ራዕይ››በማዘናጋት የስልጣን ማጠናከሪያ
ብሎኖችን ወደ ማጥበቁ አዘንብሏል፡፡ይህ ግን የትም የማያደርስ አዙሪት ነው፡፡ አዙሮ አዙሮ ወደ ነበርንበት የሚመልስ፤ ባለበት የሚያስረገጥ፡፡ እናም እንደ ቀደሙት ጊዜያት
የመፍትሄውን ቁልፍ ከጥልቁ ባሕር ለማግኘት ከመባዘን፣ ወደ መስኩ ወጥቶ የትውልዱን የለውጥ መንፈስ ማጤንና ዘመኑን መዋጀት፣
ብሔራዊ መግባባትን ማንበር፤ ለተለየ ሀሳብ ዋጋ መስጠት፣ ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲ ጋር በትይዩ መነጋገር፣ ከስልጣን ሀገርን
ማስቀደም፣ ከግል ጥቅም ህዝብን ማስበለጥ፣ ከጠመንጃ ይልቅ ለህግ መገዛት፣ ድርድርን ከቅሸባ እና ሴራ ማንፃት፣ ‹‹ሁሉም ሰው በህግ
ፊት እኩል ነው›› በሚለው የህግ መሰረት ያለቅድመ ሁኔታ ማመን ከኋላ ፀፀት ያድናል፡፡
ከዚህ በተቃራኒው እንደ አቶ መለስ ዘመን በ‹‹እፍርት››ኮሮጆ መገልበጥ፣ ሰላማዊ ዜጐችን በጠራራ ፀሐይ በጥይት መደብደብ፣ ሀምሳ እና
መቶ ሺህ ህዝብ በየእስር ቤቱ ማጎር፣ ግብርን በማብዛት በድህነት መደቆስ… የሆነ ወቅት ላይ ከአንዱ ስፍራ የተኛ ‹‹ሰይጣን››ን መቀስቀሱ
አይቀሬ ነው፡፡ ከአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌለው ጦር ሰራዊት መገንባቱ የተሳካላቸው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምም ቢሆኑ በዚህ በኩል
አልተሳካላቸውም፡፡ ጭቆናን በማበርታት ያሸነፈ ማንም የለምና፡፡ ሌላው ቀርቶ ህይወታቸው አልፎም የስርዓተ-መንግስቱ‹‹መንፈስ››
ተደርገው የተወሰዱት አቶ መለስ ዜናዊም እንዳሻቸው የሚያዙት እዕልፍ አላፋት ሰላይ ቢኖራቸውም፣ እስከ ህልፈታቸው ድረስ በሚሊዮን
የሚቆጠሩ ካድሬዎችን ቢሰበስቡም… ለተቃውሞ አንደበት የሚከፍትባቸው፣ ተናግረው የማይታመኑ ከመሆን አላመለጡም፡፡ ምክንያቱም
ህዝብ ሁልጊዜም ሲጨቆን፣ ሲጨፈለቅ የ‹‹ሀይድራ ራስ›› ይሆናልና፡፡
‹‹ሀይድራ›› (Hydra) በጥንታዊው የግሪክ አፈ-ታሪክ፣ የንጉስ ኡራስተስ (Eurystheus) ዘመን ተጋሪ እንደነበረች አፈ-ታሪኩ ያትታል፡፡
‹‹ሀይድራ›› ተፈጥሮዋ እንደማንኛውም ሰው ሳይሆን በተለየ መልኩ ዘጠኝ የሚናደፉ ራስ (ጭንቅላት) ይዛ የተወለደች ስትሆን፣
ከየትኛውም ጉልበተኛ ጋር ስትፋለም በለስ ቀንቶት ከራሶቿ መሀል አንዱን በሰይፍ ከጎመደባት፣ በምትኩ ሁለት ታበቅላለች፡፡ ሁለቱን
ሲያጭዱባት፣ አራት አዳዲስ ራስ ታበቅላለች፡፡ አራቱ-ስምንት፤ ስምንቱ…
በኢትዮጵያ ላለው የፖለቲካ ጭቆናም፣ ምላሹ የ‹‹ሀይድራ ራስ››እየሆነ ነው፡፡ ሲያዳክሙት-የሚጠነክር፣ ሲጥሉት-የሚገለብጥ… በአወለያ
