ይህንን አጀንዳ ለማቅረብ ያሰብኩት ባለፈው ሳምንት ነበር፤ ይሁንና ‹‹የምስራቅ ኢትዮጵያ ፖለቲካ 2›› የሚለው ፅሁፌ አንድም ወቅቱ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ቀን›› ዋዜማ በመሆኑ፣ ሁለትም በይደር የተላለፈው የዚሁ ተከታይ ፅሁፍ መቋጨት ግድ በማለቱ ነበር፡፡ እናም ‹ቦ ጊዜ ለኩሉ› እንዲል ጠቢቡ፣ የዘገየው አጀንዳችን የዕውቁ ደቡብ አፍሪካዊው የፀረ አፓርታይድ ትግል መሪ ኒልሰን ማንዴላን ህልፈት ተከትሎ ዓለም ‹በተሳሳተ የታሪክ ወንዝ› ከመፍሰሱ ጋር ተነፃፅሮ ይቀርብ ዘንድ ገፊ ምክንያት ሆኗል፡፡ በርግጥ የአጀንዳው ተጠየቅ ማንዴላን አኮስሶ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክን ማወደስ አይደለም፤ ንጉሡን ያገለለውን ጨካኝ የታሪክ ፍርድ መሞገት እንጂ፤ በአናቱም ከውስጥ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ዘመን የተሻገረ ቂም የሀገር ባለውለታን ታሪክ ማደብዘዙን መተቸት
ነው፡፡
‹ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ›
ከአማራና ኦሮሞ ፊውዳል ቤተሰብ እንደተወለደ በህይወት ታሪኩ ዙሪያ የተሰናዱ ድርሳናት የሚያወሱለት ምኒሊክ፣ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ 4ኛ በ1882 ዓ.ም. ከ‹ማሀዲስቶች› (ሱዳናውያን ያቀጣጠሉት የነፃነት ንቅናቄ መጠሪያ ነው) ጋር በተደረገ ጦርነት መሰዋቱን ተከትሎ ነው ወደ ንግስናው የመጣው፤ ሆኖም ዘውድ ከመጫኑ በፊት፣ በአፄ ዮሐንስ ስር ሆኖ የሸዋና ወሎ አካባቢዎች ‹ንጉሥ› እንደነበረ ይታወሳል፡፡ በነገራችን ላይ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የተነሳው ጀርመናዊው ቢስማርክ የተከፋፈለች ሀገሩን ለማዋሀድ ‹‹ነፍጥና መስዋዕትነት›› (With blood and iron) ግድ መሆኑን እንደ አወጀው ሁሉ፣ ተመሳሳዩን መንገድ የመረጠው ምኒልክም፣ ዘግይቶ በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች እንደ ‹ወረራ› ያስቆጠረውንና ‹ግዛት ማስፋፋት› ተደርጎ የተወሰደውን ወሰን የማፅናት ዘመቻው (በዚህ መሀል ‹ባይፈፀሙ ኖሮ› የሚያስብሉ ስህተቶች መሰራታቸው ሳይዘነጋ) በአፄ ዮሐንስ ዘመን መንግስት የተካሄደ እንደነበረ ይታወቃል፡፡
የሆነ ሆኖ በአፄ ዮሐንስ የመጨረሻ ዘመን አካባቢ (እ.ኤ.አ. በ1884/5) አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን ለመቀራመት ጀርመን በርሊን ላይ ተሰባስበው ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያንም ዒላማ ያደረገ ቢሆንም ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ተገቢውን ትኩረት የሰጠው አይመስልም፡፡ በወቅቱ ከአመታት በፊት ከደንከል ባላባቶች አሰብን በመግዛት የእግር መርገጫ ያገኘችው ጣሊያን ኤርትራን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራ ወደ ኢትዮጵያ ለመስፋፋት ኃይሏን እያደራጀች የነበረ ከመሆኑም በላይ፣ በአፄውና በምኒልክ መካከል ቅራኔ እንዲፈጠር ሳትታክት ማሴሯ ለጊዜያዊ ድል እንዳበቃት ይነገራል (ዝርዝር ታሪኩ ሰፊ በመሆኑ አጀንዳችንን እንዳያስረሳን እዚሁ ገታ እናድርገውና ወደ ጉዳያችን እንመለስ)
