ይህ ጵሁፍ በ Dec 2009 በአቦጊዳ ድህረ ገጵና ኢትዮ ሚዲያ ለንባብ የበቃ ነው። ዛሬ በድጋሜ እዚህ የለጠፍኩት፤ በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ ትኩሳት፤ ዛሬ ላይ ሆነን ለመገምገም እንዲያመቸንና፤ የዛሬ አቋማችንን ለመፈተሽ እንዲያመቸን ነው። ለጵሁፉ ግድፈት ይቅርታ እየጠየኩ፤ መልካም ንባብ እንዲሆንልዎ እመኛለሁ።
የዚህ ፅሁፍ አላማ የተቃዋሚ ድርጅቶች ለምርጫ 2002 እንሳተፍ ቢሉ፤ የመራጩ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበት ለመጠቆም ነው። ሁላችንም እንደምናስታውሰው፤የኢትዮጵያ ሕዝብ የዲሞክራሲ ጥማቱን (በምርጫ 97) ይሆነኛል ያለውን ድርጅት በመምረጥ አሳይቷል። ይሁን እንጂ ገዢው መደብ የህዝቡን ድምፅ በጉልበት በመቀልበስ፤ የዲሞክራሲ ጥማቱ ዕውን እንዳይሆን አድርጓል።
በመሰረቱ በአለም ላይ የአምባገነኖች ታሪክ እንደሚያሳየን ከሆነ፤ አምባገነኖች ምርጫ የሚባል ቀመር ለነሱ እንደማይመች ነው። ምርጫ እንኳን ቢደረግ ሕዝብን በማስፈራራትም ሆነ፤ በማጭበርበር የሕዝብን ድምፅ እንደሚቀለብሱት ነው። አምባገነኖች በሚመሩት አገር ላይ ደግሞ ዲሞክራሲን በምርጫ ማምጣት፤ “ግመልን በመርፌ ቀዳዳ እንደማሽሎክ ይቆጠራል።” ለምሳሌ የወያኔው ገዢ አቶ መለስ ዜናዊ በቅርቡ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ የ “ምርጫ ዘጠና ሰባትን” ስህተት በ “ምርጫ ሁለት ሺህ ሁለት” አንደግምም የሚል ነው። ይህ እንግዲህ የሚያመላክተው “ለሁለት ሺህ ሁለት ምርጫ ያለውን ቀዳዳ በር በምንችለው መንገድ እንደፍነዋለን ማለታቸው ነው።” እንግዲህ አሁንም የወያኔው መሪ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲመጣ አለመፈለጋቸውን ነው የሚያሳየው። ታዲያ ይህ ሁሉ ሁኔታ ባለበት ሰዓት፤ አሁን በሀገር ውስጥ ያሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች፤ በምርጫ 2002 ተወዳድረው የሚያመጡት መሰረታዊ የዲሞክራሲ ለውጥ ምንድነው? የሚለው ጥያቄ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አእምሮ ውስጥ ያለ ጥያቄ ነው። እኔም በግሌ ሁሌም የምጠይቀው ጥያቄ ነው።