ግቢ የተጀመረውን የእስልምና እምነት ተከታዮች ጥያቄን ለማፈን የተወሰደው የኃይል እርምጃ ጥያቄውን ከአወለያ አውጥቶ በመላ
ኢትዮጵያ በሚገኙ መስጂዶች የሚጠየቅ አድርጎታል፡፡ የጥያቄ አቅራቢውን ተወካዮች እስር ቤት መክተቱ የቀለለ ስራ ቢሆንም፣ በሚሊዮን
የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ለአፈናው የ‹‹ሀይድራ ራስ››ሆነዋል፡፡ በኦርቶዶክስ የክርስትና እምነት ላይ የሚደረገው ጣልቃ ገብነትን መቃወም
በጥቂት የሲኖዶሱ እና የማህበረ ቅዱሳን አባላት ብቻ ተገድቦ ቢቆይም ጫናው ሲከፋ ግን፣ ብዙሃኑን የእምነቱ ተከታይ ‹‹ያገባኛል›› በሚል
መንፈስ አሰልፏቸዋል፡፡ ጥቂት የህትመት ውጤቶችን ለማፈን የተደረገው ሙከራም መቶ ሺህዎችን በ‹‹ማህበራዊ ድረ-ገፆች›› ሀሳባቸውን
እንዲገልፁ ገፍቷል፡፡ በአጠቃላይ ከገዥው ፓርቲ የተለየ ድምፅ ያሰሙ ንፁሀኖች ቢታሰሩም ‹‹እኔም አሸባሪ ነኝ››፣ ‹‹እኔም እስክንድር ነጋ
ነኝ››፣‹‹እኔም በቀለ ገርባ ነኝ››፣ ‹‹እኔም አንዱአለም አራጌ ነኝ››… በሚሉ ሚሊዮኖች ተተክተዋል፡፡ አንዱ-ሁለት፤ ሁለቱ-አራት፤ አራቱ-
ስምንት፤ ስምንቱ… የሀይድራ ራስ!
ከዕለት ወደ ዕለትም የህዝባዊው ግፊት አቅም እየበረታ መሄድ፣ በድፍረት መብታቸውን የሚጠይቁ ኢትዮጵያውያኖች ቁጥር መጨመር
በአቶ መለስ ህልፈት የተዳከመውን ገዥው ፓርቲ እንቅልፍ የነሳ ጉዳይ ይመስላል፡፡ ይህ ህመም በተለይም በ‹‹ንጉስ አንጋሾች›› የፖለቲካ
ጨዋታ ወንበሩን የያዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ላይ ከሁሉም በበለጠ መልኩ ይበረታል፡፡ ምክንያቱም ባለ ‹‹ጠንካራ
መዳፍ›› ነባር ታጋዮች ኃይለማርያምን ከተፈጥሮ ባህሪያቸው አፈንግጠው ቁጡ እንዲሆኑ፣ መለስን መስለው እንዲተውኑ፣ ሕዝባቸውን
‹‹በእሳት እየተጫወትክ ነው›› በሚል ዛቻ እንዲያስፈራሩ እና እንዲያሸማቅቁ፣ በአደባባይ እንዲዋሹ… በአሮጌው የፖለቲካ ልማድ
እየሞረዷቸው ነው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ከአስተዳደራቸው ፊት ለፊት የኑሮ ውድነት፣ የተቀጣሪ ሰራተኛ ደሞዝ አለማደግ፣ የሸቀጥ
ዋጋ መናር፣ ስራ አጥነት፣ የትራንስፖርት እጥረት፣ የፍትህ እጦት፣ የመኖሪያ ቤት ችግር…. አንጥፎ እና ጎዝጉዞ መንገድ በመዝጋት
እየጮኸባቸው ነው፡፡ እሪ! እያለ፡፡
ሆኖም አሁንም ‹‹ኳሷ በእግራቸው ስር ናት››፤ ምርጫውም እንዲሁ በእጃቸው ነው፤ ወይ ህገ-መንግስቱን፣ ወይ አንጋፋ ታጋዮችን… ማን
ነበር ‹‹እንደ ገና ዳቦ ከላይም፣ ከታችም እሳት ነደደብህ›› ያለው?