‹ጂኦ ፖለቲካው› ይህንን ይመስል በነበረበት በዛን ዘመን ‹ዳግማዊ ምኒሊክ› በሚል ስያሜ ዘውድ የደፋው ንጉሥ፣ የረቀቀውን የጣሊያንን ፖለቲካዊ ሴራ ከመበጣጠስም አልፎ በወርሃ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ‹አድዋ› በተባለ የሀገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተደራጀውንና ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀውን ሠራዊቷን ድል በመንሳት አለምን ጉድ አሰኝቷል፤ ይህ ሁኔታም ከባርነት በታደገው በራሱ ህዝብ ዘንድ፡-
‹‹ምኒሊክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ››
በሚል ሲያስወድሰው፣ በገዛ መሬታቸው ነፃነታቸውን ተነጥቀው በቅኝ ግዛት ስር ባደሩ በርካታ አፍሪካውያን ሀገራት ሰማይ ደግሞ ‹‹ኢትዮጵያኒዝም› የሚል መነቃቃት እንዲናኝ መግፍኤ ሊሆን በቃ፤ ዛሬም ድረስ ጥቂት የማይባሉ የምዕራብና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ሰንደቅ-አላማቸው ከአረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለም ጋር የተያያዘበት ምክንያትም ይኸው ነው፡፡
እምዬ ምኒሊክ
ዳግማዊ ምኒሊክ ከሰሜኑና ከመንግስቱ መቀመጫ የራቁትንና የተበታተኑትን ህዝብ ወደ አንድ በማምጣት የሀገሪቱን ግዛት ከቀድሞ ነገስታት ይዞታ በእጅጉ በሰፋ መልኩ ካፀና በኋላ የተማከለ ስርዓት ለማንበርና ሀገር ለማዘመን መሰረታዊ የሆኑ አስተዋፅኦዎች አድርጓል፤
የአጼ ምኒልክ ሀወልት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
የአስተዳደር መዋቅሩንም በሚኒስትሮች ከመከፋፈል አንስቶ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው አበርክቶቹ በወቅቱ ከአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓና አሜሪካን አካባቢ ካሉ በርካታ ሀገሮች ሳይቀር የተሻለ ታሪክ ባለቤት እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ለእንዲህ አይነቱ ክቡር ስራዎቹ ትንሿ ማሳያ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ገዥያችን ኢህአዴግ፣ ያውም ‹ከሚቀጥለው ምርጫ በኋላ ሙሉ በሙሉ አዳርሳለሁ› እያለ ፕሮፓጋንዳውን የሚነዛበት የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚነት የተጀመረው በምኒሊክ መሆኑን ማስታወሱ ነው፤ በጊዜው በቅርቡ ከሚያገኘው ‹ጅረት› ከከብትና አህዮች ጋር ተጋፍቶ ጥሙን ይቆርጥ የነበረው ህዝብ፣ በድቡልቡል ብረት ሆድ (በቧንቧ) ውስጥ ተጉዞ ደጁ ድረስ ንፅሁ ውሃ ሲመጣለት፣ ንጉስ ምኒሊክን እንደሚከተለው አሞግሶ እንደ ነበር በርካታ ድርሳናት ያወሳሉ፡-
‹‹እንዲህ ያለ ንጉሥ፣ የንጉሥ ቄናጣ፤ ውሃ በመዘወር አየር የሚያወጣ፤ ያደፈው ሊታጠብ፣ የጠማው ሊጠጣ፤ አሁን ከዚህ ወዲያ ምን ጥበብ ሊመጣ፡፡››