ይሁን እንጂ ሁላችንም መገንዘብ ያለብን ነገር፤ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አምባገነንነት በሰፈነባቸው አገሮች ላይ፤ መሰረታዊ የዲሞክራሲ ለውጥ ለማምጣት ብዙ ፈተናዎች እንደሚገጥሙት ነው። ስለዚህ በደፈናው ከገዢው መደብ አንድምታ በመነሳት፤ ሰላማዊ ትግል ሞቷል፤ ሰላማዊ ትግል አያስፈልገንም ማለቱ፤ በመሰረቱ እያንን አስከትሎ ወደፊት ለምንመሰርታት አዲሲቷ ኢትዮጵያ የሚገጥሙንን መሰናክሎች ካለመረዳት ይመስለኛል። ሰላማዊ ትግል መሳሪያ ላላነገተ ሰው ብቸኛ መሳሪያው ነው። ሰላማዊ ትግል ( የገዢው መደብ እምቢተኝነት እየጸና በሄድ እንኳን) ባለው ህዝባዊና ድርጅታዊ አወቃቀር የገዢውን መደብ አስገድዶ ስልጣኑን የሕዝብ ሊያደርግ የሚችልበት መንገዶች አሉ። ለምሳሌ እንደዚህ አይነቶቹ ነገሮች፤ በተለያዩ የአለም አገራቶች ታይተዋል። በጎረቤት ሀገር ኬንያም ታይቷል። ገዢው መደብም እራሱ ለፃፈው ህግ እስካልተገዛ ድረስ በተለያዩ ሀገሮች የተከሰቱት አመፆች፤ እራሱ ላይ ላለመድረሳቸው ምንም አይነት ዋስትና የለውም። ገዢው መደብ በደጋፊዎቹና በተቃዋሚዎቹ መሀከል የፈጠረውን ውጥረትም በምናደርገው ሰላማዊ ትግል ልናረግበው እንችላለን። ለዚህ ነው በሀገራችን ዘላቂ ዲሞክራሲ እስኪሰፍን ድረስ ሰላማዊ ትግል ለሀገራችን ወሳኝነት አለው የምንለው።
በእርግጥ ሰላማዊ ትግል ቆራጥ መሪ ያስፈልገዋል። እንደ “እምዬ ምንይልክ” ያለ አስተዋይና ቻይ መሪ ያስፈልገዋል። እያንን ደግሞ ለማድረግ የሁላችንም ተሳትፎ ወሳኝነት አለው። ጠንካራ መሪን መፍጠር የሚቻለው ደግሞ እኛ በመሪዎቻችን ላይ በምናሳድረው ፖለቲካዊ ተጽዕኖ፤ ለመሪዎቻችን በምንሰጠው ክብርና በቀናነት በምንለግሳቸው ምክር ናቸው። ነገር ግን፤ ካለምንም ተሳትፎ እንደው በደፈናው በመሪዎች ላይ የሰላ ሂስ በማቅረብ ብቻ ጠንካራ መሪን መፍጠር አንችልም።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የዚህ ፅሁፍ መነሻ፤ የ “ተቃዋሚ መሪዎች ወደምርጫው ይግቡ ሳይሆን፤ ቢገቡ የመራጩ ድርሻ ምን መሆን አለበት? የሚል ነው።”
እንደ እውነቱ ከሆነ፤ የ “ተቃዋሚ መሪዎች” ወደምርጫ ቢገቡ፤ የመራጩ ተሳትፎ መሆን ያለበት? ለሚለው፤ መራጩ ካለምንም ማንገራገር የሚደግፉትን ድርጅት መምረጥ አለባቸው የሚል ነው የኔ አስተያየት። ምክንያቱም የተቃዋሚ ድርጅቶች፤ በምርጫው ተሳትፈው፤ መራጩ ግን በምርጫው ካልተሳተፈ እና የሚደግፈውን ድርጅት መምረጥ ካልቻለ ጉዳቱ ለገዢው መደብ ሳይሆን፤ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ነው። ሌላወ ደግሞ የገዢው መደብ ካለምንም ከባድ ፉክክር ምርጫውን በቀላሉ ሊያሸንፍ ስለሚችል ነው። እያንን ስልም፤ ገዢው መደብ የራሱ ደጋፊዎች በሚሰጡት ድምፅ ብቻ ሊያሸንፍ ይችላል በሚል ነው። ተቃዋሚው ድርጅት ለምርጫ እስከተሳተፈ ድረስ ወያኔ በአለም አቀፉ ዙሪያ ተቀባይነት እንዲያገኝ ይረዳዋል። የሚፈልገውንም እርዳታ በቀላሉ፤ ከምህራብ አገሮች ሊያገኝ ይችላል።
