Tuesday, June 25, 2013

አዲስ መጽሀፍ፣ “ድርጅታዊ ምዝበራ” (በአክሎግ ቢራራ)

አዲስ መጽሀፍ፣ “ድርጅታዊ ምዝበራ” (በአክሎግ ቢራራ)


“የኢትዮጵያ እድገታዊ መንግስትና”፣ የስልጣን ባለጸጋዎች ኢኮኖሚ

ኢትዮጵያ ድሃ የሆነችው የሚበቃት ሃብት ስለሌላት ሳይሆን አዙሪት የያዘው ፖለቲካና የተንሻፈፈ ፖሊሲ ስለተጣቧት ነው። የዶክቶር አክሎግ ቢራራን መጽሃፍ ሳነብ የተማርኩትም ይህንኑ ሃቅ ነው። ችግሮቻችን ሁሉ ዞረው-ዞረው ከአስተዳደር ብልሹነት ጋር ይያያዛሉ።
ዛሬ፤ ሃገራችን ፈረንሳይን የሚያህል ለም መሬት አስረክባ ነው ለካ ፈረንሳይ እርዳታ የምትጠይቀው። ከዚያችው ከደካማ ጎኗ ደሞ 11.7 ቢሊዮን ዶላር ተሰርቆባታል። በየአመቱ፤ ከ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ እርዳታ እየተቀበለች ያንኑ የሚያህል ገንዘብ ደሞ በየአመቱ ትሰረቃለች። በገባችበት የኢኮኖሚ፤ የማህበረሰብዊና የፖለቲካ ውድድሮች ውስጥ ከዓለም ሃገራት ከመጨረሻዎቹ ሁሌም አታጣም። ስደትና ረሃብ ልዩ መታወቂያችን ሆነዋል። የነዚህ ችግሮች ባህሪያትና እርስ በርስ የመመጋገባቸው ጉዳይ በዚህ መጽሃፍ በሚገባ ተመርምሯል።
ዶክቶር አክሎግ በዚህ መጽሃፋቸው የኢትዮጵያን መሰረታዊ ችግሮች ውልቅልቅ አርገው በማሳየታቸው ብቻ አይደለም የተደመምኩት። ከሁሉ በላይ ከገባንበት አረንቋ እንድንወጣ መንገዱን ለማሳየት በመቻላቸው ነው። ኢትዮጵያዊያን፤ በተለይም፤ ወጣቱ ትውልድ ችግሩን በሚገባ ተረድቶ መፍትሄ እንዲያመጣ ካስፈለገ ይህን መጽሃፍ ደጋግሞ ማንበብ አለበት።
ነጻነትና የሕግ የበላይነት መኖር ለውስብስብ ችግሮቻችን መፍትሄ መሆኑን ዶክቶር አክሎግ አበክረው መክረዋል፡፡ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ያገለለውን የህወሓት የኢኮኖሚ ፒራሚድ በሚገባ ስለውታል። በአጠቃላይ፤ ችግሮቻችንን ሁሉ ንቅስ አርገው አውጥተው በሚገባ ቋንቋ ተንትነውታል። በውነቱ፤ ያነበቡት እንዴት ታድለዋል።
ጌታቸው ዘለቀ፤ ሶል፤ ደቡብ ኮርያ፤ የልማት ኢኮኖሚስት
ዶክቶር አክሎግ ቢራራ በዚህ መጽሃፍ በማያሻማ ቋንቋ የኢትዮጵያን ሕዝብ የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚ፤ የሶሻልና በአጠቃላይ የሕብረተሰቡን ከአስተዳደር ብልሹነት የመነጩ ውስብስብ ችግሮች፤ በጥናት፤ በምርምርና በማስረጃ የተደገፈ ትንተና አቅርበዋል።
እነዚህ ሁለገብ መሰሪ ችግሮች የመነጩት ከጠባብ ጎጠኛ፤ አናሳ ጎሳ አምባገነናዊ መንግሥት፤ የሕዝቡን መብቶች ረገጣ፤ የፕሬስ ነጻነት አፈና፤ የሕግና የፍትህ መጥፋት፤ የሙስና አሳፋሪ በሆነ ደረጃ መስፋፋት፤ በተደራጀ መልክ የአገሪቱን ከለጋስ አገሮችና ዓለም አቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች የተገኘ እርዳታና ብድር፤ እንዲሁም፤ የአገሪቱን አንጡራ ሃብት ዘረፋና ወደ ውጭ አገር ማሸሽ ዘመቻ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል። ደራዊው ከዚህ ሁለገብ ውስብስብ ችግሮች መውጣት የሚቻልበትን ከስራ ሊውሉ የሚችሉ መፍትሄዎችን ጠቁመዋል። ችግሮቹ እድሜ፤ ጾታ፤ ጎሳ ስለማይሉ፤ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ተባብሮ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሄውን መሻት አለበት። የወጣቱ ትውልድ በህወሓት/ኢህአዴግ መንግሥት የሚጠብቀው የስራ ድልድል ስደትና ውርደት ስለሆነ፤ ይህን መጽሃፍ ፈልጎ ማንበብና የችግሮቹን ክብደት መገንዘብና ማጤን ይኖርበታል። የወጣቱ ትውልድ ኦሮሞ፤ አማራ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ ወዘተ፤ ወዘተ ሳይል በሕብረት ለነጻነቱና ለመብቱ መታገል ግዴታው ሆኗል።
ይህ መጽሃፍ በተለይ አገር ቤት ለሚገኘው ህብረተሰብ በፍጥነት እንዲሰራጭ ማድረግ የሁላችንም ግዴታ ነው።
ግርማ ተፈራ፤ ቀድሞ የዓለም ባንክ ባልደረባ የነበሩ
Review of Dr. Aklog Birara's new book in Amharic

No comments:

Post a Comment