Thursday, February 5, 2015

ደህና ሁን አይባልም! (አስራት አብርሃም )

ደህና ሁን አይባልም! አስራት አብርሃም 
በፓርቲያችን አንድነት ስለሆነው አሳዛኝ ሁኔታ እና አሁን እየተሰማኝ ስላለው ስሜት የተወሰነ ነገር ብል ደስ ይለኛል፤ ውስጤ ያለው መከፋት ይወጣልኝ እንደሆነም አላውቅም። ዓላማ ደህና ሁን አይባልም፤ ራዕይ ድህና ሁን አይባልም፤ ነገር ግን የሰው ልጅ አቅሙ ውስን ነው፤ አንዳንድ ነገሮች እንዳይሆኑ ማድረግ አይችልም። ራዕይህ በግድ ሲቀማ፣ ዓላማህ በይሁዳ መንገድ በሰላሳ ብር ሲሸጥ ያን እያየህ ምንም የሚታደርግበት አቅም ካጠረህ፤ ያ እንዳይሆን መከላከልና ማስቀረት ካልቻልክ ምን ማድረግ ይችላለህ! እነዚህ ሰዎች እኮ ፓርቲ ብቻ አይደለም የዘረፉን፤ ዓላማችን፣ ራዕያችን ጭምር እንጂ!  

አንድነት እንዲያ ከሁሉም አቅጣጫ ጠላት በዝቶበት የነበረው፤ የደረሰበትን ከፍታ በትክክል መገንዘብ የሚችል ፖለቲካዊ ንቃተ ህሊና በዚህ ሀገር ስለሌለ ነው። ምክንያቱም ያገራችን ፖለቲካ ከሀገራዊ ጥቅም፣ አብሮ አሸናፊና ተጠቃሚ ከመሆን ስነልቦና፣ ከዓላማ እና ከሀሳብ ልዕልና ይልቅ በብሄር እይታ የታጠረ፤ በጥላቻና በአጥፍቶ መጥፋት የሚቃኝ በመሆኑ ነው። እግዚሄር ለአንድ ኢትዮጵያዊ “ምን ላደርግልህ ጠይቀኝ? የምትፈልገውን ሁሉ ንገረኝ አደርግለሃለሁ፤ ነገር ግን ላንተ ያደረኩልህን ለጎረቤትህ ደግሞ እጥፍ አደርግለታለሁ” ቢለው የጎረቤቱን ሁለት ዓይን እንዲጠፋ በመፈለግ “የእኔን አንዱ ዓይኔን አጥፋው” አለው ይባላል፤ የእኛ ሀገር ፖለቲካም እንደዚያ ዓይነት ነው! ራስን ጎድቶ ሌላውን የበለጠ የመጉዳት ስነልቦና የተጠናወተው ነው። ኢህአዴግ አንድነትን እንዲያ ለዓይኑ እንኳ የጠላው ለስልጣኑ ስለሚሰጋ ብቻ አይመስለኝም፤ ከዘመነ ኢህአዴግ በኋላ ከእርሱ የሚሻል ስርዓት እንዲመጣ ስለማይፈልግም ጭምር ሊሆን ይችላል። በመሰረቱ አንድነት እንደፓርቲ በዚህ ሀገር መኖሩ ብቻ በራሱ በፖለቲካው ለሚርመሰመሱ ባለ ትንንሽ ራዕይ ፖለቲከኞች በተለይ ደግሞ አሁን ላለው ስርዓት ስድብ ነበር። 
አንድነት እኮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደየቋንቋውና እንደየባህሉ ፓርቲዬ የሚለው፤ የሁሉም የጋራ እሴት ነበር። አዳማ ብትሄድ በኦሮምኛ የሚወያዩ አባላት የነበሩት፤ መቀሌ ብትሄድ በትግርኛ ወረቀት የሚበትኑ አባላት የነበሩት፤ ደቡብ ከምባ፣ ቁጫ ብትሄድ በወላይትኛ ስለሀገራቸው የሚመክሩ አባላት የነበሩት፤ በዚህ ዘመን ልናስበው የማንችል የኢህአፓ ዓይነት ህብረ ብሄራዊ  የሆነ፤ ፍፅም በሀሳብና በዓላማ ላይ የተመሰረተ ፓርቲ ነበር። አንድ ምሳሌ ላንሳ፤ አንድነት ምርጫ ቦርድ በተባለው የመሸጦ ተቋም አማካኝነት እንደተቀማን የተነገረ ዕለት እነ አስናከ ሸንተማ፣ እነ ምርቱ ጉታ፣ እነ ተስፋዬ ዋቅቶላ፣ እነ መሳይ ትኩ፣ እነ አማኑኤል መንግስቱ ቁጭ ብለው ተንሰቅስቀው ሲያለቅሱ ሳይ እኮ በአንድነት ላይ የነበረኝ ተስፋና እምነት ይበልጥ ትክክል እንደነበር ነው የተረዳሁት።  እነዚህ ከላይ የጠቀስኩዋቸው የአንድነት አባላት ከትልቁ የኦሮሞ ህዝብ የተገኙ የአዲሱ ትውልድ ፈርጥ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይሄ ለምሳሌ ያህል ነው ያመጣሁት፤ ትግራይ የነበሩ አባላት፤ ሰሜን ሸዋ የነበሩ አባላት፤ ደቡብ የነበሩ አባላት፤ ጎንደር፣ ባህርዳር ሳግ እየተናነቃቸው በስልክ አዋርቶውኛል። ሌላው ይቅርና የሌላ ፓርቲ አባላት የሆኑ ጭምር በሁኔታው በጣም አዝኗል። ደጋፊዎቻችን፣ እንዲሁም ለሀገራቸው በጎ የሚመኙ ኢትዮጵያውያን ተክዟል፤ ምክንያቱም አንድነት አይደለም የፈረሰው፤ የሀገር ራዕይ፤ የሀገር ዓላማ ነው አብሮው ድውይ በሆነ የክፋት መንፈስ እንዲፈርስ የተደረገው።