ለምሳሌ፤ የገዢው መደብ ካድሬዎች ለእንደዚህ አይነቱ ግብ እንዲያመቻቸው፤ የተቃዋሚ ድርጅቶች ደጋፊ በመምሰል፤ በምርጫ 2002 ሕዝቡ ምርጫውን አድማ እንዲመታ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እያየን ነው። አንዳንድ የዋህ የተቃዋሚ ወገኖች፤ ነገሩን ካለመረዳት በወያኔ የቅስቀሳ መረብ ውስጥ መግባታቸው ልብ የሚያደማ ነገር ነው። በመሰረቱ የደጋፊው ሚና መሆን ያለበት፤ የተቃዋሚ ድርጅቶች በአጠቃላይ ወደምርጫ እንዳይገቡ ነው እንጂ፤ ከገቡ ግን ምርጫውን ህዝቡ አድማ እንዲመታ ቅስቀሳ ማድረግ ነገሮችን አርቆ ካለማየት የተነሳ መስሎ ነው ለኔ የሚሰማኝ። ምክንያቱም፤ የተቃዋሚ መሪዎች በምርጫው ተሳትፈው፤ ነገር ግን፤ መራጩ ሳይመርጣቸው ቢቀር እና ወያኔ ቢያሸንፍ፤ ወያኔ የሰላ ተቃውሞ በአለም አቀፉ ህብረተሰብ አይገጥመውም። እኛም፤ በአለም አቀፉ ህብረተሰብ የምናሰማው ጩኸት ሰሚ አያገኝም። “የቁራ ጩኸት ሆኖ ነው የሚቀረው።” ይልቅ የምርጫው ግዜ እየደረሰ ስለሆነ፤ የተቃዋሚ መሪዎች አገር ውስጥ ያሉትን ኢትዮጵያውያኖች፤ ዳያስፖራውንም ጨምሮ በቀጣዩ ምርጫ ስለመግባትና አለመግባት ውይይቱን ባስቸኳይ መጀመር አለባቸው። አለበለዚያ ህዝቡን ከወዲሁ ሳያሳምኑ እና ሳይቀሰቅሱ ለምርጫ ቢሳተፉ ጉዳቱ የሚሆነው ለተቃዋሚ መሪዎች ነው። ከመራጩምጋ ውይይቱን ካደረጉ፤ መራጩ አቋሙን በቀላሉ ገምግሞ ለምርጫው እራሱን ሊያዘጋጅ ይችላል።
ስለዚህ ከላይ ላለው ማሰሪያ እንዲሆን፤ የመራጩ ድርሻ መሆን ያለበት፤
ሀ) የ “ተቃዋሚው ድርጅት” ከዘጠና በመቶ (90%) በላይ ወደምርጫ ከገባ፤ መራጩ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚደግፈውን ድርጅት መምረጥ አለበት።ለ) በውጭ ያሉ የደጋፊዎች ሚና መሆን ያለበት ደግሞ የ “ተቃዋሚው ድርጅት” አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ፤ ወደምርጫ እንዳይገባ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል እንጂ፤ ከገባ በሁዋላ መራጩ እንዳይመርጥ ቅስቀሳ ማድረግ ከላይ እንደተገለጸው ጉዳቱ የሚሆነው ለተቃዋሚው ድርጅት ወገን ብቻ ነው።
የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ፤ የፖለቲካ እስረኞች ሳይፈቱ በሚደረግ ምርጫ፤ ምን አይነት ውጤት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ?!
