Wednesday, January 28, 2015

አንድነት በመጪው እሁድ የጠራው ሰልፍ ውጥረት ፈጥራል

አንድነት በመጪው እሁድ የጠራው ሰልፍ ውጥረት ፈጥራል

ጥር ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአንድነት ፓርቲ ለእሁድ ጥር 24 በደሴ ለሚያካሄደው ሰልፍ ከከተማው አስተዳዳር እውቅና ያገኘ ሲሆን ፤ የአዲስ አበባው ግን እያወዛገበ ይገኛል።
ከፓርቲው ጽህፈት ቤት የወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በደሴ ሰልፉ  አራዳ አከባቢ ከሚገኘው የአንድነት ቢሮ ተነስቶ  ሆጤ አደባባይ ይጠናቀቃል።
ከ2: 00 ሰ ዓት  እስከ 7:00 ሰዓት በሚቆየው በዚህ ሰልፍ ፤የደሴና የአከባቢዋ ህዝብ በነቂስ በመውጣት ምርጫ ቦርድና ገዥው ፓርቲ በ አንድነት ላይ እየፈጸሙት ያለውን ደባ ያወግዛል ተብሎ ይጠበቃል ።
አንድነት በመጪው እሁድ በአዲስ አበባ ፣ በባህርዳር ፣ በደብረታቦር እና በሌሎች የክልል ከተሞች ላይ ሰልፍ ለማድረግ በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ አሳውቋል። አንድነት በአዲስ አበባ በኩባ አደባባይ ለሚያደርገው ሰልፍ መስተዳድሩን ያሳወቀ ቢሆንም፤ እስካሁን ድረስ ከመስተዳድሩ ምንም ምላሽ አልተሰጠውም።
በሀገሪቱ ህግ መሰረት አንድ አካል ሰልፍ ለማድረግ አሳውቆ በ48 ሰዓት ውስጥ በቂ ምላሽ ካልተሰጠው ያ ሰልፍ ህጋዊ እንደሆነ ይቆጠራል። ይሁንና እስካሁን ለፓርቲው ምላሽ ያልሰጠው የአዲስ አበባ አሰተዳደር ፦<<ወደ መዲናዋ እንግዶች ስለሚመጡ  ሰልፍ አይደረግም”በማለት ለሌሎች አካላት መናገሩ ተሰምቷል። የኢሳት ምንጮች  አንድነት  ያስገባውን የሰልፍ ማሳወቂያ ደብዳቤ ተከትሎ በ አዲስ አበባ መስተዳድር ሰራተኞች መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

No comments:

Post a Comment