ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት፤ "ወንድ አንድ ሰው ሞተ"
ጌታቸው ኃይሌ
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትን "ወንድ አንድ ሰው" የምለው ወታደራዊ ፍልሚያ ላይ ውሎ ድል ሲነሣ
አይቸው አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ፥ "እስመ፡ ቀትልክሙ፡ ኢኮነ፡ ምስለ፡ ዘሥጋ፡ ወደም፡ ዘእንበለ፡
ምስለ፡ መኳንንተ፡ ጽልመት" (ጦርነታችሁ ሥጋና ደም ሆነው ከሚታዩ ጋር ሳይሆን ከጭለማ ገዢዎች
ጋር እንጂ) እንዳለው፥ የጭለማ ገዢ ከሆነው ከድንቁርና ጋር ግብ ግብ ገጥሞ ሲያሸንፍ የዓይን
ምስክር ስለሆንኩ ነው። የተሰጠው ጸጋ በሞያው ወንድ አንደ ሰው አድርጎታል።
ታደሰ ተወልዶ ብዕሩን እስኪያነሣ ድረስ፥ የኢትዮጵያ የመካከለኛው ዘመን ታሪክ በጭለማ ውስጥ
ነበር። "ማን ይናገር? የነበር፤" እንዲሉ፥ የታደሰን ፈለግ ተከትየ አንዳንዴም መሪዬ እያደረግሁ
የጎበኛቸውን ምንጮች ለመጎብኘት ዕድል አጋጥሞኛል። ሌሎች እንደ ገለባ ከሚቈጥሩት ክምር ውስጥ
ስንዴ ሲያመርት አይቸዋለሁ። ያነበብኳቸው የታደሰ ድርሰቶች ሁሉ በሀገር ወዳድነትና በእውነተኛነት
ላይ የተመሠረቱ የአንባቢያቸውን ዕውቀት የሚያዳብሩ ቋሚ ምንጮች ናቸው። Church and State in Ethiopia በሚል ርእስ
ያዘጋጀው ጥናት በታተመበት ዘመን ከታተሙት ሌሎች የኢትዮጵያ ታሪክ መጻሕፍት ሁሉ በባለ ሞያዎች ዘንድ በይበልጥ የሚጠቀስ
መጽሐፍ ሆኗል። ከገበያ ላይ እየተጣራ አስቸግሮ በተደጋጋሚ ታትሟል፤ ገና ወደፊትም በተደጋጋሚ እንደሚታተም አልጠራጠርም።
Church and State in Ethiopia ከታተመ ወዲህ የተገኙ መረጃዎች የያዙት ዕውቀት እዚህ መጽሐፍ ውስጥ ባለው ላይ
የሚጨመር እንጂ መጽሐፉ ያዘለውን የሚተኩ አይዶሉም። ስለመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያን ታሪክ የሚጽፍ ተመራማሪ የታደሰን
Church and State in Ethiopia መነሻ ካላደረገ፥ የሰውየውን ድክመትና የሥራውን ሕጸጽ ራሱ መመስከሩ ነው።
አፄ ይኩኖ አምላክ የኢትዮጵያን ሥልጣን ለመያዝ የወሰደው የጦር ስልት ምን እንደሚመስል የታወቀው ታደሰ በጻፋት አጭር ድርሰት
ነው።
የደቂቀ እስጢፋኖስን ንቅናቄ ዓለም በሰፊው ሊያውቅ የቻለው ታደሰ በጻፋት አጭር ድርሰት ነው። የነዚህን መነኮሳት ታሪክና
ሃይማኖታዊ ፍልስፍናቸውን ታደሰ በእንግሊዝኛ እስኪጽፍልን ድረስ፥ ግዕዝና ሌሎቹን የአውሮፓ ቋንቋዎች የማያውቅ ሁሉ በሀገራችን
የለውጥ እንቅስራሴ መኖሩን አያውቅም ነበር።
ደብረ ሐይቅ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያን የመካከለኛውን ዘመን ታሪክ በአደራነት ጠብቃ ያኖረች ቅድስት ገዳም መሆኗን ያወቅነው
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራት በጻፋት አጭር ድርሰት ነው።
ፕሮፌሰር ታደሰ ታምራትን የምናስታውሰው በሰጠን ዕውቀት ብቻ ሳይሆን፥ ለታሪክ ተመራማሪዎች፥ በተለየም ለወጣት
ኢትዮጵያውያን፥ መልካም አርአያ በመሆኑ ጭምር ነው።
ታደሰን የምናስታውሰው በምሁርነቱ ብቻ አይደለም። ሃይማኖቱን የጠበቀ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ልጅ በመሆኑ
ጭምር ነው። ቋንቋዋን ግዕዝንና የምታስተምረውን ትምህርት የተማረው የቆሎ ተማሪ ሆኖ ነው። ወደአሜሪካን እንደመጣ፥
የምሠራበት ዩኒቨርስቲ ጋብዞት ከእሱና ከባለቤቱ ከወይዘሮ አልማዝ ጋር ለጥቂት ቀናት አብረን ነበርን። "እንግዲህ" አለኝ በጨዋታችን
ማህል፥ "እንግዲህ ሕይወታችንን እዚሁ አገር ማሳለፋችን የማይቀር ከሆነ፥ የመጀመሪያው ግዴታየ ችግራችንን ስንነግረው የሚረዳልን
መንፈሳዊ አባ ነው" ያለኝ ምሁሩን ታደሰን ባስታወስኩ ቊጥር አብሮ ይታወሰኛል።
ታደሰን የምናስታውሰው በምሁርነቱ ብቻ አይደለም። የቅኔ ዕውቀቱ አለዝቦት ይሁን ወይም የተፈጥሮ ስጦታው ባላውቅም፥ ጨዋታው
ለዛ የተላበሰ በመሆኑም ጭምር ነው፤ ያስቃል፤ ያሳስባል። የራሱን ክብደት እያስታወሰ ይቀልዳል። ታደሰ እውነትም አሳቢና አስተዋይ
ጭንቅላቱ ከቁመቱ በልጦ መጥቆ የሄደ ሰው ነበር።
እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ ያበረከታትን ታደሰን የችሎታውን ያህል ሳንጠቀምበት በችኮላ ወሰደብን። ታላቅ የፍሬ ዛፍ ተገረሰሰ።
እግዚአብሔር ሰጠን እግዚአብሔር ነሣን። የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን። ነፍሱን ከነ አቡነ ተክለ ሃይማኖት፥ አቡነ ኢየሱስ
ሞአ፥ አቡነ እስጢፋኖስ ጋር ያሳርፍልን። የታደሰ ስም ከመቃብር በላይ መኖኑ ለልጆቹ፥ ለዘመድ አዝማዶቹ፥ ለወዳጆቹ መጽናኛ
ይሁናቸው። አሜን።
ሺካጎ፥ ቅዳሜ ግንቦት 24 ቀን 2005 ዓ. ም. (06/20/2013)

No comments:
Post a Comment