በአስተዳደር ዘይቤውም ቢሆን እንደ አባቶቹ ‹ፍለጠው፣ ቁረጠው› አለመሆኑን የሚያሳየው በፍቃደኝነት የውህደቱ ተባባሪ የሆኑ ክፍለ ሀገሮች፣ ያለብዙ ጣልቃ ገብነት፣ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ማመቻቸቱ ነው፡፡ ይህንን ሁነት ዛሬ ሀገሪቷ እየተመራችበት ካለው ሐሳዊ ‹ፌደራሊዝም› አንፃር ብንመዝነው የምናገኘው ጥሬ ሀቅ ከኦሮሚያው ፕሬዚዳንት አለማየሁ አቱምሳ፣ ወይም ከአማራ ክልሉ አያሌው ጎበዜ ይልቅ፣ የምኒሊኩ አባጅፋር በጅማ ክፍለ ሀገር ወይም ራስ መንገሻ ስዩም ትግራይ ላይ የነበራቸው የአስተዳደር ነፃነት የተሻለ መሆኑን ነው፡፡ ይህና ይህን መሰል ጉዳዮች ለንጉሱ ሰፊ ተወዳጅነት ከማስገኘታቸውም በላይ ‹‹እምዬ ምኒሊክ›› የሚል የአክብሮትና ፍቅር ስያሜ እስከማጎናፀፍ መድረሱ በተለያዩ ዜና መዋዕሎች ተገልጿል፡፡
ታሪክ የጨከነችበት ጀግና
በኢትዮጵያ የ3ሺ ዘመን ታሪክ በጀግንነትም ሆነ ዳር ድንበር በማስከበር አቻ የማይገኝለት፣ ከህልፈቱ በኋላ በቅኝ አገዛዝ ስር በወደቁ ሀገራት ለተደረጉ የነፃነት ትግሎች አባት መሆን የቻለ፣ በዓላማችን ለመጀመሪያ ጊዜ የዘመናዊውን አውሮፓ ሀገር በጦር መሳሪያ ማሸነፉ የተሳካለት መሪ ሀገሩና ታሪክ የሚገባውን ቦታ በመንፈግ የጨከኑበት ይመስለኛል፡፡
ታህሳስ 3 ቀን 2006ዓ.ም ህልፈቱ 100ኛ ዓመቱን የደፈነው የኢትዮጵያችን ባለዕዳ ዳግማዊ ምኒልክ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት እንደታየው ሁሉ ዘንድሮም ዕለቱን መንግስት በቸልታ አልፎታል፡፡ በግልባጩ ከአፍሪካ መጨረሻ ልጆች ተርታ የምትመደበው ደቡብ አፍሪካን ከአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ ለማውጣት (ምንም እንኳ ባይሳካለትም) የታገለው ኒልሰን ማንዴላ ማለፉን ተከትሎ ‹የአፍሪካ የነፃነት አባት› በመባል ያልዘራውን ሲያጭድ፣ ያልዋለበትን ሲሰበስብ ቁጭት ባረበበት አርምሞ አስተውያለሁ፡፡ ጉዳዩን ይበልጥ አስተዛዛቢ የሚያደርገው ደግሞ መንግስታዊ ሚዲያዎች የማንዴላን ‹የአፍሪካ አባት›ነት ከመተረት አልፈው፣ የኢትዮጵያን የምስረታ ታሪክ ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ወደ ወጣበት 1980ዎቹ መግፋታቸው ነው፤ በርግጥ ትርክቱ ራሱ ማንዴላ ‹‹ረዥሙ የነፃነት ጉዞ›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሐፉ ‹‹ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት የተወለደባት ሀገር ናት›› ሲል ከመሰከረው እውነታ ጋር ጭምር መጣረሱ በግልፅ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡
የ‹ማዲባ› እውነታዎች
ጥቂት በማይባሉ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን Xhosa-ጎሳ ስም ‹ማዲባ› (አባት) በሚለው የአክብሮት መጠሪያ የሚታወቀው ኒልሰን ማንዴላ በሀገሩ የሰፈነውን የዘር መድሎ አራማጅ የ‹አፓርታይድ› ስርዓትን ለማፍረስ፣ ዛሬ ከተደረበለት ‹የሰላማዊ ትግል› አቀንቃኝነት ካባ ይልቅ፣ ጠብ-መንጃ አንስቶ የመታገል አስፈላጊነትን ከላይ በጠቀስኩት መፅሀፍ ውስጥ የገለፀው ‹‹ልዝብ ተቃውሞ እንዳበቃለት በስሜት ተውጬ ተናገርኩ፤ ከዚህ በኋላ አፓርታይድን ለማፍረስ አመፅ ብቸኛው አማራጭ ስለመሆኑ አስረገጥኩ›› (I spoke emotionally, saying that the time for passive resistance had ended. I said that