 የማህበራዊ ሳይንስ ልሂቃን እንደሚሉት የፖለቲካ ትግል የባህል አብዮት ትግል አንዱ አካል ነው። በነባሩ ወይም አሁን ባለው ፖለቲካዊ ባህል እና ወደፊት እንዲመጣ በሚፈለገው ፖለቲካዊ ባህል መካከል የሚደረግ የአስተሳስብና የአስራር ትግል ማለት ነው! እንደ አለመታደል ሆኖ በአሁን በሀገራችን እየተካሄደ ያለው ትግል አዲስ ፖለቲካዊ ባህል ለማምጣት ሳይሆን አሁን ባለውና ድሮ በነበረው መሀል የሚደረግ ነው። ከአፄ ዮሐንስ ፖለቲካ እና ከአፄ ምኒልክ ፖለቲካ ገና አልወጣም። አንድ መቶ ዓመት ወደኋላ የቀረ ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነው ገዝፎ እየተደመጠ ያለው። እንዲያውም ከበፊቱ በባሰ ሁኔታ ኋላቀርነትና ምክንያት አልቦነት እየተጠናወተው ነው የመጣው። የዘመኑ መንፈስ እንደዚያ ያለ ነው፤ የዘመኑ መንፈስ ስለ ሀገራዊ ክብር ስለጋራ ጥቅም፣ ስለአብሮ መኖርና ስለመግባባት ብዙ ቦታ የለውም። በቀል፣ ጦርነት፣ መጠፋፋት፤ “እኛ ጋም እሳት አለ” ማለትን ነው የተያዘው፤ ሰላም አይደለም እየተሰበከ ያለው ጦርነት ነው። ይህን ስርዓት በሌላ የተሻለ መንገድ የምናስወግድበት ብልሀት አልተገለፀልንም፤ በተለመደው ለሶስት ሺህ ዘመናት በተጓዝንበት የጦርነት መንገድ ለማስወገድ ነው እየተንደረደርን ያለነው። ስርዓቱም “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል!” እንዳለችው እንሰሳ ሆኗል።

ዓላማ ነበረንና የውስጥ ስሜታችን ዋጥ አድርገን፤ ከዚህ መንፈስ ጋር ነበር ስንታገል የነበርነው። አንድነት ወደፊት የሚያራምድ፣ የሀገሪቷንና የህዝቧን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ ዓላማና ራዕይ ይዞ እንዲወጣ፤ ከዚያም ከዚህም የለቃቀማቸው ድሪቶዎች እየነቀልን፤ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ያልናቸው ጉታንጉቶች እያለዘብን በትጋት እየገነባነው ነበር። ትንሽ የሚቆጨኝ ይህን የመሰለ ዓላማ በፈራረሰ ግንብ ላይ ለማነፅ መነሳታችንና በመጀመሪያ መሰረቱን በደንብ አድርገን በፍጥነት ያለማጥራታችን ነው። ያም ቢሆን ግን አሁን ከተወሰነበት ፖለቲካዊ ውሳኔ እናድነው ነበር ማለት አይደለም። ያለ ምንም ጥርጥር አንድነት እንዲያ እንዲጠፋ ርብርብ የተደረገበት

ከልማዳዊውና ከኋላቀር ፖለቲካዊ አመለካከት እየወጣ የነበረ ፓርቲ በመሆኑ ነው። በተለይ በበላይ አመራር ስር የነበረው አንድነት ለእኔ በሀገራችን እንዲኖረን የምፈልገው ተምኔታዊ (ideal) ፓርቲ ነበር። እኔ ከዚህ በኋላ ከዚህ ከፍታ መውደቅ አልፈልግም፤ የእኔ የምለው አንድነት፣ እሴቶቹና ዓላማዎቹ ከውስጤ ማንም ሊቀማኝ አይችልም፤ በመንፈስ አብሬው መኖር እችላለሁ፤ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ተጠቃሚ የሚያደርግ፤ በህግ የበላይነትና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ህዝባዊ ስርዓት እንዲተከል፤ ለየትኛውም የህብረተስብ ክፍል ስጋት የማይሆን ለውጥ እንዲመጣ በቻልኩት መንገድ ሁሉ እሰራለሁ። ከዚያ በመለስ ግን የግድ በፓርቲ ፖለቲካ ካልታቀፍኩ ለሀገሬ አስተዋፅኦ አላደርግም የሚል እምነትም የለኝም። እኔ የብዙ ሞያ ባለቤት እንደሆንኩ ይሰማኛል፤ ቢያነስ መፃፍና በማስተማር እችላለሁ። አቅሜንና እውቀቴን እያጎለበትኩ፤ ለሀገሬ ይጠቅማል በምለው ሞያ ሁሉ እየተሳተፍኩ፤ ወደፊት እንዲመጣ የምፈልገው ሀገራዊ ለውጥ እውን እንዲሆን ብርቱ ጥረት አድርጋለሁ፤ ምክንያቱም የምታስፈፅመበት ስልትና እስትራቴጂ ትቀይራለህ እንጂ ዓላማና ራዕይ ደህና ሁን ማለት ስለማይቻል ነው።  

No comments:

Post a Comment