አጀንዳ-፪
የታሳሪ ልጆች… ዓውደ ዓመትአውደ አመት በደረሰ ቁጥር በልጅነቴ ያሳለፍኳቸው ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ትዝታዎቼ በየተራ በዓይነ ህሊናዬ ድቅን ይሉብኛል፡፡
በተለይም ከሁሉ አብልጬየምወደው ዘመን መለወጫ በተንበሸበሸ ደስታ አስክሮኝ ነበር የሚያልፈው፡፡ ሁሉም ነገር በአዲስ የተሞላ፣
አዲስ ነገር፣ አዲስ ፀሀይ፡፡ አዲስ ልብስ፣ አዲስ ጫማ፣ አዲስ ደብተር፣ አዲስ መፅሀፍ፣ አዲስ የትምህርት ክፍል… ሌላው ቀርቶ
መንደራችንና ትምህርት ቤታችን የሚያሸበርቀው አዲስ በፈኩ አደይ አበባዎች ነበር፡፡ ሬዲዮኑ፣ ቴሌቪዥኑ እየደጋገመ፡-
‹‹መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ
ከአበቦቹ መሀል ወጣች ፅጌሬዳ›› በሚለው ዜማ ደስታን ያበዛል፡፡ እንዴት ጣፋጭ ነበር?
አውደ-አመት ትዝታውን ጥሎ የሚያልፈው ለልጆች ብቻ አይደለም፡፡ በወላጆችም ዘንድ አይረሴ ሆኖ የሚያልፍበት ጊዜ ተቆጥሮ
አያልቅም፡፡ እነሆም ከትውልድ ትውልድ፤ ከዘመን ዘመን ተሻግሮ የመጣው የአውደ-ዓመት አከባበር በደሳሳ ጎጆም ሆነ በእምነበረድ
በአጌጡ አንፀባራቂ ዘመናዊ ቪላ ቤቶች እንደየአቅማቸው ደስታን የማንገስ ኃይል አለው፡፡ ለቸበርቻቻው፣ ለሆታው፣ ለፈንጠዝያው፣
ለተንዛዙት የበዓል ድግሶች…ያለ የሌለ ጥሪት (በበዓሉ ማግስት የኑሮ ምህዋር መሽከርከሯን የምታቆም ይመስል) ለማድመቂያ ይውላል፡፡
የጥላሁን ገሰሰ ‹‹ምግብማ ሞልቷል›› ጥዑመ ዜማም ከሞላ ጎደል ቦታውን የሚያገኘው የአውደ-ዓመት ዕለት ነው፡፡ እናም፡-
‹‹አመት አውደ አመት
ድገምና አመት…›› እየተባለለት በፍፁም ደስታ ያለፈ የበዓል ትዝታ፤ አመቱ ዞሮ ሲመጣ አንዳች ካጓደለ ማሰቀቁ አይቀሬ ነው፡፡ ጉድለቱ
ልጆች ባሉበት ቤት ከሆነ ደግሞ ሀዘኑ ፅኑ ይሆናል፡፡ በተለይም አባት ወይም እናት በቤቱ ከሌሉ፣ በጎረቤት ቤት በአሉ ሲደምቅ፣ የዕድሜ
አቻ (ባልንጀራው) በአዲስ ልብስ አምሮ ከአባት ከእናቱ ጋር ሽር ሽር ሲወጣ… በሰቀቀን ለሚመለከት ልጅ፣ እንዲህ የሚል ሙዚቃ ጣራና
ግድግዳን ጠረማምሶ አልፎ ሲሰማ፡-
‹‹አውደ አመቱ
ሲመጣልን በአመቱ ኩራታችን
ስንኖር በአገርኛው በወጋችን
ደስታ ፍቅር ሰፍኖ በአገራችን
አሲና ገናዬ ስንጨፍር…›› ልብ ይሰበራል!
…የሆነ ሆኖ በዚህ ፅሁፍ ፍላጐቴ የአውደ አመት ትዝታን መተረክ አይደለም፡፡ ሰሞኑን የተከበረው የገና በዓል በልጅነቴ ይፈጥርብኝ
ከነበረው ስሜት ተነስቼ፣ አባቶቻቸው በግፍ ለእስር የተዳረጉባቸው የእነ እስክንድር ነጋ ልጆችን የአውደ አመት ውሎን፤ ከአባትና ልጅ
ግንኙነት አንፃር ያጎደለውን ለመመልከት ነው፡፡
…ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተወልዶ፤ በቃሊቲ ማረሚያ ቤት አፍ የፈታው እና ዳዴ ማለት የጀመረው የእስክንድር ነጋ ልጅ ናፍቆት እስክንድር
የዘንድሮ ገናን ከአባቱ ጋር አላሳለፈም፡፡ የአምናንም እንዲሁ፡፡ (ስለሚቀጥለው ገና እንኳ ዛሬ መተንበይ አንችልም፡፡ ምክንያቱም መለስን
በዚህ በዓል አናያቸውም ብሎ ማንም ያሰበ አልነበረምና)አዲስ ልብስና ጫማም ቢገዛለት እንደ እድሜ እኩዮቹ አይፈነድቅም፡፡ ሽርሽርም
ከአባቱ ጋር አይሄድም፡፡ በሚማርበት ትምህርት ቤት‹‹ኢንዲያን ስኩል›› ወላጆች በተገኙበት በሚከበር ፕሮግራም ላይም እንደ ጓደኞቹ
ከአባቱ ጋር መሄድ አይችልም፡፡ አባቱ በግፍ ታስሮበታልና፡፡ እናቱም (ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል) ብትሆን፤ አንዴ ቃሊቲ፣ አንዴ ትምህርት
ቤት እርሱን በማድረስና በመመለስ ከሚባክነው ጊዜዋ ተርፏት በፕሮግራሙ ላይ ተገኝታ ልጇን ማስደሰት አትችልም፡፡
የአንዱዓለም አራጌ ልጆችም የዚሁ ሰለባ ናቸው፡፡ ሩህ እና ጎህ አንዷዓለም ይባላሉ፡፡ ጎህ ገና በቅጡ አፍ አልፈታም፡፡ ከተወለደ ሁለት
ዓመት ከጥቂት ወራት ቢሆነው ነው፡፡ ሩህ አንዷዓለም ግን ስድስት አመት ሞልቶታል፡፡ አባቱ ‹‹አሸባሪ›› ተብሎ የታሰረውም ሩህ አዲስ
ት/ቤት አንደኛ ክፍል በገባ እለት ነው፡፡ ባለቤቱ ዶ/ር ሰላምም ልክ እንደ ናፍቆት እናት ሁሉ አንዴ ቃሊቲ፣ አንዴ ሩህን ት/ቤት
ከማመላለስና ህፃኑ ጎህን ከመንከባከብ፣ እንዲሁም ከዕለት ተዕለት የመስሪያ ቤቷ ስራ ተርፎ ለሩህ የሚሆን ጊዜ ሊኖራት አይችልም፡፡የበቀለ ገርባ ቤትም (የችግሩ አይነት ቢቀየርም) በተመሳሳይ የትካዜ ድባብ የተሞላ ነው፡፡ አቶ በቀለ የአራት ልጆች አባት ሲሆን፣ የመጨረሻ
ልጁ አስራ አራተኛ ዓመቱን ይዟል፣ የስምንተኛ ክፍል ተማሪም ነው፡፡ በዚህ ቤተሰብ ያለው ችግር የልጆቹ ነፍስ አለማወቅ አይደለም፤
