Monday, March 11, 2013

እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ !! ቁጥር-2 (ከይመሩ ሙሄ)


እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ !! ቁጥር-2 (ከይመሩ ሙሄ)
በትምህርት ቤታችን ሜዳ
ከክፍል በፊት ማለዳ
እንደመንግሥት ወታደር
ሠልፍ ገብቼ በመሥመር
ከክርስቲያን ጓድኞቼ፣ ቆሜ በመሠበጣጠር
‘ተጠማጅ አርበኛ፣ ባገር መውደድ ቀንበር’
የዘመርኩ በስሜት ባግባቡ
ሲሠቀል ባንድራችን ውቡ፤
ወይም ፀሓይ ሣትጠልቅ
ወደ ቤታችን ሣንለቀቅ
ፍፁም የሆነ ፀጥታ
በሰፈነበቱ አፍታ
ዘምሬ ‘ደሙን ያፈሰሰ’
ድምፄ ባንዲራዬን ያወደሠ፤
ያረጋገጥኩ በዜማዬ
ስለውቡ ባንዲራዬ
ከግዑዝ ጨርቅነት አልፎ
ሕያውነት ተጎናፅፎ
እንደሚታይ ልቆ ገዝፎ፤
በማይጨውና በአድዋ፣ በናቅፋና በአሥመራ
በጅጅጋ ተፈሪ በር፣ በወልወል በካራማራ
ክርስቲያንና እስላሙ፣ የተሠዋለት በጋራ
ለውብ ውቡ ባንዲራችን፣ መሆኑን የማውቅ ጠንቅቄ
እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፣ ቅርሴን የምይዝ አጥብቄ።
* * * * * * * * * * *
በአዋጅ በለለው አቻ
በእድገት በሕብረት ዘመቻ
-2-
ተበትኜ ከዳር እስከዳር
ከክርስቲያን ጓዶቼ ጋር
ትምህርቴን ትቼ በይደር
አቋርጬ ወንዝ ተራራ
በሽታ ረሃብ ሣልፈራ
ለፀሓይና ለቁር
እንቢ ብዬ አልበገር
ወገኔን ፊደል አስግዤ
መፃፍ ያሥተማርኩ እጁን ይዤ
በምላሱ ኮቤ አርጥቦ፣ ያሥቆምኩ በጣቱ መፈረም
ሰው ለምኖ ማሥነበብም፤
‘አቦ ያብቃህ ለታላቅ ቦታ!
የኔ ጋሻና መከታ!
የኔ ታላቅ ባለውለታ!’
ብሎ የመረቀኝ ከልቡ
እኔም አሜን ያልኩ ባግባቡ።
ወገኔ ዓይኑን እንዲገልጥ
ግዴታ መብቱን እንዲያረጋግጥ
በከተማም ሆነ በገጠር
ሕዝብ ያዘጋጀሁ በማህበር
ገና በአፍላ ዘመኔ፣ ኑሮን ሣልቀምስ አጣጥሜ
ከክርስቲያን ጓደኞቼ፣ ትካሻ ለትካሻ ገጥሜ
ከፀረ ለውጦች ተፋልሜ
ደረቴን ሠጥቼ ለጦር
እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፣ ያገሬን ጥሪ የማከብር።
* * * * * * * * * * *
-3-
ክርስቲያን ጓደኞቼ ሲያገቡ
ሚዜ የሆንኩ በአግባቡ
አምኖብኝ ቤተስቡ፤
የሚዜኔቴን ግዴታ
የተወጣሁ በእስክስታ
ጭብጨባው እየነጎደ፣ አታሞው እየተመታ፣
ከመሃላቸው ገብቼ፣ የዘፈንኩ ተቀብዬ
እስኪሰነጠቅ ላንቃዬ፤
ማለዳ ብቅ ስትል ፀሓይ
ዘመድ አዝማዱ ባንድ ላይ
ተቀምጦ በተርታ
ተውጦ በፍፁም ፀጥታ
በታላቅ ጉጉት ሲጠብቅ
የሙሽሮቹን አዳር ለማወቅ
የምስራቹን ያበስርኩ፣ እዩት የደሙን ሸማ ብዬ
ነጭ ሻሽ የተላበሰ፣ ወስከምቢያ በጄ አንጠልጥዬ፤
ሚዜ የወጋሁ ዘመድ አዝማድ
በግንባሬ ያስለጠፍኩ ቀይ ባውንድ
ያሽቃረርኩ ጉሮሮዬ እሥኪነቃ
ሆታ ያቀለጥኩ፣ እስክባል በቃ
እኔ ኢትዮጵያዊ እስልም ነኝ
ሌላ መሆን የማልመኝ፤
ሌላ ባህል የማያምረኝ።