violence was the only way to destroy apartheid) በማለት እንደነበረ በታሪክ የተመዘገበ እውነታ ነው፤ ዓላማውን ለማሳካት የሚችለውን ሁሉ ማድረጉም እውነት ነው፤ ፍትሀዊዋ ደቡብ አፍሪካ ትፈጠር ዘንድ ሀገሬ ኢትዮጵያ ከነተከታዮቹ ከስንቅና ትጥቅ በተጨማሪ ወታደራዊ ስልጠና መስጠቷም እውነት ነው፤ ለ27 ዓመታት ያህል በነ‹ሮቢን ደሴት› ዘግናኝ እስር ቤቶች መሰቃየቱም እውነት ነው፤ ተፈጥሮ የቸረችውን ውድ ማዕድን አቅፎ የያዘው የደቡብ አፍሪካ ድንግል መሬት በአፓርታይድ ባለሟሎች መገሰሱም እውነት ነው፤ ይህ ስርዓት የማታ ማታ ለአለም አቀፍ ጫና መንበርከኩም እውነት ነው፤ የመጨረሻው የአፓርታይድ መሪ ፕሬዝዳንት ፍሬደሪክ ዴክለርክ፣ ማንዴላንና ጓደኞቹን ከእስር መፍታቱ፣ በፓርቲያቸው (የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ) ላይ የተጣለውን የሕግ ዕገዳ ማንሳቱ እውነት ነው፤ ማዴባ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው የያዙ ነጮችን በወንጀል አለመጠየቁም ሆነ የሀብት ክፍፍልን ፍትሀዊ በሆነ መንገድ እንኳ ሊያርም አለመሞከሩ እ.ኤ.አ. በ1993 ዓ.ም. ከዴክለርክ ጋ በጋራ ለኖቤል ተሸላሚነት እንዲበቃ ማድረጉ እውነት ነው፤ በዓመቱ (እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም.) እርሱና ፓርቲው በምርጫ አሸንፈው ስልጣን መያዛቸውም እውነት ነው፣ ከደቡብ አፍሪካ ዘግይቶ ነፃነቱን ያገኘ ሀገር አለመኖሩም እውነት ነው፡፡ … ይህ ሁሉ ከመሆኑ አንድ ክፍለ ዘመን በፊት ሀገሬ ምኒሊክን በመሰለ ጀግናና አርቆ አስተዋይ መሪዋ ነፃነቷን አለማስደፈሯ እውነት
ነው፤ እነሆም እነዚህ ሁነቶች ናቸው የዓለም ታሪክ ለኒልሰን ማንዴላ ሲበዛ ቸር፣ ለዳግማዊ ምኒልክ ደግሞ እጅግ ንፉግ በመሆኑ ለሀፍረት የዳረገው፡፡ ርግጥ ነው በምዕራባውያን ‹‹ዕውቀት ምርት›› (Knowledge Production) የተቃኙ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በነጭ የበላይነት እና በአውሮፓ ሥልጣኔ ላይ ሽንፈት ላወጀው ታላቁ የአድዋ ድል ዕውቅና መንሳታቸው የሚገርም ሊሆን አይችልም፡፡ ‹የጥቁር ህዝቦች ድል› ሲባል…
ህልፈቱን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኒልሰን ማንዴላን በተመለከተ በርካታ ተረታ ተረቶች ነግረውናል፡፡ ከትውልድ ሀገሩ ባሻገር ለሌሎችም የአለም ህዝቦች ነፃነት ከታገለው ቼ ጉቬራ ጋር ከማነፃፀር አንስቶ እንደ ብቸኛ የ‹ጥቁር ሕዝቦች ድል› አባት አድርገው የማይመጥነውን ገድል አሸክመውታል፡፡ ጥያቄውም እዚህ ጋ ነው፤ ከምዕራብ አፍሪካ እስከ ላቲን አሜሪካዋ ጃማይካ ድረስ ለነፃነትና ለአንድ (ፓን) አፍሪካ መነቃቃት መግፍኤ የምኒልክ አድዋ ድል? ወይስ የማንዴላ በእስር ቤት መንገላታት? ወይስ በ‹ይቅርታና ምህረት› ስም ዛሬም የመላ ሀገሪቱን ኢኮኖሚ በብረት መዳፋቸው እንደጨበጡ ከመቀጠል መታደግ የተሳነው የአፓርታይድ ‹ውድቀት›? ለአፍሪካ ‹አባትነት›ስ ቢሆን ከማንዴላና አፄ ኃይለስላሴ ማን ይቀርባል? እሺ! ሌላው ቢቀር በ2004 ዓ.ም ኩዋሚ ኑኩሩማ ‹የአፍሪካ አባት› ተብሎ በህብረቱ ቅፅር ግቢ የመታሰቢያ ሐውልት በቆመለት ጊዜ ስለማንዴላ ምንም ነገር አለመባሉስ ምንን ያመላክታል?