የፖለቲካ አስረኞች ሳይፈቱ በሚደረግ ምርጫ ተቃዋሚው ወገን፤ የሚያስመዘግበው የፖለቲካ ድል ውጤቱ እምብዛም አመርቂ አይደለም። ምክንያቱም፤ ባለፈው በተደረገው ምርጫ ተያይዞ የታሰሩትም ሆኑ፤ በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩ ማንኛቸውም፤ የኢትዮጵያ ልጆች ከእስር ሳይፈቱ ወደምርጫ የሚኬድ ከሆነ፤ ደጋፊውም ሆነ እጩ ተወዳዳሪው የሚያደርገው ፖለቲካዊ ትግል በፍራቻ የተሸበበ ነው የሚሆነው። በፊት በፖለቲካ አመለካከታቸው የታሰሩት ሳይፈቱ እኔ ምን ዋስትና አለኝ ከሚል የተነሳ ተወዳዳሪው በሚወዳደርበት አካባቢ እንኳን የሚያደርገው ፖለቲካዊ ቅስቀሳ፤ አንደው ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር፤ የሚያመጣው ፋይዳ ብዙም አይኖርም። ብዙም ዘልቆ፤ መሄድ አይችልም። ስለዚህ እያንዳነዱ በምርጫ እወዳደራለሁ የሚሉ አገር በቀል የፖለቲካ ድርጅቶች ወደምርጫ ከመሄዳቸው በፊት በተቻላቸው መጠን ልዩነታቸውን ወደጎን በማድረግ፤ የጋራ ችግራቸው ወደሆነው፤ የደጋፊዎቻቸውን መፈታት ቅድሚያ በመስጠት ውይይት ሊጀምሩ ይገባቸዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ፤ የተከበሩ ኢንጅነር ሀይሉ ሻወልም፤ የሚታገሉት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እስከሆነ ድረስ እና ባለፈውም በተፈራረሙት የምርጫው ስነምግባር ደንብ ውስጥ እስረኞችን የማስፈታቱ አብይ ጉዳይ በስነምግባሩ መካተቱን ከግምት በማስገባት፤ በይበልጥ የወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን መፈታት እውን ማድረግ ይኖርባቸዋል። ገዢው መደብ፤ የገባውን ቃል መተግበር ቢሳነው፤ የተከበሩ ኢንጅነር ሀይሉ ሻወል የሚመሩት ድርጅት ምርጫውን አድማ ለመምታት በቂ ምክንያት ይኖረዋል። በዚህን ወቅት፤ ሌሎችም የፖለቲካ ድርጅቶች የነሱን መንገድ በመከተል በምርጫው ላለመሳተፍ አድማ ሊመቱ ይችላሉ።
የሀገር ውስጥ ፓርቲዎች ግንኙነት ከዳያስፖራውጋ?
በመሰረቱ፤ የአገር ውስጥ ድርጅቶች፤ የዳያስፖራውን ኢትዮጵያዊ ጠቃሚነት በመገንዘብ፤ ሁሉም ድርጅቶች በተወካዮቻቸው አማካኝነት፤ ከዳያስፖራው ኢትዮጵያዊጋ መሰረታዊ ግንኙነት መመስረት አለባቸው። ዳያስፖራው ኢትዮጵያዊ፤ የቅንጅት መሪዎች እስር ቤት ከገቡበት ግዜ አንስቶ፤ እስካሁን ድረስ የህዝባችን ልሳን ሆኖ እያገለገለ ያለ ሀይል ነው። ለቅንጅት መሪዎች ከእስር መፈታትም፤ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተ ሀይል ነው። ከፍተኛ የኢኮኖሚ እገዛም አድርጓል። እያደረገም ይገኛል።
ይህን፤ ከላይ ያለውን ከግምት በማስገባት፤ በአገር ውስጥ ያሉ፤ ሰላማዊ የተቃዋሚ ድርጅቶች፤ የዳያስፖራውን ወሳኝነት በመገንዘብ፤ በሚያደርጉት አንዳንድ ፖለቲካዊ ወሳኔ፤ በተወሰነ ደረጃ የዳያስፖራውን ወገን ቢያማክሩ ገንቢ ነው የሚል ግንዛቤ አለኝ። በሚያደርጉት ውይይትም፤ የዳያስፖራውን የስጋት ውጥረት ሊያረግቡት ይችላሉ። ዳያስፖራውም ቢሆን አገር ውስጥ ያለውን አስገዳጅ የሆኑ ነገሮች በመገንዘብ፤ በተቃዋሚ መሪዎች የሚሰጠውን አዎንታዊ ሀሳቦች በመቀበል፤ በሚወስዱት እርምጃ ድጋፉን መስጠት ይገባዋል። በሚወስዱት ፖለቲካዊ እርምጃም፤ ስህተት ከሆነ እንኳን ሀሳባቸውን እንዲገመግሙ ግፊት (ተፅዕኖ) ማድረግ ይኖርበታል እንጂ ስድብ አዘል ሂስ ማድረጉ ፋይዳ ቢስ ነው። በዚህ አጋጣሚ፤ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችለውም ወያኔ ነው።
No comments:
Post a Comment