በአቶ በቀለ መታሰር የማስተዳደሩ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ በባለቤቱ በወ/ሮ ሀና ረጋሳ ጫንቃ ላይ መውደቁን ተከትሎ የደረሱ ጫናዎች
ናቸው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፣ ሴቲቱ በአዳማ ከተማ በሚገኘው ጎሮ ሁለተኛ ደረጃ የ‹‹አፋን ኦሮሞ›› መምህር ሆና ከማስተማሯ ጎን ለጎን
በአዳማ ዩንቨርስቲ የማታው የትምህርት ክፍለ ጊዜ ተምራ በ‹‹ኢዱኬሽናል ፕላኒግ ማናጅመንት›› የዲግሪ ትምህርቷን በማጠናቀቋ፣
የምታስተምርበት ትምህርት ቤት ደረጃዋን እንዲያሻሽልላት ማስረጃዎቿን ታቀርባለች፡፡ ከትምህርት ቤቱ የተሰጣት ምላሽ ግን ፍፁም
ያልጠበቀችው ነበር፤‹‹የአመለካከት ችግር ስላለብሽ ከደረጃሽ ዝቅ ብለሽ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንድታስተምሪ ተወስኗል››፡፡ ይህ
ኢ-ፍትሀዊ እርምጃም ሞራሏን ነክቶ ስራዋን በገዛ ፍቃዷ እንድትለቅ አድርጓታል፡፡ መቼስ ከዚህ የበለጠ ግፍና መከራ በልጆች እናት ላይ
ደርሶ ከማየት በላይ የሚረብሽ ነገር የለም፡፡
ፍትህ ውብሸትስ ቢሆን? እንደ ናፍቆት እና ሩህ የአባት ክትትል እና እንክብካቤ ሊያገኝ አይችልም፡፡ አባቱ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ
በአሸባሪነት ተወንጅሎ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ከገባ ድፍን አንድ ዓመት ከስድስት ወር አልፎታል፡፡ ፍትህ ትምህርት የጀመረው አባቱ
ከታሰረ በኋላ ነው፡፡ እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ በሚገኘው ሆሊ ሴቪየር የኬጂ ተማሪ ነው፡፡ ይህ ህፃን ከሁለት ሳምንት በፊት (ታህሳስ 14)
4ኛ አመቱን አክብሯል፡፡
(በነገራችን ላይ የህዝበ-ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ሆነው ከተመረጡ በኋላ በስርዓቱ አምባገነንነት የታሰሩት መንፈሳዊ
መሪዎች ህፃናት ልጆችም የዚሁ ችግር ሰለባ ናቸው፡፡ አቡበክር አህመድ የአራት ልጆች አባት ሲሆን፣ የመጨረሻው ልጁ ኦማር የተወለደው
ከታሰረ በኋላ ነው፡፡ አህመዲን ጀበልም የሁለት ልጆ አባት ሲሆን፣ ሁለተኛ ልጁ ሱመያ የተወለደችው እርሱ ከታሰረ በኋላ ነው፡፡ ካሚል