የሆነው ሆኖ የማንዴላ ታሪክ ሰማይ ሰማያት መሰቀሉ የሚያሳየው እውነታ አንድ ነው፤ አህጉሪቷ በዚህ ትውልድም ከነጮች የበላይነት መዳፍ ገና ነፃ አለመውጣቷን፤ እንዲሁም የፕሮፓጋንዳ ጋጋታው ማዲባ ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ በትግል፣ ሃያ ሰባት ዓመታትን ደግሞ በአስከፊ እስር ቤት ተሰቃይቶም፣ የነጭ ደቡብ አፍሪካዊያንን ጥቅም ባስከበረ መደራደሪያ የተደረገ የስልጣን ሽግግርን የመቀበል ኃላፊነት በመውሰዱ፣ በልዋጩ የተሰጠው የተጋነነ የታሪክ ሽልማት ይመስለኛል፡፡ ይህንን መከራከሪያ የሚያረጋግጥልን በአንድ ወቅት ፍሬደሪክ ዲክላርክ ‹‹በደቡብ አፍሪካ የዲሞክራሲ ሽግግር የተማርኳቸው አምስት መረዳቶች›› በማለት ‹‹Recipe For Freedom›› በተሰኘ ርዕስ በአንድ ኮንፍረንስ ላይ ባደረገው ንግግር ‹‹ኤ.ኤን.ሲ ጠመንጃ እንዲጥል እና የብዙሃን ድምፅ የበላይነትን በሚሰብከው የሊበራል ዲሞክራሲ መርህ እንዲገዛ፣ እኛ ደግሞ የአፓርታይድ ስርዓት እንዲያበቃ መስማማታችን ለሽግግሩ ወሳኝ ምዕራፍ ነበር›› ማለቱን ስናስታውስ ነው፤ በወቅቱ ማንዴላ ይህንን ስምምነት ከመቀበል ውጪ የተሻለ አማራጭ አልነበረውም የሚለው ሙግት ሳይዘነጋ ማለት ነው፤ ምክንያቱም የማታ ማታ ይህችም ድል ብትሆን የተገኘችው በፓርቲው ‹ኤ.ኤን.ሲ› ጥንካሬ ብቻ ሳይሆን፣ የአፓርታይድ መሪዎች ከዚህ በኋላ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ በዚህ መልኩ መቀጠል አለማስቻሉን መረዳታቸው እና ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በስርዓቱ ላይ ያሳደሩትን ጫና መሸከም አለመቻላቸው መሆኑን ትሁቱ ኒልሰን ማንዴላ ጭምር ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ በርግጥ ማዴባ ይህንን ድርድር ለመቀበል ‹አሻፈረኝ› ቢል ኖሮ የዛሬዋን መልከአ-ደቡብ አፍሪካም ሆነ የእርሱን ዕጣ ፈንታ መተንበዩ አስቸጋሪ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በጥቅሉ ማንዴላ በዚህ አይነቱ የ‹ሰጥቶ መቀበል› መርህ አፓርታይድ በተቋም ደረጃ እንዲፈርስ ሲያደርግ፣ በግልባጩ የስርዓቱ መሪዎችና ተባባሪዎች ላይ ምንም አይነት ያደረ ተጠያቂነትም ሆነ የኢኮኖሚ ጥያቄ (የሀብት ክፍፍል) እንደማያነሳ ተስማምቷል ወደሚል ጠርዝ የሚገፋን ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁናቴ ስናጤን ነው (ዛሬም በነጮችና በጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን መካከል ሰፊ የሀብት ልዩነት ለመኖሩ በርካታ ማሳያዎች አሉ) መቼም ጥቁር ፕሬዝዳንት፣ ጥቁር ባለስልጣናት፣ ጥቁር አምባሳደር፣ ጥቁር አውሮፕላን አብራሪ… ሊኖሩ የተቻለው በማንዴላ ብርቱ ትግል ነው የሚል ሞኛ ሞኝ መከራከሪያ የሚነሳ አይመስለኝም፡፡
በአናቱም የማንዴላ አይነት ሀገር ወዳድ አፍሪካዊ መሪ፣ በአህጉራችን ጥቂት አለመሆናቸውን መዘንጋት የለብንም (ኩዋሚ ኑኩሩማ፣ ሴኮ ቱሬ፣ ኬኔት ካውንዳ፣ ጆሞ ኬኔያታ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ፣ መሀመድ ቤንቤላህ፣ ሮበርት ሙጋቤ… እያልን በስም መዘርዘር እንችላለንና፤ ሁሉም ሀገራቸውን ነፃ ማውጣቱ የተሳካላቸው ነበሩ) ይሁንና አስቀድሞ ሀገሩን ከቅኝ አገዛዝ መታደግ የቻለ መሪ ከዳግማዊ ምኒሊክ በቀር አንድም ማግኘት አይቻልም፤ የዘመናዊ አስተዳደር መሰረትን ከየትኛውም አፍሪካ ሀገር ቀድሞ በራሱ ሰዎች ያዋቀረ ንጉስም እርሱ ብቻ ነበር፡፡ ሁሉም አህጉር ተጋሪዎቻችን በሂደት ነፃ የወጡ ከመሆናቸውም በላይ፣ መንግስታዊ መዋቅሮቻቸውና ተቋማቶቻቸው ቅኝ ገዢዎቻቸው ሲጠቀሙበት የነበረው ነው የቀጠለው፡፡
እነዚህ እውነታዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ የማይዘነጋው ሌላው ቁም ነገር ተወዳጁ ማንዴላ እድሜ ዘመኑን ሙሉ የኢትዮጵያ ወዳጅ እንደነበረ ህይወቱ ማለፉ ነው፤ ይህንን ጉዳይ በደንብ የሚያስረግጥልን የቀድሞ መንግስት ባለሥልጣን የነበረው ዶ/ር ካሳ ከበደ የማዲባን ህልፈት አስመልክቶ ከኢሳት ቴሌቭዥን ጋር ባደረገው ቃለ-መጠይቅ ‹ማንዴላ ነገሩኝ› በማለት የተናገረው አስገራሚ ጉዳይ ነው፡፡ ይኸውም ኢህአዴግ ወደ አዲስ አበባ፣ ሻዕቢያ ወደ አስመራ ለመግባት በተቀረቡበት በእነዛ የውጥረትና የፍርሃት ጊዜያት፣ እርሱ የሁለቱንም ድርጅት የአመራር አባላት ጠርቶ እንዳነጋገራቸውና የተከፈፈለች ኢትዮጵያን ማየት አለመፈለጉን ገልጾላቸው ሀገሪቱ በአንድነቷ እንድትቀጥል መፍትሄ አድርጎ ያቀረበው ሃሳብ ኢሳያስ አፈወርቂ ‹ፕሬዚዳንት›፣ መለስ ዜናዊ ‹ጠቅላይ ሚኒስትር› ሆነው በጋራ እንዲመሩ የሚል ነበር፡፡ ሆኖም የአማፅያኑ መሪዎች ሀሳቡን አጣጥለው ሳይስማሙ በመቅረታቸው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሁለት ሀገር ለመሆን በቁ፤ በዚህም ክፉኛ ያዘነው ማዲባ የሀገሩ ፕሬዝዳንት ከሆነ በኋላም ለአፍሪካ ህብረት ስብሰባ እንኳ ወደ ኢትዮጵያ ድርሽ ብሎ አለማወቁ ነው፤ ካሳ ከበደ ‹‹ማንዴላ የተከፋፈለች ኢትዮጵያን ከማየት፣ ቀድሞ የሚያውቃትን አንዲት ኢትዮጵያ በአእምሮውና በልቡ እንደያዘ መቃብር መውረድን መርጧል›› ሲል ለኢሳት ቴሌቪዥን ተናግሯል (በነገራችን ላይ የማዲባ ህልፈት በሳዑዲ ዓረቢያ በስቃይ ላይ የሚገኙ
ወገኖቻችንን ጩኸት እንዲደበዝዝ /ጨርሶ እንዳይሰማ/ እስከ ማድረግ የደረሰ ይመስለኛል፤ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ከተጎጂ ወገኖቻችን ጎን የመቆም መነሳሳት እየፈዘዘ ሄዷል፡፡ በርግጥ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሀገራዊ ሀላፊነታቸውን በመወጣታቸው በግሌ ማመስገን የምፈልጋቸው አካላት አሉ፤ የመጀመሪያው የኢሳት ቴሌቪዥን ጣቢያ ነው፤ ቪቫ ኢሳት! ሁለተኛው ደግሞ ይህ ችግር ከመፈጠሩ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ሲወተውቱና ሰቆቃውን ከቦታው ድረስ ሲያሳውቁን የነበሩት ጋዜጠኛ ነብዩ ሲራክ እና ጋዜጠኛ ግሩም ተ/ሃይማኖት ናቸው፤ እንደናንተ አይነቱን ተቆርቋሪ ወንድሞች ያብዛልን! አንድ ቀን ያ የምንናፍቀው ትንሳኤ እውን ሆኖ፣ ሀገራችን ሁላችንንም ያለ አድሎ እኩል አቅፋና ደግፋ ማስተዳደር ስትችል በአደባባይ መመስገናችሁ አይቀርም፤ ታሪክም አይዘነጋችሁም) ይህ ሁኔታም የሚነግረን ማዲባ ከየትኛውም ሀገር መሪ የበለጠ፣ የኢትዮጵያችን ቅን አሳቢ እንደነበረና በእነዛ ክፉ ቀናቶቹ የተደረገለትን ውለታ አለመርሳቱን ነው፡፡ በርግጥም ይህ ሰው ሀገሬን ለሁለት እንድትከፈል ከፈቀዱትና ካመቻቹት መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ የበለጠ ኢትዮጵያዊ ሊያስብለው የሚያስችሉ ስራዎች አሉት፤ ከዚህ አውድ አንፃርም ህልፈቱ በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበር መደረጉም ሆነ ባንዲራችን ለሶስት ቀን ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ መወሰኑ ሲያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡
‹ፀረ-ምኒሊክ›ነት ለምን?