* * * * * * * * * * *
-4-
‘ኢትዮጵያ ትቅደም ያለምንም ደም’ እንዳልነበረ ሲዘመር
ማስመሰል አሸንፋ ሠፍና፣ የነበረው ሆኖ እንዳልነበር
በደርግ ጥይት ተደብድበው፣ የተቀጩ በቀይ ሽብር
ያልታደሉ ለማየት፣ የሕይወትን ቀትር ጀንበር
አንርሳ እንደነበሩ፣ ወጣት እስላሞችም ጭምር፤
ወላጆቻቸው ያለቀሡ፣ በመሪር ሓዘን የተጦሩ
የተነፈጋቸው እድሉ፣ በወግ በማእረግ መቅበሩ፤
አድራሻው ባልታወቀ፣ በተቆፈረ በችኮላ
ባንድ ጉድጓድ በጅምላ
ከክርስቲያን አጋሮቻቸው
ተንተራርሠው ተቃቅፈው
ለሰው ልጅ በማይገባ ወግ
የተቀበሩ በሰው በላው ደርግ
ኢትዮጵያን በደማቸው ያራሡ
ወጣት እስላሞች አይረሡ!!
* * * * * * * * * * *
በአዲስ አበባ ከተማ እምብርት
የሰማእታቱን ጴጥሮስ ሓውልትእያየሁ ያደግኩ ጧት ማታ
በፋሽስት መትረየሥ እሩምታ
ሕይወቱን ያጣው ለኔም ጭምር
መሆኑን የማምን ያለጥርጥር
እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፣ ጴጥሮስን እንደቅርሴ የምቆጥር።
* * * * * * * * * * *
የጧት እስላሞች ባረቢያ
መድረሻ ሲያጡ መሸሸጊያ
-5-
በሠጠቻቸው መጠጊያ
በሮቿን ቧ! አድርጋ ከፍታ
ክንዶቿን በሠፊው ዘርግታ
ላቆየችቻቸው በእቅፏ፣ ለእስልምና ባለውለታ
በሆነችው ኢትዮጵያ፣ ተወልጄ በማደጌ
ኩራቴ ነው ማእረጌ።
* * * * * * * * * * *
ጥንፈኝነት የሚመረኝ፣ በምንም ስሙ ቢጠራ
ጥራትና ብቃትን ግን፣ ማሥተናገድ የማልፈራ
ጥራት ጥራት፣ ብቃት ብቃት
ሊኖራቸው የሚችሉት
አብሮ በሠላም መኖርን፣ ሲያላብሡ እንጂ ለሕዝቡ
ሥለሆኑ ፍቅር ሠላም፣ ዋና የሃይማኖት ግቡ
ብዬ የማምን አበክሬ
እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፣ ከግር ጥፍሬ
እስከራስ ፀጉሬ
ለኢትዮጵያዊነቴ የምሞት፣ ሃይማኖቴንም አስከብሬ፤
* * * * * * * * * *
ባገራችን ያባባል ዘይቤ
የቆርጦ መቀጠል ግንዛቤ
ያልሆነ ማውራት ነበረ፣ ውሸት ጨምሮና አጋኖ
መዋሸቱም ማጋነኑም፣ እንደተጠበቀ ሆኖ
በ’ጅሓዳዊ ሓረካት’ ግን፣ ኢሕአደግ በርግጥ ቆርጦ ለጠፈ
እንደድሃ ድራብ በተጣጣፈ
ከዚህም ከዚያም በተጠለፈ
ዘገባው ሓቅን ቀሠፈ፣
-6-
ውሃና እሳትን አዋሃደ
ዓይንና አፈርን አዛመደ፣
አልቃይዳ አልሸባብ ቦኮሃራም
ምንድነው ዝምድናቸው ከሠላም?
ኧረ! ማን ቢወልድ ማ?
ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ፤
ማንን ሊያሳምን ዳግማዊ ‘አኬልዳማ’?
ስለሆነም፣ የኢሕአደግን መርዝ ዓላማ
ሕዝቡ ጠንቅቆ ስለተረዳ
ሰላማዊው ትግል ባሠበት፣ እንኳን እንደታሰበው ሊጎዳ!
ስለዚህ፣ የክርስቲያኑ ወገኔ
ግማሽ አካሉ በመሆኔ
የምኩራራ የምጀነን፣ የምመካ የምኮፈሥ!
እኔ ኢትዮጵያዊ እስላም ነኝ፣ ተጀምሮ እስኪጨረሥ!!!
* * * * * * * * * *

No comments:

Post a Comment