ሸምሱ ከአራት ልጆቹ የመጨረሻዋ ኢናስ ከተወለደች ገና ዘጠኝ ወሯ ነው፡፡ ጋዜጠኛው የሱፍ ጌታቸውም የሶስት ዓመቱን ኦማር ለባለቤቱ
ትቶ ነው የታሰረው፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ፡፡ እናም በግፍ አባቶቻቸው በመታሰራቸው የኢድ-አልፈጥርም ሆነ የአረፋ በዓል ያለ አባት
ያሳለፉት ህፃናት ሁናቴ አጥንት ድረስ ዘልቆ በሚገባ ሀዘን ያሳምማል)
እነዚህ ህፃናት የአለምን ክፋትና ደግነት መረዳት ባይችሉም፤ ከአባቶቻቸው ጋር ያላቸውን የነፍስ ትስስር በደመ-ነፍስ ያውቁታል፡፡
የሚገርመው ደግሞ ሁሉም አባቶቻቸውን የሙጥኝ ማለትን መፈለጋቸው ነው፡፡ ለዚህም ነው በሳምንት አንዴ አባቶቻቸውን ለመጠየቅ
ቃሊቲ ሲሄዱ፣ እየተኮላተፉ ‹‹ሚስ እንዲህ ብላ…››እያሉ ስለመምህሮቻቸው ለአባታቸው ለመንገር የሚውተረተሩት፡፡ ሆኖም እንዲያ
ተኮለታትፈው የሚናገሩትን እንኳ ሳይጨርሱ የመጠየቂያዋ ደቂቃ አልቃ ከአባታቸው ተነጥለው፤ ከእናታቸው ጋር ወደ ቤት እንዲመለሱ
በጠባቂ ፖሊሶች ይገደዳሉ፡፡ ይሄኔም ምርር ብለው ያለቅሳሉ፡፡ እነዚህ የነገ ሀገር ተረካቢ ህፃናቶች አባታቸው አብሮአቸው ወደ ቤት ለምን
መሄድ እንደማይችል አይገባቸውም፡፡ እናቶቻቸውም ቢሆኑ ሊገባቸው በሚችል ቋንቋ ሊያስረዷቸው አይችሉም፡፡ በእርግጥም
የእናቶቻቸው አንዱ ፈተና፣ እሪ እያሉ የሚያለቅሱትን ህፃናት አባብሎ ወደ ቤት መመለሱ ነው፡፡ ምክንያቱም ህፃናቶቹ የ‹‹እስር ቤት››
ወይም የ‹‹አሸባሪነት››ትርጉም የሚረዱበት እድሜ ላይ ገና አልደረሱም፡፡ እናም የዘንድሮ አውደ ዓመትንም እነዚህ ልጆች በዚሁ ድባብ
ውስጥ ነው ተቀብለው የሸኙት፡፡
… ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የአብዛኛው ባለስልጣናት ልጆች አውደ አመቱን በማስታከክ ከሚማሩባቸው አውሮፓ እና ቻይና ከሚገኙ
ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎች በዘመናዊ አውሮፕላን ወደ ወላጆቻቸው እየመጡ ደስታን ሸምተው፣ የነገ ትዝታን ቋጥረው ይመለሳሉ፡፡ በአናቱም
ከፖለቲካው ባሻገር የጉልበተኛ ነጋዴ ልጆች ናቸውና አውደ ዓመቱን አስመልክቶ ውድ የገና ስጦታ ይበረከትላቸዋል፡፡ አባቶቻቸውም የገና
በዓልን ‹‹አሲና ገና…››ን እየጨፈሩ፤ አሊያም‹‹እንዳያልፉት የለም፤ ያ ሁሉ ታለፈ››ን እየደጋገሙ ሻምፓኝ ተራጭተው ቢያሳልፉት