የህወሓት መስራቾች ለትግል በረሃ ከወጡበት ዘመን ጀምሮ፣ ቂም ቋጥረው ደም የተቃቡት ከደርግ አገዛዝ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሀገሪቱ ታሪክም ጋር እስኪመስል ድረስ በአፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ላይ ተጠምደው እንደነበር ይታወሳል፤ በተለይም ለአፄ ምኒሊክ ስምና ስራ ያላቸው ጥላቻ ወሰን አልባ ነው፡፡ የድርጅቱ ‹ማኔፌስቶ› የተዋቀረበት ሳጋና ማገርም በሀገሪቱ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪ ቡድን የበላይነት (ጭቆና) መኖሩን አውስቶ የአንድነትና የዘመናዊት ኢትዮጵያ አባት ዳግማዊ ምኒሊክን አንኳሶና አጠልሽቶ አዲስ ታሪክ መፍጠሩ የትላንት ትዝብት ነው፡፡
የህወሓት አፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ትኩረት ያደረገው፣ ምኒልክ ሀገር ከማቅናት አኳያ በኦሮሚያና ደቡብ አካባቢ የፈፀማቸውን የኃይል እርምጃዎች በማጎን ቅዋሜውን ‹ህዝባዊ› ማስመሰሉ ላይ ነው (በኃይለሥላሴ ዘመን የታነፀውን የዳግማዊ ምኒልክ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሀውልት ይፍረስ እስከማለት ደርሶ እንደ ነበር አይዘነጋም) በእኔ እምነት ንጉሡን አስመልክቶ የሚነሱ መከራከሪያዎች ‹ወሰን በማፅናቱ ዘመን የተከሰቱ ጥፋቶችን መቀነስ ይቻል ነበር› የሚሉ ናቸው ካልተባለ በቀር ‹ዘመቻው አያስፈልግም ነበር› ማለቱ ‹ዛሬ መረከብ የነበረብን የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የወላይታ…. ተብለው በብሔር የተከፋፈሉ ሀገራት መሆን ነበረበት› እንደማለት ይመስለኛል፡፡
የሆነው ሆኖ የምኒልክ ወሰን የማፅናት ዘመቻ አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያ እንዲያካትት የሄደበት መንገድ፣ ዘመኑ የፈቀደው ብቸኛ አማራጭ እንደሆነ ይሰማኛል፤ እናም በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ያሉ የሀገረ-መንግስት (Nation State) ህልዮቶችን መቶ ዓመት ወደ ኋላ ወስዶ የምኒሊክን ኢትዮጵያ ለመመዘን መሞከሩ ቢያንስ ምሁራዊ ታማኝነት ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡ ርግጥ ነው አማርኛ ቋንቋ አፍ መፍቻቸው ካልሆኑ የጦር አበጋዞቹ ጭምር ወደ ደቡባዊቷ ኢትዮጵያ ሲዘምት፣ የተከሰተው ዕልቂት ዘግናኝ እንደነበረ፣ የተናዱት ‹ወጥ ማንነቶች› ብዙ እንደነበሩ ባይካድም፣ በተጨማሪም እርሱን የምንወቅስባቸው ተጨባጭ በደም የተፃፉ ሁነቶች ቢኖሩም፣ ያንን ክቡድ የነፃነት መንፈስ ለማቆሸሽ መምረጡ የዛሬይቱንም ሆነ የነገይቱን ኢትዮጵያ መከራዎች ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡
በአናቱም በግራም በቀኝም ያሉ የሀገሬ የተቃውሞ ልሂቃን፣ በዚህ ንጉስ አገር ገንቢነት ላይ ያላቸው አረዳድ ጠርዝ ለጠርዝ የሚያቆማቸው መሆኑ ስለነገይቱ ኢትዮጵያ በጋራ እንዳያልሙ እንቅፋት መፍጠሩን እረዳለሁ፡፡ ይሁንና የታሪክ መሰረቶች ላይ የሚቆሙ መተናነቆችን መሻገሪያው ብቸኛው መፍትሄ ጉዳዩን ለታሪክ ባለሙያዎች መተው ብቻ ይመስለኛል፡፡ ከዚያም የአፄውን በጎ ምግባሮች በጋራ እያወደሱ፣ የተሻለች ሀገር ትኖረን ዘንድ በህብረት መትጋት ቢያንስ ከቀጣይ ትውልዶች ከሳሽነት ነፃ ያደርጋል፡፡
በመጨረሻም ምንም እንኳ ዛሬ ዕውቅና የመንሳቱ አዝማሚያ እየጠነከረ ቢመጣም፣ ሀገሬ በአፄ ምኒልክና ሕዝባቸው ጀግንነትና መስዋዕትነት በምድራችን ታሪክ በነጭ ወራሪ ኃይል ላይ የመጀመሪያውን የበላይነት ከመቀዳጀት አልፋ፣ ለመላው አፍሪካውያን የነፃነት መገለጫ የመሆኗን ጉዳይ ለጊዜው ማደብዘዙ የተሳካ ቢመስልም፣ ከታሪክ መዝገብ የሚፋቅ ባለመሆኑ ‹ቪቫ ምኒልክ› እያልኩ ባርኔጣዬን ከፍ አደርግለታለሁ፡፡
ነፍስ ይማር ማዲባ! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!
No comments:
Post a Comment