ከልካይ የላቸውም፡፡ መቼም የታግሎ ማሸነፍ አንዱ ጥቅም ይህ ነው፡፡ በእርግጥ ይሄ የእነሱ ፖለቲካ ነው፡፡
የእነ እስክንድር ፖለቲካ ደግሞ ለአሸናፊዎቹ የተመቸ አይደለም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ ‹‹ከ20 ዓመት የዘለለ ፖለቲካ አልፎበታል›› ሲሉ፤
አሳሪዎቹ ደግሞ ፖለቲካችን 40 እና 50 ዓመትም ቢቆይ ‹‹ወይን›› ነው ይላሉ-እያደር የሚጣፍጥ፡፡ እነአንዱዓለም አራጌ ‹‹የኢህአዴግ
ፖሊሲዎች ወጣት ስራ አጥ እና ድሃ አርሶ አደሮችን የሚፈለፍል ነው›› በማለት ይከሳሉ፡፡ እነ በረከት ደግሞ ‹‹ስራ ፈጣሪ እና ኢንቨስተር
አርሶ አደርን ያበዛ ነው›› ሲሉ ያስተባብላሉ፡፡ እነ በቀለ የምርጫ ድምፅ እንዳይጭበረበር ሲታገሉ፤ እነ ኃይለማርያም ደሳለኝ ደግሞ
‹‹ህዝቡ ድምፃችን ይከበር በሚል ሰልፍ ወጥቷል››፣‹‹የመለስን ራዕይ ለማስቀጠል ወስኗል›› እያሉ ይሳለቃሉ… እንግዲህ እነዚህ
ሁኔታዎች ናቸው የ‹‹አሳሪ›› እና ‹‹ታሳሪ›› ፖለቲካን የወለዱት፡፡ በዚህም ነው እነ ናፍቆት በስርዓቱ ፖለቲካ በአባት ናፍቆት የሚሰቃዩት፡
፡የሆነ ሆኖ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር በአንዳች ኃይል ካልተገደበ በቀር ቀጣዩን ትውልድ ‹‹አባት አልባ›› እና ‹‹ባለ አባት›› በሚል
ጎራ ከፍሎ የሚጓዝ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ በዚህ መስመር የቱንም ያህል ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› ቢባል፤ የቱንም ያህል‹‹የአባይ ግድብ››
ቢባል ዳገቱን ጨርሶ መውጣት አይቻልም፡፡ ለጊዜው ነው እንጂ ከለምለሙ መስክ መድረስ አይቻልም፡፡ በየዓመቱም‹‹አሲና ገናዬ…››ን
መጨፈሩ የሚሳካ አይመስለኝም፡፡ በዚህ የተበላሸ ፖለቲካ አባታቸውን ያጡት ብቻ ሳይሆኑ፤ አባት የሆኑ ሁሉ በመንግስት ላይ ያቄማሉ፡፡
ልክ እንደ ‹‹ሀይድራ ራስ›› ሺህ ሲታፈን እጥፍ ሆነው ይቆጣሉ፤ የልጅን ፍቅር ያውቃሉና፡፡ የተቆጣ ህዝብ ደግሞ ውሎ አድሮ ምን
ሊወልድ እንደሚችል መተንበይ አይቻልም፡፡ አፈሩን ገለባ ያድርግለትና ጋዳፊም ቢሆን ‹‹ቤንጋዚን ለውድቀቴ መነሻ ትሆናለች›› ብሎ
አንድም ቀን ጠርጥሮ አያውቅም፡፡ የሆነው ግን ያልጠረጠረው ነው፡፡ እንግዲህ ለ41 ዓመታት በስልጣን ላይ ሲቆዩ እንኳን እንዲህ ቅልጥ
ያለ በጦር መሳሪያ የታገዘ አመፅ ቀርቶ፤ ማጉረምረም እና ኩርፊያም ሰምቶ አያውቅም ነበር፡፡ ይህ ግን ሊቢያውያን የሚያጉረመርሙበትና
የሚያኮርፉበት ምክንያት አልነበራቸውም ማለት አይደለም፤ ‹‹ሰኔ እና ሰኞ››ን ሲጠበቁ ነበር ማለት እንጂ፡፡ እናም ከእለታት አንድ ቀን
ከሊቢያ ከተሞች አንዷ በሆነችው ቤንጋዚን ‹‹ሰኔ እና ሰኞ››ተገናኙ፤ ተገናኝተውም ሲያበቁ ‹‹ንግርቱ››ን እውን አደረጉት፡፡
ለዚህ ነው ዝምታን እንደ ‹‹ይሁንታ›› አትውሰዱት የሚል የአዋቂዎች ምክር በየግድግዳው ላይ የተቸከቸከው፡፡ ለምሳሌ በእነ ናፍቆት፣
ጎህ፣ ፍትህ… እንግልት እና ስቃይ ብዙዎች ሀዘን ገብቶአቸዋል፡፡ ነገር ግን ከአቅም ማነስ ወይም ከፍራቻ ዝምታን መርጠዋል፡፡ ቁም ነገሩ
የሀዘን ብቻ ሳይሆን የዝምታም ዳርቻ መኖሩ ነው፡፡ በአራት ኪሎኛ አገላለፅ ደግሞ ‹‹ሁልጊዜ ፋሲካ የለም››፤ ቦታ መቀያየር ይኖራልና፡፡
አባራሪው ተባራሪ ሊሆን ይችላል፡፡ አሳሪውም ‹‹ታሳሪ የምሆንበት ቀን ቢመጣስ?›› ብሎ ሊሰጋ ይገባዋል፡፡ የዛሬን አያድርገውና በአንድ
ወቅት እነ ለገሰ አስፋው አሳሪ ነበሩ፡፡ ድብርት ካንጎላጃቸው በነሲብ መንገደኛን እያነቁ ይወነጅሉ ነበር፡፡ ወንጅለው ሲያበቁም ደስ ካላቸው
‹‹ቀይ ሽብር ይፋፋምብኝ›› የሚል ወረቀት ደረቱ ላይ ለጥፈው በጥይት ግንባሩን ያፈርሱታል፡፡ ሲያሰኛቸው ደግሞ በየቀበሌው
እያዞሩ‹‹አብዮቴ ማሪኝ›› እያስባሉ አናዘው፣ ሞራሉን ገለው ይለቁታል፡፡ ይህ ግን ለዘላለም የሚቆይ ፀጋ አይደለምና፤ ቀኑን ቆጥሮ፣ ግፉን
መዝግቦ የላዩ እታች፤ የታቹ እላይ ሆነ፡፡ ወይም አሳሪዎች ተሰብስበው ታሰሩ፡፡ ለ20 ዓመትም በሰፈሩት ቁና ተሰፍረው ሲማቅቁ ቆዩ፡፡
‹‹ማሩን፣ ይቅር በሉን…›› እያሉም የዘሩትን አጨዱ፡፡
ከዚህ መማር ያልቻለ ከቶ ከምን ሊማር ይችላል? የቅንጅት አመራር አባል ይቅርታ ጠየቀ፣ ብርቱካን ሚደቅሳ አጥፍቻለሁ አለች፣ ደበበ
እሸቱ በራሱ ላይ መሰከረ… ይሄ ሁሉ ፖለቲካ ነው፡፡ ያውም ያረጀ ያፈጀ፡፡ …የሚሻለው እንደ እነለገሰ አስፋው መከራ እስኪያስተምር
ከመጠበቅ ይልቅ ከፊደል መማር ነው፡፡
(ማስታወሻ፡- በዚህ ፁሁፍ የተነሳው ሁለተኛው አጀንዳ የዛሬ ዓመት የገናን በዓል አስመልክቶ ተዘጋጅቶ የነበረ ቢሆንም፣ የዘንድሮንም
የበዓል መንፍስ ስለሚወክል ማሻሻያ ተደርጎበት መቅረቡን በትህትና እገልፃለሁ)

No comments:

Post a Comment